Wednesday, June 25, 2014

የመጨረሻዉ መጀመሪያ


በቅርቡ በተከታታይ አገር ቤት ዉስጥ ቅርጽና ይዘት እየያዙ የምናያቸዉና ማንም አሌ የማይላቸዉ ግዙፍ እዉነታዎች ሁሉም በአንድነት የሚጠቁሙት አይቀሬዉ የወያኔ መጨረሻ መጀመሩን ነዉ። ከዚህ ቀደም በግልጽ እንዳየነዉ ወያኔ አንድ ቦታ ሲሸነፍ ሌላ ቦታ እያሸነፈ በጉልበትም በተንኮልም የፖለቲካ የበላይነቱን እንደያዘ ከሃያ ሁለት አመት በላይ ቆይቷል። ወያኔ ለአመታት ህዝብን ያታለለባቸዉ የዉሸት ክምሮችና ህዝባዊዉን ትግል ወደ ኋላ ለመጎተት የተጠቀመባቸዉ ስልቶች ዛሬ ሁሉም ሙጥጥ ብለዉ አልቀዉበት ዬኔ ነዉ ብሎ በሚመካበት ትግራይ ዉስጥ ጭምር መግቢያና መዉጪያዉ የጠፋዉ የተከበበ አዉሬ መስሏል። በያዝነዉ የ2006 ዓም ሁለተኛዉ አጋማሽ ወያኔ ጨካኙን የአግአዚ ኃይል እዚህም እዚያም አሰማርቶ ከሚቆጣጠራቸዉ ጥቂት አደባባዮች ዉጭ እንደቀድሞዉ በግልጽ ወጥቶ ወያኔን የሚያሞግስ ወይም የወያኔን የሌለ ገድል የሚናገር ሰዉ የለም። በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የትግል ስልቶች ወያኔን የሚታገሉ ኃይሎች አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ኃይላቸዉና ቁርጠኝነታቸዉ እየጨመረ መጥቶ ወያኔ ያንን የተለመደ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዉን እዲወስድና የራሱን የመጨረሻ እሱ እራሱ ሳይወድ በግዱ እንዲያፋጥነዉ እያደረጉት ነዉ።
የአገራችንን አንድነት ሊያላሉና ኢትዮጵያ የሚለዉን ታሪካዊ ስም ከታሪክ ዉጭ ማድረግ ከሚችሉ አደገኛ የወያኔ ባህሪዮች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ዘረኝነቱና ለአገር አንድነትና ዳር ድንበር መከበር ያለዉ የግድየለሽነት ባህሪይ ነዉ። ዛሬ ወያኔ በአራቱም ማዕዘን በየቀኑ አየጨመረና እያየለ የሚሄደዉን የህዝብ ቁጣ ለማብረድና አፋፍ ላይ ለደረሰዉ ስርዐቱ ተጨማሪ ግዜ ለመግዛት የሚወስዳቸዉ እርምጃዎች ከዚሁ ከዘረኝነት ባህሪይዉ የሚመነጪ እርምጃዎች ናቸዉ። ወያኔ ዕድሜዉ ሊበረክት የሚችለዉ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነት የሚታገሉ ኃይሎች መግባባት ሲያቅታቸዉ መሆኑን ያዉቃል፤ ስለዚህም በተቻለዉ መጠን ኢትዮጵያዉያንን የሚለያዩና ግጭት ዉስጥ የሚከትቱ አጀንዳዎችን አየፈጠረ ይወረዉርልናል። ከእነዚህ አገር አጥፊ የወያኔ አጀንዳዎች ዉስጥ አንዱ ህዝብን በዘር ከፋፍሎ እርስ በርሱ እንዲጋጭ ማድረግ ነዉ። ለምሳሌ በቅርቡ ደቡብ ኢትዮጵያ ዲላ ከተማ ዉስጥ በንግዱ ህብረተሰብ ላይ የነጋዴዎችን አቅምና ትርፍ ያላገናዘበ ግብር በመጫን በአንድ በኩል ነጋዴዎቹ በዞኑ አስተዳዳሪዎች ላይ እንዲነሱ በማድረግ በሌላ በኩል ደግሞ የዞኑ አስተዳዳሪዎች ነጋዴዎቹን የምትሰሙን ከሆነ ስሙን አለዚያ ክልሉን ለቅቃችሁ ሂዱ የሚል አስነዋሪና የዜግነት መብትን የሚጋፋ መልስ እንዲሰጡ በመገፋፋት በጌዲኦ ብሄረሰብና በዲላና አካባቢዉ በብዛት በንግድ ስራ ላይ በተሰማራዉ የጉራጌ ማህበረሰብ መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ለማድረግ ሞክሯል። ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዉስጥም እንደዚሁ የጋምቤላ ህዝብ ከጋምቤላ ዉጭ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡትን ኢትዮጵያዉያን ክልሉ የእናንተ አይደለምና ለቅቃችሁ ዉጡ ብሎ እንዲያሰገድድ በመገፋፋት በኢትዮጵያዉያን መካከል ቂምና ጥላቻ እንዲፈጠር አድርጓል። ባለፉት አምስት አመታት ወያኔ ጋምቤላ ዉስጥ ገበሬዉን እያፈናቀለ መሬቱን ለዉጭና ለአገር ዉስጥ በተለይ ለትግራይ ባለኃብቶች በርካሽ ዋጋ ማስረከቡ የሚታወስ ነዉ። ይህ ባዕዳንን ጋምቤላ ላይ እያሰፈረ ኑና እረሱ እያለ የሚለምን ነዉረኛ አገዛዝ ነዉ ዛሬ ኢትዮጵያዉያንን ከጋምቤላ ዉጡ እያለ የሚያሰገድደዉ።
ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ምን ያክል እንደተጠላ ለማወቅ ባለፈዉ ቅዳሜ መድረክ አዋሳ ዉስጥ የጠራዉን የተቃዉሞ ሰልፍ መመልከቱ ይበቃል። የአዋሳና የአካባቢዉ ህዝብ በዚህ መድረክ በጠራዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ የተገኘዉ ፌዴራል ፖሊስ፤ የክልሉ ፖሊስና የአገዛዙ ካድሬዎች በእያንዳንዱ ሰላማዊ ሰልፍኛ ላይ ያወርዱት የነበረዉን ዛቻ፤ ማስፌራሪያና ና የስድብ ናዳ ከምንም በለመቁጠር ነዉ። በዕለቱ የአካባቢዉን ሰላምና የሰልፈኛዉን ደህንነት አስጠብቃለሁ ብሎ በአዋሳ አደባባዮች ላይ የተሰማራዉ የወያኔ የፖሊስ ኃይል በህግ የተሰጠዉን ኃላፉነት ትቶ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር እርምጃዎች ሲወስድ ታይቷል።
ወያኔ ብሶቱን አይቼ 17 ዐመት ታገልኩልት የሚለዉና ዛሬም እወክለዋለሁ ብሎ የሚነግረን ክልል ቢኖር የትግራይ ክልል ነዉ። ዛሬ ትግራይ ዉስጥም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሞቱት ለዚህ አይደለም ብለዉ ብረት አንስተዉ ወያኔን አምርረዉ የሚታገሉ የትግራይ ወጣቶች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነዉ። አስራ ሰባት አመት ሙሉ በወያኔ የማይጨበጥ ተስፋ ተታልሎ በከንቱ ህይወቱን የገበረዉ የትግራይ ወጣት ዛሬ እዉነቱ ገብቶት ወያኔን በትግራይ ህዝብ ስም መነገድህን አቁም እያለዉ ነዉ። በቅርቡ በመቀሌና በአካባቢዋ የታየዉ ከፍተኛ ፀረ ወያኔ እንቅስቃሴ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወያኔ ለዚህ የሸተተ ስርአቱ ዕድሜ ለመግዛት ቢፍጨረጨርም “ከወደቁ በኋላ መራገጥ ለመላላጥ” ካልሆነ በቀር ካሁን በኋላ ወያኔዎች በስልጣን ላይ መቆየት ቀርቶ የዘረፉትን ኃብት የሚያሸሹበት ግዜም ልንሰጣቸዉ አይገባም።
የወያኔ ጠመንጃና የሚቆጣጠራቸዉ የአፈና ተቋሞች አላናግር ወይም አላስተነፍስ እያሉት እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ስለተገደደ ነዉ እንጂ አመጸኞቹ የወያኔ መሪዎች ለተቀረዉ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ታገልንለት ብለዉ በስሙ ለሚነግዱት የትግራይ ህዝብ በፍጹም የማይበጁ ፀረ አገር ኃይሎች መሆናቸዉን የትግራይ ህዝብ ካወቀ ቆይቷል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የትግራይ ህዝብም በቃ በስሜም አትነግዱ ወንድሞቼንና እህቶቼንም አትበድሉ ብሎ ደጋግሞ እየነገራቸዉ ነዉ። ዛሬ ብዙ የትግራይ ወጣቶች እዚያ የዛሬ ሰላሳና ሰላሳ አምስት አመት አባቶቻቸዉ የታገሉበት ጫካ ዉስጥ ገብተዉ እነሱም በተራቸዉ የዛሬዉን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በጠመንጃ ጭምር በመፋለም ላይ ይገኛሉ። ወያኔ የመጨረሻ መደበቂያዬ ይሆነኛል ብሎ ይተማመንበት የነበረዉ የትግራይ ክልል ዛሬ ግልጽ በሆነ መልኩ የወያኔን መጨረሻ ለማየት የሚቸኩሉ ጀግኖች ክልል እየሆነ ነዉ።
የትግራይ ጫካዎችን ጨምሮ ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች “ጨርቅ” ብለዉ ያንኳሰሱትን የኢትዮጵያ ባንዲራ በክብር አንግበዉ ከቋጥኝ ቋጥኝ የሚዘልሉት የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አርበኞች ወገንን የሚያኮሩ ዘረኞቹን የወያኔ መሪዎች ደግሞ ምነዉ ባልጀመርነዉ የሚያሰኙ የአገርና የወገን አለኝታ ሆነዋል። ዛሬ ወያኔ የትግራይን ምድር የእግር መረማመጃ እስኪጠፋ ድረስ በወታደርና በታንክ ያጠረዉ ይህንኑ በትግራይ ወጣቶች የተገነባ ህዝባዊ የነጻነት ኃይል ስለፈራ ነዉ። አምባገነኖቸ በደም የሚቀባበሉት የተፈጥሮ ባህሪያቸዉ ሆኖ ነዉ እንጂ የታንክና የወታደር ጋጋታ ህዝባዊ ኃይልን የሚያቆም ቢሆን ኖሮ እነሱ ዛሬ ሚኒልክ ቤ/መንግስት ዉስጥ ገብተዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ሊረግጡ ቀርቶ ከተፈጠሩበት ደደቢት በረሃ ስንዝር ሳይራመዱ የእሳት እራት ሆነዉ ይቀሩ ነበር። ወያኔ ዛሬ በምድርና በአየር የታጠቀዉ መሰሪያና ሰራዊት ደርግ ከታጠቀዉ መሳሪያና ከነበረዉ ወታደራዊ ብቃት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፤ ሆኖም ለነጻነቱ ቆርጦ የቆመን ህዝብ የሚገታ ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ሰለሌለ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ አግኝቶ ደርግን መደምሰስ ችሏል። የዛሬዉ አምባገነን ወያኔም ዕድል ከደርግ የተለየ አይደለም። ወያኔ ያሰኘዉን ያክል ቢታጠቅ፤ ያሻዉን ያክል የድንበር አካባቢዎችን በታንክና በወታደር ብዛት ቢያጥር . . . . ደፋርና ጭስ መዉጪያ አያጣምና የወያኔ መሸነፍና መደምሰስ ጉዳይ ቀን እስኪያልፍ ያለፋል ካልሆነ በቀር ያለቀለት ጉዳይ ነዉ።
