Sunday, March 31, 2013

“የኢህአዴግ እብሪትና ትዕቢት አገርንና ህዝብን የሚያጠፋ ነው”

አቶ ግርማ በቀለ 33ቱ ፓርቲዎች ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ

ፍኖተ ነጻነት መጋቢት 21 ቀን 2005 ዓ.ም.
የዛሬው እንግዳችን አቶ ግርማ በቀለ ይባላሉ ፡፡ አቶ ግርማ በቀለ በቅርቡ የትብብር ሠነድ የተፈራረሙት 33ቱ ፓርቲዎች ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ እና የኦሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት /ኦህዴህ/የተባለ ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- ፔቲሽን ፈራሚ ፓርቲዎች አሁን በምን እንቅስቃሴ ላይ ናቸው?
Ato Girma Bekele opposition politician based in Ethiopia
አቶ ግርማ በቀለ 33ቱ ፓርቲዎች ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ
አቶ ግርማ፡- የፔቲሽን ፊርማው ወደ ትብብር ሠነድ ከተሸጋገረ በኃላ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ የቀጣይ 6 ወራት ተግባር እቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ ትብብሩን ለሚቀጥለው 6 ወራት የሚመራ ቋሚ አስተባባሪ ኮሚቴ ለማስመረጥ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ እስከ አሁን ድረስ ስንቀሳቀስ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ከውስጥም ከውጪም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁን የደረስንበት ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- ትብብሩ ስስ ነው፤ ትንሽ ቆይተው አለመግባብት ይፈጥራሉ፤ሁሉም አብረው አይዘልቁም የሚሉ ወገኖች አሉና እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ግርማ፡- የማራቶን ውድድር አብረው የጀመሩ ሁሉ አይጨርሱም፡፡ እጅግ ውስብስብና ፈታኝ በሆነ ሠላማዊ ትግል አብሮ የጀመረ ሁሉ አብሮ ይጨርሰሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ትግሉ እየጠራና እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተራገፈና እየተንጠባጠበ ሊቀር ይችላል፡፡ እስከ አሁን በይፋ ለቅቄአለሁ ብሎ በይፋ መግለጫ የሰጠ ፓርቲ ባይኖርም በተግባር ግን እስአሁን አምስት ድርጅቶች ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል፡፡ ነገ ሌላ ሊቀጥል ይችላል፡፡ 15 ወይም 20 ፓርቲ ነጥሮ ቢወጣ አያስገርምም ቁምነገሩ ቁጥሩ ላይ አይደለም ዋናው ቁም ነገር ፓርቲዎቹ ሕዝብና አገር የሚፈልገውን ተግባር እያከናወኑ ናቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ከህዝብ የሚጠበቀው አመራሩን በቅርብ መከታተለና መቆጣጠር ነው፡፡ ድክመቶችንና ችግሮቹን ብቻ እየነቀሱ በማውጣት መተቸት ሳይሆን እኔንም ያገባኛል ብሎ ከትግሉ መቀላቀል ያስፈልጋል፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- ህዝብ ዘንድ እንዴት እንደርሳለን? ህዝቡንስ እንዴት ወደ ትግሉ እናስገባለን ብላችሁ ታስባላችሁ?
አቶ ግርማ፡- ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች ከህዝብ እንዳይገናኙ የማያደርገው ጥረት የለም፡፡ ህገመንግስቱን ጥሶ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት ፣ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ እየከለከለ ነው፡፡ እኛ ግን መብታችንን ተጠቅመን ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ በሚባልበት ሁኔታ የሚዲያ አፈና ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ያሉትን ሚዲያዎች ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎችን ድህረ ገጾችን በመጠቀም ዓላማችንን እናስተዋውቃለን፡፡ የየፓርቲዎችን መዋቅር እንጠቀምበታን፡፡ የሲቪክስ ማህበራትን መዋቅርም እንዲሁም የመንግስት ሚዲያዎችን እንጠቀማለን ፡፡ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ እንጠቀማለን፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- የወቅቱን የአገሪቱን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ግርማ፡- እንደ 33ቱ ፓርቲዎች በጋራ ገምግመን የደረስንበት ድምዳሜ የለም፡፡
ጥያቄህን እንደ ግል የማምንበትን ልመልስልህ፡፡ አገራችን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቀችበት ጊዜው ነው፡፡ አገራችን ዛሬ በማንኪያ የተያዘች፤ ከሥሯ ድንጋይ የሚጠብቃት እንቁላል ሆናለች፡፡ አገራችን በዚያ ድንጋይ ላይ ወድቃ እንዳትከሰከስ ሁላችንም እጃችንን ዘርግተን እንቁላሏን ለማዳን መጠባበቅ አለብን፡፡ የኢህአዴግ እብሪትና ትዕቢት አገርንና ህዝብን የሚያጠፋ ነው፡፡ የሀገራችን ሁኔታ አሁን ካለበት ወደ ባሰ ደረጃ እየተጓዘ ነው፡፡ ህዝብን እያገለለ ሚዲያን እያፈነ የተለየ ሐሳብ ያለውን ሰው እያጠፋ መጓዝ ይፈልጋል፡፡ ይህ ጉዞ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ህዝቡ ተረድቶታል፡፡ እባካችሁ ተባበሩና ምሩን ሲል ቆይቷል፡፡ እኛም ተባብረናል፡፡ ከእንግዲህ በቁርጠኝነት አገር የማዳን ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- አንዳንድ ወገኖች መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እየገባ ነው፣ የተወሰነን ብሔር ለማጥቃት የተነጣጠረ ዘመቻ ጀምሯል ይላሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ግርማ፡- ከጅምሩ የዚህን መንግስት አነሳስ ስንመለከት ገና በረሃ እያለ ዋና ጠላቶች ናቸው ብሎ የፈረጃቸው አሉ፡፡
ከብሔረሰብ አማራን ከሃይማት ኦርቶዶክስን በጠላትነት ፈርጇል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ እነዚህን ሁለቱን ማጥፋት ያስፈልጋል ብሎ አቀደ፡፡ ሁለቱም የአገርና የህዝብ ጠላቶች ናቸው በማለት እንደዓላማ ወይንም እንደ አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡ ከተለያየ ቦታ የተገኘ መረጃ የሚያለክተውም ይህንኑ ነው፡፡
ገና ትግራይ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ከየቤተክርስቲያኑ ካህናትን በማባረር ቤተክርስቲያኖችን በካድሬ ቄሶች እንዲመሩና እንዲተዳደር አድርጓል፡፡ የመንግስት ሥልጣን ከያዙበት ቀን ጀምሮ በአማራውና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ሲፈፀም የነበረውን ሁሉ የምናውቀው ነው፡፡ ይህን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡
ሰሞኑን በአማራው ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውንም ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የሃይማኖት ት/ቤታችንን ራሳችንን እናስተዳድር የሃይማኖት መሪዎቻችን እኛን አይወክሉም፤ መጅሊሳችንን ራሳችን እንሰይም፤ አህባሽ የተባለ ባዕድ አስተምሮ ከውጭ አምጥታችሁ አትጫኑብን፤ ብለው በሠላማዊ መንገድ የጠየቁ የተከበሩ የሙስሊሙ የሃይማት አባቶች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ድርጊት እየተመለከትን ነው፡፡ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ለሠላማዊ ትግል አስተማሪ በሆነና በሠለጠነ መንገድ ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡
መማር ለሚችል ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ትግስትና ሠላማዊ ተቃውሞን ተምሯል፡፡ የወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ህዝብን በሃይማኖት ከፋፍሎ ለማፋጀትና ዕድሜውን ለማራዘም ያደረገው ጥረት ከሽፎበታል፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት የጠየቁት ጥያቄ መንግስት በሃይማኖታቸው ጣልቃ እንዳይገባባቸው ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ከእንግዲህ ሙስሊሙ ክርስቲያኑ መላው የአገሪቱ ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ ይህን ሥርዓ ለመቀየር በቁርጠኝነት በጋራ መታገል ነው፡፡

Saturday, March 30, 2013


ከቤሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ አማሮች በጨካኙ የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት ወከባ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተሰማ

ቀደም ብሎ ከቤሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ አማራዎች፣ የደረሰባቸው እልቂትና እንግልት ሳያንሳቸው አሁን ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት እያስፈራሩዋቸውና እያዋከቧቸው መሆኑን ተፈናቃዮችን ያነጋገረው ዘጋቢያችን በላከልን ሪፖርት ገለጸ። እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው በምእራብ ጎጃም ዞን በፍኖተሰላም ከተማ ሜዳ ላይ ወድቀው የሚገኙት አማራ ተወላጅ አርሶደአሮች ከክልሉ ዋና ከተማ እና ከዞኑ የተውጣጡ የወያኔ ሆድ አደር ባለስልጣናት ትናንት ሰብስበው ያነጋገሩዋቸው ቢሆንም ፣ ሆድ አደር ባለስልጣናቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ መልስና ማስፈራሪያ የሰጧቸው መሆኑ ታውቋል።
ዘጋቢያችን አክሎ እንደገለጸው የወያኔ ሆድ አደር ባለስልጣናት ተፈናቃዮቹን ከተማውን ለቀው ወደ ወረዳቸው እንዲሄዱ ያስጠነቀቁዋቸው ሲሆን፣ የተቀሙትን ሀብትና ንብረት በተመለከተ ጥያቄ ሲያቀርቡ ደግሞ “ቀድሞ ማን ሂዱ አላችሁ አናውቅም” በማለት የመለሱላቸው መሆኑን ገልጿል።
ከቤሻንጉል ጉምዝ ተፈናቅለውና ከሞት ተርፈው ቀያቸው የደረሱትና በገዛ ቀያቸው ያለምንም መጠለያ ሜዳ ላይ ተጥለው የሚገኙት 2 ሺህ አባወራዎች፣ ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ በሽታ ተነስቶ ህጻናትና ሴቶች ሊያልቁ ይችላሉ በማለት ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ መሆናቸው ተያይዞ የደረሰን ዘግባ ያመለክታል።
በሌላ በኩል ደግሞ  አሁንም የቤንሻንጉል ጉሙዝን ክልል ለቀው ባልወጡ አርሶአደሮች ላይ የሚፈጸመው ግድያና እንግልት መጨመሩ የታወቀ ሲሆን የተፈናቃዮችን ሀብት ለመዝረፍ በተደረገ ሙከራ ትናንት አንድ ግለሰብ በጥይት ተመትቶ መሞቱና ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን ከስፍራው የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።


