Thursday, April 18, 2013


ሰበር ዜና – ‹‹ለፓትርያሪኩ መመሪያ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል›› የተባሉት ኣባይ ፀሃየ ከደጅ ተመለሱ

  • በሦስት ቡድኖ የተደራጀው የጨለማው ቡድን ‹‹የኣባይ ፀሃዬን አመራር›› ያቀናጃል
  • መመሪያው÷ የልዩ ጽ/ቤት፣ ፕሮቶኮል፣ ጥበቃ ሓላፊዎችን ምደባ ይመለከታል ተብሏል
  • ‹‹ኣባይ ፀሃዬ ከስኳር ኮርፖሬሽን በተጨማሪ ጠቅላይ ቤተ ክህነትን በበላይነት እንዲመሩ ከመንግሥት ትእዛዝ ተላልፏል፡፡ የትግራይ ተወላጆች የግቢውን አመራር ሙሉ በሙሉ እንረከበዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን በትግራዎት እንጂ በአማራ አትመራም፡፡ ለሚኒስትሮች የሚፈለገውን ጥቅም እያቀረብን እናስፈጽመዋለን፡፡››
/ኣባይ ፀሃዬ ለፓትርያሪኩ የሚሰጡትን ‹‹አመራር›› ከእነ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ጋራ ያስተባብራሉ የተባሉት በምሥራቅ ትግራይ የደብረ ኣላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም አበምኔት አባ ገብረ መድኅን ኀይለ ጊዮርጊስ ዛሬ ጠዋት የተናገሩት/
  • ፓትርያሪኩ ‹‹አባ›› ነኝ ባዩን ከግቢው እንዲያርቁላቸው መመሪያ ሰጥተዋል፤ ተፈጻሚነት ይኖረው ይኾን?
  • መንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያን አመራርና ምእመኑ ጉዳዩን ከምር አጢነው አቋም እንዲወስዱ ተጠይቋል፡፡
abai-tsehaye-tigraionline
አቶ ኣባይ ፀሃዬ
ከአምስተኛው ፓትርያሪክ ኅልፈተ ሕይወት በኋላ፣ የመንበረ ፓትርያሪኩን ላዕላይ መዋቅሮች በመቆጣጠርና ለተቋማዊ ለውጥ የታቀዱትን ተግባራት በማምከን÷ 1)ቡድናዊና ግለሰባዊ ጥቅሙን አስጠብቆ ለመቆየት፣2)ኦርቶዶክሳዊ ማንነትን በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ደብዛውን ለማጥፋትበልዩ ኹኔታ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የጨለማው ቡድን÷ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በጎጠኝነት፣ በፖሊቲካዊ ታማኝነትና በጥቅም ስቦ እና አቅርቦ ማሰለፍ መጀመሩ ተዘገበ፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መምሪያዎችና ድርጅቶች ውስጥ በሓላፊነት ደረጃ የተቀመጡ ጥቅመኞችን ጨምሮ የታወቀ ሹመት የሌላቸውን ነገር ግን የሁሉ ፈጣሪና ገባሪ ለመኾን ‹‹ሥልጣን›› ያገኙ ግለሰቦችን የሚያካትተው የጨለማ ቡድኑ÷ በፓትርያሪኩ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ላይ ማሰለፍ የጀመረው‹‹የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ነው›› ተብሏል፡፡ ቡድኑ በዚህ ስትራተጂው የህወሓት/ኢሕአዴግን ባለሥልጣናት ተጽዕኖ በመጠቀም በማንኛውም ቦታ በተለይም በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር ላይ ተጽዕኖውን ለማጠናከርና ያሻውን ለመፈጸም ማቀዱ ነው የተነገረው፡፡
ይኸው ስትራተጂ ባለፉት ኻያ ዓመታት መንበረ ፓትርያሪኩ ለክፍፍልና ትርምስ የተዳረገበት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ለጥቃትና ድብደባ የተጋለጡበት እንደነበር ያስታወሱት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች፣ ስልቱ በመልኩ አዲስ ባይሆንም በይዘቱ ግን ቡድኑ የተለየ ቁመና ይዞ የተደራጀበት መኾኑን ያስረዳሉ፡፡ እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ ፅልመታዊ ቡድኑ ለሦስት ኀይል ተከፍሎ በተለያዩ ግለሰቦች የሚመራ ሲሆን የተመረጡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እየተፈራረቀ በመወትወት/በማግባባት ተመሳሳይ ጉዳይን ከተለያየ አቅጣጫ እያስተነተነ ስለጉዳዩ አንድ ዐይነት ቀለም/ሥዕል ለመፍጠር ግፊት ያሳድራል፤ ለኾነ ርምጃ የሚያበቃ ውሳኔ እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡ በዚህም ቡድኑና አባላቱ ለመንግሥት ቀራቢና ተቆርቋሪ፣ ለቤተ ክርስቲያን አሳቢ መስለው ጋርዮሻዊና ግለሰባዊ ጥቅማቸውንና ሥልጣናቸውን ያስጠብቃሉ፡፡
ለሦስት ኀይል የተከፈለውን ‹‹የጨለማ ቡድን›› የሚመሩት ግለሰቦች፡-
  • አባ ገብረ መድኅን ኀይለ ጊዮርጊስ – በምሥራቅ ትግራይ የደብረ ኣላማ አሲራ መቲራ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳምአበምኔ
  • አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል – በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ዋና ሓላፊ                              
  • ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ – በመዋቅር የማይታወቀው የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅContinue reading 

በረኀብ የተዳከሙት ደቀ መዛሙርት ልመና በፖሊስ ታገደ፤ ፖሊስ ደቀ መዛሙርቱን ለመርዳት ከሚሞክሩ ምእመናን ጋራ ተወዛግቧል

  • ሓላፊዎቹ ከመምህራን የቀረቡላቸውን ሦስት ማግባቢያዎች በሙሉ ውድቅ አድርገዋል
  • ደቀ መዛሙርቱ በኮሌጁ አስተዳደር ላይ ክሥ መመሥረታቸው ተጠቁሟል
  • በአዲስ አበባ ዘመድ/መጠጊያ የሌላቸው ደቀ መዛሙርት በእጅጉ ተቸግረዋል
  • ፓትርያሪኩ ‹‹ጣልቃ አልገባም›› ማለታቸው የመምህራኑን ጥረት ጎድቷል
  • ‹‹ሃይማኖት የሌለው መምህር አያስተምረንም ባልን በረኀብ እየተቀጣን ነው›› /በደቀ መዛሙርቱ ከተለጠፉት ጥቅሶች አንዱ/
ሚያዝያ 7 ቀን 2005 ዓ.ም፤ ንጋት ላይ ነው፡፡ በአራት ኪሎ ወ.ወ.ክ.ማ በኩል ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴCollege bld 01 ካቴድራልበሚያስገባው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሦስተኛ በር በርካታ ምእመናን ተሰባስበዋል፡፡ ዕለቱ የቅድስት ሥላሴ ወርኀዊ በዓል መታሰቢያ እንደመኾኑ የምእመናኑ ቁጥር ከፍተኛ ነበር፡፡ በኮሌጁ ቅጽር ውስጥ ቆመው ጥቁር ቀሚሳቸውን እንደለበሱ መሥመር ይዘውና ፊታቸውን በካቴድራሉ መውጫና መግቢያ ላይ አድርገው በዝምታ የቆሙትን ደቀ መዛሙርት ይመለከታሉ፡፡ የብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ገጽታ ድካምና ጉስቁልና ይነበብበታል፡፡ ከፊት ለፊታቸው ነጭ ጨርቅ ተዘርግቷል፡፡
በኮሌጁ በር ላይ የተለጠፉት ጥቅሶች ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አኳኋን የተገኙበትን ምክንያት የሚያስረዱ ነበሩ – ‹‹ሃይማኖት የሌለው መምህርአያስተምረንም ባልን በረኀብ እየተቀጣን ነው››፤ ‹‹ወንጌል ይዘውበረኀብ እያሠቃዩን ነው››፤ ‹‹የረኀብ እሳት እየገረፈን ነውናረኀባችንን አሥታግሱልን››፤ ‹‹እየሞትንም ቢኾን ሙስናንና ዘረኝነትን እንዋጋለን››፡፡ ከምእመናኑ የቻሉት በአጥሩ አሻግረው/አሾልከው በጨርቁ ላይ ምጽዋት ይጥሉላቸዋል፤ ያልቻሉት አዝነው ይሄዳል፡፡ አንዳንዶቹም ወደ ቅጽሩ ቀረብ ብለው ማብራሪያ ይጠይቃሉ፤ ምን እንርዳችኹ ባዩም ጥቂት አልነበረም፡፡ ኮሌጁ መዘጋቱንና ከሳምንት በላይ ምግብ መከልከላቸውን ለምእመናኑ ያስረዱት ደቀ መዛሙርቱ ችግራቸውን ገልጠው ይናገሩ ነበር፡፡
ትዕይንቱ የተቀየረው ከቆይታ በኋላ በስፍራው የደረሰው የፖሊስ ኀይል በወሰደው ርምጃ ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ርዳታ መጠየቃቸውን የተከላከለው ፖሊስ በኮሌጁ መግቢያ በር ላይ የተለጠፉ ወረቀቶችን ቀዳዷል፤ ምእመናኑም እንዲበተኑ አድርጓል፡፡ የታሸገ ውኃ እንኳ በአጥር ለማቀበል የተደረገውን ሙከራ ፖሊስ እንዳይገባ ሲከላከል ታይቷል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በግቢያቸው ውስጥ ተወስነው ርዳታ እየጠየቁ ባለበት ኹኔታ የፖሊስ ኀይሉ ከጸጥታ ማስከበር ባሻገር የወሰደውን ርምጃ ፊት ለፊት የተቃወሙ ምእመናን ከፖሊስ አባላቱ ጋራ ሙግት ገጥመው ታይተዋል፡፡ የሙግቱን ፋይዳቢስነት የተረዱ ጥቂት ምእመናን፣ ‹‹ምንም ቢኾን ልጆቻችን ናቸው፤›› በሚል ሰብሰብ ብለው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ለማነጋገር ወደ መንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ያመራሉ፡፡
ምእመናኑ በበጎ ሐሳብ ተነሣስተው ያደረጉት ሙከራ ግን እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን በቅዳሴ መግቢያ ሰዓት ለማግኘት ሲጠባበቁ የነበሩት ምእመናኑ የገጠማቸው ኀይለ ቃልና ማመናጨቅ ነበር፤ ከቅዱስነታቸውም የሰሙት ቃል ቢኖር ‹‹ወደ ቅዳሴ እየገባኹ ነው›› የሚል እንደነበርና በዚህም ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ ቅንነትና ለኮሌጁ ማሰብ ብቻ ለውዝግቡ እልባት ለመስጠት በቂ ነው የሚሉት ምእመናኑ፣ ደቀ መዛሙርቱ በምርጫው ወቅት ይዘውት የነበረውን አቋም በማስታወስ ‹‹ምናልባትም መፍትሔውን አዘግይቶ ለመበቀል ይኾን?›› የሚል ጥርጣሬ እንዳደረባቸው አልሸሸጉም፡፡ Continue reading 

