Tuesday, January 13, 2015

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ Ethiopian Border Affairs Committee




ያለማቋረጥ ጥቃት የሚደርስበት
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት

ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
ጥር 4 ቀን 2007 ዓ/ም ( January 12, 2015 )
ካለፉት 23 ዓመታት ጀመሮ ኢትዮጵያን በወረራ የተቆጣጠረው የትግራይ ሕዝብ ነፃ-አውጭ ግንባር (ሕወሓት) ገዥ ኃይል
በተለይ ከጎረቤት አገር ሱዳን ጋር በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሁለ-ገብ ስምምነቶችን መፈራረሙ የሚታወስ ነው። የሁሉም
ስምምነቶች ድምር ውጤትም ሲታይ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሔራዊ ልዕልናና ጥቅም ሆነ ተብሎ ለመጉዳት የተደረጉ
የተንኮል ስምምነቶች እንደሆኑ በግልጽ ያስረዳሉ።
ከሁመራ ሰሜን ጫፍ አንስቶ እስከ ጋምቤላ ድረስ ሰፊ ድንግል የእርሻና ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት ያለውን የድንበር
መሬት ቆርሶ ከሰጠው ስምምነት አንስቶ በቅርቡ የሕወሓት ፓርላማ ካፀደቀው ሕገ-ስምምነት ድረስ ያሉት አጠቃላይ
ስምምነቶች በሙሉ ትኩረታቸው የሱዳንን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስጠብቁ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት
እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ፤ በተቃራኒው የሕወሓትን የለም መሬት ወረራና ነጠቃ በተለይም በጎንደርና በጎጃም
የሚያጠናክሩ፤ እንዲሁም የሁለቱን አምባገነን የገዥ ኃይላት መንበረ-ሥልጣን እንዳይናጋ የሚያግዙ ናቸው።
በቅርቡ በሕወሓት ፓርላማ የፀደቀው ሕገ-ስምምነት የሚያመለክተው ነገር ቢኖር ይህንኑ ሃቅ ነው። በሕገ-ስምምነቱ
መሠረት ሁለቱ አገሮች እንደነሱ አባባል በድንበሩ አካባቢ አሉ ስለሚሏቸው “ ወንጀለኞች ’’ መረጃዎችንና አስፈላጊ የሆኑ
ሠነዶችን ለመለዋወጥ፤ የሚፈለጉ ግለሰቦችን አፍነው ይዘው ለማስተላለፍ የሚያስችላቸው እንደሆነ ተገልጿል። አልፎ
ተርፎም፤ በየድንበራቸው አካባቢ የጋራ መከላከያ ኃይል ለማቋቋም ሕገ-ስምምነቱ መሠረት እንደሚሆን ታውቋል።
የሱዳን መንግሥትና የሕወሓት መሪዎች ሥልጣን የያዙት በነፍጥ ኃይል ስለሆነ፤ አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ገጸ-ባሕሪይ
አላቸው። ይኸም፣ ሁለቱ አምባገነኖች ለዴሞከራሲ ልዕልና፤ ለእኩልነት መስፈን፤ ለሕግ የበላይነት፤ ለሰበዓዊ መብት
መከበር፤ ለፍትህ መስፈን የሚታገሉትን ዴሞከራሲያዊ ኃይሎችንና ሰብዓዊ መብት ታጋዮችን በግፍ መግደል፤ ያለፍርድ
ማሰር፤ ማሳደድ የዕለት ተግባራቸው ነው።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እነዚህን የዴሞክራሲ ኃይሎች ነው፤ “ወንጀለኞች፣ አሸባሪዎች፣ ጽንፈኞችና ነውጠኞች” እያለ
የሚፈርጃቸው። ሕወሓት በቅርቡ ያጸደቀው ሕገ-ስምምነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለሱዳን መንግሥት የሰጠውን የድንበር
ለም መሬት ወደ ፊት ምንም ዓይነት ችግር እንዳይገጥመው የጥበቃ ዋስትና ለመስጠት ሆን ተብሎ የተቀመረ ሰነድ ነው።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ በተደጋጋሚ እንዳሳሰበው ሕወሓት በፓርላማውም ይሁን በግሉ የሚያደርጋቸውን
ስምምነቶች ሁሉ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅሞች ሆን ተብሎ ለመጉዳት ያነጣጠሩ በመሆናቸው ነው የሚያወግዘውና
የሚቃወመው። ስለዚህ፣ ስምምነቶቹ ሁሉ ለሱዳንና ለሕወሓት ጥቅሞች የቆሙ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል።
