Wednesday, December 3, 2014

ምን አይነት ሰላማዊ ሰልፍ?


በተክሉ አባተ (teklu.abate@gmail.com)
ለመጀመሪያ ጊዜ በሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፍኩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ግቢ ተማሪ እያለሁ ነበር:: በአራት ዓመት
የትምህርት ቆይታዬ በርከት ያሉ ሰልፎች ተካሂደዋል:: አንዳንዴ የምግብ ጥራት ማሽቆልቆሉን በመቃወም ሌላ ጊዜ ነጻነትን
ፍትህንና ዴሞክራሲን እንዲሁም የመሬት ክፍፍልን በመቃወም:: ምግብን በተመለከተ የተቀናጁ ሰልፎች አጀማመራቸው
ምግብ-ነክ ይሁን እንጅ መደምደሚያቸው ፖለቲካ ነበር:: ድንገት ከሰልፉ መካከል አንዱ ተነስቶ "ፍትህና መብት ይከበር"
ካለ ተሜ ወዲያው ተቀብሎ ያስተጋባዋል:: አንዳንዶች ደግሞ በራሳቸው ተነሳሽነት ቀድሞ የተዘጋጀ የጽሁፍ መፈክር ብቅ
ያደርጋሉ:: በአቅራቢያቸው ያለ ተሜ እያነበበ ያስተጋባዋል:: ሌላው ይቀበለዋል:: የአንገት ስር እስኪወደር ድረስ ይፎከራል::
ስሜት እየጋለ ይሄዳል:: የተሰላፊው ቁጥር የሚጨምረው ሰልፉ ከተጀመረ ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ ነው:: መጀመሪያ
ላይ ፈራ ተባ እያሉ ከዳር ሆነው የሚመለከቱ ይበዛሉ.: በኋላ ድንገት ሰልፉን የሚቀላቀሉ ይበዙና ተሰላፊው ዋናውን በር
የሚወጣው በሦስትና አራት ረድፍ ባለው ረጅም መስመር ነው::
የሚገርመው ሰልፉ ሰላማዊ ተብሎ ቢጀመርም ሰይፋዊ ሆኖ ይጠቃለላል:: ካድሬ ሰላይ ፖሊስና ወታደር ሙያቸውን
የሚያስመሰክሩበት ልዩ አጋጣሚ እስኪመስል ድረስ አካባቢውን ያጥለቀልቁታል:: ከጥቂት ማስፈራራት በኋላ ወደ ርምጃ
ይሸጋገራሉ:: ተሜም እድሉን የሚለካበት ጊዜ ይገጥመዋል:: ግርግርና ዱላ በጥበቃ አካላት ይጀመራል:: ጥጋቸውን ይዘው
በሚጠባበቁ አይፋ በሚባሉ ወታደራዊ መኪናዎች ተሜ ወደ ማሰቃያ ጣቢያዎች ይወሰዳል:: በደንብ የሚደበደቡ: የሚታሰሩ:
ከትምህርታቸው የሚባረሩ: ማስጠንቀቂያ የሚሰጣቸው ብዙ ናቸው:: ጀርባቸው እስኪላጥ እግራቸው እስኪጠቁር በፖሊስ
የሚሰቃዩ ሞልተዋል:: በተለይ ሸጎሌ ተብሎ ከሚጠራው መጠርነፊያ ጣቢያ የተወሰዱት ያጋጠማቸው ስቃይ 'ታሪካዊ' ነበር::
በባዶ እግራቸው እንደጦር በቆመ አሸዋ ላይ ያሴዷቸው ነበር:: በካድሬዎች ወከባ የተነሳ ትምህርት ያቋረጥንባቸው ጊዜያትም
ነበሩ::
የበለጠ የሚገርመው ደግሞ ለቀናት ከሚዘልቀው አካላዊ ስቃይ ይልቅ ተማሪዎች የሚደርስባቸው ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት
ነበር::ተማሪዎች ከእስርና ከስቃይ ለመውጣት ከፈለጉ መንግስትን ይቅርታ እንዲጠይቁ ይገደዳሉ:: ከዚያም በማናቸውም
ተመሳሳይ ሰልፎች ወይም ዝግጆቶች ላይ ወደፊት እንደማይሳተፉ በሚገልጠው ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ ይደረጋሉ:: በመሆኑም
ከእስራታቸው በኋላ ትንፍሽ እንኳን የማይሉ እየተበራከቱ መጥተው ነበር:: እስካሁንም ድረስ ያንን የገቡትን 'ቃል
ኪዳን' ታሳቢ በማድረግ በመሳቀቅ የሚኖሩ አሉ::
ውጤታቸው ምንም ይሁን ምን የተደረጉ ሰልፎች መደረግ የነበረባቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ:: ውጤት ያመጡ ሰልፎች
ነበሩ:: እነወይዘሮ ገነት ዘውዴ እና እነ ዶክተር ዱሪ ላባቸው እስኪመጣ ድረስ በተሜ ተፋጠዋል:: ቀላል የማይባሉ