    ለማያዉቅሽ ታጠኚ

    ማስረሻ መኮንን ነኝ ከቃሊቲ
    እንደምን ሰነበታችሁ ግንቦቶች -  እቺ ደብዳቤዬ እንደምትደርሳችሁ አልጠረጠርም፤ ካልደረሰችም እርግጠኛ ነኝ እናንተዉ ፈልጋችሁ ታገኟታላችሁ።  ለመሆኑ እንደምን ከረማችሁ? ዘረኞቹ የወያኔ ካድሬዎች በዚያ ሰሞን ዉጭ አገር ካሉ ሽብርተኞች ጋር ትገናኛለህ ብለዉ ዘብጥያ ወርዉረዉኝ ይሄዉና ሳላናግራችሁ ሳታናግሩኝ ድፍን አንድ አመት አለፈን። መቼም የማይለመድ ነገር የለም መታሰርም ኑሮ ሆኖ ይሄዉና እስር ቤቱን ለመድኩት። ደሞስ የወያኔ እስር ቤት ለምን አይለመድ! ባልታሰር የማላገኛቸዉን ጓደኞቼን፤ ምሁራንንና፤ የእስልምናና የክርስትና እምነት ሊቃዉንትን እዚህ እስር ቤት ዉስጥ ነዉ እንዳሰኘኝ የማገኛቸዉ። ለሁሉም ምን አለፈችሁ ምን አነበብክ፤ ምን ጻፍክ፤ ምን አሰብክ፤ ማንን አሳደርክ እያለ የወያኔ ካድሬ በየቀኑ ከሚጨቀጭቀኝ እዚህ የአገሪቱ ምሁርና አዋቂ የበዛበት እስር ቤት ዉስጥ ብኖር ይሻላል ብዬ አትፍቱኝ ብያቸዋለሁ . . . . . . .  የሚሰሙኝ ከሆነ!
    ግንቦቶች የዛሬዉ ጉዳዬ  የእስር ቤት ኑሮዬን መተረክ አይደለም፤ ጉዳዬ ሌላ ነዉ። ግን ስለ ልጅነት ጓደኛዬ ስለ ታሪኩ ሳልነግራችሁ ባልፍ ቅር ይለኛል። ታሪኩ የወያኔን ፖሊሶች ግልምጫ ከምንም ሳይቆጥር ሁሌ እየመጣ የሚጠይቀኝ የልጅነት ጓደኛዬ ነዉ። ታሪኩ የሚበላ ምግብ ብቻ ሳይሆን የሚነበብ ጸሁፍም ይዞልኝ ይመጣል፤ እኔም የጻፉኩትን ለአንባቢ ያደርስልኛል። የሚገርመዉ ታሪኩ የኮድ ስሙ ሳይሆን እናቱ ያወጡለት ትክክኛ ስሙ ነዉ፤  ስሙን ልደብቅለት ስሞክር  . . .   ስሜን ይወቁት ምን ያደርጉኛል ብለህ ነዉ . . . .  አንተዉጋ ነዉኮ የሚያመጡኝ. . . . . . ደግሞስ በየቀኑ ከምመላለስ አንዱኑ አብሬህ ብታሰር ይሻላል የሚል ቆራጥ ሰዉ ነዉ ታሪኩ።
    ጓደኛዬ ታሪኩ በዚህ ሳምንት ይዞልኝ የመጣዉ መጣጥፍ ገና ገልጬ ሳላየዉ  ያ እጅ እጅ ያለኝ የኢህአዴግ አርማ ከሩቁ ታየኝና ቀና ብዬ ምነዉ ታሪኩ አልኩት።  አንብብ አለኝና ድምጹ ራቀኝ።  ምን ሆነ ብዬ ቀና ብዬ ስመለከተዉ ፖሊሶቹ እየገፈታተሩ ከእንግዳ መቀበያዉ ክፍል አስወጡትና ሳይሰናበተኝ ዝም ብሎ ሄደ። እኔም ወደ መኝታ ክፍሌ ገባሁና መጣጥፉን ማንበብ ጀመርኩ። ታሪኩ ሰጥቶኝ የሄደዉ ወረቀት የሚጀምረዉ የኢህአዴግ 9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ “በመለስ አስተምህሮዎች፤ ጠንካራ ድርጅትና የልማት ሀይሎች ንቅናቄ ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ባህርዳር ዉስጥ ይጀምራል እያለ ነዉ። ወረቀቱ ላይ የሰፈረዉ የዉሸት ብዛት እንኳን እኔን አንባቢዉን ጽሁፉን የተሸከመዉን ግዑዙን ወረቀትም የሚቀፍፈዉ ይመስለኛል።  ዮሐንስ ወንጌል ላይ የዉሸቶች ሁሉ አባት የተባለዉ ዲያቢሎስ ትዝ አለኝ። እርግጠኛ ነኝ ወያኔ ያኔ ቢኖር ኖሮ ዉሸት ሌላ አባት ይኖረዉ ነበር። በሦስት ገጾች ተቋጥሮ ከተቀመጠዉ የወያኔ የዉሸት ድሪቶ ዉስጥ አይኔ ያረፈዉ “በመለስ አስተምህሮዎች”፤ “ጠንካራ ድርጅት” ና “የልማት ሀይሎች ንቅናቄ” በሚሉ ሦስት ቱባ ቱባ ዉሸቶች ላይ ነበር። የወያኔዎች ነገር አንዳንዴ በጣም ይገርመኛል። ጥጋባቸዉና ትዕቢታቸዉ ሲፈጠሩ ጀምሮ የተደፈነዉን ጀሯቸዉን ጨምሮ ደፍኖታልና የኢትዮጵያን ህዝብ አይሰሙም እንበል . . . . . .  ግን እንዴት የክርስትና እምነታችን መሠረት የሆነዉ ትግራይ አፈር ላይ የበቀሉ ሰዎች ፈጣሪያቸዉን አይሰሙም!  እግዚአብሔር እኮ ሃያ አንድ አመት ሙሉ ታግሷቸዉ የገሀዱን አለም የመለስ ዜናዊን አስተምህሮ ብቻ ሳይሆን የአባ ጳዉሎስን የመንፈሳዊ አለም አስተምህሮም ስለተጠየፈ ነዉ ሁለቱንም ሰዎች ተራ በተራ የወሰዳቸዉ። ታድያ መምህሩንና ደቀመዝሙሩን ለሀያሉ እግዚአብሔር ቁጣ ያጋለጠዉን ክፉ አስተምህሮ እንደገና እዚህ ምስኪን ህዝብ ላይ ለመጫን የሚሞከረዉ ለምንድነዉ? ለመሆኑ የመለስ አስተምህሮ ምንድነዉ . . . . . . ስድብ፤ንቀት፤ ጥላቻ፤ ዘረኝነት፤ኢትዮጵያንና ታሪኳን መጥላት፤ አማራን በየሄደበት ማሳደድ፤ የኑሮ ዉድነት፤ ስደት፤ እስር፤ ግድያ፤ የመሬት ቅርምት፤ ብሔራዊ ዉርደት፤  . . . . . .  እስኪ ወያኔዎች እናንተ አራሳችሁ ንገሩኝ ምንድነዉ የመለስ ቅርስ ዬቱ ነዉ የመለስ አስተምህሮ?
    ግንቦቶች እዚህ ወረቀት ላይ ካነበብኳቸዉ ነገሮች ሁሉ የሰቀጠጠኝና አይኔን ማመን ያቃተኝ . . . . . . . 9ኛዉ የኢህአዴግ ጉባኤ የአገራችን የልማትና የዲሞክራሲ ጉዞ መሐንዲስ የነበሩት ጓድ መለስ ዜናዊ የሚታሰቡበት ጉባኤ ነዉ” የሚለዉን ሳነብብ ነዉ። ሃያ አንድ አመት ሙሉ የመጻፍና የመናገር መብቶችን አፍኖ፤ የሚቃወመዉን እየገደለና በአንድ አናሳ ብሄረሰብ የበላይነት ዙሪያ 90 ሚሊዮን ህዝብን ረግጦ የገዛዉ መለስ ዜናዊን የዲሞክራሲ መሐንዲስ ማለት ወይ ዲሞክራሲን ወይም ምህንድስናን አለዚያም ሁለቱንም አለማወቅ ይመስለኛል። ደግሞም እዉነቱን  ለመናገር መለስን የዲሞክራሲ መሐንዲስ ከማለት መንግስቱ ሀ/ማሪያምን የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አባት ማለት የሚቀል ይመስለኛል . . . . . . . . ትዝ የሚለን ከሆነኮ ኢትዮጵያ ዉስጥ የመጀመሪያዎቹ የክልል መንግስታት መንግስቱ የፈጠራቸዉ የትግራይ ራስ ገዝ፤ የኤርትራ ራስ ገዝ፤ የአሰብ ራስ ገዝና ኦጋዴን ራስ ገዞች ነበሩ።
    ለመሆኑ. ….  የመለስን ራዕይ ከግቡ ማድረስ ኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ ቢሆን ኖሮ ለምን አገሩን ለቅቆ እየተሰደደ በየዉቅያኖሱና በየበረሃዉ የእሳት እራት ሆኖ ይቀራል? እሲኪ ንገሩኝ እናንተ ወያኔዎች ምርጫችን የመለስን ፈለግ መከተል ቢሆን ኖሮ ቁጥሩ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ለምን “ድምጻችን ይሰማ” እያለ በየአደባባዩ በእናንተ ዱላ ይደበደባል? ደግሞስ በየቀኑ ስለማሪያም ስሙኝ እያለ የማትሰሙት የኢትዮጵያ ህዝብ እሱ እናንተን ለምን ይሰማል? እናንተ ወያኔ በአምሳያዉ የፈጠራችሁ የኢህአዴግ ቡችሎች እናንተም ስሙ . . . . . . . እስኪ ምን ይሁን ብሎ ነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የናቀዉን፤ የሰደበዉን፤ ያዋረደዉን፤ የገደለዉንና በዘረኝነት አለንጋ የለበለበዉን ሰዉ ራዕይ ከግቡ ለማድረስ ቃል የሚገባዉ? ወያኔም ሆነ ኢህአዴግ ወይም አግአዚ ጆሮ ካላችሁ ስሙ . . . . .  የኢትዮጵያ ህዝብ ቃል የገባዉ እናንተ በፈቃደኝነት ከተነቀላችሁለት ፈቃዳችሁን ለማክበር አለዚያም እሱ እራሱ ነቅሎ ሊያጠፋችሁ ነዉ።
    ኢህአዴግ ለ9ኛዉ ጉባኤ ሲዘጋጅ መሪ ቃል ብሎ ካስቀመጣቸዉ ሦስት ትልልቅ የዉሸት ድሪቶዎች ዉስጥ ሁለተኛዉ “ኢህአዴግ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ነዉ የሚለዉ አባባል ነዉ። ነገሩ “ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ”.. . . .  እንደሚባለዉ ተረት ሆኖ ነዉ እንጂ ገና ከጧቱ ሲፈጠር ጀምሮ ኢህአዴግ መች ጠንካራ ድርጅት ሆኖ ያዉቃል? የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚወክሉትን ህዝብ ብዛትና ያላቸዉን የፖለቲካ ጡንቻ ተገንዝበዉ እንቅስቃሴያቸዉን ከፖለተካ ጡንቻቸዉ ጋር ማገናዘብ ቢችሉ ኖሮ እዉነትም የኢህአዴግ ጠንካራ ድርጅት ተብሎ ሊጠራ ይችል ነበር፤የኛም ትግል ወያኔ የፈጠረዉን ስርአት ለመደምሰስ ሳይሆን እንማንኛዉም በሰለጠኑ አገሮች ዉስጥ እንደሚታየዉ የፖለቲካ ህደት ትግላችን በምርጫ ህዝባዊ ሀላፊነትን ለመቀበል ብቻ ይሆን ነበር።ኢህአዴግ በወያኔ አንጎል የሚያስብ፤ በወያኔ አፍ የሚናገርና የወያኔን መንገድ የሚከተል ተሳቢ ድርጅት በመሆኑ ነዉ ዛሬ አገራችን እጅግ በጣም አደጋኛ ቦታ ላይ የምትገኘዉ።
    ደግሞስ ዘረኞቹ የህወሀት መሪዎች የዘረፉትን መካፈል አቅቷቸዉ ሲጣሉ፤የኦህዴድ አባላት በአራት ቡድን ተከፋፍለዉ አንዱ የወያኔ ባሪያ ሆነን እንቀጥል ሲል ሌላዉ ደግሞ ነጻነቱን ለማወጅ እየተዘጋጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ምኑ ታይቶ ነዉ  የህአዴግ ጠንካራ  ድርጅት ነዉ የሚባለዉ? የሚንገዳገዱና በዉስጣቸዉ በተነሳ ቅራኔ የተነሳ ለመፍረስ አንድ ሐሙስ የቀራቸዉን ድርጅቶች ያቀፈዉ ኢህአዴግ እንዴት ሆኖ ነዉ ጠንካራ ድርጅት ሊሆን የሚችለዉ?ባለፉት አምስትና ስድስት ወራት በግልጽ እንደተመለከትነዉ ህወሀትና ኦህዴድ እርስ በርሳቸዉና አንዱ ከሌላዉ ጋር በፈጠሩት ከፍተኛ ቅራኔ የተነሳ ሁለቱ ድርጅቶች የረባ ስብሰባ እንኳን ማካሄድ አልቻሉም፤ እንግዲህ ይህ ኢህአዴግ ነዉ ጠንካራ ድርጅት ነዉ ተብሎ የሚነገረዉ።
    ይገርማችኋል በዘመነ ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ሆኗል። ዘላን ለክረምት እንደሰራዉ ቤት ለመፍረስ አንድ ሳምንት የቀረዉ ኢህአዴግ ጠንካራ ድርጅት ተብሎ ይወደሳል፤ የኢትዮጵያ ምሁር መዋያዉ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ቀርቶ ቃሊቲ ሆኗል፤ ጋዜጠኛም መደበኛ ስራዉ መጻፍ ሳይሆን መታሰር ሆኗል።ድምጻችን ይሰማ ብሎ የጮኸ ሽብርተኛ ተብሎ ይታሰራል፤ በምሽት በር እየሰበረ ህዝብን የሚያሸብር ጀግና ተብሎ ይሞገሳል። እንግዲህ ግንቦቶች የወያኔ ጉድ ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል? እንዲያዉ በደፈናዉ እነዚህ ዘረኞች አገራችንን ጉድ በጉድ አደረጓት ማለቱ የሚበቃ ይመስለኛል።
    የጋምቤላን ገበሬ መሬት ለትግራይ ባለሀብት ሰጥተዉ ጋምቤላዉ መሬቴን ሲል “ግንቦት ሰባት” ነህ ብለዉ ይጨፈጭፉታል። ፋሺስት ግራዚያኒ መታሰቢያ ሐዉልት አያስፈልገዉም ብለዉ የተቃወሙ ኢትዮጵያዉያንን አስረዉ መረጃ ካልሰጣችሁንና የብሔር ማንነታችሁን ካልተናገራችሁ አትፈቱም እያሉ ይደበድቧቸዋ። የሚገርመዉ ነጮቹ ፋሺስቶች እንኳን ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያዉያንን በአንድ ጀምበር ሲጨፈጭፉ ያልጠየቁትን የብሔረ ማንነት ዛሬ ጥቁሮቹ ፋሺስቶች አባቶቻቸዉን የጨፈጨፈ ሰዉ እንዴት መታሰቢይ ይሰራለታል ብለዉ የተቃወሙ ኢትዮጵያዉያንን አስረዉ የዬትኛዉ ብሔር አባል ነህ ብለዉ መጠየቃቸዉ በእርግጥም ማርሻል ግራዚያኒ ሀዉልት ሳይሆን የቆመለት እሱ እራሱ መልኩን ለዉጦ የመጣ ነዉ የሚመስለዉ።
    እንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ልብ ብለህ ነገሮችን አስተዉል . . . . .  ኢነዚህ ዳግማዊ ግራዚያኒዎች ናቸዉ በየክልሉ በአምሳያቸዉ የፈጠሯቸዉን አሻንጉሊቶች አቅፈዉና እራሳቸዉን ኢህአዴግ ብለዉ ሰይመዉ ከዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ድረስ ጉባኤ፤ እድገት፤ ህዳሴ፤የመለስ ራዕይና ትራንስፎርሜሺን እያሉ እያደነቆሩህ የሚከርሙት። እነዚህ ከመልካም አስተዳደር ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑ ጉዶች ናቸዉ ሰልመልካም አስተዳደር ለሰብኩህ የሚሞክሩት። ለኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ኢህአዴግ ብዙ የሚነገረዉ ያለ አይመስለኝም . . . . . ሃያ አንድ አመት ሙሉ እንደቋጥኝ ተጭነዉበት ጀርባዉን አጉብጦታልና ያዉቀዋል። ኢህአዴግ የራሱ የሆነ ማንነት ያለዉ እዉን የሆነ ድርጅት ሳይሆን ህወሀት የራሱን እዉነተኛ ማንነት ለመሸፈን እንደብረት ቀጥቅጦ የሰራዉ የማታለያ ሽፋን ነዉ። ለዚህም ነዉ በድምሩ 439 የፓርላማ ወንበር ያላቸዉ ሦስቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች 38 ወንበር ላለዉ ለህወሀት እየሰገዱ የሚኖሩት። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አህያ ሜዳ ለሜዳ ሳሯን እየጋጠች ብትበላ ወይም እንደሰዉ ልጅ ምግብ ተሰርቶላት በሳህን ብትበላ አህያ መባሏ አይቀርም . . . . . . ኢህአዴግም እንደዚሁ ነዉ። ዘጠኝ ግዜ ቀርቶ ዘጠና ዘጠኝ ግዜ ጉባኤ እያለ ቢሰበሰብና የራሱን ብጤ ደካማና አድር ባይ ምሁራንን በየጉባኤዉ ቢያሳትፍ  አህያ ለመሸከም እንደተፈጠረች ሁሉ ኢህአዴግም እንደጋሪ ለመጎተት የተፈጠረ ድርጅት ነዉና ኢህአዴግነቱን አይለቅም።ከዛሬ ጀምሮ እስከማክሰኞ ድረስ በቴሌቪዥን የምንመለከተዉ ድራማ አላማዉ አንድና አንድ ብቻ ነዉ . .  . . . . እሱም አስቀያሚዉን ኢህአዴግ ሊፕስቲክና የፊት ማሳመሪያ ቅባት እየቀቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማሳየት ነዉ . . . .መቼም የወያኔ ነገር ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ እንደሚሉት ሆኖ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብማ ኢህአዴግ ገና  ጉባኤዉን ሳይጀምር ነዉ .. . . . . ለማያዉቅሽ ታጠኚ ብሎ የተረተበት።


      ኢትዮጵያ የገጠማት ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት ወያኔና ነጋዴዉን ማጨቃጨቁ ተነገረ

      ካለፈዉ አመት አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ  የመጣዉ የዉጭ ምንዛሬ ክምችት በፈጠረዉ ችግር የተነሳ የንግዱ ህብረተሰብና የወያኔ አገዛዝ ታይቶ የማይታወቅ ጭቅጭቅ ዉስጥ መግባታቸዉን አንድ በቅርቡ ንብረታቸዉን ሽጠዉ ወደ አዉሮፓ የመጡ ኢትዮጵአዊ ነጋዴ ተናገሩ። እኚህ ላለፉት 17 አመታት በዉጭ ንግድ ስራ  ላይ ተሰማርተዉ የነበሩ አቶ አሀዱ ወሰንየለህ የተባሉ ነጋዴ እንደተናገሩት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ከፍተኛ የዶላር እጥረት ተከትሎ ነጋዴዎች ላለፉት 8 ወራት  እቃዎችን ወደ አገር ዉስጥ ማስገባት አልቻሉም፤ አንደ አቶ አሀዱ አባባል በአሁኑ ወቅት ከዉጭ አገር የሚገቡ ዕቃዎችን የሚያስገባዉ የወያኔ አገዛዝ ብቻ ሲሆን አገዛዙ የሚያስገባዉ ደግሞ  የግንባታ እቃዎችን ብቻ በመሆኑ የዉጭ ምንዛሬዉ እጥረት የገበያ መዛባት፤ የዕቃዎች እጥረትና የዋጋ ግሽበት እንዲከስት አድርጓል ብለዋል።
      ግራ የተጋባዉ የወያኔ አገዛዝ ሰሞኑን ለነጋዴዎች ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት በዉጭ ንግድ ዘርፍ ዉስጥ የተሰማራ ማንኛዉም ነጋዴ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚችል ግልጽ ያደረገ ቢሆንም በአዲሱ መመሪያ መሰረት የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ ነጋዴዎች በቅድሚያ የጠየቁትን ያክል ገንዘብ በብር ለባንኮች የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። ለምሳሌ 100 ሺ ዶላር የሚጠይቅ ነጋዴ ቢያንስ አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር በቅድሚያ ለባንኮች የማቅረብ ግዴታ አለበት። ይህንን አዲስ አሰራር የንግዱ ህብረተሰብ በፍጹም እንዳልተቀበለዉ የሚታወቅ ሲሆን በነጋዴውና በወያኔ አገዛዝ መካከል ዉዝግብ የፈጠረዉም ይሄዉ አዲሱ መመሪያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የመለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ ብዛት ያላቸዉ ሰዎች ገንዘብ ማሸሽ በመጀመራቸዉ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት መከሰቱ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈዉ መስከረም ወር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ እንደተረከበ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምንም አይነት የዉጭ ምንዛሪ እጥረት አለመኖሩን መናገሩ የሚታወስ ነዉ።
      ኢትዮጵያ ዉስጥ የተፈጠረዉን የዉጭ ምንዛሬ እጥረት አስመልክቶ አስተያየታቸዉን እንዲሰጡን የጠየቅነቸዉ አንድ የአኮኖሚክስ ምሁር የወያኔ አገዛዝ የገንዘብ እጥረት ቢያጋጥመው አይገርምም፣ ከመለስ ሞት በኋላ የወጡ ወጪዎችን እንኳን ብናይ፣ ይህች ደሀ አገር  ያለአቅሟ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ  አውጥታለች ካሉ በኋላ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀብር ማስፈጸሚያ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ፤ የብሄር ብሄረሰቦች በአል ለማክበር ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ የመከላከያ ቀንን ለማክበር ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።  አሁን በቅርቡ ደግሞ የወያኔ ኢህአዴግን ጉባኤ ለማካሄድና  የአባይን ግድብ ሁለተኛ አመት ለማክበር ከፍተኛ ገንዘብ ከመንግስት ካዝና ወጪ ሆኗል ። እንግዲህ እንደዚህ አይነት ከፍተኛ መጠን ያለዉ ገንዝብ ከልማት ጋር ባልተያያዘ መንገድ እየወጣ አገሪቱ የገንዘብ እጥረት ገጠማት ቢባል የሚገርም ሊሆን አይገባም  ብለዋል።
      • facebook

      Friday, March 29, 2013

      “ሀገሬ ገመናሽ” (ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ፣ ክፍል ሁለት)

      በየፍርድ ቤቶችሽ የፍትህ ውርጃ ሲፈፀም ዝም አልሽ።
      ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ
      ልዕልና ጋዜጣ
      ምንጭ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ብሎግ

