Friday, November 7, 2014

ተኖረና ተሞተ! የጥበብ መገለጫው ለህዝብ መቆም ነው! ዝምታው ይሰበር!!! ነፃነታችንን ለመጎናጸፍ በአንድነት መነሳት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው!



በማንኛውም ህዝባዊ የነፃነት የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። በተለይ እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ባለ ህዝብን ከእውነተኛ መረጃ ለመነጠል ሌት ከቀን በሚሰራ አምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ባለሞያው የሚያበረክተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በዚህ ረገድ በሃገራችን ኢትዮጵያም ሥርዓቱ የሚጭንባቸው ከፍተኛ አፈና፣ ግድያ፣ እስራትና፣ ቁጥር ስፍር የሌላቸው እንግልቶች ሳይበግራቸው፤ ህይወታቸውን፣ ኑሮአቸውን፣ ቤተሰባቸውንና፣ ሃብት ንብረታቸውን ለከፋ አደጋ አጋልጠው ለሃገርና ህዝብ ነፃነት ከፍተኛ መሥዋዕትነት በመክፈል፤ ህዝብ የእውነተኛ መረጃ ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል የታገሉና እየታገሉ ለሚገኙ አያሌ ጀግኖች የህዝብ እውነተኛ የቁርጥ ቀን ልጆች ያለንን ከልብ የመነጨ አድናቆትና ክብር ለመግለፅ እንወዳለን። ውድ አርቲስቶቻችን! ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ነውና፤ ሌሎችም ጋዜጠኞችና የኪነጥበብ ባለሞያዎች የውድ ጀግኖቻችንን አረዓያነት በመከተል፤ እንዲሁም ክፍተቶችን ጠግነው በጋራና በአንድነት በመስራት ትግላቸውን አጠናክረው ለበለጠ ውጤት መዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው ልናሳስብ እንወዳለን።

ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! በአሁኑ ወቅት በገዛ ሃገርህና ችሎታህ ስራ ሰርተህ፤ እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ፤ ህይወቴንም በዚህ የስራ መስክ እገነባለሁ፤ ብለህ እንድታልም የሚያደርግህ እድል ከፊትህ ጠፍቷል። ዛሬ ሀገርህን ለተቆጣጠሩት ጥቂት አምባገነኖች አገልጋይ ለመሆን ባለመፍቀድህ ብቻ የወደፊት እድልህና እጣፈንታህ ሁሉ ተዘግቶብህ፤ በገዛ ሃገርህ የበይ ተመልካች ሆነሃል። ዛሬ እነኝህ ጨካኝ ገዢዎችህ የሚፈፅሟቸውን አሰቃቂ በደሎች ሰምተህ እንዳልሰማ ለማለፍ ብትሞክር እንኳ፤ የግፋቸው አስፈፃሚ ሎሌ ከመሆን በቀር ሌላ ምንም አይነት እድል የለህም። ከዚህም በከፋ ሁኔታ በዙሪያህ ተንሰራፍተው የሚገኙት የትምህርት ጥራት ጉድለት፣ ስራ አጥነት፣ በሱስ መጠመድ፣ ስደት፣ የተማሪ ሴተኛ አዳሪነት፣ የመጠለያ እጦት እና ሌሎች አስከፊ ችግሮች እየተፈራረቁብህና እያጠፉህ ይገኛሉ። ታዲያ በህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ውስጥ የከፋና የመረረ፤ ትርጉም የለሽ የጨለማ ህይወት እየኖሩ ካሉት ሚሊዮን እትዮጵያውያን ውስጥ ከሆንክ፤ ለተሻለ ለውጥ የሚደረገውን ህዝባዊ የሰላማዊ ትግል የማትቀላቀልበትና፤ ባለህ እውቀት የመሪነቱን ሚና በመጫወት የጠፋው ተስፋህን መልሰህ የማትጨብጥበት ምን አይነት አሳማኝ ምክንያት ይኖርሃል!?

ይህ አሳዛኝ ሂደት እስከመቼ ይቀጥላል!? ጥቂቶች እየጫኑብን የሚገኘውን በደልና ግፍ እስከመቼ ችለን በዝምታ እንዘልቃለን!? እስከመቼስ በጣት የሚቆጠሩ ጥቂት ሆዳሞች ሚሊዮኖችን እያፈኑ፤ ሃገርን እየዘረፉና፤ ህዝብን እያሸበሩ በትከሻችን ላይ ተሸክመን እንችለዋለን!? እስከመቼ የውሸት ዲስኩራቸውንና ባዶ የተስፋ ዳቦአቸውን እየተመገብን መኖር ይቻልን ይሆን!? መልሱ የሚገኘው እኛና እኛ ጋር ብቻ ነው! ከእንግዲህ የጥቂቶች ኪስ ማደለቢያ የሆኑትን ባዶ ፎቆች ከሩቁ እያየ የተስፋ ዳቦ የምንመገብበት ጊዜ ማብቃት ይኖርበታል። በአንድነት ተባብረን ጉልበታችንን አስተባብረን የመኖር ህልውናችንን የምናስመልስበት ጊዜው ቀርቧል። በሃገራችን የመኖር ተስፋችንን የምንገነባበት ጉልበቱም፣ ችሎታውም፣ እውቀቱም፣ ብቃቱም በእጃችን ነውና፤ ለነፃነታችን በአንድነት ቆመን ህዝባዊ የበላይነታችንን በማረጋገጥ ታሪካዊ ግዴታችንን ለመወጣት ሁላችንም ዝግጁ እንሁን።

No comments:

Post a Comment