ደርግ ስልጣን በያዘባቸዉ የመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ዉስጥ ወታደራዊ አገዛዝ አንቀበልም ብለዉ ደርግን መግቢያና መዉጪያ ካሳጡት የህብረተሰብ ክፍሎች ዉስጥ ትልቁን ሚና የተጫዉተዉ ወጣቱ ትዉልድ ነበር። ይህ ወጣት ትዉልድ በኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል ዉስጥ ምን ግዜም ቢሆን ትዝታዉ የማይደበዝዝ አኩሪ የመስዋዕትነት ትግል ያካሄደና ያለምንም ፍርሃት ዉድ ህይወቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ መብትና ነጻነት መከበር አሳልፎ የሰጠ ጀግና ትዉልድ ነዉ። ዛሬም አዲስ አበባ፤ አዋሳ፤ ባህርዳር፤ ጅማ፤ አምቦ ጊምቢና በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተማዎች የሚኖረዉ ወጣት እኔም አገሬም አብረን ከምንጠፋ እኔ ሞቼ አገሬን አኖራለሁ በሚል ኢትዮጵያዊ እልህ ተነሳስቶ የወያኔን የመጨረሻ እያፋጠነ ነዉ። የወያኔን እገድልሃለሁና አጅ እቆርጣለሁ የሚል ዛቻ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ በብዕራቸዉ ህዝብን እያስተማሩ ቃሊቲ ከገቡት ጀግኖች ጀምሮ ከተማ ዉስጥ ከወያኔ ጋር መኖር በቃኝ ብለዉ ጠመንጃቸዉን ተሸክመዉ ጫካ እስከገቡት ቆራጥ አርበኞች ድረስ ኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤዋን ለማብሰር የተዘጋጁ እልፍ አዕላፋት ጀግኖች አሏት።
በገጠሪቱ ኢትዮጵያም መሬቱን ተቀምቶ የተሰደደዉ ወጣት ልክ እንደ ከተማዉ ወጣት በወያኔ ላይ አምርሮ ዱር ቤቴ ብሎ ጫካ ከገባ ቆይቷል። አባቶቹና አያቶቹ ያቆዩለትን መሬት በወያኔ የተቀማዉ የጋምቤላ ገበሬ መሬቴን አለዚያም ህይወቴን ብሎ ወያኔን ማንቀጥቀጥ ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። የሰሊጥ ማዕከል የሆነዉን ለምለም መሬቱን በወያኔ የተቀማዉና ዛሬም የአባቶቹን አጽም የተሸከመዉን መሬት ለባዕዳን ለመስጠት የሚዶለትበት የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ በወያኔ ላይ ጥርስ ከመንከስ አልፎ ቃታ መሳብ ጀምሯል። እነዚህ ከትግራይ እስከ ጋምቤላ ከጋምቤላ እስከ ጎንደር በአራቱም ማዕዘናት የሚታዩ ህዝባዊ አመጾች የሚያሳዩን አንድ ትልቅ ነገር አለ፤እሱም ወያኔ በህዝብ የተጠላ ብቻ ሳይሆን ህዝብ አንቅሮ የተፋዉ ከቆሻሻም ቆሻሻ መሆኑን ነዉ።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘረኝነት በጉልህ ከሚታይባቸዉና በዘረኝነት ፖሊሲ ላይ ተመስርተዉ ከተዋቀሩ አገራዊ ተቋሞች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የመከላከያ ተቋም ነዉ። የኢዮጵያ መከላከያ ተቋም በተለይ ዋናዉን የዉግያና አገርን የመከላከል ስራ የሚሰራዉ የሰራዊቱ ክፍል የተሰባሰበዉ ከመላዉ የአገሪቱ ክፍሎች ቢሆንም ይህ ተቋም ሁለት ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑና ሆን ተብለዉ የጎደሉ ጉድለቶች አሉበት።አንደኛዉ ጉድለት ሠራዊቱን በተለያየ ደረጃ ከሚመሩና ከሚያዝዙ ወታደራዊ መኮንኖች ዉስጥ ከ95% በላይ የአንድ ዘር ተወላጆች መሆናቸዉ ሲሆን ሁለተኛዉ ትልቅ ጉድለት ደግሞ በኢትዮጵያ ሠራዊት ዉስጥ አግአዚ የሚባል የአዉሬዎች ክምችት የሚገኝበት አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገሩና ከአንድ ክልል የመጡ ተዋጊዎች ያሉበት ሠራዊት መኖሩ ነዉ። የአገሬን አንድነትና ዳር ድንበር አስከብራለሁ ብሎ ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባሰበዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዘር ተከፋፍሎ የወያኔ መጠቀሚያ መሆን ሰልችቶታል።በተለይ ይህ ሰራዊት ብዛቱን በሚመጥን ቁጥር የመሪነትና የአዛዥነት ቦታ ስለማይሰጠዉ ሁል ግዜ በሚንቁትና በሚያንቋሽሹት የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች መመራት አንገሽግሾታል። ዛሬ በየበረሃዉ ለሚገኙት የነጻነት አርበኞች እባካችሁ እንገናኝና አገራችንን አንድ ላይ ሆነን ነጻ እናዉጣ የሚል የትግል ጥሪ በተደጋጋሚ የሚመጣዉ ከዚሁ በዘረኝነት አለንጋ ከሚገረፈዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነዉ። ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ በተለይ ባለፉትሦስት አመታት በኢትዮጵያ ሠራዊት ዉስጥ ትልቁ የመወያያ አርዕስት አንዴት አድርገን የነጻነት እበኞችን እንቀላቀል የሚለዉ ጥያቄ ነዉ። በሠራዊቱ ዉስጥ ሆኖ በዚህ አርዕስት ላይ የማይወያይ የሰራዊቱ አባል ቢኖር እንደ ዘይትና ዉኃ ቅልቅል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ ባዕድ አካል ሆኖ የሚታየዉ አዉሬዉ የአግአዚ ሠራዊት ብቻ ነዉ። አግአዚ ደግሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሳይሆን በኢትዮጵያ ሰራዊት ዉስጥ እንደ እንክርዳድ የበቀለ ፍጹም ባዕድና ጨካኝ የሆነ የወያኔ መገልገያ ነዉ።
ከዚህ በላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነዉ ወጣቱ፤ ገበሬዉ፤ ነጋዴዉ፤ ከተሜዉና ወታደሩ ሁሉም ወያኔን የሚቃወም ብቻ ሳይሆን ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን ለመደምሰስ የተዘጋጁ `ኃይሎች ናቸዉ። ባለፈዉ ግንቦት ወር ወያኔ ዘረኝነትንና ሙሰኝነትን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከለበትን ሃያ ሦስተኛ አመት ሲያከብር የኢትዮጵያ ህዝብ የተዋርድንበትን ቀን አናከብርም ብሎ ወያኔ የራሱን በዐል ብቻዉን አክብሮ ዉሏል። ከዚህ በተጨማሪ እጅግ በጣም ብዙ ኢትዮጵያዉያን ይህንን የባርነት ቀን እንደገና ሲከበር ማየት አንደማይፈልጉ በይፋ ተናግረዋል። በእርግጥም ካሁን በኋላ ወያኔ ግንቦት ሃያን ብቻዉንም ቢሆን እንዲያከብር መፍቀድ የለብንም። ደግሞም ወደድንም ጠላን ወይም አወቅን አላወቅን ወያኔ ግንቦት ሃያን የሚያከብረዉ ብቻ ሳይሆን እንዳሰኘዉ ረግጦ የሚገዛን እኛ አሜን ብለን ስለፈቀድንለት ብቻ ነዉ። ህዝብ በአንድ ድምጽ አልገዛም ብሎ አለመገዛቱን የሚያሳይ እርምጃ መዉሰድ ቢጀምር አይደለም በዐል ማክበር ወያኔዎች ሰኞ ያደሩበት ሚኒልክ ቤ/መንግስት ዉስጥ ማክሰኞ ማምሸትም አይችሉም ነበር።
መሬት አልባዉ የኢትዮጵያ ገበሬ ወያኔ እስካለ ድረስ ልጆቼን ብሎ ስለወደፊቱ ማሰብ ቀርቶ የዕለት ጉርሱን የማግኘት ዋስትናም የለዉም። ነጋዴዉም እንደዚሁ ነዉ። ለወያኔ ሙሰኞች ካላጎበደደና ግማሽ ትርፉን ለእነሱ ካልገበረ ነግዶ መኖር ቀርቶ በልቶ ማደር የማይችልበት ግዜ እየመጣ ነዉ። ከተሜዉ ኢትዮጵያዊስ ቢሆን እስከመቼ ነዉ ሰላማዊ ልጆቹ ከጉያዉ እየተጎተቱ ሽብርተኞች ተብለዉ ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸዉ ቃሊቲ ሲገቡ የሚመለከተዉ? እስከመቼ ነዉ ዬት ገቡ ተብለዉ አድራሻቸዉ የጠፋ ልጆቹ መንገድና ህንጻ ሲሰራ የጅምላ መቃብራቸዉ በግሬደር እየተቆፈረ ሲወጣ የሚመለከተዉ? ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የወጡት የመከላከያና ፖሊስ ሠራዊት አባላት እስከመቼ ነዉ እነሱ እራሳቸዉ በወያኔ ዘረኝነት እየተለበለቡ ለወያኔ ዕድሜ መራዘም ሲሉ ወንድሞቻቸዉንናነ እህቶቻቸዉን የሚገርፉትና የሚያዋርዱት?
ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ገዳማትን የእርሻ ቦታ አድርጓቸዋል፤ የእምነት ተቋሞችን የክፋቱ መሠረት አድርጓቸዋል፡ ምሁራንን ደግሞ አገራቸዉን ጥለዉ እንዲሰደዱ አድርጓል። ባጠቃላይ ወያኔ ያልበደለዉ፤ ያላሳቀቀዉ ወይም ተስፋዉን ያላጨለመበት የህብረተስብ ክፍል የለም። የገበሬዉ፤ የከተሜዉ፤ የነጋዴዉ፤ የወታደሩ ፤ የወጣቱና የምሁሩ ጠላት ወያኔ መሆኑን ካወቅን ዉለን አድረናል፤ ታዲያ ለምንድነዉ ይህንን የጋራ ጠላት በገራ የማናስወግደዉ? ከዛሬ በኋላ ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በሚቆይባት በእያንዳንዷ ቀን የእኛ ስቃይና መከራ መብዛቱ ብቻ ሳይሆን ጥፋቱም የኛ መሆኑን አጥብቀን ልንረዳ ይገባል። ወያኔ እንደሆነ ቀንበር ለመሸከም የተመቻቸ ትከሻ ካገኘ ምን ግዜም ቢሆን ከመግዛት፤ ከማሰርና ከመግደል ወደ ኋላ አይልም። አልገዛም፤ አልታሰርም ወይም አትገድሉኝም ብሎ በወያኔ ላይ መነሳት የዚህ ትዉልድ ኢትዮጵያዉያን ሀላፊነት ነዉ፤ ይህ ሀላፊነት ደግም በህብረት ቆመን ለአንድ አላማ በአንድነት ከታገልን በቀላሉ ልንወጣዉ የምንችለዉ ሀላፊነት ነዉ። ሰለዚህ የዛሬም ጥሪ እንደትናንቱ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወያኔን ለማስወገድ ሀላፊነቱን ይወጣ የሚል ነዉ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

Monday, June 23, 2014

በተለየ ሁኔታ በደቡብ ክልል እየታየ ያለው መንግስታዊ አፈናና ፀረ-ሕግ አቋም እንዲገታ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን!!! -ከአንድነት ፓርቲ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ



አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ባለፉት 23 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርዓቱ አምጦ የወለዳቸው ሀገራዊ አፈና፣ ማዋከብ፣ የመኖር ዋስትናን መንፈግ፤ ዜጎችን ማሰደድና ማሰር የተለመዱ ድርጊቶ ሆነው ኖረዋል፡፡ አሁንም በዚህ አስከፊ የአፈና መንገድ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ የስርዓቱ መንግስታዊ አፈናና ፀረ-ሕዝብ አቋም በመላ ኢትዮጵያ የተዘረጋ ቢሆንም ፓርቲያችን በእንቅስቃሴዎቹ ውስጥ እንደታዘበው በደቡብ ክልል በተለየ ሁኔታ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ሹማምንቶች ባደረባቸው የገዥነት መንፈስ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በማፈንና ብሎም ያለምንም ማስረጃና ምክንያት ሰላማዊ ታጋዮችን ወደ እስር ቤት በመክተት ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በፊት በክልሉ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች ከዞኑ አመራሮች ጋር ውይይት ሲያካሂዱ ድንገተኛ ወረራ ተደርጎና የግቢ በር ተሰብሮ ወደ እስር ቤት ተወስደው ነበር፤ ቁጫ ላይ ጠርተነው የነበረው ሰላማዊ ሰልፍም እንዲሁ በጉልበት፣ በእስርና አፈና እንዳይካሄድ ተደርጓል፤ ይባስ ብሎ ደግሞ የክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው አዋሳ የጠራነው ሰላማዊ ሰልፍ ተገቢውን ህጋዊ ሂደት ቢያልፍም በህገ-ወጥ እስር እንዲጠናቀቅ ሆኗል፡፡ ይህ እውነትም በክልሉ በተለየ ሁኔታ መንግስታዊ አፈናና ፀረ-ሕግ አቋም እንዳለ ያረጋገጠ ነው፡፡
አዋሳ ከተማ ላይ የጠራነው የተቃውሞ ሰልፍ በሚካሄድበት ማግስት ከ30 በላይ አባሎቻችንን፣ የዞኑን አመራሮችና ከአዲስ አበባ ለቅስቀሳ የሄደውን ቡድን ከነ መኪናው ወደ እስር ቤት በመውሰድ መንግስታዊ አፈናውን በገሀድ አሳይተዋል፡፡ በደቡብ የተፈጠረው የገዥነት መጥፎ መንፈስ የተጠናወታቸው የታች ባለስልጣናት ህግ በአደባባይ እንደረገጡ ታይቶበታል፡፡ አሳሪዎቹ በቅስቀሳ ላይ የነበሩት አባላትና አመራሮቻችን ‹‹ህጉን ጠብቀን አሳወቅን፣ የእውቅናውን ደብዳቤ መስጠት ይህን ሊሰራ የተቀመጠው አካል ድርሻ ነው፡፡ እውቅና ወረቀቱን የሚሰጠው አካል ስራውን ስላልሰራ እኛ ስራ ማቆም የለብንም፡፡›› ለሚለው መልስ ስላልነበራቸው ማሰርን እንደ መፍትሔ ወስደዋል፡፡ ህገወጡን የአትቀስቅሱ ትእዛዝ ከመቀበል መታሰር እንደሚሻል እጃቸውን ለካቴና የሰጡ አባሎቻችንና አመራሮች አረጋግጠዋል፡፡
ፓርቲያችን እንደሚገነዘበው የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ገፍቶ በወጣ ቁጥር የአምባገነኖች መደናበር ያይላል፡፡ ሲደናበሩም ህግ ይጥሳሉ፣ ህዝብ ያሰቃያሉ፣ ሀገር ይበድላሉ፡፡ አፋኞች ያልተገነዘቡት እድሜ ልክ ዕየተጨቆኑ መኖር እንደማይቻል ብቻ ነው፡፡
አንድነት እንደዚህ አይነቱን አይን ያወጣ አፈናና ፀረ-ሕግ አካሄድ በቸልታ አይመለከተውም፡፡ በክልሉ ለመዝጋት እየተሞከረ ያለውን የህዝብ ጥያቄ ከህዝብ ጋር በመሆን መፍትሔ እንዲያገኝ እናደርጋለን፡፡ በህግም እንጠይቃለን፡፡ በክልሉ ነፃ ምርጫ እንዳይካሄድና ህዝቡ በንቃት እንዳይደራጅ እየተደረገ ያለ ጥረት አካልም ነው፡፡ ያለምንም ወንጀል የታሰሩ አባሎቻችንና አመራሮቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳ እንዲፈቱ የሚመለከተው አካል ሃላፊነቱን እንዲወጣ እያሳሰብን በደቡብ ክልል እየታየ ያለው መንግስታዊ አፈናና ፀረ-ሕዝብ አቋም መታገላችንን እንደምንቀጥል እናረጋግጣለን፡፡
ድል የህዝብ ነው!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባUDJ-SEAL

Tuesday, June 17, 2014

ተባበር ወይንስ ተሰባበር!?


June 17, 2014
ከዋስይሁን ተስፋዬ
ሰኔ 10 ቀን 2006 እ.ኢ.አ.
በኢትዮጵያ ሃገራችን በፍቅር፣ በመተሳሰብና፣ በመቻቻል ለዘመናት የኖረ ህዝብ እርስ በርሱ በጥርጣሬና በጥላቻ ሲጎሻሸም፤ ቤተሰብ ከቤተሰብ መተማመን ጠፍቶ ግለኝነት ሲነግስ፤ የአብሮነታችን ማሰሪያ የሆነው ፍቅራችን ጠፍቶ አንዱ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ ጥላቻን ሲዶልት፤ መከባበራችን ረክሶ አንዱ ሃይማኖት ሌላውን ሲጠራጠር፤ ባጠቃላይ በሃገሪቱ ፍቅር ጠፍቶ ጥላቻ ሲነግስ በማየቴ አዘንኩ። ገዢው የኢህአዴግ ከፋፋይ ሥርዓት የዘረጋው አፋኝ መዋቅር ህዝብ ከጥላቻ ውጪ ሌላ ምንም አይነት መረጃ እንዳያገኝ አፍኖ፤ በሃገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን፤ ብሎም ኢትዮጵያዊነት ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና እየጠፋ እንደሆነ ሳስተውል ደግሞ ፈራሁ። በአንፃሩ ደግሞ ይህ አደገኛ ሁኔታ ለመናገር በሚዘገንን መልኩ አስከፊ በሆነበት በዚህ የጨለማ ዘመን፤ በተቃዋሚ ስም ራሳቸውን ሰይመው ‘እኔ ካልኩት በላይ ምንም ሊሆን አይችልም’ በሚል አምባገነናዊ አስተሳሰብ፤ በህዝብ ስም ለህዝብ ነፃነት ሳይሆን የራሳቸውን የግል ፍላጎት ለማሳካት የህዝብን በደል በማባባስ ላይ የተሰማሩ ስብስቦች እንደ አሸን በዝተው ስመለከት ተረበሽኩ። በመሆኑም በሃገራችን በጎ ነገር እንዲሰፍን በመመኘት፤ ያላስተዋለ ተገንዝቦ፣ አይቶ ዝም ያለም የሃገርና የህዝብ ውድቀት ነውና ማፈግፈጉን ትቶ ወደ እውነተኛው የህዝብ ነፃነት መንገድ ይራመድ ዘንድ፤ በዚህች አጭር ፅሁፍ ጥቆማዬን ለአንባቢያን ማቅረብን ፈቀድኩ።
ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነትና የሃገሪቱ ህልውና በኢህአዴግ መንግስት በጎ ፍቃድ ብቻ የሚወሰን መሆኑ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልፅ ነው። በመሆኑም መንግስት እንዳሻው ሃላፊነት በጎደለው አካሄድ ህዝብን ለዘመናት ሲያፈናቅል፤ ንጹሃን ዜጎችን መጥፎ ስም በመስጠት ባልሰሩት ሃጥያትና በተፈበረከ የሃሰት ውንጀላ በየእስር ቤቱ እንዲማቅቁ ሲያደረገ፤ የሃገሪቱን መሬት በፈቀደው መልኩ ለባእዳን ሃገራት ሲያድልና ሲሸጥና ብዙ ሌሎች በደሎችን በህዝብና በሃገር ላይ በተደጋጋሚ ሲፈፅም ማየት የተለመደ ሆኗል። በኔ አስተሳሰብ ኢህአዴግ ይህንን ማድረግ የቻለበት ዋንኛው ምክንያት የሚዲያ ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር በመቻሉ ነው። በሃገራችን የሚገኙት መንግስታዊ የሚዲያ ተቋማት የኢህአዴግን የዘረኝነት ፖሊሲ ብቻ በመስበክ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ስለ ሃገሩ አንድነት፣ ስለ ህዝቧ ፍቅርና፣ በሃገሪቱ ስላሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እንዳይሰማና እንዳያውቅ በማድረግ አስተሳሰቡ ከአካባቢው የማያልፍ ጠባብ አድርጎታል። ለዚህም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲተውኑት ያየነው ትእይንት አይነተኛ ምስክር ነው። ለአንድ ሃገርና ህዝብ የወደፊት አቅጣጫና ህልውናን በመወሰኑ ረገድ ሚዲያ እጅግ ወሳኝ ድርሻ አለው።ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው የሚዲያ ተቋማት የሚያሰራጨውን የዘረኝነትና የእርስ በርስ የጥላጫ መርዝ በመቋቋም የነፃነት ትግሉን ወደፊት መግፋትና ለውጤት ማብቃት የሚቻለው፤ ኢህአዴግ እየፈፀማቸው የሚገኙትን በደሎች ከማጋለጡ ባሻገር፤ ህዝቡ በተቃራኒው ስለአንድነትና ፍቅር እንዲሁም ስለተቃዋሚዎች በቂ እውቀት እንዲኖረውና፣ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በጋራ እንዲሰሩ የሚገባውን ጫና እንዲያደርግ፣ አልያም የመረጠውን መቀላቀል ይችል ዘንድ ሁለገብ መረጃዎችን በስፋት ለህዝብ ለማድረስ የሚሰራ የሚዲያ ተቋም መገንባት ሲቻል ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል። በተለይ እንደ ኢህአዴግ የሚዲያ ጠላት በሆነና ህዝብን በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ ከፋፍሎ የእርስ በርስ ጥላቻና ቂም ለማስፋፋት ታትሮ በሚሰራ አረመኔአዊ አገዛዝ ስር ለወደቀ ህዝብ ነፃ የመረጃ ስርጭት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ሁላችንም እንደምናየው የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ወቅት የተቃዋሚ ቡድኖች ከመጠን በላይ በመብዛታቸው ምክንያትና መረጃ በብቃት ስለማይደርሰው፤ የድርጅቶቹን አላማ፣ ግብ፣ ራእይ፣ በጎ ጎኖችና ግድፈቶች፣ እንዲሁም ሌሎች ልዩነቶቻቸውን በቅጡ መለየት ተስኖት፤ ምኑን ከምኑ፣ የትኛውን ከሌላኛው መለየት ባለመቻሉ ግራ በመጋባቱ ‘የነፃነት ትግል የውሸት፤ ፖለቲካ አይንህ ላፈር’ በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ተወስኖ፤ የሚደርስበትን ችግር ለማስቆም በጋራ ከመታገል ይልቅ በዝምታ መቀመጥን መርጦ ይገኛል። በመሆኑም የተቃዋሚ ድርጅቶች ያለ ህዝብ ተሳትፎ ብቻቸውን ሲያጨበጭቡ ይታያሉ።
ከላይ ለመግለጽ የሞከርኳቸውንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ዋንኛ መሳሪያው ብቃት ያለው የሚዲያ ተቋም መኖር በመሆኑ የተለያዩ የተቃዋሚ ቡድኖች ተቋማትን መስርተው ሲንቀሳቀሱ እናያለን። ነገር ግን እዚህጋ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ተቋማቱን መመስረት ብቻ ሳይሆን የሚያስተላልፉት የመረጃ ይዘቶችና አይነቶች እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን ነው። በኔ እይታ የሚዲያዎች አትኩሮት በተለየ ሁኔታና በስፋት፤ በተቃዋሚዎች መካከል ያሉትን ልዩነቶች፣ የተቃዋሚዎችን በጎ ጎኖችና ግድፈቶች፣ ከገዢው መደብ ጋር ያላቸውን ልዩነቶች በመረጃ ማቅረብ፣ ለሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ያለ አድልዖ እኩል መድረክ የሚሰጡና በሃገሪቷ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተቃራኒ አመለካከቶች ያሏቸውን ምሁራንንና የፖለቲካ ሰዎችን በማወያየት ህዝብ በስነልቦና በእውቀት እንዲጎለብት በስፋት የሚሰሩ ሊሆኑ ይገባል። ከዚህ መነሾነት ሲስተዋሉ በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ መረጃን ለማስተላለፍ በሚል አላማ ከሚሰሩት የሚዲያ ተቋማት አብዛኛዎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢህአዴግን መሰረታዊ አላማዎች ከማስተጋባት ያለፈ የሚጨበጥ ስራ ሲያከናውኑ አይታዩም። በእርግጥ አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ ስመለከታቸው እንደ Addis Dimts Radio፣ SBS Australia፣ የVOA እሰጥ-አገባና እንወያይ የራዲዮ ዝግጅቶች ሊመሰገኑ የሚገባ መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ።
ከአድማጮችና ከደጋፊዎች ብዛት አንፃር የኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ስለሚመስለኝ ሃሳቤን ለመሰብሰብ ይሆን ዘንድ፤ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ መሪዎች ከአድማጮች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በኢሳት ራዲዮ ምላሽ የሚሰጡበት፤ የ “ጥያቄ አለኝ” ዝግጅት ላይ፤ የኢሳት ቴሌቢዥንና ራዲዮ በማኔጅመንት ዳሬክተሩ በአቶ ነአምን ዘለቀና በጋዜጠኛ ብሩክ ይባስ ትብብር መላሽ የነበረበትን ለሁለት ሳምንታት የተላለፈ ዝግጅት ላይ ከአንድ አድማጭ የቀረበ ጥያቄንና ከኢሳት የተሰጡ መልሶችን እንደምሳሌ ማንሳት አስፈላጊ ነውና ከዝግጅቱ ከታዘብኩት ጥቂት ልበል። እኝህ ኢትዮጵያዊ የኢሳት አድማጭ ለኢሳት ያቀረቡት ጥያቄ ከላይ ካነሳሁት መሰረታዊ ሃሳብ ጋር በፅኑ ስለሚገናኝና አድማጩ ኢሳትን ሊያስገነዝቡ የሞከሯቸው ጭብጦች በአምባገነን ስርዓቶች ለአመታት ሲሰቃይ ለኖረው ህዝብ ነፃነት መጎናፀፍ ጉልህ ሚና ስለሚኖራቸው፤ ጥያቄያቸውም የበርካታ ኢትዮጵያውያንም ጥያቄ እንደሆነ ስለምገምት ለአንባቢያን ጥያቄውን አቀርባለሁ።
