ዛሬ አርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2006 አመሻሹ ላይ 11፡20 ገደማ ስድስት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን አባላት ናትናኤል ፈለቀ፣ በፍቃዱ ሀይሉ፣ አጥናፍ ብረሀነ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ዘላለም ክብረት እና አቤል ዋበላ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከያሉበት ተይዘዋል፡፡ ይህንኑ ዜና ይፋ ያደረገው የጦማሪያኑ የፌስቡክ ገጽ ሲሆን፤ ታሳሪዎቹን ለመያዝ የመጡት አካላት የማሰሪያና የመፈተሻ የፍርድ ቤት ፈቃድ የያዙ መሆናቸውን መስማታቸውን በዚሁ አጭር መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
ከሰአታት በፊት በወጣው መግለጫ፣ ““ዞን 9” የጦማርያን ስብስብ አባላት ሚያዚያ 15፣2006 በዋጣነው መግለጫ ላለፉት ሰባት ወራት የዞኑ አባላት ከፍተኛ የሆነ ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር በጠቅላላው የተጠቆመ ሲሆን ክትትሉ የተወሰኑ የቡድኑን አባላትና የቅርብ ወዳጆችን ጭምር ያካተተ ነበር፡፡ አሁን በመንግስት የተወሰደው እርምጃ የዞኑን ተመልሶ ወደ ስራ መግባት ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ሆኖም የዞን 9 አባላትና ወዳጆች በምንም አይነት ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው እነዳልነበር ለማረጋገጥ እንወዳለ፡፡” በማለት ያትታል።
በተያያዘ ዜና ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስም ዛሬ በፀጥታ ሀይሎች ቁጥጥር ስር መግባቱም ተዘግቧል።
ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በመንግስት በኩል የተሰጠ ምንም አይነት ማብራሪያ የለም።