Friday, March 15, 2013
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት
International Ethiopian Women's Organization
ከዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት የተሰጠ የድጋፍ ጥሪ !
ውድ አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ግዜ የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ለብሔራዊ የጋራ
ሕልውናዋ ሆነ የሕዝቧ ደህንነት ከመቼውም ግዜ በበለጠ ፣ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢና
አስጊ ወቅት ላይ ደርሷል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከመንጋቱ በፊት ይጨልማል
ነውና ፣ለጨለማ ግዜ የዳረገን ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ሆኖም ከጨለማ ወደ ብረሃን
መሸጋገር አይቀርም እና ከተሸጋገርን በዃላ ግን ይዘን መገኘት ያለብንን ብሔራዊ
እሴቶች እንዳናጣ ከወዲሁ በሁሉም ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል።
ከታሪክ እንደምንረዳው ሕዝብንና የራስን ማንነት ማጣት ይኖራልና ። የወያኔ ዘረኛ
የጎሳ አገዛዝ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በሴቶች ፣በክርስትናና በእስልምና
ሐይማኖት ተቋሞች በተለይም ደግሞ በቅርቡ በዐማራው ማህበረሰብ ላይ
የሚፈጽመውን በግፍ የማፈናቀልና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ባስቸኳይ ካልተገታ
ለትውልድ የሚተላለፍ ቀውስና ጥፍት ከፊታችን ተደቅኖ የሚጠብቀን መራራ ሃቅ
ነው።
እንደሚታወቀው ወያኔ የትግሬ ነጻ አውጭ ግንባር የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት
ለማፍረስና አገራችንን ለመበተን ከነደፋቸው እቅዶች ውስጥ ቀዳሚ ቦታ ከያዙት
አንዱና ዋነኛው የዐማራውን ማህበረሰብ በጠላትነት ፈርጆ ማጥቃት ፣ማዳከምና
ማጥፋት የሚለው ዓላማ ነው። በዓላማቸውም መሠረት ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት
በዐማራው ማህበረሰብ ላይ ይነጣጠር የነበረው ጥቃት ዛሬ በስፋትና በጥልቀት
ተፋፍሞ አሳሳቢና አደገኛ በሆነ ደረጃ በመካሄድ ላይ ነው። ላለፉት ጥቂት ወራት
በተለያዩ የአገራችን ግዛት ውስጥ የሚኖሩትን የዐማራው ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን
ከኑሮዋቸውና ከቤታቸው በማፈናቀል የህልውና መብታቸው ተገፎ ኢሰብአዊ የሆነ
ጥቃት እየተካሄደባቸው ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህጻናትና ሴቶች የመከራው
ገፈት ቀማሽ እንደመሆናቸው ሁሉ ለአሰቃቂ ችግርና እንግልት ተዳርገዋል። በአንጻሩ
ግን የኢትዮጵያ መሬት ለባእዳን አገሮች በገፍ እየተቸረቸረ ኢትዮጵያውያን ግን
ዐማራ ስለሆኑ ብቻ ከመሪታቸው ተፈናቅለው ለዱርና ለመንገድ አዳሪነት
ተዳርገዋል፣መሠረታዊ የመኖር መብታቸውን ተቀምተዋል።
ዛሬ የዐማራው ማህበረሰብ ለወያኔ ዘረኛ የጎሳ አገዛዝ የተቀነባበረ ኢትዮጵያዊነትን
የመበተን እቅድ ውስጥ ዋናውን ቦታ የያዘ ኢላማ ይሁን እንጂ ነገ በሌሎች
ኢትዮጵያውያን ላይ የሚከሰት መሆኑ የወያኔ ተግባራዊ ባህሪ ያረጋገጠው ሃቅ ነው።
ይህን አገር የማፍረስና ሕዝብን የማፈናቀል ሂደት ባስቸኳይ ማስቆም ፣ለዚህም
ችግርና መከራ የዳረገንን የወያኔ ዘረኛ ሥርዓትን ከመሠረቱ መንቅሎ ማስወገድ
አማራጭ የሌለው የወቅቱ የኢትዮጵያውያን ተግባር ሊሆን ይገባል። ስለዚህም ይህን
ተግባር ከግቡ ለማድረስ ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣
ንቅናቄዎች ፣የብዙሃንና የሞያ ማህበርት ሁሉ በሓይማኖት፣ በቋንቋ ፣በጎሳ፣ ሳንለያይ
በዐማራው ማህበረሰብ ላይ የሚደርሰውን ኢሰብአዊ ድርጊት በማውገዝ ችግሩ የጋራ
መሆኑን በመገንዘብ ሙሉ ድጋፋቸውንና ትብብራቸውን መግለጽ ተገቢ ይሆናል።
እንደሌሎች ኢትዮጵያዊ ጥያቄዎች የዐማራው ማህበረሰብ ችግርና ጥያቄ የሁሉም
ኢትዮጵያዊ ጉዳይና ጥያቄ ነው።በዐማራው ማህበረሰብ ላይ የሚካሄደው የመበተንና ዘር የማጥፋት ጥቃት በሁሉም
ኢትዮጵያዊ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት መሆኑን በመገንዘብ ፣ በአንድ ድምጽ ድርጊቱን
ማውገዝና ማስቆም የትግላችን አንደኛው ገጽታና አጣዳፊ የጋራ ተግባር ነው። ጥቃቱ
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያስከትለው አደጋ በዐማራው ማህበረሰብ ላይ ብቻ
ሳይወሰን በጋራ ህልውናችንና ደህንነታችን ላይ ጭምር ነው።
ባጠቃላይ በአገራችን ላይ በተለይም ሰሞኑን በሓይማኖት ተቋሞችና በዐማራው
ማህበረሰብ ላይ የሚፈጸመውን ግፍና ወንጀል ለማስቆም በሚደረገው ትግል የሴቶች
በሙሉ ወሳኝነት መሳተፍ አማራጭ የሌለው ታሪካዊ ግዴታ ነው። የሴቶች መብት
ያለ አገር ህልውና ሊከበር ስለማይችል አገርን ለማዳንም የሴቶች ሚና ወሳኝ
መሆኑን በመገንዘብ በዚህ አሳሳቢ ወቅት በድጋሚ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች
ድርጅት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የተግባራዊ ትብብርና የድጋፍ ጥሪ እናስተላልፋለን።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ !
ድል የኢትዮጵያ ህዝብ ነው !
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅት
መጋቢት, 2005 (March, 2013)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment