December 18, 2014
አበበ ሃይሉ
የቴሌቭዥኔን ጣቢያ EBC (የውጭ ጣቢያ እንዳይመስላቹህ የኛው ጉድ የሆነው የኢትዮጲያ ? ቴሌቭዥን ነው ) ላይ ሳረገው
“ሃገር ማለት ሰው ነው ፣ ሰው ነው ሃገር ማለት”
የሚል ዜማ እየሰማሁ የባቡሩ መስመር ፣የአባይ ግደብ ፣ብሄር ብሄረሰቦች ሲደንሱ፣ አረንጓዴ የተላበሰ ምድር ብቻ ባጠቃለይ የሚስብ ነገር እስክሪኑ ላይ ከሙዚቃው ጋር ይሄዳል።

በተመሳሳይ ጊዜ ፓልቶኬን ከፍቼ ስሰማ እጅግ አስደናጋጭና አሳዛኝ የሴት ልጅ የስቃይ ድምጽ ከብዙ ሰዎች ግርግር ጋር ይሰማኛል። ጆሮዬን ይበልጥ ወደ ፓልቶኩ ሳደላ፡ ና ወደዚ!ዝም በል/ይ!በለው!ዞር በል ከዚ! የሚሉና እያስፈራሩ ሰዎችን የሚደበድቡ የፌደራል ፖሊሶች ድምጽ በጉልህ ይሰማኛል ። ድንገት ግን ድምጹ ጠፋ ። የስልኩ ባለቤት ፖሌሶቹ ሳይቀሙት/ሟት አይቀርም ። ከዛም ሌላ ወንድ!በሌላ ስልክ ፓልቶኩ ላይ ማውራት ጀመረ 《ምናለ እኔም እዚ ባልሆንኩና ይሄንን ጽዋ አብሬ ልጠጣ ይገባኝ ነበር》 የሚል እጅግ ልብ የሚነካ ነገር ሲናገር አደመጥኩ። ቅዳሜ ህዳር 24 የዘጠኙ ፓርቲዎች የትብብር ሰልፍ ከጥዋቱ 3 ሰአት ላይ እንደሚጀመር ስለማውቅ እኔም ካለሁበት በጥዋት ተነሳሁ፥ ግን ምን ያረጋል በአንድ ሃገር ላይ ሁለት ፍጽም ተቃራኒ የሆኑ ኩነቶችን አንዱን በቴሌቭዥን ሳይ ሌላውን በፓልቶክ ላይ ለማድመጥ ቻልኩ።
የዘፈኑና ሰዎቹ ላይ የደረሰው ነገር ሊገናኙልኝ አልቻሉም። ” ሃገር ማለት ሰው ነው ፣“ ይህ ማለት እንደገባኝ ከሆነ ሃገር ያለ ሰው ሃገር ሊባል አይችልም ነው ። ቀጥሎም “ሰው ነው ሃገር ማለት፣” የሚለው ደግሞ ሀገርን የሚመራ ፣የተሻለ የሚያረጋት፣የራሷን ዳን ድንበር የሚጠብቅላት ፣የማንነቱ መገለጫ የሚያረጋት··· ሰው ነው ማለት ነው። ታዲያ ይህ ከሆነ ዘንዳ ሃገሬን የተሻለች ሃገር ላድርጋት አንተ ከ23 አመት በላይ አስተዳድረሃት እንደ ሃገር ልታቆማት አልቻልክም ተራዬን እኔ ልሞክር አልያም የተሻለ ይረከብ ማለትለዚህ ሁሉ ግፍ የሚያበቃ ነው እንዴ?ጥያቄው እኮ አነተን ከምድረ ገጽ ላጥፋህ አልያም እንጦሮጦስ ልክተትህ አይደለም ።
ወረቀት ላይ ለሀገሩ የሚገባትንና የሚመጥናት ነገር አንተ የያዝከው መንገድ አይደልም የሚል መፈክር በያዙ ሰዎች ላይ አንድ ቀውጢ የጦር ቀጠና አስመስሎ ግፍ መፈጸም ምን ያህል አረመኔነትና ስልጣን ባህሪያቸውን አውሬ እንዳደረገው ይበልጥ አሳይቶናል። እጅግ አሳፋሪው ነገር ደግሞ ሃና (በአስገድዶ መደፈር ህይወቷ ያለፈ)ላይ የተፈጸመው ድርጊት አንገታችንን አስደፍቶ ደሞን ፍርድ ይክሳት ዘንድ ስንጠብቅ በራሱ የህግ አካል በሆነው የፌደራል ፖሊስ ሴቶች እህቶቻችን ላይ እንደዛ አይነት አስነዋሪ የግፍ ድብደባ መፈጸም በውነት ህሊና ያለው ሰው ልብ የሚያቆስል ድርጊት ነው ። የሴቶችን መብት አስከብሪያለሁ ብሎ ወሬ ከሚነዛ መንግስት ይህ አሳፋሪ ስራ ነው። እንደውም ሴቶች እህቶቻችን ላይ ለሚደርሰው ዘግናኝ ድርጊቶች የማበረታቻ ስራ ነው። በዘፈኑ ላይ የተጠቀሰው “ሰው ” ተብሎ የተጠቀሰው አካል ማን ይሆን?ምን አልባት ገጣሚው ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት በአስፈላጊው ሰው እጅ አልገባለት መሰል?