ሕወሓት “ወንጀለኞችና አሸባሪዎች” የሚላቸው ወገኖቻችን የግፍ አገዛዙን በድፍረት በመቃወማቸው፤ በአገራችን የሕግ
የበላይነት እንዲሰፍን በመታገላቸው፤ የእኩልነት መብት እንዲኖር በመሞገታቸው፤ የአገራችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት
እንዲከበር በፅናት በመቆማቸው፤ ኢትዮጵያዊነት እንዲአብብ ያላሰለሰ ትግል በማድረጋቸውና በአጠቃላይ በአገራችን
ሕዝባዊ ሥርዓት እንዲሰፍን መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጡ ጀግና ታጋዮች በመሆናቸው እንጂ “ወንጀለኞችና አሸባሪዎች”
ስለሆኑ አይደለም።ገጽ 2
እንደ እውነቱ ከሆነ የሕወሓትና የሱዳን መሪዎች አፍነው በሚገዙት ሕዝብ ላይ በሚፈጽሙት የዘር ማጽዳት ጭፍጨፋና
ግፍ የተነሳ በዓለም-አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ሊዳኙ የሚገባቸው የለየላቸው ወንጀለኞች ቢኖሩ እነርሱ ናቸው።
ትላንት አባቶቻችና እናቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍሰው አኩሪና አንጸባራቂ ታሪክ አቆይተውልን
አልፈዋል እያለን ዘወትር ስናወሳቸው እንኖራለን።
እኛ ዛሬ ያለነው ትውልድ ግን የነገው ተተኪ ትውልድ እኛን በኩራት የሚያስታውስበት ትተንለት የምናልፈው ቅርስ ምንድን
ነው? ይህ ዘወትር በሕሊናችን የማይጠፋ ተገቢና ትክክለኛ መልስ የሚሻ መሆኑ ጠንቅቀን ማወቅ ይገባል ብለን እናምናለን።
ባለ ብዙ ወደብ አገር ዛሬ ወደብ-አልባ ሆናለች፤ ከራስ ካሳር እስከ ሞያሌ ድረስ ሠፊ የመሬት ስፋት የነበራት አሁን
ተሸራርፎ ጠበብ አገር አስቀረን፤ ዘር፣ ጎሳ፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይል በአንድ ኢትዮጵያ ስም ተከባብሮና ተፈቃቅሮ ይኖር
የነበረውን ሕዝብ የዘር ጥላቻ ነግሶ መልሰን ወደ ዘመነ መሳፍንት ሥርዓት ውስጥ ከተትነው። በዚህ አኳኋን፣ ለመጭው
ትውልድ የምናቆየው ይህንን ነው? ወይስ ይህችን ለዘመናት ተፈርታና ተከብራ ሌሎች አገሮችና ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል
የሆነችውን አገራችን አሁን ካለችበት አሳዛኝና አሳፋሪ አረቋ አውጥተን የተከበረችና የታፈረች፤ የሕዝቧ አንድነትና እኩልነት
የተረጋገጥበት አገርን ነው?
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ አገርን ጠብቆ ለመጭው ትውልድ የማስረከብ አደራን የዕለት ተዕለት መርሆው አድርጎ
ለበርካታ ዓመታት እየታገለበት ይገኛል።
ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው ሲተላለፍ የመጣን አገረን ሳያስደፍርና ሳይሸራረፍ ጠብቆ ለአዲሱ ትውልድ የማስተላለፍ
ቅብብሎሽ ዛሬም በእኛ ትውልድ ተገባራዊ የማድረግ የዜግነት ግዴታ አለብን። ስለዚህ ሁላችንም በጋራ ተነስተን ዘር፣
ሃይማኖት፣ ቋንቋና ሌሎችም የወቅቱ የትግራይ ሕዝብ ነፃ-አውጭ ግንባር (ሕወሓት) ገዥ ኃይል ከፋፋይ ዘዴዎች
በመካከላችን እንደ ግድግዳ ሆነው ሳያቆሙን በአንድ አገር ልጅነት ቆመን፤ በሕዝባችንና በአገራችን ላይ እንደ መዥገር
የተጣበቀውን የዘርና የከፋፍለህ ግዛ ፀረ-ኢትዮጵያ ሥርዓት በጋራ ታግለን ከሥሩ ፈንግለን መጣል ይኖርብናል።
በዚህ አስከፊና ፀረ-ኢትዮጵያ ሥርዓት ከርሰ-መቃብር ላይ ሉዓላዊነቷና የግዛት አንድነቷ የተከበረባት፤ እኩልነት፣ የሕግ
የበላይነትና ዴሞክራሲ የሰፈነባትና የበለጸገች አገር መሥርተን ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ ነገ ሳንል ዛሬውኑ በአንድነት
ተነስተን ታላቅ ታሪክ እንድንሰራ አገራዊ ጥራችንን እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በቆራጥ ልጆቿ ይከበራል!
ድል ለጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment