ኢትዮጵያ የገጠማት ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት ወያኔና ነጋዴዉን ማጨቃጨቁ ተነገረ

ግራ የተጋባዉ የወያኔ አገዛዝ ሰሞኑን ለነጋዴዎች ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት በዉጭ ንግድ ዘርፍ ዉስጥ የተሰማራ ማንኛዉም ነጋዴ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚችል ግልጽ ያደረገ ቢሆንም በአዲሱ መመሪያ መሰረት የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ነጋዴዎች በቅድሚያ የጠየቁትን ያክል ገንዘብ በብር ለባንኮች የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። ለምሳሌ 100 ሺ ዶላር የሚጠይቅ ነጋዴ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር በቅድሚያ ለባንኮች የማቅረብ ግዴታ አለበት። ይህንን አዲስ አሰራር የንግዱ ህብረተሰብ በፍጹም እንዳልተቀበለዉ የሚታወቅ ሲሆን በነጋዴውና በወያኔ አገዛዝ መካከል ዉዝግብ የፈጠረዉም ይሄዉ አዲሱ መመሪያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የመለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ ብዛት ያላቸዉ ሰዎች ገንዘብ ማሸሽ በመጀመራቸዉ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት መከሰቱ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈዉ መስከረም ወር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ እንደተረከበ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምንም አይነት የዉጭ ምንዛሪ እጥረት አለመኖሩን መናገሩ የሚታወስ ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ የተፈጠረዉን የዉጭ ምንዛሬ እጥረት አስመልክቶ አስተያየታቸዉን እንዲሰጡን የጠየቅነቸዉ አንድ የአኮኖሚክስ ምሁር የወያኔ አገዛዝ የገንዘብ እጥረት ቢያጋጥመው አይገርምም፣ ከመለስ ሞት በኋላ የወጡ ወጪዎችን እንኳን ብናይ፣ ይህች ደሀ አገር ያለአቅሟ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አውጥታለች ካሉ በኋላ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀብር ማስፈጸሚያ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ፤ የብሄር ብሄረሰቦች በአል ለማክበር ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ የመከላከያ ቀንን ለማክበር ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል። አሁን በቅርቡ ደግሞ የወያኔ ኢህአዴግን ጉባኤ ለማካሄድና የአባይን ግድብ ሁለተኛ አመት ለማክበር ከፍተኛ ገንዘብ ከመንግስት ካዝና ወጪ ሆኗል ። እንግዲህ እንደዚህ አይነት ከፍተኛ መጠን ያለዉ ገንዝብ ከልማት ጋር ባልተያያዘ መንገድ እየወጣ አገሪቱ የገንዘብ እጥረት ገጠማት ቢባል የሚገርም ሊሆን አይገባም ብለዋል።
No comments:
Post a Comment