      በቀደም ሳት ብሎኝ፣
      ለመጀመሪያ ልጄ ብቻ የፈረንጅ ሸራ ጫማ ገዝቼ ገባሁ። ያለወትሮዬ ማለቴ ለወትሮው ገበያ የምወጣው ሁለቱንም ልጆቼን ይዤ ስለነበረ ነው። ታዲያ ያን እለታ ማታ ትልቅዋ ልጄ ጫማውን ስትለካ፣ የታናሽ እህትዋ አይን ከሚለካው ጫማ ጋር ሲንከራተት ተመለከትኩ፤ ወይም የተመለከትኩ መሰለኝ። ‹‹ከወደድሽው ላንቺም ይገዛልሻል›› አልኳት፤ የትንሽዋን ልጄን አይን እየሸሸሁ። በውስጤ አድሏዊነት ተላወሰ። በልጅትዋ ህሊና ውስጥ ይህ ስሜት እንደማያድር ባውቅም፣ የእኔን ሃሳብ ግን ቶሎ ላስወግደው አልቻልኩም። አየሽ ሀገሬ? እንኳን ህዝበ አዳምና ሔዋንን በእኩልነት ቤት ሆኜ አኖራለሁ የሚል ሀገር፣ አንድ ተራ ምስኪን ወላጅ እንኳን በጎጆው አድሏዊነት እንዳይሰፍን ይጥራል። አንቺ ግን ሀገሬ! … አንቺ ግን ዝሆንና ጥንቸል እያፋለምሽ ለአሸናፊው ታጨበጭቢያለሽ፤ ትሸልሚያለሽ።
      መቼም ማንም ቢሆን፣ የአደባባይ ውበቱን እንጂ የጓዳ – ጎድጓዳ ገመናውን ሲነግሩት አይወድምና አንቺም ከአደባባይሽ ጀርባ መዝለቄ እንደማይጥምሽ አውቃለሁ። አደባባዮችሽማ ለዜጎችሽ የጋራ ፍትሀዊ መኖሪያነትሽን ይመሰክሩልሻል። መቼም የዜጋ ሁሉ እኩልነት የሚረጋገጠው በህግ ፊት ባለው እኩል መብት አይደል? ይህ ደግሞ ከገጠር ቀበሌሽ አንስቶ እስከ መዲናሽ ባሉ አደባባዮችሽ የሚታይ ነው። የወረዳ ፍርድ ቤት፣ የዞን ፍርድ ቤት፣ የክልል ፍርድ ቤት፣ የፌደራል ፍርድ ቤት፣ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሰበር ሰሚ ችሎት… የፍትህ ቢሮ… ይህ ሁሉ አደባባይሽን ያደመቅሽበት የዜጎችን እኩልነት ማስጠበቂያ ተቋም ነው። ሀገሬ! ለመሆኑ በእነዚህ ተቋማት ምን እያደረግሽ እንዳለሽ ታውቂያለሽ?
      አንዳንዴ ሳስበው ፍርድ ቤቶችሽና የፍትህ ተቋማቶችሽ ለዜጎች እኩል ያለመሆናቸውን የምታስታውቂበት ስፍራ ይመስለኛል። ይህን ስትሰሚ እንደምትቆጪ አውቃለሁ። ገመናው ሲሸፈንለት እንጂ ሲገለጥበት የሚወድ ማን አለ! አሁን እስቲ አንቺ ህግ አቁሜያለሁ፣ ዳኛ ሰይሜያለሁ ትያለሽ? ሀገሬ ሙች አፍሽን ሞልተሸ አትይም። ምነው ብትይ እማኝ ጠቅሼ እሞግትበት ሞልቶኛል።
      አንድ አትዮጵያዊ ለትምህርት ውጭ ሄዶ ሳለ፣ በፈቀድሽው ከታክስ ነፃ መብቱ ተጠቀመና አውቶሞቢል ገዝቶ መጣ። አንቺንና ያቆምሽውን መንግስት እያሞገሰ አራት አመት በአውቶሞቢሉ ተጠቀመና ተመልሶ ለትምህርት ሄደ።
      ባለቤቱ ደግሞ አሁንም አንቺንና መንግስቷን እያመሰገነች ስትነዳ፣ አንድ ቀን በጉምሩክ አሳሽ ጓዶች ተያዘች። መቼም ‹‹ለምን?›› ማለትሽ አይቀርም። የመኪናው ሊብሬ በባለቤትዋ ስም ስለነበር፣ አንቺ በአውቶሞቢሉ መገልገል አትችይም ተብላ፣ ተያዘች። መኪናው ታሰረ። አጣሪ ተቋቋመ። አጣሪው አጣርቶ ‹‹ባለመብቱ ባለቤትዋ በመሆኑ፣ በአውቶሞቢሉ መጠቀም መብትዋ ነው›› ብሎ ሪፖርት አቀረበ። ኮፒው ደግሞ ለሴትየዋ ደረሰ። ታዲያ ሀገሬ ጉዳዩ የቀረበለት የጉምሩክ ባለስልጣን፣ ቀረጡን ትከፍያለሽ አላት። ተያይዞ የቀረበውን ሪፖርት ተመልክቶት እንደሁ ጠየቀችው። አለመመልከቱን፣ ቢመለከተውም እንኳን ሪፖርቱ እግዚአብሔርም ቢመጣ ከመክፈል እንደማያስጥላት፤ ካልከፈለች መኪናዋ ጉምሩክ ውስጥ እንደሚታሸግበት ነገራት።  ሀገሬ፣ ሴትየዋና ባለስልጣኑ ሁለቱም ያንቺ ዜጎች፣ ሁለቱም ኢትዮጵያዊ ናቸው። ቆይ ህግሽ ላይ ‹‹አንድ ኢትዮጵያዊ›› የሚለው ሀረግ ማንን አስበሽ ያሰፈርሽው ነው? እና ሴትዮዋ ሃምሳ አራት ሺህ ብር ከፈለች። ከመክፈልዋ በፊት ግን ሀገሬ ሙች አልቅሳ ለምናዋለች። ከእግዚአብሔር በላይ ያስቀመጥሽውን ዜጋ መለመን እንጂ ምን መፍትሔ አለ! ባለቤትዋ ይህን ሲሰማ መጀመሪያ ያዘነው ባንቺ አይደለም። ባስቀመጥሽው ባለስልጣን ትእቢትና ድንቁርና ተደነቀ። ህግ ፊት አቅርቦ፣ ባለቤቱ በህግ የተሰጣትን መብት የሚጥስበት ከህግ የከበረ መብት እንደሌለው ሊያሳየው፣ ባለስልጣኑን ህግ ፊት ሊገትረው ከአውሮፓ ሲበር መጣ፤ ጠበቃ ቀጠረ።
      በቀጠሮው ቀን እሱና ጠበቃው ማልደው ፍርድ ቤት ደረሱ። ተከሳሽ አልቀረበም። የመስሪያ ቤቱ ጠበቃ እንኳን አልቀረበም። ዳኛዋ ሌላ ቀጠሮ ሰጡ። በቀጠሮውም ቀን የቀረበ የለም። ዳኛዋ ባለስልጣኑ ፍርድ ቤቱን ማዋረዱን፣ ከአንዴም ሁለቴ በቀጠሮ አለመቅረቡን ከምንም ሳይቆጥሩ ፍርዱን ገመደሉት። ባለስልጣኑ ትክክል መሆኑን፣ ሴትየዋ መያዛቸው፣ ገንዘቡንም መክፈላቸው አግባብ መሆኑን ፈረዱ።
      ሀገሬ፣ ያ ከአውሮፓ የፍትህ ጥማት ሲያበር ያመጣው ሰው፣ በፍትህ መዶሻሽ የተጨፈለቀ ዜግነቱን ይዞ ወደአውሮፓ ተመለሰ። አየሽ ሀገሬ! ለዚህ ነው የምሞግትሽ፤ እኛን ዜጎችሽን ከወባ፣ ከተስቦ ብትፈልጊም ከኤች.አይ.ቪ በላይ የጎዳን በየፍርድ ቤትሽ በህግ የበላይነት ለማያምን  ዳኛ ያስጨበጥሽው መዶሻ ነው።
      እንዴ እውነቴን እኮ ነው! ሀገሬ ሙች እውነቴን ነው። ለወባው፣ ለተስቦውና ለኤች.አይ.ቪ.ው እድሜ ለቱጃሮቹ ጓደኞችሽ እንጂ፣ መች መድሀኒት ይገደናል- መርከብ ሞልተው ይልኩልናል። ደግሞ ብንሞትስ! እድር አለን እንቀበራለን። ቆይ እድር ባይኖረንስ! ደግሞ ለመቅበር! አበሻ እንኳን ሞተሽለት ገና በጣር ተይዘሽ፣ ላይ ላዩን መተንፈስ ስትጀምሪ ነው ጉድጓድ መቆፈር የሚጀምረው። ግን ሀገሬ እንዲህ በቁማችን በፍትህ መዶሻሽ ስንሰባበር፣ እነዚህ የወባና የተስቦ መድሀኒት በመርከብ ሞልተው የሚልኩልን ጓደኞችሽ አንቺንም ሆነ መንግስትሽን ሀይ አላሉልንም። እና ሀገሬ፣ ይህ የአንቺ ብቻ ሳይሆን የነሱም ገመና ነው።
      ቆይ እኔ የምለው መንግስት ከህግ በላይ ነው እንዴ!? እስቲ ንገሪኝ ሀገሬ- መንግስት የሆኑት ከእኛው መሀከል፣ እንደኛው ዜጋ የነበሩት አይደሉም እንዴ! ዜጎችሽ አይደሉም እንዴ ‹‹መርጣችሁናል›› ብለው መንግስት የሆኑት! ታዲያ ለምንድነው የፍትህ መዶሻሽ እነሱ ላይ ቄጠማ የሚሆነው? ይኽው በአንቺ ውስጥ ከልጅነት እስከ እውቀት ስኖር መንግስት ከሳሽም ተከሳሽም ሆኖ ሲረታ እንጂ ሲፈረድበት አይቼም፣ ሰምቼም አላውቅም። ምን ያስቃል ሀገሬ! በእርግጥ ገንዘብን፣ ወይም ደግሞ ሌሎች ቀለል ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ አንድ ሁለት ፋይሎች በመንግስት ካሳ ከፋይነት እንዲዘጉ አድርገሽ ሊሆን ይችላል። ይህን ተይና እውነት ሀገር ከሆንሽ፣ እስቲ በሰብአዊና በዜግነት መብት ጉዳይ መንግስትን ከስሶ ያሸነፈ አንድ ዜጋ ጥሪ! እረ ጉደኛ ነሽ፣ ሀገሬ!
      እኔ የምልሽ የህግ ትምህርት ቤት፣ ምናምን ምን ያደርግልሻል? ለምን አምስትና ስድስት ዓመት ህግ ታስተምሪያለሽ? ለእኛ ለዜጎችሽ ያቆምሽው፣ ህግ እንዳይዛነፍ፣ በየፍርድ ቤቱ ያስቀመጥሽው መዶሻ አናት አናታችንን እያለ ቅስማችንን እየሰበረ፣ ከዜግነት ተራ እንዳያስወጣን አይደለም እንዴ! በአንቺ በሀገሬ ህግ፣ እንኳን መርጠኽኛል፣ ያለ ባለስልጣንና መንግስት ቀርቶ፣ እየሱስ ክርስቶስም ቢሆን፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ አብሮኝ ቢኖር፣ በህግ ፊት እኩል ነን። አቦ ሀገሬ በፍትህ ስም የምትሰሪው ግፍ በዛ! የምር በዛ። ወይ በቃ የህግ ትምህርት ቤቶችሽን ዝጊና ዳኛ ለምታደርጊያቸው ዜጎች እንዴት የባለስልጣንንና የመንግስትን የስልክ ትእዛዝ ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አንድ ሁለት ሳምንት አሰልጥነሽ … በቃ!
      አንዳንዴ ሳስበው ያ ታከለ የሚመኘውን ምኞት እኮ ሁላችንም ልንመኘው ነው! ሀገሬ መቼም ታከለን ታውቂዋለሽ። ለነገሩ አንዳንዶቹን አውቀሽ ችላ ትያቸዋለሽ እንጂ፣ አንቺ ዜጋሽ መቼ ይጠፋሻል። እሱም አንዱ ፍትህ መከበር አለበት፤ ያለ ህግ የበላይነት ሀገርና ህዝብ አይቆምም፣ ባይ ነው። ታዲያ የውልሽ፣ ከአመት ተመንፈቅ በፊት የቢ.ፒ.አር አሰራሩን ተቃውመሀል ተብሎ ከስራ ታገደ። ሁለት ወር ያለ ስራ ደመወዝ በላ። በሶስተኛው ወር ደመወዙ ቆመ። ሀላፊውን ሊያነጋግር ሄዶ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤውን ተቀብሎ መጣ። ታዲያ ያን ሰሞን እቤቴ መጣና፣ ‹‹ገንዘብ አበድረኝ›› ሲለኝ፣ ያው እንደወትሮው ወር መዳረሻ ገዶት ይሆናል፣ ብዬ ‹‹ስንት መቶ?›› ስለው ‹‹ሰባት ሺህ›› አይለኝ መሰለሽ!? መስሪያ ቤቱን ሊከስ እንደሆነም ነገረኝ። ገንዘቡን ለጠበቃና ለአንዳንድ ተጨማሪ ወጪ ፈልጎ ነው። ባንክ በቆጠብኩት ሁለት ሺህ ብር ላይ ከባለቤቴ ቤተሰቦች አምስት ሺህ ብር ተበድሬ ጨምሬ ስሰጠው ‹‹ተው! ይቅርብህ! የመስሪያ ቤቱን ባለስልጣን የሾመው መንግስት ነው። መንግስት ደግሞ ከሶም ተከሶም ይረታል። ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከሰስን አስብ። ቃሉ ቢለወጥም ያው መንግስት ማለት ንጉስ ነው። ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል፣ መስሪያ ቤቶችና መንግስት ያላቸው ልዩነት የተዋረድ ብቻ ነው›› አልኩት። ሀገሬ ሙች አልሰማኝም። እንዲያውም አልሰማ ቢለኝ በየመስሪያ ቤቶቻቸው የተሰየሙ ትንንሽ መንግስታትን ከሰው አቅላቸውን የሳቱ፣ ‹‹ቂጣቸውን በሳንጃ የተወጉ›› ዜጎችን በየዘመኑ ማየቴን፣ ገመናሽን ገልጬ ነገርኩት። አልሰማ ብሎ ፋይሉን በወረዳ ፍርድቤት ከፈተ።
      በወረዳ ፍ/ቤትሽ የክስ ፋይል በከፈተ በአራት ወሩ የውሳኔውን ወረቀት አምጥቶ አሳየኝ ሀገሬ ሙች እልሻለሁ ገረመኝ! አንቺ እኮ ትገርሚያለሽ! የፍርድ ቤቱ የፍርድ ውሳኔ ከማህተሙና ከፊርማው ልዩነት በስተቀር፣ ያው የተባረረበት ደብዳቤ ግልባጭ ነው። አዘነ። ሀገሬ ሙች አዘነ። የፍትህ መዶሻሸ ያረፈበትን አናቱን ቀና አድርጎ መመልከት አቃተው።
      ታከለ ግን የዋዛ ዜጋ አይደለም። ‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል››ን እየተረተ ይግባኝ አለ። ይኽው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰው ሰርቶ በየወሩ ደመወዝ ሲቀበል፣ እሱ በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች፣ የተባረረበትን ደብዳቤ እያፀደቀ ይመጣል።
      እና ታከለ ምን ተመኘ መሰለሽ! ሀገሬ ሙች እንደገመናሽ ዝግናኔ የግል ፍርድ ቤት ቢመኝ አይፈረድበትም። አንድ እሁድ ቀን አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ተቀምጠን ማኪያቶ ስንጠጣ፣ ከመንገዱ ባሻገር ያለውን የግል ሆስፒታል እየተመለከተ ‹‹በህይወት ዘመኔ ማየት የምመኘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ?›› አለኝ። ‹‹ምን›› አልኩት፤ ቁብ አልሰጠሁትም። ‹‹እዚያ ህንፃ አናት ላይ በግል ሆስፒታሉ ስያሜ ምትክ ‹‹ብርሃን ከፍተኛ የግል ፍርድ ቤት፣ መለያችን ይግባኝ አልባ ፍርዳችን ነው!›› የሚል ተጽፎ ማየት። ሀገሬ ሙች አያስቅም! ደግሞ ሰው እንጂ ሀገር ሲስቅም ሲያለቅስም አያምርበትም።
      እውነቱን እኮ ነው! በመንግስት ፍርድ ቤት መንግስትን መርታት ካልተቻለ፣ ለምን በግል ፍርድ ቤት አይሞከርም። በቃ ሀገሬ አንቺም የፍትህ ገመናሽን መክላት ካማረሽ፣ በቃ የግል ፍርድ ቤት ክፈቺ። እና የመንግስት ፍ/ቤቶች በዜጎችሽ መካከል ያለን ክስ ይመልከቱ። በማንኛውም ሁኔታ በመንግስትና በዜጋ መካከል ያለን ክስ ደግሞ በግል ፍርድ ቤት እንዲታይ አድርጊ። ያኔ የዜጎችሽ አናት መንግስት ለዳኞችሽ ባስጨበጣቸው መዶሻ አይነደልም። ዜጎችሽ ቀና ብለው ይሄዳሉ፤ ስለፍትህ ስርአትሽም መልካሙን አብዝተው ይናገራሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ አንቺ ደስ ይልሻል። አንቺ ደስ ሲልሽ ደግሞ እኛም መልሶ ደስ ይለናል።
      ስለፍትህ ገመናሽ ስናገር የሰሙ አንዳንድ ዜጎችሽ፣ ‹‹እንዴት ሰው፣ ከሰው ገመና አልፎ የሀገርን ገመና አንድ — ሁለት — እያለ ያብጠለጥላል!›› እያሉ ያብጠለጥሉኛል። እኔ ምን ተዳዬ! ሀገሬ አንቺ ራስሽ ገመናሽን መች ሸፈንሽውና እኔ እኮነናለሁ? እንዴ! የምር እኮ ነው የምልሽ! ገመናሽን እንደጋለሞታ ደጃፍ ገልጠሽዋል እኮ! አንቺ ራስሽ አይደለሽ እንዴ ተቃዋሚ፣ አሸባሪ፣ አክራሪ ብለሽ ዜጎችሽን ባሰርሽ ማግስት አኬልዳማ፣ ጀሀዳዊ ሐረካት– ምናምን የሚል ፊልም እየሰራሽ የፍትህ – ገመናሽን ቲቪ ያስገባሽው! እውነት ሀገሬ ያሳፍራል።
      ለዚህ እኮ ነው መንግስት የገባበት ክስ የዝሆንና የጥንቸል ፍልሚያ ነው የምልሽ። ያውም ሮጣ የማታመልጥ እግርዋ የተሰበረ ጥንቸል! ሲጀመር ለመንግስት ዝሆንነትን ሰጥተሻል። ጠመንጃ አለው፤ እስር ቤት አለው፤ ቲቪ አለው፤ ራዲዮ አለው፤ ዳኛ አለው፤ አቃቤ ህግ አለው። ይህ ሁሉ ካለኝ ደግሞ እኔም ብሆን፣ ዝሆን መሆን አያቅተኝም። ተቃዋሚ፣ ሽብርተኛ፣ አክራሪ ተብሎ የተመረጠው ደግሞ ጥንቸል ነው። ጥንቸል ከዝሆን ቢፋለም እድሉ አንድ ነው- ሮጦ ማምለጥ። አንቺ ግን ሀገሬ! ጥንቸሎችሽ በፍትህ ስርአትሽ ሮጠው ነፃ የሚወጡበት የመርፌ ቀዳዳ የምታህል ቀዳዳ እንኳን እንዳትኖር፤ ክሳቸው እንኳን ወጉ ተነቦላቸው የእምነት – ክህደት ቃላቸው ሳይሰማ፣ እንዴት እንዳከረሩ፣ እንዴት እንዳሸበሩ ፊልም ሰርተሽ በቲቪ ትለቂዋለሽ። በፍትህ አደባባይ ሮጠው እንዳያመልጡ የጥንቸሎቹን እግር ስብርብር አደርገሽ ማለት ያኔ ነው! .. ኧረ በእውነት ይዘገንናል! አባቶቻቸው ተጠርጥረው ከተከሰሱበት ወንጀል ነፃ የሚወጡበትን ቀን የሚናፍቁ ልጆችን … እናቶቻቸውን.. ጎረቤቶቻቸውን… አስቢ እስቲ! አንቺ በእነሱ ቦታ ብትሆኚና ፍትህን ያስከብርልኛል ያልሽው መንግስት በተጠረጠሩብሽ ላይ፣ እንደዚያ ያለ ፊልም እያቀረበ የፍትህን ጽንስ ለውርጃ ሲዳርግ ብትመለከቺ ምን ትያለሽ! ምንስ ታደርጊያለሽ! ዳሩ አንቺ ሀገር እንጂ ዜጋ አይደለሽም። ዜጋስ ብትሆኚ እግሮችዋ የተሰበሩ ጥንቸል ሆነሽ መታገል ከማይሰለቸው ዝሆን ፊት ብትቆሚ እጣሽ ምንድነው? አቦ ሀገሬ ተይኝ! ገልጠው የማይጨርሱት ገመና አድሎሻል!
      (ይቀጥላል)

      መድረክ አገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች አለ

      የግንባሩን ማኒፌስቶ ይፋ አድርጓል
      የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፤ኢትዮጵያ መስቀነኛ መንገድ ላይ ደርሳለች አለ፡፡medrke
      መድረክ ይህን ያስታወቀው መጋቢት 17 ቀን 2005 ዓ.ም በግንባሩ ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ ግንባሩ ዛሬ “የኢትዮጵያን ወቅታዊ፣መሰረታዊ ችግሮች መፍቻ ማኒፌስቶ” ያለውን ባለ12 ገፅ ሰነዱን ይፋ አድርጓል፡፡ ሰነዱ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል የሰነዱን አስፈላጊነት የሚያብራራ መግቢያ የያዘ ሲሆን በክፍል ሁለት የሀገሪቱን ችግሮች በዝርዝር አብርርቶ የመፍትሄ ሀሳቦችን ዘርዝሯል፡፡ በመጨረሻም ባለስድስት ነጥብ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ ከተላለፈው ጥሪ ውስጥም የብሔራዊ አንድነት መንግስት በጥምረት መቋቋምን የሚጠይቅ ነው፡፡
      መድረክን ወክለው መግለጫውን ከሰጡት አመራሮች መሀከል አቶ ጥላሁን እንደሻው፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ይገኙበታል፡፡ ከመግለጫውም በኋላ ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡   

      ምንጭ፡ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ

      Thursday, March 28, 2013


      መልካም መሪ ማግኘት ምንኛ መታደል ነው?!