ለውጦችም ወዲያውኑ ተደርገዋል:: እነዚያ ሰልፎች የተማሪን ህይወት ያማከሉ ቢመስሉም (አንዳንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎችተሜ ለዳቦ ጥራት እንጅ ለሃገሩ እድገት አይሰለፍም እያሉ ቢሳለቁም) ከብሄራዊ የዜግነት ግዴታዎችና መብቶች ጋር የተያያዙ
ናቸው:: ነጻነት ፍትህ እኩልነት የተጠየቀባቸው ሰልፎች ነበሩና::
የሰልፍ ሁሉ መጀመሪያ
ከላይ ያለውን ታሪክ ያነሳሁት እንደመግቢያ እንዲያገለግለኝ ነው:: ዋናው ነጥቤ በአሁኑ ጊዜም ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላማዊ
ሰልፍን አስፈላጊነት ለማመላከት ነው:: የዜግነት መብት እስካልተከበረ ድረስ ሰልፍ ይካሄዳል:: ለመብትና ለአገር ክብር
የሚደረግ ሰልፍ ሰው የመሆን አንዱ መገለጫ ነው:: ሰልፉ ግን መጀመር ያለበት ከግል ህይወት ነው:: በማይጠቅሙ ሃሳቦች
የተሞላ አእምሮ ያለው ሰው በራሱ ላይ ሰልፍ መውጣት አለበት:: መብቱ በጓደኛው ወይም በሥራ ባልደረባው የሚጣስበት
ካለ በዚያ ላይ ሰልፍ መውጣት አለበት:: አባል የሆነበት ድርጅት መብቱን የሚጥስበት ከሆነ ሰልፍ መውጣት አለበት:: ሰልፍ
መውጣትም በአካል ወደአደባባይ መንጎድን ብቻ አይመለከትም:: ፍርሃትንና ይሉኝታን አስወግዶ ሃሰተኞች ወይም መብት
እረጋጮች የሚሰሩትን ግፍ ፊትለፊት መናገርንም ያጠቃልላል:: በአደባባይ ሰልፍ ተገኝቶ በጓዳ መብቱንና ጥቅሙን የሚያስነካ
ሰው ራሱን ያታልላል:: በውስጥም በውጭም በአካልም በሥነ-ልቦናም በግልም በቡድንም በደልን መቃወም ማጋለጥም
ያስፈልጋል:: "መብቴ ተጣሰ" ብሎ ሰልፍ የሚወጣ የሌላውን ሰው መብት መጠበቅም ሊኖርበት ነው:: እያንዳንዳችን
ለራሳችን መብት ሳናቋርጥ ሰልፍ መውጣት አለብን:: ይህ ከሆነ ነው የቡድን ሰልፎች የሚያምርባቸውና ውጤታማ
የሚሆኑት:: ብዙ ሰዎች አብዝተው የሚጨነቁት ግን በቡድን ስለሚደረግ ሰልፍ ነውና ለጊዜው እሱን እንመልከት::
ውጤታማ ሰልፍ
በአጠቃላይ ሲታይ የትም ቦታ በማናቸውም ጊዜ የሚደረጉ ህግን መሠረት ያደረጉ የቡድን ሰላማዊ ሰልፎች ሁሉ ልዩ ባህርይ
አላቸው:: ዳሩ ግን አንድ ሰልፍ ግልጽ ዓላማዎችና የአፈጻጸም ስልቶች ሊኖሩት ይገባል:: ይህ ደግሞ በጊዜና በቦታ ሊወሰን
ይችላል.: ያም ሆኖ አንድን ሰልፍ ውጤታማ ነው ብሎ ለመፈረጅ በርካታ መለኪያዎችን ማሟላት ይኖርበታል:: ለእኔ የተሳካ
ሰልፍ ማለት ቀጥለው የተዘረዘሩትን የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜያት አብዛኞችን መስፈርቶ ች ያሟላል::
 ሰልፉን ተከትሎ ተሰላፊዎች በራስ የመተማመንና የእርካታ ስሜት ማግኘት አለባቸው
 ተሰላፊዎች በቋሚነት የራሳቸውንና የወገናቸውን መብቶች ለማስጠበቅ ጽኑ አቋም ይይዛሉ
 ሰልፍ ህግን በማያከብረው በመንግስት ላይ ስጋትና ፍርሃትን ማስፈን አለበት
 መንግስት ለጊዜው በይፋ ለውጦችን ለማድረግ ቃል ባይገባም ወደዚያው የሚያደርሱ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ
ማስገደድ አለበት
 መንግስት ተረጋግቶ ጭቆናውን እንዳይቀጥል ያደርገዋል
 የመንግስትን ጨቋኝነት የሌሎች ሃገራት መሪዎችና ተቋማት በደንብ እንዲያውቁት ያደርጋል
 አንዱ ሰልፍ ሌላ ሰልፍ ይወልዳል
 በሰልፉ ምክንያት የሚታሰር የሚደበደብ የሚሰደድ ወዘተ ካለ ስለእሱም ፍትህ ይጠይቃል ሌላ ሰልፍ በተሻለ ሁኔታ
ይደረጋል መንግስት በሚያደርጋቸው ጥቂት የማስታገሻ ማሻሻያዎች አይታለልም
 በመጨረሻም የሚፈለገው ለውጥ በመጠንና በዓይነት ይገኛል
የውጤታማ ሰልፍ መገለጫ ባህርያት
ከላይ የተዘረዘሩትን እንዲሁም ሌሎችን ውጤቶች ለማሳካት አንድ ሰላማዊ ሰልፍ ማሟላት ያለበት ባህርያት ይኖራሉ::
ጥቂቶችን እንዲህ ዘርዝያለሁ::
 በደንብ የተደራጀና የተመራ ሰልፍ የተሰላፊውን ቀልብ ከመሳብ በተጨማሪ ያልተሰለፉ ሰዎችም ወደፊት እንዲሰለፉ
ይጋብዛል
 ለረጅም ጊዜ ወይም በተከታታይ የሚደረግ ሰልፍ እጅግ አመርቂ ውጤት ያመጣል
 ሰልፍ በሚደረጉ መጥፎ ሥራዎች ላይ ያለን ተቃውሞ ለማሰማት ብቻ ሳይሆን ለውጥ እንዲደረግ
የሚያስገድድ መሆን አለበት
 ሰልፍ መንግስት መመለስ ያለበት ግልጽ ጥያቄዎችን ማቅረብ አለበት
 እንደ ጉዳዮች ትልቅነትና አሳሳቢነት እየታየ መንግስት መልስ የሚሰጥበት ጊዜም መገለጽ አለበት
 በተሰጠው ጊዜ መንግስት አጥጋቢ መልስ ካልሰጠ በአይነቱና በመጠኑ ልዩ የሆነ የተቀነባበረ ሰልፍና ህዝባዊ
ተቃውሞ እንደሚደረግ ማሳወቅ አለበት
 ሰልፍ አስተባባሪዎች ሊታሰሩ ወይም ሊሰው ስለሚችሉ በርካታ መሪዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል
 ህዝቡ መብቱን በሚገባ እንዲያውቅና ትግሉን በቀጣይነት እንዲመራ ማድረግ ወሳኝነት አለው
 ህዝቡ ኃይልንና ስሜትን ተቆጣጥሮ ከሰልፉ ዓላማ ላይ ትኩረትን ማድረግ እንዳለበት መነገር አለበት
 ህዝቡ በአቋሙ ከጸና ጨቋኝ መሪዎች እንደሚሸነፉ ማስተማርና ሥልጣን የህዝብ እንደሆነ ማሳሰብ ያስፈልጋል
 ፖሊስና ወታደር በሚመጣበት ጊዜ ከመሮጥ ይልቅ ሁሉም ተረጋግቶ ባለበት እንዲጸና ማድረግ ያስፈልጋል
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ህዝብ የግልም ሆነ የቡድን መብቱ ተረግጧል:: ኑሮ ከአቅሙ በላይ ሆኗል:: ይህ አላንስ ብሎ ያሰበውን
እንዳይናገር አንደበቱ ተዘግቷል:: በተጨማሪም መንግስት አንዱ ህዝብ በሌላው ላይ እንዲነሳ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው::
በመሆኑም እውነተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አማራጭ የሌለው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሆኗል.: አገር ቤት ሆነው
የሚታገሉት ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድነት መድረክ በመፍጠር ሰላማዊ ሰልፍ ከህዳር 27/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር
28/2007 ዓ/ም ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ:: ይህ በዓይነቱ የተለዬ ሰልፍ በሁሉም ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ
ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባል:: በአካል በሞራል በሃሳብና በገንዘብ መደገፍ ይኖርብናል:: የሰልፉ አስተባባሪዎችም እጅግ ጥበብ የተሞላበት እቅድ ነድፈው ህዝቡን ደረጃ በደረጃ መምራት አለባቸው:: መንግስት
ሊያሟላቸው የሚገቡ ጉዳዮች በቁጥር ተለይተው እስከነ ጊዜ ገደባቸው መቅረብ አለባቸው:: ጥያቄዎች የማይመለሱ ከሆነ
ቀጣይነት ወዳለው ህዝባዊ ተቃውሞ ማሸጋገር ያስፈልጋል:: መስቀል አደባባይን እንደ ዋና ቢሮ አድርጎ በመላ ኢትዮጵያ
ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ ማድረግ ወሳኝነት አለው:: ሰልፉ በመጠንና በቦታ ባደገ ቁጥር የመንግስት ጫና እየላላ
ይሄዳል:: በመጨረሻም የህዝብ መብት ተከብሮ ሥልጣን ለህዝብ ይሆናል:: ከዚያም ኢትዮጵያውያን ዜግነታቸውን
እያጣጣሙ ሃገራቸውን እንደገና በኅብረት ይገነቧታል:: አላስፈላጊው ስደትና ስቃይ ታሪክ ሆኖ ይቀራል::

No comments:

Post a Comment