Tuesday, March 12, 2013


ከተዘጋው በር ጀርባ
ተመስገን ደሳለኝ
እነሆ በሶስተኛው በር ተገናኝተናልና አብዝቼ አላማርርም፡፡ ባማርርስ የት እደርሳለሁ? ማነው አገዛዙንስ
ከስሶ የረታ? ደግሞስ ከመቼ ወዲህ ነው በሀገሬ መሬት ላይ ህግ የበላይ ሆኖ የሚያውቀው? ለማንኛውም
የጠፋው ብርሃን በዚህ መልኩ ዳግም ይፈነጥቅ ዘንድ ስለተከፈለው ዋጋ ወይም ውጣ ውረድ ገድል የመፃፍ
ፍላጎት የለኝም፡፡ ፍላጎቴ ከባልደረቦቼ ጋር በፀና መንፈስ በጀመርነው ጎዳና እንተም ዘንድ የመንግስትን
አፈና አውግዛችሁ የሞራል ድጋፍ ለሰጣችሁን ኢትዮጵያውያን፤ እንዲሁም የአለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት
ተሟጋች ተቋማት ላሳያችሁት አጋርነትና ተቆርቋሪነት፣ በሀገሬ ላይ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይሰፍን ዘንድ
ዋጋ በከፈሉና እየከፈሉ ባሉ ወንድምና እህቶቼ ስም ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ ነውና-ቺርስ ለነፃነታችን!
…አሁን በዚህ አምድ ላነሳው ወደ አሰብኩት ርዕሰ ጉዳይ ልንደርደር፡፡
የዘንድሮ ጥር እና የካቲት ወራት ለየት ባለመልኩ በሁለት ክስተቶች ላይ ትኩረት ስበው ነበር ያለፉት፡፡ አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ያሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ገዥው ኢህአዴግን
የሚመለከት ነው፡፡ የእኔ የዛሬ ትኩረትም ሁለተኛው ነውና ጉዞ ወደ አጀንዳችን፡፡
እንደመግቢያ
በኢትዮጵያ የፖለቲካውን መዘውር የጨበጡ ገዢዎች በሙሉ አራምደዋለሁ ብለው በይፋ የሚያውጁትን ርዕዮተ-ዓለም ለማስረጽ
የሚሄዱባቸው መንገዶች የየራሳቸው መለያ (ገፅታ) እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ
ዴሞክራሲያዊ ግንባር በርካታ መለያዎች አሉት፡፡
በቀደሙት ስርዓታት ከማይታወቁ እና የኢህአዴግ መለያ ከሆኑት መካከል ለ‹‹ዶክመንተሪ ፊልም›› ያለው ፍቅር ዋነኛው ነው፡፡ ለዚህም
ይመስለኛል ‹‹አስገኘሁት›› ከሚለው የኢኮኖሚ እድገት አንስቶ፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ እስከሚፈፅመው ቅጥ-ያጣ ጉልበተኝነት ድረስ
መከራከሪያው በጉምቱ ፖለቲከኞቹ የሚዘጋጀው ዶክመንተሪ ፊልም ብቻ የሆነው፡፡ ህገ-መንግስት፣ የተለያዩ ህጎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣
መመሪያዎች… በስርዓቱ መዝገበ ቃላት ላይ ቦታ ኖሯቸው አያውቅም፡፡
በሀገር ጉዳይ እና በመብት ጥያቄ ላይ ‹‹የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ›› ወይም ‹‹ሊያደርጉ ይችላሉ›› ብሎ የጠረጠራቸውን እልፍ-አእላፍ
የኦሮሚያ ተወላጆችን በኦነግ ስም ለመምታት በርካታ ዶክመንተሪ ፊልም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተስተናግዷል፡፡ እነ እስክንድር ነጋን
እንዳሻው ከሚቆጣጠረው ፍርድ ቤት ተሽቀዳድሞ በሽብርተኝነት ለመወንጀል የቀረበውን ‹‹አኬልዳማ›› የተባለውን ቀሽም ፊልምስ ከቶስ
ማን ይረሳዋል? የእስልምና ሀይማኖት መንፈሳዊ መሪዎች ላይ ለተመሰረተው የሀሰት ክስ ማስረጃ ‹‹ይሆነናል›› በሚል ቀመር ተዘጋጅቶ፣
ባለፈው ወር እንድንመለከተው የተደረገው ‹‹ጀሃዳዊ ሀረካት›› ፊልምም ስርዓቱን ራሱ ምን ያህል እንዳከሰረው ከማንም የተሰወረ
አይደለም (በነገራችን ላይ ‹‹መለስ እንደወታደራዊ ሳይንስ መሀንዲስ›› የተሰኘው ዶክመንተሪ ፊልም አቶ መለስን በእጅጉ በተጋነነ ስብዕና
አፍርሶ ለመስራት የተደረገ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ለሰራዊቱ አመራር እጅግ ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ሰምቻለሁ፡፡ በተለይ በኢትዮ-ኤርትራ
ጦርነት ወቅት መለስ ስለነበራቸው ሚና አስመልክቶ የተተረከው ክፍል የፊልሙን ቅሽምና በሚገባ የሚያሳይ እንደሆነ ነው ያነጋገርኳቸው
ያረጋገጡልኝ፡፡ እዚህች ጋ የምናገኘው ተጨማሪ አስቂኝ ነገር ሰራዊታችን ሻዕቢያን ከድንበራችን በኃይል ለማባረር ከምርጥ የጦር ታክቲክ
/ብልሀት/ ይልቅ የሰው ኃይልን በብዛት መጠቀሙ ተደጋግሞ ሲተችበት የቆየ እውነት ሆኖ ሳለ ‹‹መለስ የጦር ጠበብት በመሆኑ በነደፈው
ስልት ነው ኤርትራን ያሸነፍነው›› የምትለዋን የፊልሙን ‹‹ውዳሴ-ዘመለስ›› ስናደምጥ ነው)
የሆነ ሆኖ ‹‹ጀሃዳዊ ሀረካት›› የተሰኘውን ፊልም ስመለከተው እንደተለመደው ተራ ከመሆኑም በላይ እርስ በእርስ በሚጣረሱ ጭብጦች
የተሞላ ሆኖ አግኝቸዋለሁ (በዚህ ፊልም ላይ ከእነ ማስረጃዬ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)፡፡ ይሁንና ለነገ ሊተው የማይገባው አንድ ጉዳይ
ግን አለ፡፡ ይኸውም በመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በሚኒስትር ደኤታ ማዕረግ ምክትል ሀላፊ የሆነው አቶ ሽመልስ ከማል
ከሁለት ሰዓት ዜና በኋላ በታየው ‹‹ጀሃዳዊ ሀረካት›› ፊልም ላይ ያልተካተተ፣ ነገር ግን በእኩለሌሊቱ የኢቲቪ ስርጭት ወቅት በድንገት
የታየውን (ኡስታዝ አቡበከር ሁለት እጆቹ በካቴና ታስረው መርማሪዎቹ ለሚጠይቁት ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ የሚያሳየውን) ፊልም
በተመለከተ ለ‹‹ኢትዮ ቻናል›› የሰጠው ቃለ-መጠይቅ ነው፡፡ ለቁም ነገር ባይሞሉ ወሬዎች ከተሞላው የአቶ ሽመልስ ምላሽ ውስጥ እስኪ
አንዷን እንምዘዝ፡፡

No comments:

Post a Comment