Friday, February 22, 2013


የወያኔ የትምህርት ፖሊሲ በችግር የተጠላለፈ መሆኑን የአለም ባንክ ጥናት አጋለጠ

ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በፖለቲካዉና በኤኮኖሚዉ ዘርፍ አንዳደረገዉ በትምህርቱም ዘርፍ አንድ ብሔርን ብቻ ለመጥቀም ሆን ብሎ የቀየሰዉና በ1984 ዓም በስራ ላይ ያዋለዉ የትምህርት ፓሊሲ ዛሬ ጥራቱ ከቀን ወደ እያሽቆለቆለ ጭራሽ በራሱ የማይተማመን ደካማ ትዉልድ እየፈጠረ መሆኑንና ይህ ጎታች የትምሀርት ስርአት በአጭር ግዜ ዉስጥ ካልተለወጠ ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትወጣዉ ማጥ ዉስጥ እንደምትወድቅ የአለም ባንክ አሳወቀ።
ወያኔ የራሱን ዘረኛና ድብቅ አላማ ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ያለ ጥናትና በቂ ዝግጅት ያደረገዉ የትምህርት ስርአት ለዉጥ አስር ዓመት በማይሞላ ግዜ ውስጥ ሶስት ጊዜ የመማሪያ መጽሐፍትን በመቀያየር የትምህርቱ ዘርፍ ተረጋግቶ የሰመረ አቅጣጫ እንዳይይዝና አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የሰዉ ኃይል ማፍራት እንዳትችል አድርጓታል። የአትዮጵያ ጉዳይ የሚያንገበግባቸዉ መምህራንና የልጆቻቸዉ የወደፊት ዕድል የሚቆረቁራቸዉ ወላጆች እንዲሁም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸዉ ተማሪዎች የወያኔ የትምህርት የፖሊሲ ያለበትን ችግርና የጫነባቸዉን ዕዳ በመረጃ አስደግፈዉ ቢያቀርቡም ወያኔ በማንኣለብኝነት ተነሳሰስቶ ጥያቄ ያነሱትን አገር ወዳድ ኃይሎች በሙሉ እስራት፤ሞትና ስደት እንዲገጥማቸዉ አድርጓል።
ባለፈዉ ታህሳስ ወር የአለም ባንክ የኢትዮጵያን የትምህርት ፖሊሲ አስመልክቶ አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ዉስጥ በሰጠዉ መግለጫ ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንዲፈነጭ የረዱት አዉሮፓዉያን፤ኣሜሪካና የኣለም ባንክ ጭምር የችግሩን ኣሳሳቢነት በጥናትና ምርምር በተደገፈ ሰነድ በማስረዳትና ከሌሎች ኣገሮች ጋር በማወዳደር የኢትዮጰያ የትምህርት ፖሊሲ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑን በማጉላት ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱ ከፍተኛ ኣደጋ ላይ እንደምትወድቅ ገልጾ የሁሉም ክፍሎች የትምህርት ካሪኩለም መከለስና መለወጥ አለበት ሲል ኣስጠንቅቀዋል።
አንድ በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ዉስጥ የብዙ አመት ተሞክሮ ያላቸዉና የአለም ባንክ ባደረገዉ የአገሪቱ የትምህርት ዘርፍ ጥናት ዉስጥ ቁልፍ ቦታ የነበራቸዉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት የአለም ባንክ ጥናት በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በአንድ ክፍል ዉስጥ በኣማካኝ 64 ተማረዎች ይገኛሉ ይበል እንጂ በኣንዳንድ ት/ቤቶች 100ና ከዚያም በላይ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ዉስጥ እንደሚገኙ በአይኔ አይቻለሁ ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ እሳቸዉ የሚገኙበት የአለም ባንክ የጥናት ቡድን ወደ ኣዋሳ ኣካባቢ ት/ቤቶችን ለመጐብኝት በሄደበት ወቅት ኣንድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ዉስጥ ተገኝተዉ  በየክፍሉ ዉስጥ ምን ያህል ተማሪ እንዳለ ርዕሰ መምህሩን ጠይቀዉ ከ100 እሰከ 120 የሚደርሱ ተማሪዎች ይገኛሉ የሚል መልስ እንዳገኙና ለመሆኑ ፈተና እንዴት ትሰጣላችሁ በለዉ ሲጠይቁ  “ወረቀት እናባዛና ለእያንዳንዱ ተማሪ በመስጠት ዉጭ ሰርተው ይመጣሉ” የሚል መልስ ከርዕሰ መምህሩ እንዳገኙ ተናግረዋል።
ሌላዉ የአለም ባንክን ያሳሰበዉ ጉዳይ ደግሞ በወያኔ የትምህርት ስርዐት ዉስጥ ዘልቀዉ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ለስራ የሚሰማሩ ተማሪዎች ዕድሜ ጉዳይ ነዉ። የአለም ባንክ ባወጣዉ ጥናታዊ መረጃ ላይ ትልቅ ችግር ነዉ ብሎ ያስቀመጠዉ 10ኛ ክፍልን በ15 ዓመታቸዉ ጨርሰዉ ወደ ቴክኒክ ሙያ ከሄዱ በኋላ የ1 ዓመት፤ የ2 ዓመትና የ3 ዓመት ስልጠና ወስደዉ ወደስራ የሚሰማሩ ብዙ ተማሪዎች  ዕድሜያቸዉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከተቀመጠዉ የእድሜ ክልል ማለትም ከ18 ዓመት በታች የመሆናቸዉ ጉዳይ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የመጽሐፍት አለመሟላት ወይም በወቅቱ አለመቅረብ፤ የቤተ መጽሀፍትና የቤተሙከራ አለመኖር፤ የመምህራን ቁጥርና ጥራት እጅግ በጣም አነስተኛ መሆን፤ በየትምህርት ቤቱ የመቀመጫና የሌሎችም ቁሳቁሶች አለመሟላትና የትምህርት እድል ብሔርንና ጐሳን ማእከል ማድረጉ የአለም ባንክ በኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ላይ አይቶ በጥናቱ ዉስጥ ያካተታቸዉ ዋና ዋና ነጥቦች ናቸዉ። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱት አመታዊ ኮታን ለመሟላት እንጂ ተማሪዉንና የአከባቢዉን ህብተሰብ እንዲጠቅሙ ታቅዶ አለመሆኑን የአለም ባንክ ጥናት አጋልጧል።

    No comments:

    Post a Comment