      በታምሩ ገዳ
      በየትኛውም የእድገት  ደረጃ  ይሁን የፖለቲካ  አመለካከት ወይም የሃይማኖት  ስርአት  ውስጥ ለሚገኝ ማህበረሰብ ሁነኛ መሪ ማግኘት ከእድሎች ሁሉ ትልቁ እድል ነው  ቢባል ማጋነንPope Francis breaks with tradition and refuses to move into a palatial apartment  አያስብልም፡፡
      ለዚህ ይመስላል የሮማ  ካቶሊክ ቤ\ክርስቲያን   በቀርቡ 266ኛዋን  መሪ (ፓፓ ) ለመምረጥ የሃይማኖቱ አባቶች  በቫቲካን ከተማ  በተሰባሰቡበት  ወቅት በ 150,000ዎች  የሚቆጠሩ ምእመናን ቀጣዩ የሃይማኖታችን አባት  ማን ይሆኑ? በማለት  የምርጫው ውጤቱን ለማወቅ  በታላቁ  የቅዱስ  ጴጥሮስ  አደባባይ ተሰባስበው የነበረው፡፡ በዚህ የምንፈስ  ቅዱስ መሪነት  በተካሄደው  የመጪው  የቤተክርስቲያኒቱ  መንፈሳዊ አባት መረጣ    ላይ  የብዙዎቹ ምርጫ ሆነው  የቀረቡት  ከ120 ሚሊዮን  በላይ የእምነቱ ተከታዮች  ያሏት አገር  ብራዚል  ከሳኦ ፖሎ ከተማ  የመጡት  አርክቢሾፕ ኦዲሎ ሺረር ነበሩ፡፡ ለምን? ቢባል አርክ ቢሾፕ ኦዲሎ  በቫቲካን ውስጥ  በሚገኙ  ታላላቅ መነኮሳት  ዘንድ ቀረቤታ ያላቸው አባት በመሆናቸው ነበር ፡፡ይሁንና የምርጫው ስነስርአት ሲጠናቀቅ  አባ ጆርጁ ቤርጎባሌዮ የ1.2 ቢሊዮን ህዝብ(በአለማችን ላይ ያለው የካቶሊክ አማኞች ቁጥር  መሆኑ ነው) አባት ናቸው  የሚለው  ዜና  ሲሰራጭ በዙዎች  አባ ጆርጁ  ቤርጎባሌዮ ወይም አባ ፍራንሲስ ማናቸው?  የሚለው ጥያቄን መጠየቅ ጀመሩ፡፡ የብጹነታችውን ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁት  በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ አዲስ አባት  አገኘን (we have a Pope!)ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ለወትሮው ፓፓው  ለህዝቡ የሚጸልዩት ወይም  ህዝቡን የሚባርኩት እርሳቸው ሲሆኑ በአሁኑ ግን እርሳችው ለተስብሳቢው ህዝብ  !እባካችሁ  ጸልዩልኝ!” ሲሉተማጽነዋል፡፡
      ላለፉት ስምንት አመታት  በፓፓነት ማእረጋቸው ሲያገለግሉ ቆይተው በህመም  ምክንያት  በቅርቡ ስልጣናቸውን በፍቃደኝነት  የለቀቁት  አቡነ ቤኔዲክት  16ኛውን በመተካት  ሰልጣኑን የተረከቡት  አቡነ ፍራንሲስ አባታቸው ጣሊያናዊ የባቡር  ላይ ሰራተኛ   ሲሆኑ የፋሺስቱን  አገዛዝ  በመሸሽ በእርጀንቲና  ቦነስ አይረስ  ከተማ  ፍሎረነስ  በተባለች  አንስተኛ አካባቤ  መኖር ጀመሩ ፡፡ ልጃቸው  አቡነ ፍራንሲስ በ1936 እኤአ  እዚያው አርጀንቲና ውስጥ ተወለዱ፡፡  ለደሆች እና ለተፈጥሮ ሃብት ተቆርቋሪ ከነበሩት  ከቅዱስ ፍራንሲስ  (ከሃብታም  ቤተሰብ ተወልደው ስለደሃዎች እና ጭቁኖች መብት መከበር ሲሉ በሮም  ጎስቋላ ስፍርዎች  ከመጻጉዎች እና ከደሃዎች ጋር ይኖሩት ከነበሩት የኦሲሱ  ቅዱስ ፍራንሲስ ናቸው ) መጠሪያ ሰያሜ ያገኙት አዲሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን  አባት  የሆኑት ብጹነታቸው ለደሃዎች   ደህንነት እና  እኩልነት  የሚሟገቱ ታላቅ  አባት እንደሆኑ ብዙዎች ይመስክሩላቸዋል፡፡አባ ፍራንሲስ  በብዙ መልኩ ከቅንጦት እና ምቾት ካለው  አለማዊ  ኑሮ  ይልቅ ዝቅተኛ የሆነ (ሎው ፕሮፋይል) የሚመርጡ ሲሆኑ እነዚህ ምልካም ተግባሮቻቸው  መካከል  በቅዳሴ ጊዜ  በአለማዊ ሰዎች  ዘንድ  ከተዋረዱት  በእግዚአብሄር  ፊት ግን  እኩል ከሆኑት  በቦይነስ አይረስ  ከተማ  ከሚገኙ የቀድሞ ሴትኛ አዳሪዎች  ጋር አብረው  በመጸለይ የሃይማኖታዊ   አባትነታቸውን  እና አርያነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ለስልጣነ ክህነታቸው  ሲባል ለግላቸው የተመደበላቸውን ዘመናዊ ሌሞዚን  መኪና  ከእነ ሹፌሩ  እርግፍ አድርገው በመተው (ሹፌሩን በማሰናበት)  እራሳቸው  በህዝብ የማመላለሻ አውቶቡስ  በመገልገል  የደሃው ህዝብ አካል መሆናቸውን   አስመስክረዋል፡፡
      (ወደእኔ ይመጡ ዘንድ ህጻናትን አትከልክሏቸው፡-አባ ፈራንሲዮስ ህጻን  ልጅ ታቅፈው)
      በአጠቃላይ አኗኗሯቸው  ቀለል ያለ ኑሮን የሚመርጡት ብጹነታቸው የላቲን አሜሪካ  ካፈራቻቸው  የመጀመሪያው  የሮማ  ካቶሊክ ፓፓ ሲሆኑ እርሳችው መመረጥም  በቤተክርስቲያኒቱ  ውስጥ  ላላፉት 1300 አመታት ከአንድ አካባቢ (ከአውሮፓ ብቻ ) ይመጣ የነበረው የፓፓነት  ስርአትን   በመለወጥ  ፋኖ ወጊ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ይመስላል በአሜሪካ:  በአፍሪካ  በደቡብ አሜሪካ እና በእሲያ  የሚገኙ  በቢሊዮኖች  የሚቆጠሩ የካቶሊክ እምነት ተከታዩች   እንዲሁም በርካታ የአገር መሪዎች  የብጹነታቸው ምመረጥን (viva il papa !!) በማለት  እንደ ታላቅ ድል የቆጠሩት ፡፡ብዙዎችም ፓፓው ድህነትን በማስወገድ  ዘመቻ እንዲሳተፉ ተማጽነዋቸዋል፡፡ ምንም እንኳን በጹነታቸው  በግላቸው ለምእመናኑ እና  ለደሃው ህዝብ ቅርብ የሆኑ  መንፈሳዊ አባት  ቢሆኑም  የትውልድ አገራቸው  አረጀንቲና በ1970ዎቹ  እኤአ  በነበረው ወታደራዊ  ጁንታ ሳቢያ  አገዛዙን  በመቃወማቸው ብቻ ህይወታቸውን  ላጡ ከ30,000 በላይ  ሰላማዊ
      ዜጎች  ቤተክርስቲያኒቱ ተቃውሞዋን አላሰማችም  የሚል ብርቱ  ወቅሳ ቀርቦባታል፡፡ይህንንም ወቀሳ በተመለከተ አቡነ ፍራንሲስ  በ2010 እኤአ በአርጀንቲና ውስጥ ለሚታተም አንድ ጋዜጣ በሰጡት ሰፊ አስተያየት  አርሳቸው ሰዎች እንዳይታሰሩ  ሙያቸውን  በመቀየር እንዲደበቁ ወይም አገራቸውን ጥለው  እንዲሄዱ በማደረግ የታሰሩትም እንዲፈቱ በመሟገት የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን በመግለጽ ውንጅላውን አስተባብለዋል፡፡
      ቀደም ባሉት ጊዜያት   በአንዳንዳንድ ምግባረ በልሹ ካህናት  የተነሳ ከሙስና  እንስቶ ጨቅላ ህጻናትን  የመድፈር  እና መሰል  ክሶች የቀረቡባት  የሮማ ካቶሊክ  ቤተክርስቲያን  በቤቷ  ውስጥ የተጋረጡት  ችግሮችን  ለመቅረፍ የአቡነ ፍራንሲስ  ወደ ቤተክርስቲያኒቱ በአባትነት  መምጣት  መልካም አጋጣሚ ቢሆንም  አባጣ ጎባጣ የሆኑ መንገዶችን ለምጥረግ  በርቱ  ፈተናዎች ከፊታቸው  የጠብቋቸውል ተብሎ ይጠበቃል፡፡የብጹነታቸው  የግል ታሪክ ጸሃፊ የሆኑት  ሴርጆ ሩቤን  ሰለአዲሱ ፓፓ  ባህሪ ሲገልጹ  “በእሁኑ ወቅት  በለውጥ ጎዳና ላይ ያለን ይመስለኛል ፡፡ይህ ሁኔታ  ግን ቀላል  አይደለም፡፡ብጹነታቸው ቤተክርስቲያኔቱ  ወደ አደባባዮች(ጎዳናዎች) መውጣት  ስትችል  ብቻ ነው የህዝቡን ችግር መረዳት የምትችልው ብለው ያምናሉ( poor Church for the poor )፡፡” ሲሉ ተናግርዋል፡፡ በደግነታቸው  እና በእውነተኛ ርህራሄያቸው  በበርካታ የካቶሊክ  ማህበረሰብ ዝንድ  እውቅና ያገኙት አቡነ ፍራንሲስ  የፓፓነቱን ስልጣን ከያዙ  በሁዋላ እንኳን  ያ ደግነት የተላበሰ ባህሪያቸውን ባለመለወጥ ሰሞኑን ከእርሳቸው ጋር ለሚኖሩ  ካህናት  እራሳቸው  ምግብ  አብስለው በማዘጋጀት እራት እንዲቋደሱ አድርገዋል፡፡ አርፈውበት በነበረ አንድ ሆቴል ውስጥም ለተስተናገዱበት ወጪ  ከገዛ ኪሳቸው ገንዘብ በማውጣት  ከዚህ ቀደም የነበረውን የቀይ ምንጣፍ እና ልዩ መስተንግዶ ባህልን  ወደጎን አድርገውታል፡፡
      ብጹነታቸው  ባለፈው አርብ ጠዋት ላይ  በቫቲካን ከተማ  ከሚገኙ  የዝቅተኛው  ማህበረሰብ ክፍል ከሆኑት  (ብሉ  ኮላርስ )  እየተባሉ ከሚጠሩት  የቤተመንግስታቸው  አትክልተኞች እና  የጽዳት  ሰራተኞች  ጋር  በጋራ  በመሆን  የህብረት ጸሎት ያደረሱ  ሲሆን በስተመጨረሻም አያንዳንዱን ሰራተኛ  በግል አነጋግረዋል፡፡ለወትሮው  ለጳጳስ  ወደ ተዘጋጀው  የክብር መቀመጫ ከመሄድ  ከምእምናን  በስተሁዋላ  በመቀምጥ  እንደተራው ምእመናን  ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ  የጋራ ጸሎት  አድርገዋል፡፡ ሰሞኑን ምእራባዊያኖች ባከበሩት የ40 ቀናት እና 40 ሌሊት  ጾም(የሁዳዴ ጾም)  ክፍል አንዱ የሆነው ጌታ እየሱስ ክርስቶስ ከሃዋራቱ ጋር የመጨረሻውን እራት(Lord’s Supper) የበላበት እና  የሃዋሪያቶቹን እግር በማጠብ  እነርሱም የእርሱን እርያነት እንዲከተሉ ትህትናውን ዝቅ ብሎ  ያሳየበትን  ምእራፍ በማሰታውስ  ብጹነታቸው ካሳል ዴል ማርሞ (Casal del Marmo) በተባለ የወጣት አጥፊዎች እስር ቤት በመሄድ ከህግ ታራሚዎቹ ጋር  አብረው እንደሚያሳልፉ  ከቫቲካን የወጣው መግለጫ  ያመለክታል፡፡
      የቤተመንግስት  ነገር ከተነሳ  ከላይ እንደተገለጸው  ቀላላ ኑሮን ዘወትር የሚመርጡት  ብጹነታቸው አሁንም ወደ ቫቲካን  ተዛውረው  “በቤሊዮን የሚቆጠረው  ምእመናን አባት በመሆኖት ለክብሮት ሲባል የቀድሞው የአቡነ ቤኔዲክት 16ኝውን  ሆነ የቀደምት አባቶች ቤተመንግስትን ይረከቡ” ቢባሉም አሻፈረኝ በማለት  በፓፓው ምርጫ ሰሞን እዚያው ቫቲካን ውስጥ አርፈውበት በነበረው ባለ ሁለት ክፍል ሆቴል ውስጥ  ለጊዜው መቀመጥን  መምረጣቸው ተነግሯል፡፡ይህ ማለት ቤተመንግስቱን ሙሉ በሙሉ አይጠቀሙሙበትም ማለት ሳይሆን  ከመደበኛ ስራዎቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት እንግዶችን ለምቀበል ስብስባዎችን ለማካሄድ  ወደ ጽፈት ቤታቸው ጎራ ማለታቸው አልቀረም፡፡  አብዛኞቹ ባለስላጣናት ስልጣን በያዙ ማግስት ዘመድ አዝማዶቻችውን  ለመጥቀም ሲሯሯጡ  ወይም ቀደም ሲል አስቀይመዋቸው የነበሩ ወገኖችን ለማባረር አሌያም ከእነአካቴው ለማጥፋት ላይ ታች በሚሉበት   አሁን ባለንበት በ21ኛው  ክ\ዘመን  በየትኛውም ጎራ ይሁኑ በየትኛውም ስፍራ አንደ አቡን ፍራንሲስ  የመሰለ መንፈሳዊ አባት ማግኘት  ለሃይማኖቱ ተከታዩች ብቻ ሳይሆን እምነት ለሌላቸውም(አለማዊያን) ቢሆን  ጥሩ አርእያ መሆኑ የሚቀር አይመስልም፡፡  (tamgeda@gmail.com)

      Wednesday, March 27, 2013

      የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል አብረን እንታገል የሚል የትግል ጥሪ አደረገ


      የኢትዮጵያ ህዝብ ሃያ አንድ አመት ሙሉ ከቀለደበት  የወያኔ ኢህአዴግ አገዛዝ እጅግ በጣም የተሻለ አማራጭ ኃይል እንዳለዉና ይህንን ለኢትዮጵያ አንድት፤ ለህዝቦቿ እኩልነትና ነፃነት በቆራጥነት የቆመዉን አማራጭ ኃይል የኢትዮጵያ ህዝብ በፍጥነት እንዲቀላቀልና የትግሉን የመጨረሻ ምዕራፍ እንዲጀምር የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል አገራዊ ጥሪ አደረገ። የወያኔ ንቀት፤ጥላቻና ህዝብን ማሸበር ማብቃት አለበት ብለዉ አምርረዉ በተነሱ ወጣቶች፤ምሁራንና ወታደሮች በቅርቡ የተቋቋመዉ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል በላፈዉ ሳምንት እንዳሳወቀዉ በወያኔ ተራ ካድሬዎች መረገጥና እየተገፋ እስር ቤት መወርወር የሰለቸዉ ኢትዮጵያዊና በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ በህዝብ ነጻ ፍላጎት ተመስርቶ ህዝብን በታማኝነት የሚያገለግል ስርአት ለመመስረት ምትፈልጉ ኢትዮጵዉያን ሁሉ ወያኔ እስካለ ድረስ ይህንን ህዝባዊ ስርአት ካለመስዋዕትነት ማምጣት አይቻልምና ለድል ሊያበቃን የሚቸለዉን መስዋዕትነት ለመክፈል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተጠንቀቅ እንዲቆም አገራዊ የአደራ ጥሪዉን አስተላልፏል። የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል ይህንን ጥሪ ያደረገዉ የወያኔ ህወሀት ተሸካሚ ፈረስ የሆነዉ ኢህአዴግ ካለፈዉ ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን እስከዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን ድረስ ባህርዳር ላይ ጌታዉን ተሸክሞ ያካሄደዉን ትርጉም የለሽ የወሬ ጉባኤ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላለፈዉ መልዕክት ነዉ።
      ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘረኝነት ገመድ አስሮ እየረገጠ የሚገዛዉ ወያኔ ለዚህ የበቃዉ በዘረኝነትና በጥላቻ አነሳስቶ ያሰታጠቃቸዉ ገበሬዎች በከፈሉት መስዋዕትነት ነዉ ያለዉ ይሄዉ ህዝባዊ ኃይል ሠላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ እራሱን ከእነዚህ የቀን ጅቦች ለማላቀቅና አገራችንን የእኩሎች አገር ለማድረግ ማንኛዉንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት አለበት ብሏል። የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረዉ የፍትህ፤የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግል ግቡን እንዲመታ የመጀመሪያዉን እርምጃ የወሰደዉና ትግሉ የሚፈልገዉን የደም መስዋዕትነት ለመክፈል የትግሉ ግንባር የመጀመሪያዉ ደጃፍ ላይ የተሰለፈዉ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል ካሁን በኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ የወያኔን ዘረኝነት፤ዝርፍያ፤ጥላቻና ንቀት ለማስቆም መፍትሄዉ ከአገር እየተሰደዱ በየባህሩና በየበረሀዉ መሞት ሳይሆን ለስደታችን፤ ለመዋረዳችንና ለመረገጣችን ቀንደኛ ምክንያት የሆነዉን የወያኔ ስርአት እዝያዉ አገር ቤት ዉስጥ ፊት ለፊት በመጋፈጥ ብቻ ነዉ ብሏል።
      የወያኔ እህአዴግ ዘመን አብቅቷል፤ከአሁን በኋላ ዘመኑ የኛ የኢትዮጵያዉያን ነዉ ያለዉ የግንቦት ሰባት ዝብባዊ ኃይሎች ቃል አቀባይ ይህንን የኛ የሆነዉን ዘመን እዉን የምናደርገዉና የኢትዮጵያን ህዝብ ከዘረኝነት ነጻ የምናወጣዉ እንደአንድ ሰዉ ቆመን በጋራ ስንታገል ነዉ እንጂ የአገር ማዳኑንና የመስዋዕትነቱን አደራ ለተወሰኑ ወገኖች ብቻ በመተዉ አይደለም ብሏል። በመቀጠልም ወያኔን ፊት ለፊት ተፋልሞ ወንድሞቹንና እህቶቹን ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአባቶቹ በአደራ የተረከባትን ኢትዮጵያን ለልጆቹ ለማስተላለፍ የሚናፍቅ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ከዛሬ በኋላ ዬት ሄጄ ወያኔን ልታገል የሚል ስጋት እንዳይሰማዉ አሳስቧል።ባለፈዉ ታህሳስ ወር እራሱን ለህዝብ ይፋ ይደረገዉ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ አያሌ ኢትዮጵያዉያን በየቀኑ እየተቀላቀሉት ሲሆን ይህንን የህዝብ ተገንና አለኝታ የሆነ ኃይል በመቀላቀል የአዲስቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ለመሆን የምትፈልጉ በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ አገራት የምትገኙ ኢትዮጵያዉያን ህዝባዊ ኃይሉ በተከታታይ ለሚያወጣቸዉ መግለጫዎችና ህዝባዊ ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት እንዲትተባበሩ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ኃይል ጥሪዉን ያስተላልፋል።

