Tuesday, March 12, 2013


እንደገና መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን
ከሺመልስ
የኢትዮጵያ ህዝብ በረጅም ጊዜ ታሪኩ በተደጋጋሚ መስቀለኛ መንገድ ላይ ወድቋል። በሁሉም ጊዜ ግን የነጻነት ተስፋው
እየተቀማ እንደገና ላዲስ ፍዳ ተዳርጓል። በተለይ ያሁኑ ትውልድ ሁለት የታሪከ አጋጣሚዎችን ማለትም በ1966 በደርግ ቀጥሎም
በ1983 በወያኔ ተነጥቆ ወጣት ልጆቹን፣ የእድገት ተስፋውንና ሰላሙን ተነጥቆ አሁንም የዓለም ጭራ አንደሆነ ለሌላው ሶስተኛ ጊዜ
መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው። አሁንም ካለፉት ሁለት የታሪክ አጋጣሚዎች የተሻለ ሁኔታ ላይ እንዳልሆን በቅን ልቦና ለሚመረምር ሁሉ
ግልጽ ነው። አብዛኞቻችን ባለፈውና ባሁኑ ስቃያችን ላይ የምንንጨረጨረውንና የምንባዝነውን ያህል በወደፊት ተስፋችን ላይ ምንም
ያልተዘጋጀን፣ እንድያውም ለመውደቂያችን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ያለን እንመስላለን። ነንም።
አሁን በመንገዳገድ ላይ ያለው የወያኔ አመራር የራሱ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን የህዝቡ ድክመትም በዋናነት እያፋፋ ያቆየው ነው።
እሱ የተፈጥሮ እድሜውን ጨርሶ በመውደቅ አፋፍ ላይ ቢሆንም የለውጥ ፈላጊው ጨቅላነትና ዳዴ ባይነት የሌለውንና የማይገባውን
እድሜ ቀጥሎለታል። የወደፊት ጉዞአችንን አደገኛ የሚያደርገውም በተፈጥሮው ሊወድቅ የተዘጋጀ ስራት አልሞት ባይ ተጋዳይነትና
አይቀሬ ውድቀት ሲመጣ ያልታሰበ ነጣቂ መጥቶ ሌላ የመከራ ስርዓት ሊያነግስብን የሚችል መሆኑ ነው። ሟርተኛ አትበሉኝ። ሁለቱን
የታሪክ አጋጣሚዎች እንደሌሎቻችሁ ለማየት፣ በውስጣቸውም ለማለፍ የበቃሁትን ያህል ለመጭውም ጊዜ የሚሆነኝ አዲስ ተስፋ
አልጨበጥሁምና ነው።
ጓደኞቻቸውን ሆነ ተቃዋሚያቸውን በመጠላለፍ የስልጣንን ልጓም ጨምድደው ይዘው ለሥርዓቱ እድሜ እየተዋሱ በማቆየት
የተካኑት መለስ ለራሳቸው እድሜ መቀጠል ባለመቻላቸው የድርጅታቸውን እድሜም ነው ግማሽ ወገቡ ድረስ መቃብር የከተቱት።
ህወሃት በተለይም መለስ የፈጠሯቸውና  እንደ ጅኒ በጠርሙስ ውስጥ ከተው በፈለጉ ጊዜ እያወጡ የሚጠቀሙባቸው ተቀጥያ
ድርጅቶች ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ…..ግማሽ አካላቸው ከጠርሙሱ ወጥቷል። መልሶ የሚከታቸው የመለስ እጅ የለም። እንዳገራችን
የባህል መድሃኒተኛ ብቅ የሚሉ የህወሃት ደባትርትንም መለስ ሲኮረኩሙ ኑረው መተታቸውን ለሌሎች ሳያስተምሩ ከማንም በላይ
ህወሃትን ገድለውት አልፈዋል።
በሙስናና ባስተዳደር ዝቅጠት የነተቡት እነዚህ ተቀጥያ ድርጅቶች ያበጠው ማንነታቸው መልሶ ጠባቡ የህወሃት ጠርሙስ
ውስጥ እንዳይገባ የሚያደርጉትን ግብግብ የሚቋቋም ሃቅም ሆነ ጥበብ አሁን ህወሃት ውስጥ የተገኘ አይመስልም። ይባስ ብሎ በዕውር
ድንብሩ እየወሰዱት ያለው ጸረ ህዝብና ጸረ ዴሞክራሲ የሆነ እርምጃ፣ የተቀናበረ መንግስታዊ ስራ መስራት አለመቻል፣ የህዝቡ ኑሮ
ማሽቆልቆልና የኤኮኖሚው መንኮታኮት የሚይዙትንና የሚጨብጡትን አሳጥቷቸዋል። በእስልምናና በክርስትና እምነቶች ላይ
የሚያደርጉት ጭፍን ጣልቃገብነት ብሎም ሁለቱን የእምነት ተከታዮች በማቃቃር መሳርያቸው ለማድረግ የተያያዙትን ሩጫ የህዝቡ
ተቃውሞ የማይወጡት አቀበት አድርጎባቸዋል።
