Sunday, February 24, 2013

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ድምጻችን ይሰማ በማለታቸው በፌደራል ፖሊስ አባላት ተደበደቡ

በትናንትናው እለት በተለይም በሻሸመኔ፣ ድሬዳዋ፣ መቱና በርካታ ከተሞች የጁመአን ስግደት ተከትሎ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ድምጻችን ይሰማ በማለት ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ ባደረጉት ሙከራ የዘረኛውና አምባገነኑ የወይኔ አገዛዝ የፌደራል ፖሊስ አባላት መደብደባቸውንና በርካቶችም መታሰራቸውን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ በላከልን ዘገባ ገለጸ።
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ከፍተኛ ተቃውሞ ከታየባቸው ከተሞች መካከል ውስጥ አንዱ በሆነው የሻሸመኔ ከተማ፣ በርካታ ሙስሊሞች በ04 መስጊድ ተገኝተው ድምጻችን ይሰማ መሪዎቻችን ይፈቱ በማለት ተቃውሞአቸውን መግለጻቸውና በተመሳሳይ መልኩም ተቃውሞዎች በበደሌ፣ መቱና ድሬዳዋ መካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
ዘረኛውና አፋኙ የወያኔ አገዛዝ የሙስሊሞችን ተቃውሞ ለማስቆም ድብደባና እስራትን የጨመረ የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርግም ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ውጭ አድማሱን እየተስፋፋ ከመሄድ በስተቀር የመቀነስ ሁኔታ ሊታይ አለመቻሉን ዘጋቢያችን በላከው ሪፖርት አክሎ ገልጹአል።
በተያያዘ ዜና ሰሞኑን በተለያዩ የተቃዋሚ ሃይሎች ድረ ገጾች ላይ እንደተዘገበው በአሜሪካ የሞኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዛሬው እለት በዋይት ሀውስ ፊት ለፊት ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ታውቁአል።
ድምፃችን ይሰማ ዋሺንግተን ዲሲ እንዳስታወቀው፤ ሰልፉ የተዘጋጀው የዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በሙስሊሞች ላይ እየፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማውገዝና ረዥም ጊዜ ላስቆጠረው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ትግል አጋርነትን ለመግለጽ ነው።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላነሱት የመብት ጥያቄ የወያኔ አፋኝ ስርአት ቀና ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆኑም በላይ ህግን በሚፃረር ሁኔታ በመብት ጠያቂዎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የጠቆመው ድምፃችን ይሰማ፤ ከዚያም አልፎ በሙስሊሙ መሪዎች ላይ የእስር፣የግርፋትና የማንገላታት ድርጊት መፈፀሙን አመልክቷል።
ድምጻችን ይሰማ ዋሽንግተን ዲሲ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከሐምሌ 12 ጀምሮ 17 ዋነኛ የሙስሊሙን ሰላማዊ ትግል መሪዎችን ጨምሮ በርካታዎች እንደታሰሩ፣ እንደተገረፉ እና እንደተሰቃዩ ሪፖርት ማውጣቱን አስታውሷል። አያይዞም የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በእስር ላይ የሚገኙት መሪዎቻቸው በፖለቲካ ተጽጽኖ ስር ከወደቀ ፍርድ ቤት ፍትህን ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎ ፈጽሞ እንደማይጠበቅ ዓለማቀፉ ማህበረሰብና ለጋሽ ሀገራት ሊያውቁት እንደሚገባም ድምፃችን ይሰማ ዲሲ ጠቁሟል። በመሆኑም የ ወያኔው ዘረኛ አገዛዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና ወንጀል እጅግ ሳይዘገይ በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ትኩረት ያገኝ ዘንድ ኮሚቴው ጠይቋል።
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆኑ ወንድሞቻችንም በወያኔው አገዛዝ የተለያዩ አፋኝ ፖሊሲዎችና አሠራሮች ተጠቂ መሆናቸውን እንደሚገነዘቡ የጠቀሰው የድምፃችን ይሰማ ዲሲ መግለጫ፤በመሆኑም ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ዛሬ በዋይት ሀውስ ፊት ለፊት ሙስሊሞች በሚያካሂዱት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ አብረው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በንዲህ እንዳለ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ሰመጉ) በቅርቡ “ጅሃዳዊ ሃረካት” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈው ዘጋቢ ፊልም የተከሰሱ ሰዎችን ሕገመንግስታዊ መብት የጣሰ ነው ሲል በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ሰመጉ በዚሁ መግለጫው በፌዴራል ፖሊስና በብሄራዊ ደህንነት እና ጸጥታ ባለስልጣን ተዘጋጅቶ በኢቲቪ እንዲቀርብ የተደረገው ፊልም ተጠርጣሪዎቹ በሕገመንግስቱ መሰረት በተከሰሱበት ወንጀል ከፍርድ በፊት እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብታቸውን የጣሰ መሆኑን ጠቁሞ ይህ በመሆኑም ከአሁን በኋላ ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤት የመከላከያ ምስክሮችን የማቅረብ አቅማቸው አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሶአል፡፡
የፌደራል ፖሊስ እና የብሄራዊ ደህንነት እና ጸጥታ ባለስልጣን እንደ ህገመንግስት ተቋምነታቸው በአሁኑ ሰአት በፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል ማእከል አቃቢ ህግ በነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ በከፈተው የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ በምርምራ ያገኙትን ማስረጃ እንደሚያቀርቡ ቢጠበቅም፣ ተቛማቱ በህገመንግስቱ አንቀጽ 20 የተደነገገውን ዜጎች ፈርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር መብታቸውን በመጣስ ፣ ተከሳሾች ወንጀል ስለመፈጸማቸው አውጅዋል ሲል አስታውሷል።
ዘጋቢ ፊልሙ ፍርድ ቤቶች በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት የሚያዛባ ይሆናል ያለው ሰመጉ፣ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በወያኔ አገዛዝ በኩል የተወሰደውን ድርጊት ከማውገዝ ባተጨማሪ ዘጋቢ ፊልሙን ያዘጋጁት እና እንዲሰራጭ ያደረገው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ድርጅት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የሚመለከተው አካልም ድርጊቱን በማውገዝ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ጠይቋል።

No comments:

Post a Comment