ምስጋና ይህን ወሳኝ ጥያቄ ላቀረቡት ለእኝህ ቀና ኢትዮጵያዊ የኢሳት አድማጭ ይድረስና፤ ባይሳካም የጉዳዩን ወሳኝነት ለማሳሰብ አቀራረቡን የበለጠ ግልፅ አድርገው በሁለተኛው ሳምንትም በድጋሚ ጠይቀዉት ነበር። ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና፤ እንደኔ አረዳድ የጥያቄያቸው መንፈስ ይህን ይመስላል፤ “እስካሁን ድረስ የተለያዩ መረጃዎችን ስትሰጡን ኖራችኋል። ነገር ግን የምትሰጡን መረጃዎች የኢትዮጵያ ህዝብን ወደ ድል ሊያበቁ አልቻሉም። ሁላችንም እንደምናየው ወያኔ የሚፈልገዉን ነገር ከማድረግ የሚያግደው ምንም ሃይል ሊፈጠር አልቻለም። የዚህ ዋና ምክንያት ደግሞ የምትሰጡት መረጃ ወያኔ በደሉን ከህዝብ ለመደበቅ የጭቆና ስልቱን በመቀየር ስህተቱን እንዲያርም ከማድረግና ከማገልገል በስተቀር ለህዝብ የረባ ፋይዳ አላስገኘም። ለወያኔ ደካማ ጎኑን እንደምትነግሩት ሁሉ፤ ለተቃዋሚዎችም ስህተታቸውን እንዲያርሙ እንድታሳስቧቸው ዘንድ፤ ብሎም ተቃዋሚዎች እየሰሩት በሚገኙት በደል ምክንያት ለነፃነቱ ላለመቆም ሳይወድ እንዲሸሽ ለተገደደው የኢትዮጵያ ህዝብ ብርታት እንደሚሆነው በማስገንዘብ ከብዙ አድማጮች አስተያየት ቢሰጣችሁም፤ ተግባራዊ ልታደርጉ አልቻላችሁም። የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ሃይሎች ኢህአዴግ ከሚያጠፋው በላይ በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ጥፋት እያደረሱ ይገኛሉ፤ ምክንያቱም እኔ ካልኩት ሃሳብ በላይ ማንም ሊሆን አይችልም ብለው ስለሚያምኑ፤ ልስራ ብሎ የሚመጣውን አንዱ ሲያዳክም፤ አንደኛው ሌላኛውን ሲያጠፋ እያየን እንገኛለን። ፊትለፊት አምጥታችሁ አገናኝታችሁ በጋራ እንዲሰሩ ልዩነቶቻቸውን ህዝብ አውቆ እንዲፈርድና የመረጠውን እንዲቀላቀል የማትረዱት ለምንድነው?”።
ለጥያቄው በትብብር የሰጡትን መልስ መሰረት በማድረግ ለአቶ ነአምን ዘለቀና ለጋዜጠኛ ብሩክ ይባስ ማሳሰብ የምፈልጋቸው ነጥቦች፤ የእኚህ አድማጭ ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያከ መሆኑን፣ የተጠየቀው ጥያቄ እርስዎ(አቶ ነአምን) አስረግጠው እንዳስገነዘቡን የኢሳትን ነፃ ሚዲያነት የሚጋፋ ሳይሆን በተቃራኒው ኢሳት እንደ አንድ ለኢትዮጵያ ህዝብ መረጃ ለማቀበል የሚሰራ ነፃ የሚዲያ ተቋም በስፋትና በከፍተኛ ትኩረት ሊሰራበት የሚገባዉን ወሳኝ ጭብጥ የያዘ መሆኑን፣ ለህዝብ ነፃነት የሚበጀው አንድ የተቃዋሚ ድርጅት ትእይንት ባዘጋጀ ቁጥር ብቻ ወይንም ገዢው መንግስት በህዝቡ ላይ በደል በፈጠመ ጊዜ ብቻ የተቃዋሚ መሪዎችኒና ታዋቂ ግለሰቦችን ማነጋገር ሳይሆን፣ የህዝቡን የመረጃ ክፍተት መሰረት ያደረገና ዘላቂነት ያላቸው የተጠኑ ውይይቶችን ለህዝብ ጆሮ ማቅረብ እንዳለበት ለማስገንዘብ የቀረበ መሆኑን አውቃችሁ ግዴታችሁን ለመወጣት ብታተኩሩ መልካም ነው፣ የሚሉ ናቸው።
በዚህ አጋጣሚ የኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚያደርሳቸውን በደሎች በማስተጋባት ብሶቱን ለማሰማት እለት ተለት የሚያደርገውን ጥረት ለማድነቅ እወዳለሁ። ሆኖም በኔ እይታ ይህ የኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን ጥረት ብቻውን፤ ለህዝብ ብሶቱን ከማሰማት ያለፈ አስተዋዕፅዎ ይኖረዋል ብዬ አላምንም። በመሆኑም ኢሳት እንደ ነፃ የሚዲያ ተቋም ህዝቡ በቂ መረጃን አግኝቶ እየደረሱበት የሚገኙትን ከመጠን ያለፉ ችግሮች ለማስቆምና፤ ብሎም ለነፃነቱ በጋራ ትግሉን ይቀላቀል ዘንድ ለማስቻል፤ የህዝብ ብሶትን ከማሰማት ባለፈ እጅግ በጣም ብዙ መስራት የሚጠበቅበት መሆኑን በማስገንዘብ፤ የህዝብ ነፃነትን እውን ለማድረግ በሚደረገው ትግል ላይ እንደ ሚዲያ ሃላፊነቱን ለመወጣት መጠነ ሰፊ የሆነ የዝግጅትና የአቀራረብ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርበት ጥቆማዬን አቀርባለሁ።
ይህን ሃሳብ ሳካፍል ፅሁፌን ያየ ያነበበ የኢትዮጵያ ልጅ ሁሉ፤ እኔ የተረዳሁትን ተረድቶ መፍትሄውን እንዲፈልግ፤ አልያም ሃሳቤን ለማካፈል የሞከርኩት ‘ነፃ ሚዲያ ያጎናፀፈኝን እድል’ ተጠቅሜ ነውና፤ ከተሳሳትኩ የመታረም መብቴ የተጠበቀ መሆኑን እንዲረዳልኝ እጠይቃለሁ። ስለሆነም የኔ ማጠቃለያ የነፃ ሚዲያዎች ትኩረትና የአንባቢያን ጠቃሚ አስተያየት እንደሚሆን በእጅጉ ተስፋ አደርጋለሁ።
ቸር እንሰንብት
ከዋስይሁን ተስፋዬ
ttwasyhun@gmail.com

Wednesday, June 11, 2014

ኦባንግ “ከምርጫው” በፊት ለተቃዋሚዎች “ምርጫ” አቀረቡ


ometho
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና አግባብ አላቸው ለሚሏቸው አካላት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተቀምጠው እንዲመክሩ ማሳሰቢያ ሰጡ፡፡ ኢህአዴግ በውስጥ ችግሩ፣ በውጭ ተጽዕኖ ወይም በፖለቲካው የተፈጥሮ ባህርይ የሚከስምበት ደረጃ መድረሱን ያሳሰበው በ”ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ስምና ፊርማ የተበተነው የአኢጋን ደብዳቤ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን አጥብበው እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡ ይህንን ለኢትዮጵያና ለሕዝባቸው ሲሉ መሥራት የማይችሉ ከሆነ ከኢህአዴግ በላይ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የፖለቲካ ዕርቅ በመጀመሪያ በተቃዋሚዎች ደጅ ሊተገበር እንደሚገባው ያሳሰበው አኢጋን፤ ይህንኑ ዕርቅ መሠረት በማድረግ ወደ ኅብረት እንዲመጡ በደብዳቤው ገልጾዋል፡፡ ወደ ኅብረት ሲመጡ የፖለቲካ ሥልጣን የመጨበጥ ዓላማቸውን ወደ ጎን መተው እንዳለባቸውና ኢትዮጵያን በማዳን ተግባር ላይ እንዲያተኩሩ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
መግለጫው ሲቀጥልም “የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ካለው ግንኙነት አኳያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰበስባል፡፡ በቅርቡ አንድ ታዋቂ የምዕራቡ ዓለም የፖሊሲ አውጪ ሲናገሩ ኢትዮጵያውያን የምዕራቡ ዓለም ነጻ ያወጣናል ብለውበጭራሽ ማመን የለባቸውም፡፡ ከውጭ የሚላከውን ዕርዳታና ድጋፍ ብናቆም እንኳን ይህ የሚሆን አይደለም፡፡ የለውጥ አራማጅና መሪመሆን ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ናቸው እንጂ ለጋሽ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሊረዱ ይገባል፡፡ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ በሚፈጥሩበት ጊዜ እኛ የግድ እንድንደግፋቸው ያደርጉናል በማለት ለጋራ ንቅናቄያችን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል” በማለት በመረጃ ላይ የተደገፈ ጭብጥ አቅርቧል፡፡
ሰሞኑን የዚህ ዓመት የSEED ተሸላሚ የሆኑት ይህ የአቶ ኦባንግ የምርጫ አማራጭ ግልጽ ደብዳቤ መጪውን ሁኔታ በሚከተለው ሁኔታ ገልጾታል፤ “አገራችን በበርካታ ድሎች ያንጸባረቀ ታሪክ ያላት ነች፡፡ ከሁሉ በበላይ የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል በድጋሚ የሚፈጸምበት ጊዜቢኖር አሁን ነው፡፡ የዓድዋን የጦር ድል በፖለቲካው መድረክ እንድገመው፡፡ መጪውን ምርጫ ፖለቲካዊ የዓድዋ ድልየምንጎናጸፍበት እናድርገው፡፡ ነጻነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛው ራሳችን እንደአድዋ ድል አንድ ሕዝብ ሆነን በመውጣት የራሳችን የምናደርገበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቅንነት ካለ የጦር ሜዳውን አድዋ በፖለቲካውሜዳ ላይ መድገም ይቻላል፡፡ አንድ ሊያደርጉንና ሊያስተባብሩን የሚችሉ “ምኒልኮችን” ለመጠቀም ፈቃደኛና ቅን እንሁን፡፡
በአኢጋን አድራሻና በዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ ስምና ፊርማ የተሰራጨው ይህ የማሳሰቢያ ግልጽ ደብዳቤ አኢጋን በተለይ በዕርቅ ዙሪያ የሚጠየቀውን ማንኛውንም ጥያቄ ድጋፍ እንደሚሰጥ ያረጋገጠ ነው፡፡ የደብዳቤው ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

“ነጻነትነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም!”