የቅ/ሥላሴ መን/ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ቀሚሳቸውን አንጥፈው ሲለምኑ ዋሉ

  • የኮሌጁ ካፊቴሪያ ለደቀ መዛሙርቱ ምግብ እንዳያዘጋጅ በሊቀ ጳጳሱ ታዝዟል
  • ሊቀ ጳጳሱ ሁሉም መምህራን በመደበኛው የቀን መርሐ ግብር እንዳያስተምሩ ከልክለዋል
  • ሊቀ ጳጳሱ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ሥራውን እንዳይጀምር አድርገዋል
  • በሊቀ ጳጳሱ ዙሪያ የተሰለፈው የቤተ ክህነቱ የጨለማ ቡድን ፓትርያሪኩንም እያሳሳተ ነው
  • ደቀ መዛሙርቱን ለማስወጣት የተጠራው የፖሊስ ኀይል ርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልኾነም
  • በኮሌጁ የሚዘዋወሩ ስመ ደኅንነቶች ደቀ መዛሙርቱን፣ መምህራኑንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን እያስፈራሩ ነው
ይህ ፻ውን የሐራ ዘተዋሕዶ ዘገባ ለንባብ ያበቃንበት ጦማር ነው፡፡ ከጦማሮቹ የሚበዙት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ተቋማዊ መገለጫ ለመኾን ስለ ደረሰው ጥቅመኝነትን የመከባከብ፣ ሙስናንና የአሠራር ብልሹነትን የማንገሥ፣ ከሙሰኞችና ጥቅመኞች ጋራ የመደራደር አስተሳሰብና ተግባር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር እና የደቀ መዛሙርቱ ውዝግብ አያያዝና እየተወሳሰበ የመጣበት ኹኔታ ከዚህ የተለየ መነሻ የለውም፡፡
የኮሌጁ መምህራን እንደሚናገሩት፣ የትምህርት አስተዳደሩ እንዲሻሻልና የደቀ መዛሙርቱ አካዳሚያዊ መብቶች እንዲከበሩ የቀረቡ ጥያቄዎችንሓላፊነት በተሞላበት መንገድ ደቀ መዛሙርቱን ከመምህራኑ ጋራ በግልጽ በማወያየት ምላሽ መስጠት ይቻላል፡፡ ይህም ካልኾነ የመማር ማስተማሩን ጤናማነት/ሰላማዊነት ለመጠበቅ ተቃውሞ የቀረበባቸውና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ መስማማት ያልቻሉ መምህራን ከሓላፊነታቸው ገለል እንዲሉ ማድረግ ነው፡፡
His Grace Abune Timothy
ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ
(የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ)
እየኾነ ያለው ግን ላለፉት 14 ዓመታት በኮሌጁ የበላይ ሓላፊነት ከቆዩ ሊቀ ጳጳስ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በቅ/ሲኖዶስ የተቋቋመው ኮሚቴ የማጣራት ሥራውን ጨርሶ ጥያቄያቸው ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የተቃውሟቸው ሁለቱ ሓላፊዎችና መምህራን ወደ ክፍል ገብተው እንዳያስተምሩ በመከላከላቸው እልክ የተጋቡት ሊቀ ጳጳሱ ‹‹ያቋረጣችኹትን ትምህርት በአግባቡ አልጀመራችኹም››በሚል የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ከመጋቢት 30 ቀን ጀምሮ የተዘጋ መኾኑን የኮሌጁን ክብ ማኅተም ይዞ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጠዋት በወጣ ማስታወቂያ አሳስበዋል፤ በቁጥር 181 ያህል የሚኾኑት የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርትም ንብረት አስረክበው በአስቸኳይ ከኮሌጁ እንዲወጡ አዝዘዋል፡፡