        ዘጠኝ ቦላሌ…” ከይኸነው አንተሁነኝ



        ከይኸነው አንተሁነኝ
        መጋቢት 26 2013
        የክህደት ቁልቁለት አሉ ታላቁ ምሁር!!! የክህደት ውርስ የበቀል ዛር እያስጎራ፣ የሚሆነውንም የማይሆነውንም እያስቀባጠረ ሃያ አንድ ዓመት እያንደረደረ ወርውሮ እዚህ ያደረሰው ሕወሃት ስለመድረሱ እንጅ ወደ ፊት ስለሚሆነው ወይም ስለሚያደርገው ከግምት በላይ የሚያውቀው ነገር ያለ አይመስልም። አውቃለሁ ብሎ ያቀዳቸው ተማከርኩ ብሎ ያወራቸው ሁሉም እንዳይሆን እንዳይሆን እየሆኑበት መሆኑ ይሰማል። ብዙ የተነገረለት ስንት የተባለለት ”የሕወሃቱ የእድገት ትራንስፎርሜሽን”ም ብዙም እንዳልጨበጠ የሚወራው ሳይሆን እየሆነ ያለው የምድሩ ላይ እውነት እያሳበቀበት ነው። ወትሮም ያልነበረው የሁለት አሃዝ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ፉከራም ወደ ሗላ እየባረቀ ”ለነዚህ ያህል ዓመታት ሁለት አሃዝ ተከታታይ እድገት ለምን ድህነትንና ስደትን በመጠኑ እንኳ ሊቀርፍ አልቻለም?” የሚለውን የዓለም ማሕበረሰብ ጥያቄ ባልተሳከረ መልኩ ለመመለስ ለሕወሃት አስቸጋሪ ሆኖበታል። ምክንያቱም የኑሮ ውድነቱ፣ ርሃብ እና ችግር የሚያንገላታው የሕዝባችን ቁጥር፣ የተማረ የሰው ሃይል ስራ አጥነት እንደጉድ መጨመር፣ ሁሉን አቀፍ ስደት ለመናገር ከሚያስቸግር በላይ መሆን እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከምንም ጊዜ በላይ ዋጋው  ረክሶ የታየባቸው ዘመናት በሙሉ በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን በተለይም ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አመጣሁ እያለ በሚለፍባቸው በነዚሁ ዓመታት ነበርና ነው። ለዚህም ይመስላል የዘንድሮው የሕወሃት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ለዓመታት የሙጥኝ ያላትን ያችን ጉደኛ አስራ አንድ ቁጥር ለቆ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወዳስቀመጡት የእድገት ትንበያ አሃዝ ለመድረስ ወደ ታች የተምዘገዘገው።
        መብትን የመጠቀም ጉዳይም ጥንቅቅ ብሎ በሕወሃት ጉያ ገብቶ ከተቆለፈበት ቆየ። ሕወሃቶች የዓለምን ማሕበረሰብ ጩኸት በመፍራት ወይም ለፖለቲካችን ይጠቅሙናል ብለው ለይስሙላ ከተዋቸው በጣት የሚቆጠሩ ፀሐፊዎችና ተናጋሪዎች በቀር ማንም እንዳይጽፍ እጁን አስረዋል፣ እነዳይናገር አፉን ለጉመዋል በስርአት አንዳያስብም  በተለያዩ መንገዶች ህሊናውን ቶርች በማድረግ ሕዝባችንን እያደነዘዙት ይገኛሉ።
        በፖለቲካው ረገድም እውቅና አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የፖልቲካ ፓርቲዎች ሕዝባቸውን ሰብስበው ማነጋገር፣ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተው ባንድ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ማቅረብ፣ ለሕዝባቸው ለሀገራቸው ይበጃሉ ይጠቅማሉ ያሉዋቸውን ሃሳቦች አቅርበውና አጸድቀው የሀገሪቱ ሕግ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት በጠባቡ ሕወሃት በሽብርተኛነት እያስወነጀለና እያስቀጣ መሆኑን በዚህ ሰአት ማብራራት ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆን ትቸዋለሁ።
        ሕወሃት በተከተለው የተንጋደደ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ ሕዝባችን በኑሮ ውድነት ተመታ፣ በርሃብ በስደት ተንገላታ፣ ብዙው የበይ ተመልካች ሆነ፣ ልመና ማሳፈሩ ቀርቶ ደንብ እየሆነ መጣ፣ ስርቆት የጀግንነት መለኪያ እንጅ የማሕበረሰብ ጠባሳ መሆኑ ተረሳ፣ ማንኛውንም የቢሮ ስራ ለማስፈጸም እንደ ባላባቱ ስርአት እጅ መንሻ የመጀመሪያው ተመራጭ መንገድ እየሆነ መጣ፣ ከራስ ይልቅ ለሕዝብ ከእኛ ይልቅ ለሀገር ያሚል ሕሊና እንዲጠፋ ክረምት ከበጋ ተሰራ፣ ባጠቃላይ ሕወሃት መራሉ የወደቀ ራዕይ የሌለው ተስፋው የደበዘዘ የተነገረውን ዝም ብሎ የሚቀበል እንጅ ለምን ብሎ የማይከራከር ትውልድ ለመፍጠር ተጋ። የተሳካለትም ይመስላል። ሌላው ዓለም በዳቦ ሂሳብ ላይ አምስት ሳንቲም ስትጨመር ሀገሩን በሙሉ በሰልፍ ሲያተራምስ እየታየ በሀገራችን የሚወርደው ይህ ሁሉ የመብት ረገጣና አድሎ፣ ግርፋቱና እስራቱ ሕዝባችንን አደነዘዘው እንጅ አላስነሳውምና። ይህ የሕዝባችን ዝምታም ሕወሃት በያዘው የመከፋፈል መንገድ እነዲገፋበት ሁሉንም የስልጣን ቦታ በራሱ ሰዎች እንዲቆጣጠር አደረገው እንጅ የአመራር አንጀት አልፈጠረለትም።
        ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌ ከአዋሳ ናዝሬት እስከ ባህርዳር የህወሃቱ ገዥዎችና ጀሌዎቹ የአገዛዝ ወንበራቸው ላይ ቢያፈጡም የሻጉራ መተያየታቸውን ግን አላቆሙም- ዘጠኝ ቦላሌ… መሆኑ ነው ነገሩ ። የአመለካከት ልዩነት ጥቂት እንዴው ትንሽ ከመስመር የወጣ ቡድንተኝነት ከተገኘም ከሕወሃት የግል አብዮት ሃዲድ ማስፈንጠሪያ በስርአት ያልተተገበረው የይስሙላው መተካካት ተግባር ላይ ይውላል። ስልጣን ዘመድ ወገን የለውም ያባላል ያጫርሳል። ሕወሃት ለዚሁ ለማይረባ ስልጣን ስንቱን አራግፎ እዚህ እንደደረሰ እራሱ ያውቀዋል።
        በሂወት የሌሉትም ሆኑ አሁን ነፍስ ይዟቸው የሚነገታገቱት ሕወሃቶች ሀገር ለማጥፋት አንድ ሆነውታግለው ለእንብርታቸው የተጋጩ፤ አብረው እየዋሉ የማይተማመኑ፤ እየተሻሹ የሚገፋፉ፤ እየተሳሳቁ የሚጠራጠሩ፤ ከሀገራችን አልፈው ምስራቅ አፍሪካን ሕወሃት ሕወሃት ያሸተቱ። ምላሳቸው ከዶለዶመ ራዕያቸው ከወየበ በሗላ ባቅም ማነስ ከተሰናበቱበትና ከዘራ ከጨበጡበት ወጣት ተተኪዎችን ረስተው ባባራ እድሜ   የስልጣን ወንበር ናፍቆት ያነቃቸው የሙት መንፈስ የጠራቸው የዘመናችን ጉዶች ናቸው። ባሁኑ ወቅት ስለ ሀገር የሚነገር ስለ ሕዝብ የሚሰራ መልካም ራዕይ የላቸውም ሕወሃቶች ከመቧደንና መተራመስ ከመጋባትና መፋታት በቀር።
        ይህ ወቅት ታዲያ ሕዝባችን ከገባበት የሞራል ውድቀት እንዲወጣ ብሔራዊ መነሳሳት በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰበክበት ወቅት መሆን አለበት። ይህ ጊዜ እጅ ለእጅ ተቃቅፈን፣ ልብ ለልብ ተሳስረን፣ ሃሳብ ለሃሳብ ተቆራኝተን ቀን ከሌት አንድነትን እንድንዘምር የሚሰራበት መሆን ይገባዋል። ይህን ታዲያ ሀገር እየመራሁ ነው የሚለው ሕወሃት እንዳይከውነው የራሱ ተፈጥሮ ስልጣን ሙስና ቡድንተኝነትና ዘረኝነት ከጋረደው የሕዝባችንን ሁሉን አቀፍ ሰቆቃ ለመመከትና የተሻለ ራዕይ እንዲኖረን ለማድረግ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምንል ዜጋዎች ሁሉ ይህን ጨቋኝ አገዛዝ በማስወገድና ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን በመገንባት ሀገራችንን ማዳን ሕዝባችንንም ማጽናት ይጠበቅብናል። አበቃሁ።

        Tuesday, March 26, 2013


        አሁን በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ባመዛኙ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የባንዳ ልጆች ነበሩ”

        የዛሬው እንግዳችን አቶ ታዲዎስ ታንቱ ይባላሉ፡፡ አቶ ታዲዎስ የታሪክ ምሁርና በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ነፃ ፕሬስ ውስጥ ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን በአሁን ወቅት “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ” ዋና ሰብሳቢ ናቸው ፡፡ በተለይ ለፋሺስቱ ግራዚያኒ ከተሰራው ሐውልት ጋር በተያያዘ አጭር ቆይታ አድርገናል ተከታተሉን፡፡
        በጣሊያን የሩዶልፍ ግራዚያኒንን የሐውልት ለመቃወም የሐሳቡ ጠንሳሽ ማን ነው?
        አቶ ታዲዎስ፡- የፋሽቱ ጣሊያን የኢትዮጵያውያን ዋና ጨፍጫፊ የነበረውን ሩዶልፍ ግራዚያኒ ሐውልት መሰራት ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃውሞው የተጀመረው በውጭ ሀገር ባሉ
        Interview with Ato Tadiwos Tantu
        አቶ ታዲዎስ ታንቱ
        ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት
        ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ
        ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ግን የሐሳቡ ጠንሳሽ “ለኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ኮሚቴ” ነው፡፡ ከዛ በኋላ የባለዕራዕይ ወጣቶች ማኀበር ሰልፉን ለማስተባበር ፈቃደኛ መሆኑን ገለፀልን፤ በዚህም ላይ ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚተባበረን ከገለፀ በኋላ መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰልፉን ለማካሄድmወሰንን፡፡
        ተቃወቅሞውን ለማቅረብ ያነሳሳችሁ ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር?
        አቶ ታዲዎስ፡- ብዙውን ጊዜ እኔ በጋዜጦች ስለ አርበኞች ታሪክ ያነበብኩትንና ያወቅሁትን እፅፋለሁ፣ እመረምራለሁ፡፡ የጣሊያኑ ፋሽስት ግራዚያኒ ሀገራችንን በመውረር በአባቶቻችንና እናቶቻችን አርበኞች ላይ የፈፀሙት የግፍ ግድያ አሰቃቂ እንደነበር ስለተረዳሁ፤ ያ ሲቆጨኝ ደግሞ አሁን በጣሊያን ሀገር ለእሱ ሙዚየምና ሐውልት የመሰራቱን ወሬ ከኢንተርኔት ምንጮች ስላየሁ በጣም ተናድጄ እንደውም ተቃውሞ ማሰማት አለብን ብዬ ተነሳሁ፡፡ በኋላ ደግሞ እኛም የአንተ ዓይነት ሐሳብ ነበረን ብለው የባለ ዕራዕይ ወጣቶች ማኀበር አነጋገሩን፡፡ ከዛ በመቀጠል ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ እንስራ የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ በዚህ ምክንያት ሶስቱ አካላት በጋራ ሰልፉን ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ ጀመርን፡፡ ስለዚህ ለኢትዮጵያ ጠላት አይደለም ጣሊያን ሀገር ጨረቃም ላይ ቢሆን ሀውልት እንዲሰራ አንፈቅደም፡፡
        በጊዜው ሩዶልፍ ግራዚያኒ ወንጀለኛ በመሆኑ የነበረው ፊልድ ማርሻል ማዕረግ ተገፎ ከወታደርነቱ ተባሮ በጦር ወንጀል ተከሶ 19 ዓመት ተፈርዶበት ቅጣቱን ሳይጨርስ ከእስር ቢለቀቅም እ.አ.አ. በ1955 ዓ.ም. ሞቷል፡፡ ታዲያ ይህ በጊዜው ወንጀለኛ ለተባለው ሰው ሐውልትም ሆነ የመታሰቢያ ሙዚየም ማሰራት ኢትዮጵየውያንን መናቅና የአባቶቻችንን ክብር የሚነካ በመሆኑ ሊሰራለት አይገባም፤ እንደውም ለፈፀመው እልቂት ጣሊያን በቂ ካሳ ስላልከፈለች ካሳ መክፈልና በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይገባታል የሚል አቋም ይዘን ነው የወጣነው፡፡ ስለዚህ ግራዚያኒ ከነ አዳፋ ታሪኩ ሌላው እንዳይደግም ሲወሳ መኖር አለበት እንጂ እንደ ጀግና ሐውልት ሊሰራለት፣ሊወደስና ሊመሰገን አይገባም እንላለን፡፡
        በወቅቱ የደረስው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ይቻላል?
        አቶ ታዲዎስ፡- በወቅቱ ግራዚያኒ በፊርማው በግፍ ኢትዮጵያውያንን ያስጨፈጨፋቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ከነደብዳቤው አለ፤ የዚህ ቅጂ እኔም ጋር አለ ይታወቃል፡፡ በተለይ የካቲት 12-14 ቀን 1929 ዓ.ም. ከ30 ሺህ በላይ ዜጎቻችንን በግፍ አዲስ አበባ ላይ እራሱ ግራዚያኒ አስጨፍጨፏል፡፡ ከ250 በላይ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ መነኮሳትን አስጨፍጭፏል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በ1938 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው አለም አቀፍ ጉባኤ ያቀረበው ሰነድ እንደሚያስረዳው 760,300 ሺህ ዜጎች ወዲያው ሲገደሉ 525,000 ደግሞ ከነቤት ንብረታቸው እንዲቃጠሉ ተደርጎ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከሁለት ሺህ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው መነኮሳት ተገድለዋል፣ በርካታ ቅርሶች ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡ በርግጥ ከተዘረፉ ቅርሶቻችን መካከል እስካሁን የተመለሰው የአክሱም ሐውልት ብቻ ነው፤ ሌሎቹ ግን አሁንም እዛው ናቸው፤ ሊመለሱልንም ይገባል፡፡ ከዛ ውጭ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶች በወቅቱ ተዘርፈው ተወስደዋል፤ 7 ሺህ ግመሎችም ተገድለውብናል፡፡ ይህም በሰነድ በተደገፈ ማስረጃ ለዓለም አቀፉ የሰላም ጉባዔ የቀረበ ነው፡፡ በወቅቱ ሰነድ ያልቀረበባቸውና ሰፊ ጥናቶች ሊደረግባቸው የሚገቡ በርካታ ጥፋቶች ተፈፅመዋል፡፡
        ይህንን ተቃውሞ በዋነኝነት ማቅረብ የነበረበት መንግስት ነበር የሚሉ ወገኖች አሉ፤ እርስዎስ ምን ይላሉ?
        አቶ ታዲዎስ፡- እኔም እስማማለሁ፤ ነገር ግን መንግስት ማዘጋጀት ካልቻለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማዘጋጀት ይችላል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ መንግስት ተቃውሞ ያላቀረበው ከጣሊያን የሚያገኘው ዕርዳታ ይቀርብኛል በሚል ይመስለኛል፡፡ እኔ እስከማውቀው ይሄ መንግስት ዕለታዊና የፖለቲካ ገበያ ጥቅምን መሰረት ያደረገ እንጂ ወደፊት ትውልድ የሚኮራበትን ስራ የመስራት ዓላማ የለውም፡፡ ከዚህ በፊት የቀደሙ አባቶቻችን የሰሩትን በጎ ታሪኮች ሲያንቋሽሽ የኖረ መንግስት ስለሆነ እንዲህ ዓይነት የአባቶቻችንና እናቶቻችን አርበኞች ታሪክና ክብር የሚያስጠብቅ ስራ ይሰራል ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ስሜት ያለው፣ ብሔራዊ ስሜትን የጠበቀ ህዝባዊ መንግስት ቢሆን ኖሮ ህዝቡን አስተባብሮ ይሄንን ስራ በቀዳሚነት መስራት የነበረበት እሱ ነበር፡፡ ስለዚህ መንግስት ባያደርግም ዜጎች ይህንን ሰልፍ የማድረግ መብት ስላላቸው እኛም ሰልፉን አድርገናል፡፡
        የኢትዮጵያ መንግስት የሀውልት ግንባታውን አለመቃወሙ ምን ያስረዳናል?
        አቶ ታዲዎስ፡- ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በእጅ አዙር ለሀውልት ግንባታው እውቅና እንደሰጠ ይቆጠራል፤ ይህንን እኔም አምናለሁ፡፡ ከዚህም በላይ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ባመዛኙ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የባንዳ ልጆች የነበሩ ናቸው፡፡ እንደውም ነፃነታችንን ባወጅንበት ሁለት ዓመት ሳይሞላ በአርበኞች ላይ ጦርነት የከፈቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለግራዚያኒ የጀግና ሐውልት መሰራቱን ባይቃወሙ አይገርመኝም፤ ምክንያቱም እነሱ የማን ልጆች ናቸው? እስኪ በስልጣን ላይ ካሉት (ከኢህአዴግ) መካከል ለሀገሩ እና ለወገኑ ብሔራዊ ስሜት፣ ነፃነትና ክብር የተዋጋ የአርበኛ ልጅ አንድ ሰው ካለ ንገረኝ? አንድም ሰው የለም፡፡ ስለዚህ የባንዳ ልጅ ለጨፍጫፊው ግራዚያኒ በእጅ አዙርም ሆነ በቀጥታ እውቅና በመስጠት ድጋፍ ቢያደርጉ አያስደንቀኝም፡፡
        እናንተ ሰላማዊ ሰልፉን ከማድረጋችሁ አንድ ቀን በፊት መጋቢት 7 ቀን 2005 ዓ.ም ስምንት ሰዎች መታሰራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ክስተት በሰልፉ ወቅት እስር እንደሚኖር አልጠቆማችሁም?
        አቶ ታዲዎስ፡- እሱን አውቀንም ነው ሰልፍ የወጣነው፡፡ አንድ ቀን አስቀድሞ ሌሎች ቢታሰሩም መውጣት አለብን ብለን ነው የወጣነው፤ እኛም ብንታሰር ሌሎችም እንደሚወጡ እናውቃለን፡፡ ችግር ይፈጠራል ብለን አልተውንም ፤መተውም የለብንም፡፡ ምክንያቱም ይሄ የሀገርና የወገን ጉዳይ ነውና፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሰልፉ ላይ የተገኙትን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
        የታሰራችሁት ምን ወንጀል ሰርታችኋል ተብላችሁ ነው?
        አቶ ታዲዎስ፡- ፍቃድ አልጠየቃችሁም ፣ አላስፈቀዳችሁም በሚል ነው፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በነበሩ የአጼ ኃይለስላሴ፣ በደርግ ዘመንም ሆነ አሁንም በወያኔ አገዛዝ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ፈቃድ ይጠየቃል የሚል የተፃፈ ህገመንግስትም ሆነ አዋጅ አልነበረም፤የለምም፡፡ ዋናው ከእኛ የሚጠበቀው ሰላማዊ ሰልፍ እንደምናደርግ ማሳወቅና አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግ ማድረግ እንጂ ፈቃድ መጠየቅ አይደለም፡፡ ይህንንም ለእኛ ጥቅም እንጂ እነሱን ለማስደሰት አይደልም፡፡ እኛ ደግሞ የሀገሪቱን የተፃፈ ህግ ተከትለን ሰልፉን ከማድረጋችን 10 ቀናት አስቀድመን አሳውቀናል፡፡
        ኢትዮጵያውያንን በግፍ ለጨፈጨፈው ግራዚያኒ የተሰራለትን ሐውልት በመቃወማችሁ በኢትዮጵያ መንግስት መታሰራችሁ ምን ስሜት ፈጠረባችሁ? ለእኛ የበለጠ የተነሳሽነት ስሜት ሰጥቶናል፡፡ ጉዳዩንም አጠናክረን እንድንሄድ ትልቅ የሞራል ድጋፍ ሆኖናል፡፡
        ከእስር ሲለቋችሁ ምን ብለው ነው?
        አቶ ታዲዎስ፡- ምንም ሳይሉን ለሁለት ሰው አንዳንድ ዋስ በማስጠራት ለቀውናል፡፡ ምክንያቱን ግን አልነገሩንም፤አላወቅንም፡፡ ከዛ ስትፈለጉ ትመጣላችሁ ብለው በዋስ ለቀውናል፡፡
        በታሰራችሁበት ወቅትስ የገጠማችሁ ችግር አለ?
        አቶ ታዲዎስ፡- በርግጥ እኔ ላይ ድብደባ አልፈፀሙም እንጂ ተመትተው ፊታቸው በተለይም አፋቸው አካባቢ የደማ ወጣት አይቻለሁ፡፡ ፊታቸው ያባበጠ ወጣቶችንም አይቻለሁ፡፡ ሌሎችንም ወጣቶች እንደደበደቧቸውም ሰምቻለሁ፡፡ በተለይ ደህንነቶች ማታ መጥተው በግል እያስጠሩ በቢሮ ያናግሩ ነበር፡፡ ስራው ግን የፖሊሶች እንጂ የደህንነቶች አልነበረም፡፡ በታሰርንበት ዕለት ያለምግብና ውሃ ቀን ሙሉ እንድንውል ተደርገናል፡፡ በተለይ እስር ቤቱን ስቃይ አራዳ ፖሊስ መምሪያና ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ ያለውን ስታይ ዕቃ ለማስቀመጥ ሆነ ለሌሎች እንሰሳቶች ለአንዲት ደቂቃ እንኳን እንዲቆዩበት አይመችም፡፡ እስር ቤቱን ስታይ በጣም ያሳዝናል፤ እዛ የገቡ እኮ ጤነኛ ሆነው የመውጣታቸው ዕድል እራሱ አነስተኛ ነው፤ለበሽታ የሚያጋልጡ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ብቻ በጣም ያሳዝናል፡፡ ይሄ ደግሞ የወንበዴ ስራ ነው፤ ይሄንን መንግስት ማረም አለበት፡፡ ሌላው መርማሪ ፖሊሶችና ደህንነቶች ያልተገቡና ከእስሩ ጋር የማይገናኙ የግል ህይወትን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ፣ የኢ-ሜይል የይለፍ ቃል ይጠይቃሉ፣… ብቻ ብዙ ነው፡፡ በግል እኔን ደግሞ ፊታቸውን በኮፊያ የሸፈኑና ጥቁር መነፅር ያደረጉ ደህንነቶች ዋስ ጠርቼ ከወጣሁ በኋላ አንተ የአርበኞችን ታሪክ እያነሳሳህ ወጣቶችን እያነሳሳህ ስለሆነ ብታርፍ ይሻልሃል፤ በግል ልናናግርህ እንፈልጋለን እያሉ ለማስፈራራት ሞክረዋል፡፡ እኔ ግን በህጋዊ ደብዳቤ ያውም ያመንኩበት ካልሆነ ብትጠሩኝ አልመጣም፤ አላናግርም ብያለሁ፡፡
        ከዚህ በኋለስ ይህን ተቃውሞ ለመቀጠልስ እቅዱ አላችሁ?
        አቶ ታዲዎስ፡- አዎ አለን፡፡ ይህ ተቃውሞ ምላሽ አግኝቶ ያሰብነው እስኪሳካ እንቀጥላለን፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ሁኔታውን በተመለከተ እያጠናን ስለሆነ ወደፊት ሀገር ውስጥ ያለነው ውጭ ካሉ ወገኖቻችን ጋር በመመካከር ምን መልክ መያዝ እንዳለበት ስንወስን ይፋ እናደርጋለን፡፡
        በመጨረሻም የሚሉት ነገር ካለ ዕድሉን ልስጥዎት
        አቶ ታዲዎስ፡- ህዝቡ ዓላማችን ከግብ እንዲደርስ የተለመደ ድጋፉን ከመስጠት ወደ ኋላ እንዳይል አደራ እላለሁ፡፡

        ነብር ዥንጉርጉርነቱን “ግራ ዘመም” ኢትዮጲያዊ ክሽፈቱን

        በክፍሉ ሁሴን
        ታምራት ነገራ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ”መጽሃፍ ላይ የሰጠውን አስተያዬት ካነበብኩትProfessor Mesfin Woldemariam is one of Ethiopia's well-known intellectuals በኋላ የመጣብኝ ሃሳብ ሰውዬው የሚለውን ያውቀዋልን? የሚል ነው። እንደምፀት ሆኖ አሁን በማላስታውሰው ምክንያት ግን በወቅቱ በወደድኩለት አንድ የፌስቡክ አስተያዬቱ ብዙም በአንባቢነትና አለማቀፍ ነገሮችን በመተንተን ችሎታው የማላማው ይልቁንም የእሱን አይነት ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች “የአዲስ ኪዳን በግ ቅዱስ ካህን፤ የፅድቅ ንጉስ የአለም መድህን” እያልኩ የምመሰጥበት ሌላ ጓደኛዬ በዚያው እኔ የታምራትን አስተያዬት “ላይክ” ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የፌስቡክ ባልንጀሮቼ ባቃመስኩበት ወቅት “ይህ ታምራት የሚለውን ያውቀዋልን?”ሲል የጠየቀውን አስታወሰኝ። ምናልባት ጌታን በተቀበለና ባልተቀበለ መካከል ያለ ልዩነት ይሆን?
        ጌታን እስከዛሬ ባልቀበልም (ጌታ ነው ከሚሉትም ጋር ጌታ አይደለም ብዬ ጠብ እንደማላበቅልም ልብ ይባልልኝ) ባንዳች ምክንያት ወልይ ሆኜ ነው መሰለኝ ታምራት “ነብር ዥንጉርጉርነቱን፤ ኢትዮጲያዊ ክሽፈቱን” በሚል ርዕስ በሰጠው አስተያዬት ልክ እንደ ዳግም ልደቱ ክርስቲያን ወዳጄ እኔም በተራዬ “የሚለውን ያውቀዋልን?” እንድል አስገድዶኛል። ታምራት የፕሮፌሰር መስፍን “መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ” ከመውጣቱ በፊት “The Ethiopian mind” በሚል ሊፅፍ እንዳሰበ ከነገረን በኋላ የፕሮፌሰርን መፅሃፍ ሲያነብ አንድ ላይ አጠቃሎ አስተያዬቱን እንደሚያቀርብ አሳወቀን፤ በዚያው በፌስቡክ ላይ። አከታትሎም “አርታኢዎቹ” ማስረሻ ማሞ እና ዳኝነት… እንዳሹበት አሳወቀን። ከጥቂት ቀናት በኋላም አስተያዬቱን በአዲስ ነገር የፌስቡክ ገጽ ላይ ለበደው። የእኔም በታምራት አስተያዬት እና አጻጻፍ ላይ መደናገር ከዚህ ይጀምራል።
        ፕሮፌሰርን ፅሁፋቸውን ወደአንባቢ ከማድረሳቸው በፊት “ለአንድ ሁለት ዙር” ትችት ለአርታኢ የመስጠት ትህትና የላቸውም የሚለው ታምራት የእሱን ፅሁፍ ሳነብ ከአርታኢ ምንም የተጠቀመ አልመሰለኝም። ብዙ ነው ባይባልም እንኳ እሱ ፕሮፌሰር መስፍን ለአርታኢ አይሰጡም ብሎ ከተቸበት አኳያ ሲታይ ቀላል የማይባሉ የፊደል ግድፈቶች በጽሁፉ ላይ እዚህም እዚያም ይታያሉ። ለምሳሌ በአንቀጽ 3 ላይ “መናጡ እንደቀረልኝ” ሊል ፈልጎ “እየደቀረልኝ”ይላል። እንዲሁም ፕሮፌሰርን “ኢትዮጵያን ከመውደዳቸው የተነሳ ለማቀፍ ሲንደረደሩ ሊያንቋት ከሚዳዳቸው የቀኞች ወገን “ፓትያርክም” እያለ ይገድፋል። እንዴት በአርታኢ የሚያምን እና አርታኢን የተጠቀመ ጸሃፊ ፅሁፍ ውስጥ እንዲህ ያለ ግድፈት ሊኖር እንደቻለ አልገባኝም። ከሁሉም በላይ ታምራት በፕሮፌሰር መስፍን መፅሃፍ በተነሱት ቁምነገሮች መመሰጡን እየነገረን 238 ገጽ ከያዘው የፕሮፌሰር መስፍን መፅሃፍ ውስጥ ቁምነገር ያገኘው እና እንዲጽፍበት የጎነተለው በ 46 ገጾች ውስጥ ብቻ ያሉት “ቁምነገሮች” እንደሆኑ ይነግረናል። እንደታምራትም ባይሆን በትንሿ የአንባቢነት ዘመኔ ከያዘው ዳጎስ ያለ ገጽ ውስጥ ከ 80 ከመቶው በላይ ጅል ከሆነ ሃያ ፐርሰንቱ “ቁምነገር” ጋር ለመድረስ ተካልቦ በሚያካልበው የዛሬ ጊዜ ላይ ትዕግስት እንደማይኖር ጠንቅቄ ተረድቻለሁ። እና ታምራት ከሰማንያ ፐርሰንት በላይ በ “አላስፈላጊ ሐሳቦች” እና “አርቲ ቡርቲ” ተጥለቅልቋል የሚለው መጽሃፍ ላይ እንዴት ጊዜውን ወስዶ “ትችት” እስከመጻፍ እንደተጎነተለ አልገባኝም። አርታኢዎቹ በዚህ በኩል እንዲህ ያለ ሞጋች ጥያቄ ቢመጣብህ እንዴት ትከላከለዋለህ ሳይሉት ቀሩ ወይስ ያሉትን ሳይሰማቸው ቀረ? ወይስ ደግሞ “ዴሞክራት” አርታኢ የቋንቋ ግድፈት ከማሳደድ በቀር እንዲህ ያለ ጉዳይ ውስጥ አይገባም? ቋንቋን በማረምም ሆነ ሃሳብን በማጥራት በኩል ለታምራት ያልጠቀሙ አርታኢዎች ለፕሮፌሰር መስፍን ምን ይፈይዳሉ?
        የ “ቀኝ ዘመም” ፖለቲካ እንዲህ ከሆነ
        በደርግ ዘመን ነፍስ እንደማወቄ ኢሕአፓ የሚባለው ቡድን የእሱን አላማ የሚጠይቁትንና የሚቃወሙትን በተለይም መኢሶን የተባለውን የባላንጣውን ቡድን “ቀኝ መንገደኛ” እያለ ስም በማጥፋት ብቻ ሳይመለስ በጥይትም እንካ ቅመስ ይል እንደነበር አስታውሳለሁ። በንባብ ላይ ንባብ እየጨመርኩ እንዳቅሚቲ ለመንቃት በማደርገውም ጥረት በውጪው አለም ፖለቲካም የ”ቀኝ” የ”ግራ” የሚባል ፍረጃ እንዳለ ተረዳሁ። ያም ሆኖ በግሌ ገና ሳየው ጠረኑ ልክ (Just) የሆነ እና ልክ ያልሆነን (Unjust) ፖለቲካን የማፈነፍንበት ግን ስም ያልሰጠሁት የራሴን መስፈርት ስለቀየስኩ የቱ የ”ቀኝ” የቱ የ”ግራ” በሚለው እሰጥ አገባ ውስጥ ጊዜዬን አባክኜ አላውቅም። ሆኖም ታምራት የፕሮፌሰር መስፍንን መጽሃፍ “ባዘለው መልካም መልዕክት ከመሳብ ይልቅ” ከ”ቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጋር ተደባልቆ “ስለቀረበ “በጠረኑ ብቻ ብዙ ሰው ሊገፈተር ይችላል” የሚል የተምታታ ነገር ስላቀረበ የ”ቀኝ” የ”ግራ” የሚሉት ፖለቲካ ፈሊጥ ከየት እንደመጣ እና ማን በቀኝ ማን በግራ እንሚፈረጅ ማወቂያው ጊዜ አሁን ነው ብዬ ተነሳሁ። እናም ኮሌጅ መበጠስ ሳያስፈለግኝ እድሜ ለዊኪፔዲያ ፈሊጡ ከፈረንሳይ አብዮት የመጣ መሆኑን አጫወተኝ። እጅግ የሚገርመው እንደዊኪፔዲያ ትንተና ከሆነ የፕሮፌሰር አመለካከትም ሆነ የፖለቲካ አቋም የግራ የሚባል እንጂ ከቀኝ ዘመም የሚሰለፍ አይደለም። ፕሮፌሰሩ ያልተገራ ስልጣንን አደብ እንዲገዛ እና እንዲገራ እውነትን ለስልጣን እየነገሩ (speak truth to power) እንዲል ፈረንጅ በሶስት አገዛዝ እድሜ ልካቸውን እንዳልባጁ በጥራዝ ነጠቅነትና በጀሌነት ራሱን “ግራ ዘመም” አድርጎ ሲግበሰበስ የነበረው እና የኢትዮጵያን ሕዝብ በ”መሬት ለአራሹ” እና “የብሄር ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል መብት” ባዶ መፈክር ከግለሰብ ጉልተኞች በሰፊው ሕዝብ ስም ለአገዛዝ ጢስኝነት አሳልፎ የሰጠውና ለአደገኛ የመከፋፈል የጎሳ ፖለቲካ የዳረገው ክፍል እስከዛሬ ፕሮፌሰር መስፍንን የ”ቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጠማቂ” እና አከፋፋይ ያደርጋቸዋል። የእዚህ አንድምታ ፕሮፌሰሩን ወግ አጥባቂ እንዲያም ሲል አድሃሪ አድርጎ በመሳል ራስን ተራማጅ እና “የላብ አደር/ወዛደር፤ አርሶ አደር፤ ጭቁን ብሄር ብሄረሰብ እና የሰፊው ሕዝብ/ሕዝቦች” ተቋርቋሪ አድርጎ ለማቅረብ ነው። ይህንን ክፍል ነው ታምራት “ብዙው ሰው” ሲል ከሳለው በኋላ በፕሮፌሰር መስፍን “የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጠረን” ይገፈተራል የሚለን። በገዛ ራሳቸው አእምሯቸውን ከ1969 ዓ.ም በኋላ እንዳያድግ አድርገው የዘጉትን ግለሰቦች ፕሮፌሰር ምን ማድረግ ይችላሉ? የቀኝ ዘመም ፖለቲካ እንደ ፕሮፌሰር ከሆነ እጅግ አድርጎ የሚስብ እንጂ የሚገፋተር አይደለም። ታምራት በሚኖርበት አሜሪካ ሁለት የታወቁ አንዱ አሁንም በሕይወት ያለ አንዱ ከሶስት አመት በፊት የሞተ ስመጥሩ የማህበረሰብ፣ የፖለቲካና የታሪክ ተንታኞች ይገኛሉ። በሕይወት ያለው ኖም ቾምስኪ ሲሆን ሟቹ ደግሞ ሆዋርድ ዚን ይባላል። ሁለቱም በቀይ ህንዶች እና በጥቁር አሜሪካኖች ላይ የተፈጸመውን ግፍ እያነሱ እንዲሁም የአሜሪካንን የሌሎችን አገሮች የመቆጣጠር (Hegemonic) አባዜ ያለውን የውጭ ፖሊሲውን የሞገቱ ሲሆን አንድም ጊዜ ግን በአሜሪካ ግፍ የተፈጸመባቸውን የተለያየ ዝርያ ያላቸውን አሜሪካኖች በዘር አንጻር የዘር “ነጻ አውጪ ፖለቲካ” እንዲያቀነቅኑ እንደእኛ “ግራ ዘመም” የብሄር ብሄረሰብ ተቋርቋሪዎች አልመከሩም። እንደእሱ ያለው አመለካከት ከኢትዮጲያ በኋላ በተፈጠረችው እና በራሱ የታምራት ቋንቋ “ተቀራራቢ ምናባዊ” አሜሪካንን ለመፍጠር በተሳካላት አገር አገርን እንደመክዳት ይቆጠራል ሃሳቡን ማንሳት እንኳ ባይከለከልም። በአጠቃላይ የፖለቲካ አመለካከታቸውም ሆነ እድሜያቸው ከፕሮፌሰር መስፍን ብዙም የማይራራቁት እነዚህ አሜሪካኖች የሚፈረጁት በግራ ፖለቲከኛነት እንጂ በ”ቀኝ ዘመም” ፖለቲካ ጠላ ጠማቂነት አይደለም። የቀኝ እና የግራው ፍረጃ እንዲህ ግልጽ ከሆነ ለምን ታምራት ሊያጨናብረን ፈለገ? ሳያውቀው የእኛዎቹ “የግራ ዘመም” የብሄር ብሄረሰብ ተቋርቋሪ “ፖለቲከኞች” ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ይሆን? ጥያቄውን የመመለስ ያለመመለስ መብቱ የታምራት ሆኖ ሳለ ይህን ጽሁፉን ከአድናቂዎችም በላይ አምላኪዎችንም ያፈራችው የአዲስ ነገር ፌስቡክ ገጽ ላይ ስለለበደው አስተያዬቱ እንደወንጌል እንዳይወሰድ ሌላውን ገጽታ ማሳያት ግዴታዬ ሆኖ ተስምቶኛል። እናም ፕሮፌስር መስፍንን ፈረንጅ (whispering campaign )በሚለው የረቀቀ ስልት እንዴት እና ለምን ለሶስቱም አገዛዝ ቅርብ የነበሩ የተለያዩ ግለሰቦች ስማቸውን ለማጥፈት እና ሥራቸውን ለማቃለል እንደተነሳሱ ላሳይ። ታምራት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ነው ለማለት ሳይሆን በእነሱ ተጨናብሮ ሊያጨናብር ተነስቷል ግን እላለሁ። ፕሮፌሰር መስፍንን መጀመሪያ በበጎ ከማያነሷቸው ሰዎች ውስጥ የእድሜ እኩያቸው ከሆኑትና የሙያ “አቻቸው” ከሆኑት ውስጥ እንደሚገኙበት በተለያየ አጋጣሚ ለመታዘብ ችያለሁ። እነዚህ ሰዎች እንደእሳቸው ባለዲግሪ ቢሆኑም ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) “አይተኙበት ጀንዲ ዲግሪማ ነበረን በአይነት በብዛት” የሚላቸው አይነት ሰነፎች ሲሆኑ በምሁርነታቸው እያነበቡ እና እየተመራመሩ ከማደግ ይልቅ ለዘውዱ ሥርዓት እጅ እየነሱና እየተሞዳሞዱ ማደግን የኑሮ ዘዴ አድርገው የያዙና ለልጆቻቸውም ሲመክሩ የነበሩ ናቸው። የመስፍን ፍጹም በራስ መተመማን ሁልጊዜ የእነዚህን ሰዎች ድኩማንነት የሚያስታውስ ስለሆነ በቅናት መንፈስ መስፍንን ማብጠልጠል አንዱ መላ ነበር። መስፍንን እና እንደእሳቸው የዘውዱን ሥርዓት የአካዳሚክ ነፃነታቸውን ተጠቅመው የሚተቹትን ለማግለል ሲባል በአክሊሉ ካቢኔ ለመስፍን የግምቢ አውርጃ ገዢነት ሹመት ሲሰጥ ለሌሎች ደግሞ የክፍ ለሃገር ከተማ ከንቲባነት እና በሞስኮ ከተማ አታሼነት ተሰጠ። ሌሎቹ ያለምንም ማንገራገር ሹመቱን ሲቀበሉ መስፍን ግን ስለሹመቱ ከንጉሱ ማብራሪያ ካላገኙ እንደማይሄዱ ተናገሩ። የአክሊሉ ካቢኔም “ሹመቱ የተሰጠህ ከመተቸት ውጭ የተሻለ አስተዳደር ታመጣ እንደሆነ እንድታሳየን ነው” አላቸው። ሲመልሱም “በአውሮፕላን ስሄድ አየር ላይ መናጥ ሲበዛብኝ አስተናጋጁን ምነው መናጥ በዛ ስለው መልሱ ከቻልክ የማብረሪያው ክፍል (cockpit) ግባና አውሮፕላኑን አብረው ሊሆን አይገባም። “ሲሉ የአካዳሚክ ነጻነቱን ተጠቅሞ በሚያስተምር ምሁር ላይ አጸፋዊ እርምጃ መወሰድ እንደሌለበት አስረዱ። ለዚህ ጠንካራ አቋማቸውም ጥቂት ቀናት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲከርሙ ሆነ። ይህንን የፕሮፌስር መስፍንን የአካዳሚክ ነፃነትን የማስከበር ፅኑ አቋም “የማስተዳደር ሥራ ስለማይችል ነው ሹመቱን ያልተቀበለው” በሚል ስማቸውን የሚያጠፉ የእድሜ እኩዮቻቸው አጋጥመውኛል። በደርግ ጊዜ በመርማሪ ኮሚሲዮኑ ተመርጠው ለጥቂት ጊዜ በመስራታቸው የተነሳ ስድሳዎቹን እንዳስረሸኑ አድርገው የሚያስወሩ ስራፈቶችና ይህንኑ የሚያምኑ ጅሎች እስከዛሬ መኖራቸውንም ታዝቤያለሁ። የደርግ ዋና ሰዎች መንግስቱ ኃ/ማሪያምንም ጨምሮ እስከዛሬ ድረስ ሳይገድሏቸው በመውደቃቸው እንዲሁ ስማቸውን ለማጥፋት እንደባጁ አሉ። ግን በወያኔ የውሸት ፍርድ ቤት ለማስመሰል እንኳ የሚበቃ ቅንጣት ማስረጃ ስለሌለ መንግስቱም ሟቹ መለስም አንዳቸው የወያኔ ሰው ነው ሌላኛቸው ደግሞ የደርግ ሰው ነው ብለው ስማቸውን ከሚያጠፉ በቀር የፕሮፌሰር መስፍን የረጅም ዘመን ታሪክ ላይ ጉድፍ ማግኘት አልተቻለም። የዘውዱን ሥርዓት እቃወማለሁ ይል የነበረውና ራሱን በግራ የፈረጀው የተማሪው እንቅስቃሴም ወደብረት የአመፅ ትግል ሲያዘነብል ሃሳብ ለሃሳብ ብቻ የሚፋጭበት የአካዳሚክ ሕይወትና ጡንቻ አብረው አይሄዱም በማለት ፕሮፌሰሩ ስለተቃወሙ ከዚህ ጮርቃነት እስከዛሬ ያልወጡት ስማቸውን እንዳብጠለጠሉት አሉ። እናም ይቺ በታምራትም ፕሮፌሰሩን “የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ጠላ ጠማቂ” የማድረግ ነገር ምንጯ ከዚህ የተለየ አይደለም። ባጭሩ ፕሮፌሰሩ በፅኑ አቋማቸው የተነሳ ቀኝ ተብለው የተፈረጁበት ሁኔታ “ግራ ዘመም” ነኝ የሚለውን ኢትዮጲያዊ የዘወትር ክሽፈት የሚያሳይ ዝብዛንኬ ነው። ታምራት “ባንድም ሆነ በሌላም መልኩ ስለመክሸፍ የኢትዮጵያ ምሁራን አውርተዋል” ሲል በተማሪዎች ረብሸኝነት በጎሳ ነጻ አውጪነት እና የጎሳ ማህበራት ተሰባስበው ራሳቸውን የሽግግር መንግስት ስላሉበት ሁኔታ አለመሳካት የጻፉትን ከመስፍን የመክሸፍ ትንተና ጋር ማያያዙ አንዱ ከመጽሃፉ በኋላም እንኳ እንዴት መክሸፍ እንዳላባራ ማሳያ ነው። ታምራት የጠቀሳቸው ምሁራን በአብዛኛው ከሽፎ ስላከሸፈ ትውልድ መክሸፍን እንደሚፈልገው አድርጎ እንዲቀጥል ባለማድረጉ ስላለው ክሽፈት ካልሆነ በቀር ስለኢትዮጵያ ታሪክ ክሽፈት ጻፉ፤ ተመራመሩ ለማለት አይቻልም። እነዚህ በአብዛኛው ራሱ ታምራት ለሚለው “የምናባዊት ኢትዮጲያ ማህበረሰብ” አለመፈጠር ምክንያት ሆነው ከሽፈው ያከሸፉ ናቸው። እንዴት ሆኖ በእኔ ሞት የኢሕአዴግ የሽግግር መንግስት ክሽፈት ከኢትዮጵያ መክሸፍ ትንተና ጋር የሚያያዘው? ኢሕአዴግ የሚባለው መጥቶ ወንበሩ ላይ ሲቀመጥ የኢትዮጵያ መክሸፍ የለየለት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ኦነግ እና ወያኔ ሽግግር በሚባለው ዘመን ተጣልተው በየፊናቸው ባይሄዱ ኖሮ ክሽፈት አልነበረም ለማለት ከሆነ ከባድ ቧልት ነው።
        ታምራት “ስለኢትዮጲያ ሲባል ለምን ሐበሻ ልቡ ይፈሳል?” ሲል የጠየቀውን ጥያቄ ኢትዮጲዊነት ገብቶት ነው ብዬ ባስብ ኖሮ እወድለት ነበር። አንዱ የሐበሻን ልብ የሚያፈሰው እንደዚህ እሱ እንደጻፈው ያለ የተሳከረ ፅሁፍ መሆኑን ልነግረው እወዳለሁ። አገር ወዳድነት ሌላ ቦቃ የለውም ከመንደርተኝነት መውጣት ነው። ከመንደርተኝነት የወጣ ሰው ስለአገር ወዳድነት ማብራራት የግድ ካለበት እንደሩሲያዊው ሌሮሞንቶቭ “I love my country, but with a strange love. My reason cannot fathom it.” ማለት ብቻ ይበቃዋል። ሌላው ሃተታ በማያንሰራራ ሁኔታ ይበልጥ እንድንከሽፍ ማጨናበር ነው።