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች ያስተላለፈው ግልጽ መልዕክት
የተወደዳችሁ በኢትዮጵያ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤
በቅድሚያ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የአክብሮት ሰላምታ በማቅረብ በትግሉ መስክ የምትከፍሉትን መስዋዕትነት የሚያደንቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ ጠብቦ የለም የሚባልበት ደረጃ በደረሰበት ወቅት በምታገኙት ስንጥቅ ሁሉ እየተጠቀማችሁ ለህዝባችሁ የብርሃን ጭላንጭል ስለምትፈነጥቁ አኢጋን ሥራችሁን ያደንቃል፤ ያከብራል፡፡ እኛ በሥራችሁ ስኬት የምንመኘው ለቆማችሁለት የፖለቲካ ዓላማ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት አቅቷቸው መፈናፈኛ ላጡትም የመወሰን ኃይል እንደምትሰጧቸው በማመን ነው፡፡
አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የበርካታዎች ጥያቄ “ህወሃት/ኢህአዴግን በምን ዓይነት የተሻለ አስተዳደር እንዴት መለወጥ ይቻላል የሚለው ነው?” ይህ ጥያቄ “እኛ ኢትዮጵያውያን የዘርና የጎሣ ትንንሽ አጥሮቻንን አፍርሰን ሁሉን አቀፍ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይ?” ብለን ራሳችንን መልሰን አንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው፡፡ እንዲሁም ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠትሁሉም ነጻ ሳይወጣ ራሳችንን ነጻ ለማውጣት እንችላለን ወይ? ብለንም እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ነው፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው እንዲሁም ለመላው አፍሪካ “የሚተርፍ” እኩይ የዘርና የጎሣ ፖለቲካ በማስፋፋት አገራችንን እንደዚህ ባለ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በጣለበት በአሁኑ ወቅት የብዙዎች ጭንቀት አገራችን ወደ ምን ዓይነት አዘቀት ውስጥ እየገባች ይሆን የሚለው ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ፍርሃት ወደ ተስፋ የሚቀይር አማራጭ እስካሁን ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ አማራጭ የጠፋ ይመስል ህወሃት/ኢህአዴግም “እኔ ከሌለሁ …” እያለ ያስፈራራል፤ ተቃዋሚዎችም በእርስበርስ ሽኩቻ የህዝብ አመኔታ በማጣት ወደ አለመታመን ከመሄዳቸው የተነሳ መልሶ ተዓማኒነትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀር አለ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለኢትዮጵያ ሕጋዊ አማራጭ በመሆን ለሕዝባችን መፍትሔ የምታመጡበት ወሳኝ ጊዜ አሁን መሆኑን የጋራ ንቅናቄያችን ያምናል፡፡
እንደምታውቁት የዛሬ ዓመት ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ ነው፡፡ ምርጫውንና አመራረጡን ከሥሩ ጀምሮ የተቆጣጠረው ህወሃት/ኢህአዴግ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለን አናምንም፡፡ ሆኖም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የሚፈለገው ተግባር ከተከናወነ በአገራችን እውነተኛ ለውጥ ይመጣል ብለን እናምናለን፡፡ ዓመኔታ የሚጣልበት አማራጭ ከተገኘ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ህወሃት/ኢህአዴግን አንቅሮ ለመትፋት ከምንጊዜውም ይልቅ ዝግጁ ነው፡፡ ይህንንም የምንለው ከምንም ተነስተን ሳይሆን ድርጅታችን በአውሮጳ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ባለው የግንኙነት መስመር ከሚያገኘው ተጨባጭና ተዓማኒ መረጃ በመነሳት ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ዘንድ ህወሃት/ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያራምደው የዘር ፖለቲካ፣ የሚከተለው እጅግ ጭቋኝ ፖሊሲ፣ በየጊዜው በሚያወጣቸው አረመኔያዊ ህግጋት፣ ወዘተ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ አደጋ የጣለና ለአህጉሩ መጥፎ ምሳሌ እየሆነ በመምጣቱ በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ የመከሰቱ ጉዳይ ከምንጊዜውም በላይ አሳማኝ የሆነበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ፡፡ አሁንም ጥያቄው “ህወሃት/ኢህአዴግን ማን ይተካዋል?” የሚለው ነው፡፡ይህንን የመመለሱ ኃላፊነት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የወደቀ ቢሆንም በተለይ አገር ውስጥ ያላችሁት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ ልትመልሱት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ አመኔታ የሚጣልበት አማራጭ ሆናችሁ የመቅረባችሁ ሁኔታ ስለምርጫው ነጻና ፍትሃዊነት ከመጠየቅ ባልተናነሰ መልኩ ተጠይቆ መልስ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡
አገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለእናንተ ማስረዳት የሚያስፈልግ አይመስለንም፡፡ በየቀኑ የሚፈጸመውን በደልና ግፍ መከታተል ብቻ ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ በበቂ ሁኔታ የሚያመላክት ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ተቀጣጣይ (ክላስተር) ቦምብ በየቦታው የበተነው የጎሣ ፖለቲካ ፈንጂ ከፋፍሎ በመግዛት ለራሱ የሥልጣን ማቆያ ቢጠቀምበትም በአሁኑ ጊዜ አገራችንን ከላይና ከታች እያነደዳት ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ በአገራችን ላይ ሊፈነዳ የሚችለው ነገር ሁሉንም የሚያሳስብ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ራሱ በፈጠረው ችግርና በበተነው መርዝ ራሱን በራሱ ሊያጠፋው እንደሚችል ከድርጅቱ ውስጥ የሚታዩት የሥልጣን ሽኩቻዎች ሁሉም “ሳይቀድሙኝ ልቅደም” በሚል አስተሳሰብ እንደተወጠረ የሚያመለክት ነው፡፡ አገራችን ነጻነቷን ከመጎናጸፏ በፊት ይህንን ዓይነቱ የህወሃት/ኢህአዴግ እርስበርስ መበላላት የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን እጅግ በርካቶች ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እናንተ ባላችሁ ኃላፊነት ይህንን በውል የምታጤኑት እንደሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ያምናል፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ ከውስጥ በሚነሳበት ግፊትና የመበላላት ስጋት፤ ከውጪ በሚመጣበት ተጽዕኖ ወይም በሁለቱ ጥምረት ከሥልጣን መወገዱ የማይቀር ነው፡፡ ይህንን የሚቀበል ካልሆነም ሥርነቀል ተሃድሶ ማድረጉ እየጎመዘዘው የሚጠጣው ሐቅ ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ የሚከሰተው ለውጥ አገራችንን መልሶ መልኩን ለቀየረ በዘር ላይ ለተመሠረተ አገዛዝ አሳልፎ የሚሰጣት መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም የሚመጣው ለውጥ ሕዝባችንን እውነተኛ ነጻነት የሚያጎናጽፍ፣ ፍትሕ የሚሰጥና ወደ ዕርቅ የሚመራ መሆን ይገባዋል፡፡ አገራችን በዚህ ጎዳና ላይ እንድትጓዝ የማድረጉ ኃላፊነት የእናንተ እንደሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ያሳስባል፡፡