ሊቀ ጳጳሱ በተለይ ከቀኑ መርሐ ግብር አስተባባሪና በክፉ ምክር እያሳተ የግል ጥቅሙን ከሚያካብተው ዘላለም ረድኤት ጋራ በመኾን ያወጡትን ይህን ማስታወቂያ የተቃወሙት ደቀ መዛሙርት ግን ከኮሌጁ አልወጡም፤ መምህራኑም ከማስተማር አልታቀቡም ነበር፡፡ ይህ በእጅጉ ያስቆጣቸው ሊቀ ጳጳሱ ትላንት ጠዋት መምህራኑን አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ‹‹ማስተማር እንደሌለባችኹ ለማሳወቅ›› በሚል አጀንዳ ሲወዛገቡ ውለዋል፡፡ ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ ከቀትር በኋላ ቀጥሎ የዋለው ስብሰባው በንዴት በጦፉና አንዳንዶቹም ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ ‹‹አንተ አንቺ ቀረሽ›› እላፊ ቃላት በሚነጋገሩ መምህራን ቁጣ የተሞላ ነበር ተብሏል፡፡
‹‹የሁለት ሰዎች ችግር ኮሌጁን ሊያዘጋ አይችልም›› ያሉት መምህራኑ ችግሩን በመመካከር መፍታት እንደሚቻልና በዚህ የማይፈታ ከኾነ ግን መምህራኑን መለወጥ የተለመደ አሠራር መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መምህራኑ በቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር እንዳያስተምሩ መከልከላቸውንና መርሐ ግብሩን ላልተወሰነ ጊዜ የመዝጋት ርምጃ የገለጹት ‹‹ከእግዝአብሔር ማዕድ ለምን ትለዩናላችኹ!››በሚል እንደነበር ተዘግቧል፡፡ የቀኑ መርሐ ግብሩ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን የሚገልጸው የአስተዳደሩ ውሳኔ በደብዳቤ እንዲሰጣቸው የጠየቁት መምህራኑ‹‹የምንጠይቀውን አካል እንጠይቃለን፤›› በማለት መዛታቸውም ተነግሯል፡፡
የመርሐ ግብሩን መዘጋት ተከትሎ ሊቀ ጳጳሱ ለካፊቴሪያው ሓላፊ በቃል ባስተላለፉት ትእዛዝ ካፊቴሪያው ከትላንት በስቲያ ምሽት አንሥቶ ምግብ እንዳያዘጋጅ፣ ሠራተኞችም በምግብ ቤቱ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከትላንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ ራትና ምሳ በመከልከል በረኀብ እንዲቀጡ መደረጋቸውን በትላንቱ ስብሰባ መምህራኑ በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡
ማስታወቂያው በወጣበት ዕለት ምሽት በግቢያቸው የተሰበሰቡት ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው÷ ሁለቱ መምህራን እንዳያስተምሩ ከመከልከላቸው በቀር 90 ከመቶው የመማር ማስተማሩ ሂደት በቀጠለበት ኹኔታ በሊቀ ጳጳሱ የተወሰደው ርምጃ ተቀባይነት እንደሌለው ተወያይተዋል፡፡ በጎጠኝነትና በጥቅም ሊከፋፍሏቸው በሚሞክሩት ጥቂት የኮሌጁ ሓላፊዎች ተንኮል ሳይለያዩ ፣ በረኀብ ሳይፈቱ ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪሰጠው ድረስ በተቃውሟቸው ለመቀጠልም ተስማምተዋል፡፡ Continue reading 

