ኢህአዴግን የስለላ መዋቅርና አካሄድ አስመልክቶ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ተበራክተዋል። ኢህአዴግ ራሱን እንደሚስለው ዓይነት ድርጅት ሳይሆን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉድለት ያለበት፣ በሚዲያ ነጻነት ኋላ ቀር፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን በማሳደድ ግንባር ቀደም፣ አፋኝ ህግ በማውጣትና በማሸማቀቅ ወደር የማይገኝለት፣ ለሚያወጣው ህግና ደንብ የማይገዛ፣ የውስጥ ችግሩ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ዜጎችን ለስደት እየዳረገ እንደሆነ እየተመሰከረበት ነው።
ኢህአዴግን ሸሽተው አገር ለቀው የተሰደዱ በስደት ምድርም ኢህአዴግ እየተፈታተናቸው እንደሆነ መግለጽ ከሰነበቱ ቆይቷል። በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በጀርመን፣ በስዊድንና በእንግሊዝ አገር ስደተኞችን በመሰለል ተግባር ላይ የተሰማሩ “የስደተኛ ሰላዮች” በስፋት ስለመኖራቸው መረጃ ማቅረብ እንደሚችሉ የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። የተለያዩ ድርጅቶች በዚህ ጉዳይ ምን ያህል እንደገፉበት መረጃ ባይወጣም አቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ስራውን ያገባቸዋል ከሚላቸው ክፍሎች ጋር እየሰራ እንደሆነ በዚሁ መድረክ መገለጹ ይታወሳል። በወቅቱ አቶ ኦባንግ “ስደተኛ ሆኖ ስደተኛን መሰለል በህግ የተከለከለ ወንጀል ነውና በዚህ ጉዳይ ርህራሄ ሊኖር አይችልም” ነበር ያሉት።
ማርች 11 ቀን በኖርዌይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር አስተባባሪነት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዶ ነበር። በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የፓርላማ ተወካይ፣ የኖአስና/NOASና ዘረኝነትን የሚቃወመው ድርጅት መሪ ተገኝተው ነበር። በሰላማዊ ሰልፉ ተገኝተው ንግግር ካደረጉት መካከል ወ/ት የሺሃረግ በቀለ ይጠቀሳሉ። በኖርዌይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር ጸሐፊ ወ/ት የሺሃረግ በቀለ “እነሱ አገር ቤትም አገር አላቸው፤ በስደትም አገር አላቸው” በማለት ነበር ለ ጎልጉል አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት።
በሰልፉ ላይ ካቀረቡት ንግግር በተጨማሪ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡት ጸሐፊዋ፣ ስደተኞች ሁሉ አንድ አይደሉም። “ሆን ተብሎ የስደት መረጃና ማስረጃ ማመልከቻው ተመቻችቶላቸው የሚላኩ የወያኔ ቅጥረኛ ሰላዮች አሉ። እነሱ ባለሁለት አገር ናቸው። እኛ አንድም አገር የለንም” ብለዋል። ይህንን ጉዳይ አቅም በፈቀደ ሁሉ ማህበሩ ከአባላቱና ድጋፍ ከሚሰጡት ሁሉ ጋር በመሆን ከዳር እንደሚያደርሰው ገልጸዋል።
“ልብ እንበል” በማለት አስረግጠው የገለጹት ስለ ሁለተኞቹ ስደተኞች ነው። ስርዓቱ ባለው የግፈኛነት፣ የዘረኛነት፣ የከፋፋይነት፣ የዴሞክራሲና የነጻነት እጦት የገፋቸው እውነተኛ ስደተኞች ባግባቡ መልስ ያለማግኘታቸው ጉዳይ ነው። “እነዚህ እውነተኛ ስደተኞች እኔን ጨምሮ አገር የለንም” ሲሉ አገር አልባ የመሆንን ስሜት ይገልጻሉ። ወ/ት የሺሃረግ የኖርዌይ ሚዲያዎችና በስለላ ተግባር የተሰማሩ “ስደተኞች” እንዳሉ በይፋ ቢናገሩም መንግሥት መልስ አለመስጠቱ ቢያሳዝናቸውም ማህበራቸው ትግሉን ይበልጥ እንዲገፋበት እንዳደረገው ነው የሚናገሩት።
ጎልጉል
No comments:
Post a Comment