ይህ ደግሞ ሥልጣን ከመጨበጥ ባለፈ ምኞት ላይ የተመሠረተና እያንዳንዱ ነጠላ ፓርቲ ከሌሎች ጋር በኅብረት በመሥራት ተግባራዊ ሊያደርግ የሚገባው መሠረታዊ ዓላማ ነው፡፡ አገራችን ካለችበት ታላቅ ችግር አኳያ የፓርቲዎች መተባበርና ከተቻለም መዋሃድ ወደ መፍትሔ በሚወስደው መንገድ ላይ የመጀመሪያው ስኬት ነው፡፡ ይህ ግን በቀላሉ አይገኝም፤ ሆደ ሰፊ መሆንን፣ ከራስ ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ማሰብን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከፍተኛ የመንፈስ ልዕልናን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሥልጣንን፣ የራስን ክብር፣ የበላይነትን፣ “እኔ ከሌላው የተሻልኩ ነኝ” ማለትን፣ ወዘተ እያውጠነጠኑ ለአገር አስባለሁ ማለት በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ “ከጠላት” የላቀ የመንፈስ ልዕልና ከሁሉም ይጠበቃል፡፡
በመጪው ምርጫ ከምንጊዜውም በበለጠ በመጽናት ለለውጥና ለነጻነታችን የምንታገልበት ሊሆን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የናፈቀውን ነጻነት ሊጎናጸፍ የሚችልበት አማራጭ ሊፈጠር እንደሚችል አኢጋን ያምናል፡፡ ይህ ሊከሰት የሚችለው በአገር ውስጥ ያላችሁት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥቃቅን ልዩነታችሁን አስወግዳችሁ አጀንዳችሁን ሕዝባዊ በማድረግ በኅብረት ለመሥራት ስትወስኑ ነው፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ባደረገው ጥናት አብዛኞቻችሁ ያላችሁ ልዩነት መሠረታዊ እንዳልሆነ ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህም የሚያሳየው እርስበርስ ከሚያለያያችሁ ነገሮች ይልቅ ሊያስማሟችሁ የሚችሉት በርካታዎች እንደሆኑ ነው፡፡ በተለይ በአመራር ላይ ያላችሁ በተለያየ ጊዜ ከሌሎች ጋር የተከሰቱ ልዩነቶችና ግጭቶች እንዲሰፉ ምክንያት ከመሆን ይልቅ ለአገርና ሕዝብ በማሰብ ኢትዮጵያን የመታደግ ኃላፊነት ወድቆባችኋል፡፡ አገር ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም፤ እንደ ትልቅ የያዛችሁት ልዩነትና ችግርም ከንቱ ይሆናል፤ አብሮ ይከስማል፡፡
በተደጋጋሚ የሚሰማው ነጠላ ዜማ “በኢትዮጵያዊ ውስጥ ተስፋ የሚጣልበት ተቃዋሚ ፓርቲ የለም” የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ለዚህ ጥያቄ ዋንኛ ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው፡፡ ምክንያቱም በአስመሳይ ዲሞክራሲና ተግባራዊ ባልሆነ ሕገመንግሥት ሕዝባችንን ከመጠርነፍ አልፎ የፖለቲካ ፓርቲዎችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ሸብቧቸዋል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለው ፕሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር ያደረገ ለመሆኑ ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በኢህአዴግ ብቻ እያመካኙ መኖር ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው፡፡እያንዳንዱ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲ ዓላማው የኢህአዴግን መሰሪነትና አፋኝነት ለመስበክ ሳይሆን ሕዝብን ለነጻነት ማብቃት ነው፡፡ እታገለዋለሁ ከሚለው አካል መላቅ ካልቻለ ለትግል ብቁ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡
ሽንፈት ላይ እያተኮሩና የጠላትን ኃይለኛነት እየሰበኩ ድል አይገኝም፡፡ ልዩነትን እያራመዱ ኅብረትና አንድነት ተግባራዊ መሆን አይችልም፡፡ለአገራዊ ዕርቅ እንሰራለን እያሉ በፓርቲ መካከል ከዚያም በታች በግለሰብ ደረጃ መተራረቅ ካልተቻለ ብሔራዊ ዕርቅ ከቀን ቅዠት አያልፍም፡፡ እያንዳንዳችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ፣ መኢአድ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ ኦህኮ፣ አረና፣ እና ሌሎች እጅግ በርካታ ፓርቲዎች የተቋቋማችሁትና ዓላማ ያደረጋችሁት ኢህአዴግን እየተቃወማችሁ ለመኖር እንዳልሆነ የፓርቲ ፕሮግራማችሁ ይመሰክራል፡፡ ወይም ዓላማችሁ የራሳችሁን የፓርቲ ምርጫ የማድረግና ፕሬዚዳንት (ሊቀመንበር)፣ ምክትል፣ ሥራ አስፈጻሚ፣ … በመምረጥ አዙሪት ውስጥ ራሳችሁን ላለማሽከርከር እንደሆነ ከማንም በላይ ራሳችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ ከዚህ አንጻር በጥንቃቄና በብዙ ጥናት የተቀመጠው የፓርቲያችሁ ፕሮግራምና ዓላማ ለአገራችን አንዳች ለውጥ ሳያመጣ እንደዚሁ እንዳማረበት ቢቀመጥ ለሕዝብ የሚያመጣው ትርፍ ምንድርነው? እናንተንስ ለመቃወም ብቻ የምትሰሩ አያደርጋችሁምን? ለኢህአዴግና ወዳጆቹስ ጣት የሚጠቁሙበትን ዕድል እየሰጣችሁ እስከመቼ ትኖራላችሁ? ስለዚህ የእስካሁኑ በነጠላ የመጓዙ ጉዳይ ካልሰራ በኅብረት የመሥራቱ ጉዳይ የግድ ይሆናል፡፡ ይህ ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አኢጋን ያምናል፡፡
የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ካለው ግንኙነት አኳያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰበስባል፡፡ በቅርቡ አንድ ታዋቂ የምዕራቡ ዓለም የፖሊሲ አውጪ ሲናገሩ “ኢትዮጵያውያን የምዕራቡ ዓለም ነጻ ያወጣናል ብለው በጭራሽ ማመን የለባቸውም፡፡ ከውጭ የሚላከውን ዕርዳታና ድጋፍ ብናቆም እንኳን ይህ የሚሆን አይደለም፡፡ የለውጥ አራማጅና መሪ መሆን ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ናቸው እንጂ ለጋሽ መንግሥታት አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሊረዱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ የተሻለ አማራጭ በሚፈጥሩበት ጊዜ እኛ የግድ እንድንደግፋቸው ያደርጉናል” በማለት ለጋራ ንቅናቄያችን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ ንግግር በአገር ውስጥ ለምትገኙት ብቻ ሳይሆን በዳያስፖራ ለምንገኘውም ልንገነዘብ የሚገባው ሐቅ ነው፡፡ ነጻነት ከምዕራቡ ዓለም ብቻ ሳይሆን በዳያስፖራ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያንም ሊመጣ አይችልም፡፡ የነጻነታችንን ጥያቄ ተግባራዊ የሚሆነው እናንተ በአገር ውስጥ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኅብረት በመሥራት ሕዝባችንን ለለውጥ ስታስተባብሩት ብቻ ነው፡፡ እኛ ይህንን ከራሳችን ትከሻ ላይ ለማውረድና እናንተን በኃላፊነት ለመጠየቅ የምንጭነው ሳይሆን አገር ውስጥና ውጭ መሆናችን በታሪክም ይሁን በሌላ ምክንያት የተከሰተ በመሆኑ በቅንነትና በሐቅ የምንናገረው እውነታ ነው፡፡ እኛም ከአገር ውጭ ነን በማለት እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥ ሳይሆን በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ትግል የመደገፍ፣ የማገዝ፣ የምዕራባውያንን አመለካከት የማስቀየር፣ በአገር ውስጥ የሚካሄደውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የማሳወቅ፣ … ኃላፊነት እንዳለብን በመገንዘብ ነው፡፡ አኢጋን ይህንን ዓይነቱን ተግባር ሲያካሂድ የቆየ አሁንም ከአገር ውስጥ የሚመጣውን ጥያቄ ለመመለስና በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ሙሉ ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡
ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች እንደታየውና በፓርቲያችሁ ፕሮግራም ላይ እንደሰፈረው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ተወዳድራችሁ ሥልጣን የመያዝ ዓላማ እንዳላችሁ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን ማናችሁም ብትሆኑ በነጠላ ፓርቲነት ተወዳድራችሁ ሥልጣን በመያዝ ለውጥ እንደማታመጡ በግልጽ ልንነግራችሁ እንወዳለን፡፡ በምርጫ አሸነፋችሁ ቢባል እንኳን ሥልጣን የሌለው ቢሮ ከመያዝና የህወሃት/ኢህአዴግ አሻንጉሊት ከመሆን እንደማታመልጡ እሙን ነው፡፡ ይልቁንም ይህ ዓይነቱ አካሄድ ህወሃት/ኢህአዴግ በተለይም ለምዕራቡ ዓለም ለሚደሰኩረው የይስሙላ ዴሞክራሲ ማረጋገጫ ሆኖ በማቅረብ የኢህአዴግ ዕድሜ መቀጠያ መድሃኒት ነው የምትሆኑለት፡፡ ስለዚህ ከመጪው ምርጫ አኳያ ትግሉ የተናጠል ሳይሆን ፓርቲዎች በኅብረት በመሆን ኢህአዴግን በእርግጠኝነት ሊተኩ የሚችሉበት አማራጭ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በበርካታ አገሮች እንደሚታየው እናንተም በኅብረት በመሆን ኃይላችሁን አስተባብራችሁ ለሕዝባችሁ ስትሉ እርስ በርስ መጠላለፍ፣ መነቋቆር፣ መካሰስ፣ ወዘተ አሁኑኑ ማቆም ይገባችኋል፡፡ በእስራኤል፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ … በተለያዩ ጊዜያት እንደታየው ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት በመመሥረት ሕዝባቸውን ታድገዋል፣ አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያስ ይህ ሊሆን የማይቻልበት ምክንያት ምንድርነው? መልሱን መመለስ የሚገባችሁ እያንዳንዳችሁ የፓርቲ አመራሮች ናችሁ፡፡
ይህ ሳይሆን የሚቀር ከሆነ በቅርቡ የፖለቲካ ታሪካችን እንደታየው በዚህም ዘመን በተመሳሳይ መልኩ ይደገማል፡፡ በዘመነ አጼ ኃይለሥላሴ የተነሳው የህዝብ ብሶት ዳር ሳይደርስ ደርግ ለራሱ አስቀረው፡፡ በደርግ ዘመን መከራውንና ስቃዩን ያየው ሕዝብ ህወሃት/ኢህአዴግ “የሕዝብ ብሶት” የወለደኝ ነው ብሎ ሲመጣ የመከራው ዘመን ማብቂያው የደረሰ መስሎት ተስፋ አደረገ፡፡ “ብሶት” ወለደኝ ያለው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ታይቶ በማይታወቅ የዘር “ድንበር” ከፋፍሎ የሕዝባችንን ብሶት ለ23ዓመታት በየቀኑ እያበዛው ይገኛል፡፡ አሁንም ጥንቃቄ ወስዳችሁ ሁላችሁም ለሕዝባችን የሚሆን መፍትሔ የማታመጡ ከሆነ የሕዝባችን ብሶት እንዲቀጥል የምታደርጉ ብቻ ሳይሆን በመጪው ትውልድም ከመጠየቅ አታመልጡም፡፡
በቅንጅት ጊዜ ሕዝብ እጅግ ተስፋ አድርጎ ውጤት ሲጠብቅ ቅንጅቶች “መቀናጀት” አቅቷቸው ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረው የሕዝባችን ድል ገደል ገባ፤ በራሱ ተቀናጅቶ የነበረው ሕዝብ የህወሃት/ኢህአዴግ የበቀል እርምጃ ሰለባ ሆነ፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ከበርካታ ወገኖች ጋር ባለው ግንኙነት አሁንም ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል እያሉ ስጋታቸውን የሚገልጹልን ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ በአገራችን ላይ በርካታ ችግሮች የተጋፈጥን ቢሆንም ከፈጣሪ በኩል ግን ሁልጊዜ መፍትሔና የተበላሸውን የማስተካከል ዕድል አለ፡፡ ይህም ዕድል አሁን እንደሆነ አኢጋን ያምናል፡፡ ከዚህ አንጻር ጥቂት ሃሳቦችን ለማካፈል እንወዳለን፤
  1. በምንም መልኩ በኢትዮጵያ አማራጭ ፓርቲ የለም የሚለውን ተስፋ አስቆራጭ ንግግር አትቀበሉ፡፡
  2. ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብራችሁ ልትሰሩ የሚያስችላችሁን ነጥቦች ዘርዝሮ በማውጣት በሚያስማማችሁ ጉዳዮች ላይ የጋራ አስተሳሰብ ልትወስዱ የምትችሉበትን መንገድ አመቻቹ፡፡
  3. በዕቅዳችሁና ከሌሎች ጋር በጥምረት በመሆን ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቢሆን በዋንኛነት በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር የሚሰፋበትንና ዕርቅ የሚመጣበትን መንገድ ከመቀየስ ተስፋ አትቁረጡ፡፡
  4. የፓርቲ ፕሮግራምና ማኒፌስቶ ከሰማይ የወረደ፣ የማይገሰስ፣ የማይሻርና የማይለወጥ የፈጣሪ ቃል አይደለም፡፡ ስለዚህ ወደ ውኅደት በሚደረገው ጉዞ መሻሻል፣ መለወጥ፣ መስተካከል፣ የሚገባው የፕሮግራም አንቀጽ የፓርቲያችሁን ኅልውና አደጋ ላይ እስካልጣለ ድረስ ተፈጻሚ ለማድረግ ሆደሰፊ ሁኑ፡፡
  5. ከመሪዎች ጀምሮ በፓርቲያችሁ ውስጥ ውህደትን፣ ጥምረትን፣ … ተግባራዊ ለማድረግና በጋራ ለመሥራት ዕንቅፋት የሚሆኑ ግለሰቦችን በግልጽ መውቀስና እንዲታረሙ ወዲያውኑ ማድረግ ወሳኝነት ያለው ተግባር ነው፡፡ “እገሌን እንዴት እወቅሰዋለሁ” ወይም “አቶ እገሌ የፓርቲያችን የጀርባ አጥንት ነው እንዴት ተሳስተሃል እላልሁ” በሚሉ የይሉኝታ አስተሳሰቦች ለአንድ ሰው ሲባል አገርና ሕዝብ መከራና ስቃይ እንዲቀጥል መደረግ የለበትም፡፡ አገር ለመምራት ፓርቲ መሥርታችሁ ሕዝብን በይሉኝታ መንግሥት ማስተዳደር ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ለይሉኝታ በራችሁን ዝግ ይሁን፡፡
  6. ሁልጊዜ ለመምራት ሳይሆን ለመመራት ተዘጋጁ፡፡ የሰላማዊ ትግል መሪ መመሪያ ይኸው ነው፡፡ ለመመራት የተዘጋጀ መሪ ለመሆን ምንም አይቸግረውም፡፡ ከሥልጣንህም ተነሳ ሲባል ፓርቲውን አይገነጥልም ወይም “እኔ ከሞትኩ …” በሚል ጭፍን አስተሳሰብ በሕዝብ ላይ የውድመት ተግባር አይፈጽምም፡፡ ይህ ምንም የምንደባበቅበት ነገር አይደለም በተግባር ሲፈጸም የኖረ ነው፤ መስተካከልና መሻሻል የሚያስፈልገው ነው፡፡ ከመገልገል ይልቅ ለማገልገል ትሁት ሁኑ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ትክክለኛ አስተዳደር ነው እንጂ ህወሃት/ኢህአዴግን በሌላ መተካት አይደለም፡፡ ሕዝባችን ይህ ያንሰዋል እንጂ አይበዛበትም፡፡ ስለሆነም “ኢህአዴግ ይነሳ እንጂ” የሚለው ጠባብና ሰንካላ ሃሳብ የእውነተኛ ለውጥ መርህ ስላልሆነ በጭራሽ ለሕዝባችን አትመኙለት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግዲህ ወዲህ የሚያስፈልገው “ከጎሣና ዘረኝነት ይልቅ ሰብዓዊነት”የሚያብብባትና “አንዱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነጻ የወጣባትን”፤ ፍትህ፣ ሰላምና ዕርቅ የሰፈነባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያን ነው፡፡ ከዚህ ያነሰ ለውጥ በለውጥ ደረጃ ሊታሰብም ሆነ ሊታቀድ አይገባውም፡፡
እናንተ አገር ውስጥ ሆናችሁ በየጊዜው በምታደርጉት የመስዋዕትነት ተግባር የጋራ ንቅናቄያችን ከጎናችሁ ይቆማል፡፡ ሥራችሁንም በታላቅ አክብሮት ይከታተላል፡፡ የመስዋዕትነታችሁ ውጤት ፍሬ እንዲያፈራ የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በውጭ ከበርካታ ወገኖች ጋር ባለን ግንኙነት ለምትፈልጉን ሥራ በምንችለው ሁሉ ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናችን እንገልጻለን፡፡ በተለይ በዕርቅ መንገድ ላይ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚጠየቀውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኝነቱን ይገልጻል፡፡ ይህ ጉዳይ በዚህ ደብዳቤ ላይ ለፕሮቶኮል ብለን የምንናገረው እንዳልሆነ እንድትረዱልን እንፈልጋለን፡፡
አገራችን በበርካታ ድሎች ያንጸባረቀ ታሪክ ያላት ነች፡፡ ከሁሉ በበላይ የሚጠቀሰው የዓድዋ ድል በድጋሚ የሚፈጸምበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡ የዓድዋን የጦር ድል በፖለቲካው መድረክ እንድገመው፡፡ መጪውን ምርጫ ፖለቲካዊ የዓድዋ ድል የምንጎናጸፍበት እናድርገው፡፡ ነጻነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛው ራሳችን እንደ አድዋ ድል አንድ ሕዝብ ሆነን በመውጣት የራሳችን የምናደርገበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቅንነት ካለ የጦር ሜዳውን አድዋ በፖለቲካው ሜዳ ላይ መድገም ይቻላል፡፡ አንድ ሊያደርጉንና ሊያስተባብሩን የሚችሉ “ምኒልኮችን” ለመጠቀም ፈቃደኛና ቅን እንሁን፡፡
እርስበርሳችን እንደ ወንድምና እህት ለመተያየትና ለመግባባት ፈጣሪ ቅን ልብ ይስጠን፡፡ እናንተንም ለፍትሕ፣ ለነጻነት፣ ለሰብዓዊነት፣ ለፍቅርና ዕርቅ ስትታገሉ ማስተዋልንና ጥበብን ይስጣችሁ፡፡
ከአክብሮት ጋር ለአገራችን ፈውስ እንዲመጣ የትግል አጋራችሁ፤
ኦባንግ ሜቶ
ዋና ዳይሬክተር፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