        ህዝበ ክርስቲያንን ያሳዘነ ሥልጣን በእግዚአብሔር ቤት መቅሰፍት ነዉ! ከዉርደትና ዉድቀት ሌላ የሚያመጣዉ ተስፋ የለም!

        በአጥቃዉ ቦጋለ
        በቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነጻነት ከአደጋ ላይ ወድቋል። ታሪካዊትና ቀደምት  ቤተክርስቲያናችን  ዉስጥ በሃይል ገብቶ የመሸገዉ የገዥዉ ቡድን ለዘመናት በኖሩ የሃይማኖት እምነቶች ላይ የሃይል ዘመቻ ከፍቷል፤ የአማኙን ህዝበ  ሰላም  ነስቷል። የእርቀ ፤ የሰላምና አንድነት መድረክ ተዘግቶ ከምዕመናን ፍላጎት ዉጭ የታካሄደዉ የካድሬዎች የሃይማኖት መሪ  ሹመት እጅግ አሳሳቢ ሁኗል። መንግስት በጥንታዊታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ እጁን አስገብቶ እየፈጸመ ያለዉን ህገ ወጥ ድርጊት በጥብቅ እንቃወማለን።
        በሃይማኖት አባቶች አማካይነት የሰላምና አንድነት ጉባኤ ለሶስት ተከታታይ አመታት  ፓትርያሪክ በህይዎት እያለ ቀኖና ተጥሶ በመንግስት ጣልጋ ገብነትና አስገዳጅነት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስን አዉርዶ የተካሄደዉን  ህገወጥ ሹመት በእርቅ መፍትሄ ለመፈለግ የተጀመረዉን የሽምግልና ሂደት የወያኔዉ ቡድን አሰናክሎ እንደተለመደዉ በዘር ያዘጋጃቸዉን  የካድሬ አባት ሹሟል።  ይህንን ከንቱ የጥፋት ሹመት ህዝበ ክርስቲያን ከአሁን በፊትም በአባትነት አልተቀበለም አሁንም አይቀበለዉም። በምክክር ለመፍታት የተጀመረዉን ጥረት አክሽፎ የኔ ዘር ብቻ ስልጣን ላይ መቆናጠጥ አለበት በሚለዉ የወያኔ ጎጠኛ አባዜና ጣልቃ ገብነት በሩ ተዘግቶ  የሰላምና አንድነት ሂደቱ በሃል ተገፍትሮ  በአጣዳፊ  አሁንም እንደገና የተካሄደዉን ህገወጥ የፓትርያሪክ  የዉምብድና ምርጫ በጽኑ እናወግዛለን።
        እኛ ምዕመናን በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያሪክ ዘኢትዮጵያ የሚመራዉን ህጋዊ ቅዱስ  ሲኖዶስ ያወጣዉን መግለጫና መመሪያ  በሙሉ ድጋፍ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችን እንገልጻለን። በዘር ተደራጅቶ የእናት በተክርስቲያንችን  ታሪካዊ ጥንካሬ የሚሸረሽር ቀኖናን የሻረ ሴራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ከመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሁነነን የሃይማኖትና የህዝቦች መብት የሚያስከብር ስርዓት እስከ እስኪረጋገጥ ድረስ ከህጋዊ  ቅዱስ ሲ ሰኖዶስ  ጎን ተሰልፈን ድጋፋችን እየሰጠን  እስከ መጨረሻዉ የሰላም ምዕራፍ እንደምንቀጥል ቃል እንገባለን።
        የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በተክርስቲያን ምዕመናን/ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ
        በእግዚአብሔር ቤት አባቶችን ማሳደድ፤ በምዕመናንን የዕምነት ነጻነት ጣልቃ መግባት፤ ለእርቀ ሰላም  የቆሙ በህዝብ የተወከሉ አባቶችን አሸባሪ ናቸዉ ይታሰሩ፤ ይገረፉ፤ ይሰቀሉ የሚል ቡድን  በምንኮራባት አገራችን የጥፋት ዘመቻ ሲከፍት በቸልታ ማየትና የገለልተኛ ኑሮን ማመማቸት ፍጹም ሃይማኖታችን አይፈቅድም። አበዉ አባቶቻችንም  በችግር ጊዜ አንድ እንድንሆን መክረዋል፤ ለዘመናት በሃይማኖትና በአገር ነጻነት ተጋድሏቸዉ አስመስክረዋል፤ በችግር ጊዜ ጠላት ጥቃት ሲዘነዝርብን ያለምን ቅድመ ሁኔታ ይቅር ተባብለን በአንድ ላይ እንድንቆም እና በአሸናፊነት እንድንወጣ ህያዉ የሆነ ትምህርት አስተምረዉ አልፈዋል፤ ይህን ከትዉልድ  ወደ  ትዉልድ የተላለፈ እንደ አገርና እንደ ህዝብ አጽንቶ ያኖረንን የአበዉ ቃል ማክበርና ማስከበር ብሎም የእግዚአብሄርን ቤት በዕምነት ጸንቶ መጠበቅ ህያዉ ሥራ ነዉ።
        ዉድ ምዕመናን !
        ለሃይማኖታችን ነጻንት ከምን ጊዜዉም በበለጠ አንድነታችን አጠናክረን  በግፍ ከተሰደዱት የሃይማኖት አባታችን ከብጹዕ ወቅዱ አቡነ መርቆሪዮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፓትርያሪክ ዘኢትዮጵያን  ቡራኬ እየተቀበልን ጸሎታችን ለማሰማት ወደ ቸሩ አንድ አምላክ የምንጮህበት ዘመን አሁን ነዉ። ብጹዕ አባቶች በገዳማትና በአድባራት ተማዕጽኖ  በጾም በጾለት ተለምነዉ ተመርጠዉ በሚሾሙበት የየተቀደሰ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መንበር በዘር አድሎ ሹመት  በቅድስት አገር ኢትዮጵያ እዮተፈጸመ ያለዉን ድርጊት አጥብቀን ማዉገዝ አለብን።  መላዉ ምዕመናን ተባብረን በመታገል በቤተ ክርስቲያናችን የሚካሄደዉን ህገ ወጥ ሴራ ለማስቆም  በዕዉነት እንነሣ። በመጨረሻም የህዝብ መብትና የሃይማኖት ነጻነት በእናት አገራችን እንዲከበር ሁሉም  የኢትዮጵያ ህዝብ እጅና ጓንት ሁኖ ድምጽ እንዲያሰማ  መልክቴን አስተላልፋለሁ።
        በመጨረሻም የዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን/ካቴድራል መላዉ ምዕመናን በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ርሰ ሊቃነ ጳጳሳ ፓትርራሪክ ዘኢትዮጵያ በሚመራዉ ሲኖዶስ በህዝብ ድምጽ ወስኖ መቀላቀሉ ለኦርቶዶክስ አማኝ ሁሉ ታላቅ ደስታ ነዉ። እንኳን ደስ ያላችሁ እላለለሁ። ይህ ትልቁ የአንድነታችን ወሳኙ አካል ነዉ። ብዙዎች ገለልተኛ በሚል ዘይቤ ታፍነዉ የኖሩ ምዕመናን በድምጽ ዉሳኔ ወደ አንድነቱ ጎራ እንደሚቀላቀል እርግጠኛ ነኝ። በተለይም የዋሽንግተን ዲሲ ቅድስት ማሪያምእና  የሚኖሶታ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቅዱስ መድሃኒያለም ምዕመናን ድምጻቸዉ የሚያሰሙበት ጊዜ ደርሷልና አሁኑኑ ሳይዘገይ  ይወስኑ። የኦርቶዶክስ አንድነት ሙሉ በሙሉ ከዳላስ መቀላቀል በኋላ ተረጋግጧል።
        ቅድስት አገር ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይጠብቅ!!!
        ወስብሃተ ለእግዚአብሔር።

