Friday, May 10, 2013

የቃሊቲው ደብዳቤና የርዕዮት እውነቶች (በስለሺ ሀጎስ)


በስለሺ ሀጎስ
ሚያዝያ 23 2005 ዓ.ም ሪፖርተር ጋዜጣ በቅጽ 18 ቁጥር 44/1356 ዕትሙ “በህግ ታራሚ ርዕዮት ዓለሙ ላይ የደረሰ አንዳችም አይነት ችግር የለም!” በሚል ርዕስ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የተላከ ደብዳቤ አስነብቧል፡፡ ደብዳቤው በቅጥፈትና በክህደት የተሞላ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ባልተነሳ ጥያቄና ባልተባለ ነገር ላይ በማተት የተነሳበትን ሀቀኛ ጥያቄ አደናብሮ ለማለፍ ከአንድ ህገ መንግስታዊ ተቋም የማይጠበቅ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህ የሆነውም ርዕዮት ራሷን በማትከላከልበት ሁኔታ ውስጥ መሆኗን እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት ይመስላል፡፡ በመሆኑም በደብዳቤው ላይ የሰፈሩትን አብዛኞቹን ጉዳዮች በቅርብ ስለማውቃቸው የርዕዮትን እውነቶች የማስረዳት ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለብኝ በማመኔ ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ፡፡Reeyot-Alemu
በደብዳቤው ከታጨቁ ቅጥፈቶችና ማወናበዶች መሐከል ጸሐፊውን ጠልፈው የሚጥሉ እውነቶች ተሸሽገው ቀርበዋል፡፡ ከነዚህም መሐከል አንደኛው ርዕዮት ለብቻዋ እንድትታሰርና በጠያቂዎቿ እንዳትጎበኝ ለማድረግ ማረሚያ ቤቱ እንደተዘጋጀ ማረጋገጡ ነው፡፡ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ፣
‹‹በማረሚያ ቤት አብረዋት ከሚኖሩ ታራሚዎች ለመረዳት እንደቻልነው ርዕዮት ያለምንም ጥረትና ልፋት ዝናን ለማግኘት በመሻቷ ከታራሚዎችና ከጥበቃ አባሎች ጋር በየጊዜው ትጋጫለች፡፡ ጤናማ የሆነ ግንኙነት የላትም፡፡ በተለያየ ጊዜ በታራሚዋ ላይ የዲሲፒሊን ግድፈት በመታየቱም ማረሚያ ቤቱ ጥፋቱን በማጣራት ላይ ይገኛል፡፡ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘችም በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕግ ታራሚዎች መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 138/1999 መሠረት ተገቢውን የዲሲፒሊን እርምጃ ተቋሙ እንደሚወስድ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡›› የሚል ሀሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
በጽሑፉ ላይ እንደሚታየው ርዕዮት የዲሲፒሊን ግድፈት ማሳየቷን ማረሚያ ቤቱ ደምድሟል፡፡ ከዚህም በላይ ከጥበቃ አባሎችና ከታራሚዎች ጋር እየተጋጨች የዲሲፒሊን ግድፈቱን የምትፈጽመው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “ያለምንም ጥረትና ልፋት ዝናን ለማግኘት በመሻቷ ከታራሚዎችና ከጥበቃ አባሎች ጋር በየጊዜው ትጋጫለች፡፡ ጤናማ የሆነ ግንኙነት የላትም፡፡” በማለት በልቧ ምን አስባ ድርጊቱን እንደምትፈጽም ሁሉ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ ነግሮናል፡፡ ታዲያ ማረሚያ ቤቱ የሚያጣራው ምንድን ነው? ጥፋተኝነቷን ከነ መንስዔው እርግጠኛ ሆኖ እየነገረን፤ መልሶ ደግሞ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ አልሞ ለመተኮስ ሳይሆን፣ የሚፈልገው ላይ ተኩሶ ዒላማ ለማክበብ መዘጋጀቱን ያሳብቃል፡፡

No comments:

Post a Comment