“መለስ ህወሃትን ገድሎት ሄደ” እስከ ማለት የደረሱት ህወሃቶች በከፊል እውነታቸውን ቢሆንም ህወሃትን እየገደለ ያለውና
ሲገድለውም የኖረው ጸረ ዴሞክራሲና ዘረኛ ድርጅት መሆኑ ነው። ዴሞክራሲ ለወያኔ አጀንዳ አይመችም። ለዚህም ነው መለስ ሆነ
ወያኔ ዴሞክራሲን አጥብቀው የሚጠሉት። ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ባበበ ቁጥር የወያኔ ስውርና መሰሪ አላማ ይጋለጣል።
ዴሞክራሲ ሲሰፍን በጥቂት የህወሃት መሪዎችና ጀሌዎች አማካኝነት የአንድ ብሄር የበላይነትን አጉልቶ በማሳየት ሰፊውን
የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን በመነጠል ተጠቃሚ በማስመሰል ድጋፉን መሻታቸው ይከሽፋል። ጠባብነት የህወሃት እንጂ የሰፊው
የትግራይ ህዝብ አላማ አይደለም።  ሰራዊቱ አመራር ላይ ያሉ ዘጠና ከመቶው በላይ ከአንድ ብሄር የተውጣጡ የህወሃት አባላት
ቢሆኑም የነሱን ቅጥ ያጣ ዘረኛ አመራር የተማረረ ብዙሃኑ ሰራዊት ከህዝብ ጎን መሰለፉ ስለማይቀር ድርጅቱን ሰዓት ተሞልቶለት
በተጠመደ ፈንጅ ላይ የተቀመጠ ያደርገዋል።
ህወሃት ለጊዜውም እድሜ የሚቀጥልለትን መለስ ብቻ አይደለም ያጣው። በሱም አማካይነት ተይዞ የነበረውን የውጭ ድጋፍ
ጭምር እንጂ። በሰላም ጠባቂዎች ተልዕኮ፣ በሱማሌ ጣልቃገብነት፣ ሽብርተኝነትን ለመከላከል እየተባለ የሚዘንበው እርዳታ ጭል ጭል
እያለ ወደመጥፋቱ አዝግሟል።
በተቃዋሚዎችና በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመውና ዓለም ያወገዘው ግፍ በሙስሊም መሪዎችም ከነፈጠራ ቲያትሩ ቀጥሏል።
ከዓመት በላይ የዘለቀው ሰላማዊው ህዝባዊ ተቃውሞ እየጎለበተ መሄድ ከሌላው ጋር ተዳምሮ ወዴት እያመራ መሆኑን ወያኔዎች
በእስር ቤቶቻቸው ካጎሯቸው ከነለገሰ አስፋው ካልተማሩ ማደርያቸውንም እንዲያጋሯቸው መጠየቅ ግድ ማለቱ አይቀርም። ታምራትላይኔና ስዬ አብርሃ በስልጣን ዘመናቸው በግፍ ያሰሯቸውን የዶክተር ታዬ ወልደሰማያትን  ማደርያ እንዲጋሩ መገደዳቸው የቅርብ ጊዜ
ትዝታ ነው።
እስክንድር ነጋንና ዓንዷለም አራጌን በግፍ ከማንገላታት አልፎ መናኛ ንብረታቸውን በህገወጥ መንገድ ለመውረስ ያላፈረው
ወያኔ ኤፈርትን የመሰለ የህዝብን ንብረት የገፈፈ ድርጅት፣ ባንዲት ለሊት ወደሚሊዬነርነት የተለወጡ ባለስልጣናትና ዘመዶቻቸው
እንዴት እንደከበሩ ምን መልስ አለው? አዲስ አበባ በወያኔ መድፍ ተከባ እያለ ለሰሯት አንድና ሁለት ቤታቸው ቀለም ሲያስቡ ከነበሩ
የዛሬ እስረኛ የደርግ ባለስልጣናት በብዙ ሚሊዮን ዶላር ትላልቅ ህንጻና የንግድ ድርጅት በማቋቋም የሚሮጡት የወያኔ ባለስልጥናትና
ጄኔራሎች ምንም የተማሩ አይመስልም። ለነገሩ ሁሉም አምባገነኖች አንድ አይነት ናቸው። ያወገዙትን አሮጌ ስርዓት ኮርጀው ኮቴውን
መከተል የተፈጥሮ ግዴታቸው ነውና።
ከሃያ ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ መከራ ዋና ተጠያቂው ደርግ ነው እያልን የሞተ ከበሮ ስንደበድብ፣ የራሳችንን ድክመት
አርመን ለአዲሱ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ምንም ሳንዘጋጅለት ወያኔ ድሉን ጠልፎ ለዚህ አብቅቶናል። አሁንም ካለፈው ስህተታችን
ሳንማር ለጠፋው ሁሉ ወያኔን በባለቤትነት እየወነጀልን ከአርባ ዓመት በፊት በነበርንበት የአስተሳሰብና የድርጊት ደረጃ ላይ ሆነን ብዙ