የኮሌጁ የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርት ኮሌጁን እንዲለቁ ታዘዙ

  • መንሥኤው ‹‹ትምህርት በአግባቡ አልጀመራችኹም›› የሚል ነው
  • ‹‹ማስታወቂያው ለብቀላና እስር ሰበብ መፈለጊያ ነው›› /ደቀ መዛሙርቱ/
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር የቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርት ከዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ የኮሌጁን ንብረት እያስረከቡ ኮሌጁን እንዲለቁ አሳሰበ፡፡ ኮሌጁ ማሳሰቢያውን በዛሬው ዕለት በቀን መደበኛ ደቀ መዛሙርቱ ላይ ያወጣው ‹‹ያቋረጣችኹትን ትምህርት አግባብነት ባለው መንገድ አልጀመራችኹም›› በሚል ነው፡፡ Continue reading 

የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር አባላት የተሐድሶ ኑፋቄን እንዲዋጉ ፓትርያሪኩ አሳሰቡ

  • ማኅበሩ በሦስት አህጉረ ስብከት ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ከፍቷል
  • የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሥራ አስፈጻሚን በዳግም ምርጫ አጠናክሯል
  • መናፍቁ አሰግድ ሣህሉን ለማስመረጥ የተደረገው ሙከራ ተቀባይነት አላገኘም
  • ሁለት የፀረ – ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ሰባክያንና ዘማርያን ጥምረት አባላት በሥራ አስፈጻሚነት ተካተዋል
  • ማኅበሩ ሕጋዊ ዕውቅናና ተቀባይነት ካላቸው የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ጋራ ሁሉ ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት ዳግም አረጋግጧል
Theology Association Logoበቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ምሩቃንን በአባልነት በመያዝ የተመሠረተ ነው፤ ዋና ዓላማው÷ የወንጌል ትምህርት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ዶግማ፣ ሥርዐት፣ ትውፊት እና ንዋያተ ቅድሳት በአግባቡ እንዲጠበቁ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ነው – የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር፡፡
ማኅበሩ ዓላማውን የሚተገብርባቸውየስብከተ ወንጌል፣ የትምህርት፣ የኅትመትና ሥርጭት፣ የሕግ፣ የልማት፣ የመረጃና መዛግብት፣ የሒሳብና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም የቁጥጥር ክፍሎችን አዋቅሯል፤ እኒህን ተግባራት የሚያስፈጽሙ 12 የሥራ አስፈጻሚና አፈጻጸሙን በበላይነት የሚመሩ 12 የሥራ አመራር አባላት እንዳሉትም ማኅበሩ ያሰራጫቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ሁለቱ የነገረ መለኰት ኮሌጆች በዘረጓቸው የቀን መደበኛና ተከታታይ የማታ ትምህርት መርሐ ግብሮች ከሠለጠኑትና በቁጥር ከ1700 በላይ ከሚኾኑት ምሩቃን የሚበዙትን በአባልነት ያቀፈው ማኅበሩ÷ ከአባላቱ በሚሰበስበው ወርኀዊ አስተዋፅኦና ከበጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳውያን በሚያገኘው ድጋፍ አገልግሎቱን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ በቀድሞው ፓትርያሪክ መልካም ፈቃድና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ ጥረት በመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንደ ዋና ጽ/ቤት የሚገለገልበት ቢሮ የተሰጠው ሲኾን በአዲስ አበባ፣ መቐለ እና ጅማ አህጉረ ስብከት ሦስት ቅርንጫፍ ቢሮዎችን መክፈቱ ተዘግቧል፡፡ Continue reading 