“ሃገር ማለት ሰው ነው፣ሰው ነው ሃገር ማለት”
ይህን ሁሉ እያሰብኩ እያለ ደግሞ ወደ ማምሻውን አንድ መነጽር ያረገ ወጣት በቴሌቭዝን መስኮት ብቅ ብሎ 《 እነዚህ ቦታዎች ላይ እጅግ ሰፋፊ የልማት ስራዎች የሚካሄድባቸው ናቸው እንዴት ብለው እነዚህ ቦታዎች ላይ ሰልፍ ይወጣሉ እነዚህ ሰዎች በጥባጭ ናቸው ሰላማዊ አይደሉም》 ብሎ ሲናገር ሰማሁትና እውነትም ገጣሚው ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት አልተረዱለትም አልያም አውቆ የተኛ አይነት ጨዋታ ይዘዋል ብዬ እንድደመድም አደረገኝ። እስኪ ይታያቹሁ ተይዞ የተወጣው መፈክር ባጭሩ ብናስቀምጠው እኮ ለሃሪቱ የተሻለ አስተዳደር ይገባታል እንጂ የባቡሩ ፣መንገዱ ፣ግድቡ ይቁሙ ያለም ሰልፈኛ የለም።ሲጀምር እኮ እነዚህ የልማት ስራዎች የሚሰሩት ለሃገሬው ሰው መገልገያነት ነው ። ዜጋውን አፈናቅለህ ፣እንዲሰደድ አርገህ ፣እየገደልክና እያሰቃየህ ፣ ሃሳብህ እኔ ከማስበው ውጭ መሆን የለበትም ብለህ ልማት ነው የሚካሄደው ማለት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ እኔ እንዲህ ከተናገርኩ በስልጣን ላይ ስልጣን ፣ በሃብት ላይ ሃብት ··· አገኛለሁና ሌሎች ለምን ስቃይ ሲቀበሉ አይኖሩም አይነት የአህያዋን አይነት አስተሳሰብ ነው።
እዚሁ ዜማ ላይ እጅግ ደስ የሚልና ትልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ስንኝም አለ
“እኛ ነን ልጆቿ ምሰሶና ማገር”
ምሰሶ ቤቱን እንዳይፈርስ ፣ ተስተካክሎ እንዲቆም ፣ዘላቂነት እንዲኖረው እንደሚያረገው ሁሉ ምሰሶውን ስንነቀንቀውና ስናፈርሰው ቤቱ እንደሚወድቀው ሁሉ ምሶሳችንን ነቅንቆ ለመጣል በመፍጨርጨር ላይ ያለን መንግስት ይሄማ እንዴት ሆኖ ብሎ/ላ እራሳቸውን እስኪስቱ የተደበደቡ ፣ እጃቸውን የተሰበሩ፣ሰውነታቸው በግርፋት የበለዘ ፣ ከስራ የተፈናቀሉ ምሰሶውን መልሶ ለማቆም የታገሉ የቁርጥ ቀን የሃገሪቱ ልጆች ናቸው፡ ይህንን ነው በህዳር 24ቱ ሰልፍ ላይ ያየንው ። “ይሄንን ስቃይ አብሬ መካፈል ነበረብኝ“ የሚል ጀግንነት፣ አንተ ምትገልበት ማሳሪያና ጉልበት እንዲሁም ስልጣን ቢኖርህ እኔም ለሀገሬ ብሎ ለመሞት የተዘጋጁትን ጴጥሮሳዊያንን ነው ።
ኢትዮጲያ ለዘላለም በክብር ትኑር!
No comments:
Post a Comment