ጥሩ ነገር እንዲገጥመን ያለምንም ጥረት እየተመኘን ነው።
የለውጥ ፍላጎት በህዝቡ ውስጥ ምን ጊዜም ያለ ነው።ስለሆነም ለለውጡ መሪ ሃይል እንሆናለን  ብለው መስዋዕት የከፈሉ
አእላፍ ናቸው። እነዚህ ኣፍላ ህይወታቸውን የከፈሉ ወገኖችን መስዋዕት ከንቱ የሚያደርገው፣ የታገሉት አምባገነን ስርዓት ድርጊት
ሳይሆን የነሱን ዓላማ አንግበናል ያሉ፣ በተግባራቸው ግን ከንቱ የሆኑ “ተቃዋሚ” የሚል ካባ የደረቡ ቡድኖች አካሄድ ነው። ደርግ ሆነ
ወያኔ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ልጆችን ጨፍጭፈዋል። ይህ ሃቅ ነው። ካምባገነነ መንግስታት ምን ይጠበቅ ኖሯል? እነዚያ
የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች የውደቁለትን አላማ ይዘናል እያሉ በትናንቱ መስዋዕትና ገድል የሚመጻደቁና ከጊዜው ጋር መራመድ
አቅቷቸው ያሉት ቡድኖች እያደረሱ ያለው ጉዳት ካምባገነኖቹ ብዙ አልራቀም። ጭል ጭል እያሉ በትግል የህዝብ አንደበት የሆኑ ነጻ
ሚድያዎች ሆኑ ህብረተሰቡም ጫን ያለ ተግሳጽ ሳይጥልባቸው እያሽሞነሞነ የያዛቸው “ተቃዋሚዎች” ድክመት ላይ የሚገባ ትኩረት
አልተሰጠም። ስለሆነም እነሱም አላደጉ፣ ህዝቡንም አልታደጉትም። አሰራራቸውን በግልጽ መመርመርና በድርጊታቸው ተጠያቂነት
እንዲሰማቸው ማድረግ የሁሉም ሃቀኛ ወገኖች ተግባል ሊሆን ይገባል።
ጥቂት አስርት ዓመታት እድሜ ያስቆጠሩ ሆነ በቅርቡ ብቅ ያሉት ተቃዋሚዎች፤ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲያብብ
እንታገላለን እያሉ ይማሉ እንጂ በድርጊታቸውና በውስጥ አሰራራቸው የዴሞክራሲ ባህሪ አላሳዩም። በውስጣቸው የተፈጠረን ችግር
እንኳን ለመፍታት ጨርሶ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አልተከተሉም። አንዳንዶቹ የተቃዋሚ አመራሮች መለስ በስልጣን ከቆየበት ጊዜ
ያልተናነሰ የያዙትን ቦታ ሙጭጭ ብለው ሊተካቸው የሚችል ወጣት ሃይል ሊያሳትፉ ይቅርና ሲያሰናክሉ ነው የሚታየው።
በፖለቲካው መስክ የለመድናቸው፣ እነሱ ከመድረኩ ገለል ካሉ የተቃውሞ አካሉ የሚጠፋ መስሎን እንዲታይ የሚፈልጉ ጥቂት
አይደሉም። ኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው ክብርና ዝና ቅድሚያ እንደሚሰጡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በቀጥታም ይሁን
በተዘዋዋሪ አሳይተውናል። ህይወታቸውንና ኑሮአቸውን በሃቅ ለትግሉ እየሰጡ ያሉትን ጥቂቶችን ይህ አስተያየቴ አይመለከታቸውም።
ደጋግመን በፖለቲካው መድረክ የምናያቸው እያሱ አለማየሁ፣ ፋሲካ በለጠ፣ መርሻ ዮሴፍ፣ገነት ግርማ፣ በየነ ጴጥሮስ፣ መረራ
ጉዲና፣ ሃይሉ ሻውል፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ሌንጮ ለታ፣ ዲማ ነግዖ፣ አረጋዊ በረሄ፣ ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ ብርሃኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣
….. እነዚህና ሌሎችም በጣት የሚቆጠሩ ፖለቲከኞች በበጎውም ሆነ በክፉ ተጽዕኖ ማሳደራቸው ስለማይቀር በዲሞክራሲ ላይ ያላቸው
እውነተኛ ባህርያቸው በመጠኑም የታወቀ በመሆኑ በግልጽ መተቸትና ትክክለኛ መንገድ እንዲይዙ መደረግ ያለባቸው ናቸው።
ፈልገውም ሆነ ሳይፈልጉ ትልቅ ሃላፊነት ተሸክመዋል። ይህ ሃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር መያያዝ አለበት። የረጅም ጊዜ የፖለቲካ
ልምዳቸው ተከታይ አንዲያፈራ ምቹ ሁኔታ ካልፈጠሩና ሁልጊዜም ራሳቸውን ምትክ የለሽ አድርገው መመልከትን ካላቆሙ አላማቸው
መካን ነው። ከአርባና ከሰላሳ ዓመት በፊት በመቶ ሺዎች ተከታይ የነበራቸው ተቃዋሚዎች አፈና ባለበት አገር ውስጥ ይቅርና እንደልብ
በሚፏልሉበት ውጭ አገር ሰላሳ ሰው መሰብሰብ ሲያቅታቸው፣ አይደለም አዲስ ደጋፊ ነባር አባላቸውን ማቅረብ አለመቻላቸው በወያኔ
የመጣ ችግር ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ፖለቲካቸው መካንና አሰራራቸውም ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን የሚያሳይ ባሮሜትር
ነው።
የተቃዋሚዎች የተለያየ ህብረት ሙከራ ያልተሳካው አብዛኞቹ ከዴሞክራሲያዊ አሰራር ጋር ጨርሶ የሚተዋወቁ
ባለመሆናቸውና ጠባብ አላማ ስላላቸው ነው። በኢዴሃቅ ጊዜ የጎሹ ወልዴን፣የኢህ አፓን፣ የኢድህን ሁኔታ ያስታውሷል።ገና ባልተገኘ
ድል ግዳዩ የኔ ነው የሚል አሳፋሪ ባህሪያቸውን አሳይተውናልና። በአማራጭ ሃይሎች ጊዜ በየነ ጴጥሮስ አገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ
አሰራርን አጥፍቶ ለባልደረቦቹ ያሳየው አምባገነንነትና ወያኔን ለመጋፈጥ ያደረገው መልፈስፈስ፣ ኢህ አፓም አማራጭ ተጠናክሮ
እንዳይወጣ ውጭ ይፈጥር የነበረው መሰናክል የሚዘነጋ አይደለም። በህብረቱም ጊዜ  አገር ውስጥ ያሉትና ውጭ የሚገኙት
ተቃዋሚዎች ያሳዩት መጠላለፍ አሳፋሪ ነበር። በቅንጅት ጊዜ የሃይሉ ሻውል ልመለክ ባይነትና የብርሃኑና ሌሎችም ትንቅንቅ አሻራውእስካሁን አልጠፋም። አብረው መስዋዕት የከፈሉትን የቅንጅት አባላት ለመገናኘትና ችግሩን ለመፍታት በሽማግሎች ሲለመኑ ከባህላችን
ውጭ በትዕቢት አሻፈረኝ ያሉት ሃይሉ ሻውል ለመናኛ  አዋራጅ ውል ከመለስ ጫማ ስር ወድቀው ሲሰግዱ ያያቸው ኢትዮጵያዊ ሁሉ
አፍሯል።
ከላይ ያየናቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ያለባቸውን መሰረታዊ የዴሞክራሲያዊ አሰራር ችግራቸውን ሳይፈቱና ሳይጠነከሩ ነው
የአሁኑ የወያኔ መፍረክረክ በሂደት ላይ ያለው። መስቀለኛ መንገድ ላይ አገሪቱ የምትጘኘውም በዚህ ሆኔታ ነው። ተቃዋሚዎች ለወያኔ
መውደቅ መታገል ትተው ጸሎት ላይ ባሉበት ሁኔታ ህዝቡ አስተማማኝ የትግል መሪ አላገኘም። እውነተኛ ለውጥ ፈላጊ የህዝብ ልጆች
ፈጥነው መነሳትና የጠራ አላማ ይዘው በመታገል መታደግ ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው።
ከላይ የሰጠሁኣቸው አስተያየቶች የሚያስከፋቸው ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ። የመከፋታቸው ምክንያት በኔ ስህተት ከሆነ
ለመታረም ዝግጁ ነኝ። ለምን ተነካን ከሆነ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ገብታችሁ ብዙ ጉዳት ከማድረሳችሁ በፊት ካሁኑ ማንነታችሁ
መታወቅ ስላለበት ነውና መከፋታችሁ አይቆጭኝም።
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
March 9, 2013

No comments:

Post a Comment