የኮሌጁን ችግርና የደቀ መዛሙርቱን ጥያቄ የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቋመ

  • በቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው የተለጠፈው ማስታወቂያ ሕገ ወጥ ነው
  • ሁለቱ ሓላፊዎች ከማስተማር እንደተከለከሉ ናቸው
  • የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ‹‹ሁለቱ ሓላፊዎች እንዳይነኩብኝ›› እያሉ ነው
ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ሦስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ቀዳሚ በኾነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተባብሶ በሚታየው ሙስናና የአሠራር ብልሹነት ሳቢያ ደቀ መዛሙርቱ ያነሧቸውን አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ችግሮች የተመለከቱ ጥያቄዎች የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡
ከመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስ ፊርማ የወጣውና ለመንፈሳዊ ኮሌጁ አስተዳደር የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው÷ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ አራት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች በአመራርነትና በአባልነት፣ ሁለት የኮሌጁ መምህራንና ሁለት የደቀ መዛሙርቱ ተወካዮች በአስረጅነት የሚገኙበት ነው፡፡ Continue reading 

የኮሌጁ አስተዳደር የቀን መደበኛ መርሐ ግብር ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን አስታወቀ

  • ማስታወቂያው የተለጠፈው በመርሐ ግብሩ አስተባባሪ ዘላለም ረድኤት ነው
  • ደቀ መዛሙርቱ በተቃውሟቸው ለመቀጠል በመስማማት ትምህርት ጀምረዋል
  • ‹‹ሲያስወጡን እንተናነቃለን፤ ኮሌጁን ቅ/ሲኖዶስ እንጂ ዘላለም አይዘጋውም›› /ደቀ መዛሙርቱ
  • የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ‹‹[ለደቀ መዛሙርቱ] እንኳን ምሳ ራት አልሰጥም›› እያሉ ነው
ሙስናንና የአሠራር ብልሹነትን በመቃወም ከሁለት ሳምንት በላይ በተቃውሞ የሰነበቱት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀን መደበኛ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት በትላንትናው ዕለት ረፋድና ከሰዓት በኋላ በክፍል በመገኘት ትምህርት ጀምረዋል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ትምህርት በማቋረጥና በካፊቴሪያው ከመመገብ በመከልከል በኮሌጁ እየከፋ የመጣው ሙስናና የአሠራር ብልሹነት እንዲስተካከል፣ ለዚህም ተጠያቂ ናቸው ያሏቸው ሁለት ሓላፊዎች ከቦታቸው እንዲነሡ ያቀረቡትን ጥያቄ እየተማሩም ለመቀጠል በመወሰን ነው ትምህርታቸውን ለመጀመር የተስማሙት፡፡
በቀጣይ በሚቋቋመው ኮሚቴ መሠረት በሁለቱ ሓላፊዎች ላይ የቀረቡት ጥያቄዎች በሚገባ ተጠንተው ውሳኔ እንዲሰጥባቸው በፓትርያሪኩ የተሰጠውን መመሪያ መቀበላቸውን የተናገሩት ደቀ መዛሙርቱ÷ ሁለቱ ሓላፊዎች ማለትም የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር አስተባባሪ መ/ር ዘላለም ረድኤት እና አካዳሚክ ምክትል ዲኑ መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ በክፍል ተገኝተው ማስተማራቸውን እንደሚቃወሙና ይህም ተቃውሞ ሓላፊዎቹ ውሳኔ እስኪሰጥባቸው ድረስ እንደሚቀጥል በመስማማት ነው ትምህርታቸውን የጀመሩት፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የደረሱበት ውሳኔና ወደ ትምህርት የተመለሱበት ኹኔታ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የሰጉት የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪው መ/ር ዘላለም ረድኤት ግን ከመማር ማስተማሩ ጤናማነት ይልቅ በቀጣይ የደቀ መዛሙርቱ የተቃውሞ ስልት ግላዊ ጥቅማቸው አደጋ ውስጥ መግባቱን በማሰብ ውዝግቡን የሚያባብስ ርምጃ መውሰድን መምረጣቸው ተመልክቷል፡፡ በተካኑበት አሳባቂነትና ነገር ሠሪነት የኮሌጁን መምህራንና አስተዳደር እርስ በርስ በማተራመስ፣ ከሰሞኑ እንኳ ተቃውሞ ያነሡባቸውን ደቀ መዛሙርት ሳይቀር በጥቅም ለመከፋፈል እስከመሞከር የሚታወቁት አስተባባሪው÷ የኮሌጁን የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ በማሳሳት በትላንትናው ዕለት ባወጡት ማስታወቂያ፣ በተቃውሞ የሰነበቱት የቀኑ መደበኛ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት በዕለቱ እስከ ቀኑ 8፡00 ኮሌጁን ለቀው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡Continue reading 

አንድ የኮሌጁ ደቀ መዝሙር ከዐርብ ጀምሮ በእስር ላይ ነው

  •  ልኡኩ ከኮሌጁ አስተዳደር ወግኗል በሚል እየተተቸ ነው
  • አምስት ደቀ መዛሙርት በረኀብ አድማው ተጎድተዋል
  • የደቀ መዛሙርቱ ዕለታዊ ምግብ ዳቦና ሙዝ ኾኗል
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተጀመረው የደቀ መዛሙርት ተቃውሞ እንደቀጠለ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት÷ አምስት ደቀ መዛሙርት በረኀብ አድማው መጎዳታቸውንና አንድ ደቀ መዝሙር ደግሞ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ትምህርት በማቋረጥ የተጀመረውና ዘግይቶ በረኀብ አድማ በተጠናከረው የቀኑ መርሐ ግብር ደቀ መዛሙርት ተቃውሞ÷ ሦስት የሁለተኛ ዓመት (ዲ/ን ገብረ እግዚአብሔር፣ ዲ/ን በኀይሉ እና ዲ/ን ጥላሁን)፣ አንድ የአራተኛ ዓመት (ዲ/ን ኤልያስ)፣ አንድ የአምስተኛ ዓመት (አባ ኢያሱ ሰብስቤ) ደቀ መዛሙርት ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጧል፡፡ ከአምስቱ ደቀ መዛሙርት አራቱ የሕክምና ርዳታ አግኝተው ወደ ኮሌጁ የተመለሱ ሲኾን አምስተኛው ደግሞ በጣም በመጎዳታቸው ከሕክምና ርዳታው በኋላ ወደ ቤተሰብ መመለሳቸው ተዘግቧል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በቀን አንዴ የሚቀምሱት ከውጭ የሚገዙትን ዳቦና ሙዝ ሲኾን ከምግብ ተከልክለው በመቆየታቸው ሳቢያ ብዙዎች ከፍተኛ ድካም እንደሚታይባቸው ተገልጧል፡፡
በኮሌጁ ተባብሰው ለሚታዩት አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ችግሮች የኮሌጁን ሁለት ሓላፊዎች ቀዳሚ ተጠያቂ በማድረግ ከሥልጣን እንዲነሡ የሚጠይቁት ደቀ መዛሙርቱ÷ ዲ/ን ኀይለ ጽዮን መንግሥት የተባለ የአምስተኛ ዓመት ደቀ መዝሙር ካለፈው ሳምንት ዓርብ ተሲዓት ጀምሮ በፖሊስ ከተወሰደ በኋላ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፤ ወደ  አራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 04 ፖሊስ ጣቢያ የተወሰደውና በሰሞኑ የተቃውሞ መድረኮች ርቱዕና ብርቱ ተናጋሪ ነበር የተባለው ዲ/ን ኀይለ ጽዮን፣ ከሌሎች ተለይቶ ለእስር የተዳረገው ‹‹ተማሪዎቹን ለተቃውሞ አነሣሥተሃል›› በሚል መኾኑን ደቀ መዛሙርቱ ገልጸው፣ በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ ፍ/ቤት ቀርቦ በዋስ ይፈታል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡ Continue reading 

No comments:

Post a Comment