        Monday, March 25, 2013


        ቆብ ላይ ሚዶ ትምህርትና ተማሪ ቤት

        (ክፍል አንድ)
        ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም
        ጥር 2005
        በአለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ አንድ ልብ ያላልነው መሠረታዊ ለውጥ አለ፤ እንዲያውም የመከራችን ሁሉ ምንጭ ነው ለማለት ይቻላል፤ የመሪዎቻችን አለመማር ብቻ ሳይሆን ትምህርትን መናቅ ወይምProfessor Mesfin Woldemariam is one of Ethiopia's well-known intellectuals ጭራሹኑ መጥላት ዋና ባሕርያቸው ሆነ፤ እስከደርግ ዘመን የነበሩት የአገር መሪዎች ቢያንስ የአንደኛ ደረጃውን (ዳዊት መድገም) የአገሩን ባህላዊ ትምህርት ያከናወኑ ነበሩ፤ ከዚያ በኋላ ለጨዋ ቤተሰብ ልጆች ትምህርት ማለት በቤተ መንግሥት በመዋል የሚገኝ ልምድ ነበር፤ ተፈሪ መኮንን በአሥራ ሦስት ዓመቱ ደጃዝማች የሆነውና ሥልጣን ላይ የወጣው በመወለድ ያገኘውን ዕድል በልምድ እንዲያዳብረው ነበር፤ ተክለ ሐዋርያት ከአሥር ዓመታት በላይ ሩስያ ተምሮ ሲመለስ ተፈሪ ያገኘውን አላገኘም።
        በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ትውልድ ለሥልጣን መነሻ አይሆንም ነበር ባይባልም፣ ለእድገት ትምህርት አስፈላጊ መሆኑ በመታመኑ የዓየር ኃይል እጩ መኮንኖችም ሆኑ መኮንኖቹ ከደብረ ዘይት እየተመላለሱ ይማሩ ነበር፤ በማታው ትምህርት ብዙ የፖሊስና የጦር ሠራዊት መኮንኖች (ኮሎኔል ሚካኤል አንዶም ጭምር) ይማሩ ነበር፤ ማታ ከተማሩት የፖሊስ መኮንኖች ውስጥ ሁለቱ አምባሳደሮችም ሚኒስትሮችም ሆነው ነበር፤ ከሐረር አካደሚ የወጣ መኮንንም አምባሳደር ሆኖ ነበር፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ የደሀ ልጆች ወደሥልጣን ወንበሩ አልተጠጉም የሚሉ ካሉ የማያውቁ ናቸው፤ ትምህርታቸውን በታማኝነት ከፍነው ቀብረው ሚኒስትርና ሌላም ሹመት ያገኙ የደሀ ልጆች ብዙዎች ናቸው።
        ከዚያ ወዲህ ከጨዋ በመወለድ ሥልጣንን ከማግኘት በባለጌ ጡንቻ ሥልጣን ወደማግኘት ተዘዋውረናል፤ ትውልድን ወደእኩልነት የሚገፋ አስተሳሰብ ስንቀበል ብልግናንንና ጡንቻን ወይም ሕገ አራዊትን፣ ተሳዳቢነትንና ዘራፊነትን፣ድንቁርናንና ሚዛነ-ቢስነትን የእኩልነትና የነጻነት አካል አድርገን የተቀበልን ይመስላል፤ በስድነትና በነጻነት መሀከል ያለውን ገደል ባለጌ አያየውም፤ የጨዋ ልጅ ዳዊት ከደገመ በኋላ እንደበቅሎ እየተገራ ያድጋል፤ ከጃፓን እስከእንግልጣር ተመሳሳይ ሁኔታ የነበረ ይመስላል፤ ነገር ግን ወደአውሮፓውያን ሥልጣኔ ስንንደረደር በጃፓናውያንና በእኛ መሀከል የታየው ልዩነት እነሱ ጨዋነታቸውን እንደያዙ እኛ ደግሞ ጨዋነታችንን ትተን መነሣታችን ነው።
        አብዮት ወይም ወያኔ ማለት ትምህርትም ሆነ ጨዋነት ለሥልጣን አስፈላጊ እንዳልሆኑ በአደባባይ ማሳየት ሆነ፤ (አብዮትን ከማየቴ በፊት አብዮተኛ ነበርሁ ለማለት የምችል ይመስለኛል፤ አብዮትን ካየሁ በኋላ ግን ወዲያው ጠላሁት፤) አብዮተኛ ማለት አእምሮ የሌለው፣ ኅሊና የሌለው፣ እግዜአብሔር የሌለው፣ ሚዛን የሌለው ከጡንቻ በቀር ሌላ ኃይል የማያውቅ ማለት ሆነ፤ በጡንቻ የማይሠራ ነገር ከሌለ ትምህርት ለምን ያስልጋል? ከሁሉም ይበልጥ የሚያስደንቀውና የሚያስደነግጠው ትምህርትን በሥልጣን የመለወጡ ሙከራ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጀመሩ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ላዩን በግልቢያ የተደረጉ ጥናቶች ብዙ ቢሆኑም ጠለቅ ያለና የውስጡን መነሻ እየመዘዘ የሚያወጣ አንድም የለም።
        ደርግ ሥልጣን እንደተሸከመ በየመሥሪያ ቤቱ አንዳንድ መኮንኖችን ‹‹የለውጥ ሐዋርያ›› በሚል ስያሜ ፈላጭ-ቆራጭ አድርጎ አስቀመጠ፤ ትእዛዙ በወታደራዊ ፍጥነት እንደውሀ ከላይ ወደታች እንዲፈስ ተፈልጎ ነበር፤ ነገር ግን ሥራ ሁሉ ወደመቆም ስለደረሰ ደርግ ቶሎ ብሎ ተለወጠና የለውጥ ሐዋርያት የሚባሉትን አነሣቸው፤ ከዚያ በኋላ ደርግ በሁለት ተቃራኒ ሁኔታዎች ተወጥሮ ተያዘ፤ በአንድ በኩል ከባሕር ኃይልና ከዓየር ኃይል፣ ከሐረር የጦር ትምህርት ቤትና ከአገር ውጭም የተማሩ መኮንኖች ነበሩ፤ በሌላ በኩል ከሆለታ ማሠልጠኛ የወጡ ነበሩ፤ በነዚህ በሁለቱ በተለያየ የትምህርት መሠረት ላይ በቆሙ መኮንኖች መሀከል አጉል ፉክክርና መናናቅ ነበረ፤ በተለይም ጄኔራል አማን በተማሩት መከበቡ የተማሩትን ዓይን እንዲገቡ አደረጋቸው፤ አብዛኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቆች የሆኑ መኮንኖች በየሰበቡ የተጠረጉት በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፤ በዚህም ምክንያት ደርግ ገለባ ያንሳፈፈበት ድርጅት ሆኖ ነበር ለማለት ቢቻልም ከደርግ ውጭ የተመለመሉት ሎሌዎች (ባለሥልጣኖች) የተማሩና በማናቸውም መመዘኛ የማያሳፍሩ ነበሩ።
        የደርግ አባሎችም አለመማር ያስከተለባቸውን ጉድለት ለመሙላት በየሶሺያሊስት አገሩ የይድረስ-ይድረስ ለብ ለብ ትምህርት-ቢጤ በጉርሻ እየተሰጣቸው ተመለሱ፤ (የዛሬ ዘመን ትውልድ ያለጉርሻ ያደገ ነው፤ አሽከር ወይም ልጅ ገበታ ከመቅረቡ በፊት እጅ ያስታጥባል፤ ቆሞ፣ ኩራዝ ይዞ ካበላ በኋላ ጉርሻ ይቀበላል፤ ከዚያም እጅ አስታጥቦ ጉርሻውን ይበላል፤) በአቋራጭ ዲግሪም አገኘን ብለውም ተኩራርተው ነበር፤ በሶሺያሊስት አገሮች ሁሉ እየተሽከረከሩ ትምህርት የተባለውን ቢያርከፈክፉባቸውም ውሀ በስንጥቅ መሬት ውስጥ ሰተት ብሎ እንደሚገባ በእነሱ አንጎል ውስጥ አልገባም፤ ሆኖም በሶሺያሊስት መንግሥቶች ዓለም-አቀፋዊ ፍቅርና ብርቱ ሎሌዎችን የማፍራት ፍላጎት ለስድስት ወራት ያህል በድሎት አቆይተው የፈለጉትን ብራና አስታቅፈው ይልኳቸው ነበር፤ ብዙዎቹ ምንም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ እየያዛቸው ‹‹ዶክተር›› የሚለውን የትምህርት ማዕርግ አልደፈሩትም ነበር፤ ከመሀከላቸው አንዱ ግን እንደተመለሰ በያለበት እየዞረ ‹‹ዶክተር›› መሆኑን ሰዎች ሁሉ እንዳይረሱት እያደረገ አስታወቀ፤ ራሱን ለፌዝ አጋለጠ፤ መሳቂያ ሆነ፤ በመጨረሻም አውነቱና አጉል ፍላጎቱ እየተጋጩ በመቸገሩ ከፎቅ ላይ ተከስክሶ ሁለቱንም ራሱን (ማለት የእውነቱንም የውሸቱንም) አጠፋ፤ ያሳዝናል።
        በቆብ ላይ ሚዶ ጥቅም አይሰጥም፤ በቆብ ላይ ሚዶ ለጌጥ አይሆንም፤ ትምህርትን መሣሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት የማይችሉ ሰዎች፣ ከዚያም አልፈው ሥልጣንን በትምህርት ማስጌጥ የማይችሉ ሰዎች ሥልጣንን ያዋርዳሉ፤ በኋላ ሥልጣንም ያዋርዳቸዋል።
        (ክፍል ሁለት)
        የዛሬዎቹ ባለሥልጣኖች በደርግ ጊዜ አልነበሩም፤ የደርግን ስሕተት በማየት አልተማሩም፤ ትምህርታን አቋርጠው ወደጫካ የገቡት ከትምህርት የሚበልጥባቸው ምኞት አጋጥሟቸው ነው፤ የትምህርት ገዜያቸውን በጫካ ባለሥልጣን በመሆን፣ እነሱው ሕግ አውጪና ዳኛ፣ እነሱው የጫካ አስፈጻሚ ሆነው ቀዩ፤ ደርግ በጠራራ ጸሐይ የሚሠራውን እነሱ በጫካ ጭለማ ሲሠሩ ቆዩ፤ በሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላም በጣም ቆይተው ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን በትንሹ ተገነዘቡ፤ በጣም የተማሩ ሰዎች ጋር ሲገናኙ ማፈር አስጨነቃቸው፤ ስለዚህም ቀላሉ ነገር የተማሩ ሰዎችን አለማቅረብ፣ ትምህርታቸውን በጠባያቸው ካላጠቡ የተማሩ ሰዎች ጋር በቀር አለመገናኘት፣ እንዲያውም የትምህርትን ዋጋና ጥራት በማዋረድ አዲስ የሚመረቁት ሁሉ ለባለሥልጣኖች አንገታቸውን የሚደፉ ዓይነት እንዲሆኑ ማድረግ ዓላማ ሆነ።
        የተማሩና የሠለጠኑ የጦር መኮንኖችም ተሸናፊዎች በመሆናቸው ትምህርታቸው ዋጋ እንደሌለው ማረጋጋጫ እያደረጉ የወያኔ መሪዎች በአደባባይ ተናገሩ፤ ትንሽዋ ቢምቢ ሰውን መግደል እንደምትችል ያልተገነዘቡት ከጫካ የመጡ ሰዎች በመግደል ማሸነፍን የትምህርትን ዋጋ-ቢስነት ማረጋጋጫ አደረጉት፤ የተማሩ ሰላማዊም የጦር መኮንኖችም ዋጋ-ቢስነታቸው ኑሮአቸውን በማናጋቱ በችግር ወደሌላ ሥራ ተሰማሩ፤ ወይም አገር ጥለው ተሰደዱ፤ በሰላማዊውም ሆነ በፖሊስና በጦር ሠራዊቱ የተማረ ሰው እጥረት መፈጠሩ ለወያኔ መግቢያና መደላደያ ምቹ ሁኔታን ፈጠረ።
        በየትኛውም የሥልጣን ወንበር ላይ ለመቀመጥ ማናቸውም ዓይነት የትምህርት መመዘኛ ተሽሮ ሚዛኑ ስለተሰበረ ማንንም ከሜዳ እያነሡ በተፈለገው ወንበር ላይ ማስቀመጥ እየተለመደ ሄደ፤ በየሚኒስቴሩ ከመከላከያ ጀምሮ እስከአገር አስተዳደርና የውጭ ጉዳይ ወንበሮች ላይ የተደለደሉት ሁሉ ችሎታም ሆነ ብቃት ሳይኖራቸው ነበር፤ አንዳንዶች ብልጥ የሆኑት ከዱሮው መንግሥት ባለሥልጣኖች ውስጥ አንገታቸውን ደፍተው ሊሠሩ የሚችሉትን በጓዳቸው አስቀምጠው እንዲሠሩላቸው ያደርጉ ነበር፤ ቀንደኛ የኢሠፓ አባሎች ሳይቀሩ በጓዳ በር ተቀጥረው ነበር፤ በመሠረቱ የተማረ ሰው ለአሽከርነት አይመችም፤ ሆኖም የአሽከርነት ባሕርይ ያለው ሰው ቢማርም ትምህርቱ የባሕርዩን ጉድፍ አያጥበውም፤ አንዳንዶቻችን እንደምናውቀው ለአጼ ኃይለ ሥላሴም፣ ለኮሎኔል መንግሥቱም፣ ለመለስም በተከታታይ ታማኝ እየሆኑ ያገለገሉ ሰዎች አሉ፤ የማይታመኑ መሆናቸውን ያስመሰከሩ ሰዎች የሚታመኑበት አገር ከኢትዮጵያ ሌላ መኖሩን አላውቅም፤ ከኢጣልያ ወረራ ጀምሮ ይህ የእንጀራ ሎሌነት እየተለመደ ብሔራዊ ባሕርይ ወደመሆን እየተጠጋ ነው።
        በትምህርትና በተግባር መሀከል ድልድይ የማይገኝለት ገደል ተፈጠረ፤ ትምህርት በሎሌነት! ሎሌ ለመሆን መማር! መማር ሎሌ ለመሆን! ሎሌነት ለአንድ ሰው፣ ሎሌነት ለአንድ ቡድን፣ ሎሌነት ለአንድ እምነት፣ ሎሌነት ለሆድ! አስቡት እንዲህ ያለ ሰው ምን ይማራል? ማን ያስተምረዋል? እንዴትስ ይማራል? ተምሮስ ምን ይሠራል? የተወረሰውን አንጎል ማጣጠብ ይቻል ይሆናል፤ አእምሮን ለሚያንጽ ትምህርት ግን ነጻነት ያለው አስተማሪ፣ ነጻነት ያለው ተማሪ፣ ነጻነት ያለበት መድረክ ያስፈልጋሉ፡፡
        የሆነላቸው ባለሥልጣኖች ወደውጭ እየሄዱ ልዩ የአቋራጭ ሥልጠና እየተሳተፉ፣ አለዚያ አስተማሪዎች ለጥቂት ጊዜ እዚሁ መጥተው የአቋራጩን ሥልጠና በአጭር ጊዜ ውስጥ እየሰጡ፤ ‹‹ተማርን›› ብለው ራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን አሳመኑ፤ ለምን የውጭ አገር ሰዎች አስፈለጉ? እነሱን ለማስተማር የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አልነበሩም ወይ? እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች አእምሮአቸው ማንሣት ባይችልም ወዳጅ ዘመዶች ሳይነግሯቸው የቀሩ አይመስልም፤ ግን እንዲህ ያለውን ምክር መቀበል አላዋቂነታቸውን ማጋለጥ ስለሚሆን ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም!
        የትምህርት ጊዜያቸውን ሥልጣንን በማሳደድ ለውጠው ሳይማሩ የቀሩት ከፍተኛ የአገር ገንዘብ ወጪ እያደረጉ በስማቸው ላይ የሚጨምሩት ምልክት የትምህርትን እውነተኛ ፍቺ እንዳልተገነዘቡ የሚያሳይ ነው፤ የትምህርት ማዕርጎች ከቢ.ኤ. ጀምሮ እስከፒኤች.ዲ. የትምህርት ቤት በራፉን ሳይረግጡ በግዢ ሊገኙ ይችላሉ፤ በግዢ የሚገኘው የምስክር ወረቀት እንጂ ትምህርት አይደለም፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያን ያህል አገር እያስተዳደሩ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመከታተል ይቻላል ወይ? ከተቻለ ወይ አገር መግዛቱ ጨዋታ ነው፤ ወይ ትምህርት የተባለው ጨዋታ ነው፤ ወይም ሁለቱም ጨዋታ ነው፤ ያለትምህርት አገር መግዛት ጨዋታ ነው፤ ያለሥርዓት ትምህርት ጨዋታ ነው፤ ለአዋቂ ሰው በጥንት ነገሥታት ዘመንም ቢሆን ያው ነበረ የሚል ክርክር ማንሣቱ ራስን ያጋልጣልና የሚበጅ አይመስለኝም፤ በቆብ ላይ ሚዶ ጌጥ አይሆንም፤ ጥቅምም የለው፤ ከቆቡ ስር ያለው መላጣ ቢሆንስ!
        በትዕቢት የተወጠሩት በአገር ላይ ባለሙሉ ሥልጣን የሆኑት ሰዎች የትምህርትን መሠረታዊ ባሕርይ ስተውታል፤ በመጀመሪያ መደበኛ ትምህርት በተወሰነ የእድሜ ክልል ውስጥ ወደተማሪ ቤት ለብዙ ዓመታት እየተመላለሱ የሚያገኙት እውቀት እንጂ በሥልጣን ወንበር ላይ ተቀምጠው እያዘዙ እንደዕቃ የሚያስመጡት አይደለም፤ መማር ደረጃ በደረጃ አስተማሪዎች የሚሰጡትን ትምህርት ተከታትሎ ፈተናዎችን እያለፉ የሚጓዙበት የእውቀት ጎዳና ነው፤ ትምህርት የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነት ነው፤ አስተማሪና ተማሪ ማለት አዋቂና አላዋቂ ማለት ነው፤ በየኔታ(የኔ ጌታ)ና በልጅ መሀከል ነው፤ አስተማሪው የተማሪውን አእምሮ በሕገ ኀልዮት፣ ጠባዩን በሥነ ሥርዓት እየገራ፣ እየተቆጣ፣ እየኮተኮተ የሚያሳድግ ነው።
        ትምህርት በተማሪዎች መሀከል ያለ ግንኙነት ነው፤ ተማሪዎችን የሚገራው አስተማሪው ብቻ አይደለም፤ ተማሪዎቹም እርስበርሳቸው አንዱ ከሌላው የሚማረውና የሚገራበት መንገድ ብዙ ነው፤ እርስበርሳቸው እየተቀላለዱ፣ እየተሰዳደቡ፣ እየተራረሙ፣ እየተፎካከሩና እየተገማመቱ የሚያድጉበት ሥርዓት ነው፤ ስለዚህም ተማሪዎች ትምህርት የሚያገኙት ከአስተማሪዎች ብቻ አይደለም፤ ይህ ሁሉ ሁኔታ በሌለበት በሥልጣን ወንበር ላይ ተኮፍሶ በሎሌነት በግል የተቀጠረውን አስተማሪ ወደታች እያዩ መማር የሚቻለው እንዴት ነው? መማር ማለት ወደላይ እያዩ ነው፤ ወደታች እያዩ መማር አይቻልም፤ አንድ ሰው ስለህክምና ምንም ሳይማር አውቃለሁ ብሎ ሥራ ከጀመረና አጉል መድኃኒት እየሰጠ የባሰ ሲያሳምምና አካልን እየቀደደ መልሶ መስፋት ሲያቅተው፣ በኋላ ሕመምተኞቹን አጋድሞ ህክምና ልማር ብሎ አስተማሪ ቢፈልግ ምን ይባላል?
        ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ተርፈው ብዙ ሌሎች አገሮችን አዳርሰዋል፤ የወያኔ ሹሞች ግን በከፍተኛ ወጪ ከአሜሪካና ከእንግልጣር የውጭ አገር ሰዎችን ሲያስመጡ የነበረው አንደኛ በኢትዮጵያዊ ተበልጠው ላለመታየት፣ሁለተኛ የአለማወቃቸውን መጠን እንዳይናገር ሹልክ ብሎ ገብቶ ሹልክ ብሎ ሳይታወቅ ቶሎ ወዳገሩ የሚመለስ የውጭ ሰው በማስፈለጉ፣ ሦስተኛ የገንዘብ ችግር ስለሌለ ነው።
        ባለሥልጣን ሆኖ አላዋቂ መሆን ያሳፍራል፤ አዋቂ መስሎ አላዋቂ ሆኖ መገኘት የባሰ ያሳፍራል፤ ሳይማሩ በጉልበት ባለሥልጣን መሆን ሰውዬውን ራሱን የሚያሳፍርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ ያፈረ ባለሥልጣን በጎ ነገርን አያስብም፤ በየሳምንቱ አንዳንድ ለጆሮ የሚቀፉና አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ ነገሮችን እንሰማለን፤ አይታረሙም፤ የሚናገሩት ክፉ ነገር ነገ ክፉ ውጤትን ሊያስከትል እንደሚችል አያውቁም፤ ሥልጣን አፋቸው እንዳመጣ እንዲናገሩ ያስችላቸዋል፤ አለመማራቸው ከዚያች ቅጽበት አልፈው እንዳያዩ ይጋርዳቸዋል።
        እድገት የሚመጣው ትምህርት በነጻነት ሲመራና፣ ሥልጣን በሕዝብ ቁጥጥር ሲያዝ ነው፤ ሥልጣን በነጻነት፣ ትምህርት በቁጥጥር የቁልቁለት መንገድ ነው።