Wednesday, November 27, 2013

ሀገራዊ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔን ማስወገድ


November 18, 2013
በዳዊት መላኩ (ከጀርመን)
ኢትዮጵያውያን የወያኔ ባናዳዎች ባፈሙዝ ሀይል ስልጣን ላይ ከወጡበት እለት አንስቶ በርካቶች ለስደት፤ለእስራት፤ለሞት እና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡የሰሃራን በረሃ አቋርጠው ለማለፍ ሲሞክሩ የበረሃ እራት ሁነዋል፡፡ሌሎች ደግሞ ኩላሊታቸው ሳይቀር እየተዘረፉ ለከፋ አካላዊ እና አእምፘዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡በባህር ሲያቋርጡ የተሳፈሩበት ጀልባ በሞገድ እየተመታ በብዙ ሺ የሚቆጠሩት ለዓሳ እራት ሁነዋል፡፡በታንዛኒያ እና በኡጋንዳ ሲያልፉ በኮንቴነር ታፍነው የሞቱትን ቤት ያቁጠራቸው፡፡ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን የመን ውስጥ ተጠልፎ በውስጡ የነበሩት የአየር መንገዱ ሰራተኞች እና ተሳፋሪዎች ባሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ይህ ሁሉ ህይወት እንደቅጠል ሲረግፍ የወያኔ ባለስልጣኞች አንድም ቀን ብለው የተጎዱ ቤተሰቦችን አጽናንተው አሰከሬናቸው በክብር እንዲያርፍ አላደረጉም፡፡በሰው ሰራሽ አደጋ ለሞቱትም ጥፋተኞችን ለፍርድ ለመቅረብ ተንቀሳቅሰው አያውቁም፡፡ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድም ዳግም ስህተቶች እንዳይፈጸሙ ስምምነቶችን ተፈራርመው ያውቁም፡፡በየሀገራቱ የሰገሰጉዋቸው ዲፕሎማት ተብየዎችም ቤተሰባቸውን እንዴት አንደላቀው እንደሚያኖሩ ፤ከነማን ጋር የንግድ ሽርክና እንደሚፈራረሙ እንጂ በስደት ለሚንገላታው ዜጋቸው መብት ተከራክረው ፡ የሀገሪቱን ጥቅም ለማስጠቀም አንዳች ስራ ሰርተው አያውቁም፡፡
ዲፒሎማቶች ከሙያ ብቃት ጀምሮ ህዝባዊ ወገንተኝነትም ስለሚጎድላቸው የፓርቲውን ህልውና ለማስጠበቅ ካልሆነ በስተቀር ለህዝብ የሚጠቅም ስራ ይሰራሉ ብሎ መገመት ያዳግታል፡፡የወያኔ ዲፕሎማቶች በውጪ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ ከላይ በሚሰጣቸው መመሪያ መሰረት ብዙ የመከፋፈል ስራዎችን ሲሰሩ እነደቆዩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ዛሬ በ40/60 የኮንደሚኒየም እና በዓባይ ግድብ ግንባታ ሰበብ በውጪ ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ዶላር ለመሰብሰብ ደፋ ቀና የሚሉት ዲፕሎማቶች ለይስሙላ ያክል እንኳን አንድም ቃል መተንፈስ አልቻሉም፡፡
በወያኔዎች ዘንድ ብሔራዊ የሀዘን ቀን የሚታወጀው እና ህዝቡ በግዳጅ እየወጣ የመንግስት አገልግሎች መስጫ ድርጅቶች ሳይቀሩ ለሁለት ሳምንተ ያልክ ተዘግተው ስራቸው ሀዘን ብቻ እንዲሆን መመሪያ የሚተላለፈው የስልጣን እና የጥቅም አጋራቸው ሲሞት እንጂ ሌላው ተራ ዜጋ እማ ሞቱን እንኩዋን የሚዘግበለት የሀገሩ የመገኛኛ ብዙሀን የለውም፡፡ ግብር የሚከፍልበት ቴሌቭዥን እንዲህ ያሉ ዜናዎችን ለህዝቡ እንዳያቀርብ እነሽመልስ ከማል አፉን ጥርቅም አድርገው ይዘውታል፡፡የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሜዲያዎች የዘገቡትን እውነት በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የሀገሪቱ ቴሌቭዥን የቁጥር ጨዋታ ያዟል፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተብየው ዶ/ር ቴወድሮስ አድሀኖም ችግሩ ተጋኖ ቀረበ ነው ሲሉ ተዘባበተውብናል፡፡
ሀገሪቱን እመራለሁ ብሎ የተቀመጠ ሀይል እንዴት እንዲህ ሀገራዊ ውርደት ሊያከናነብ ቻለ? መልሱ ቀላል ነው፡፡ መጀመሪያም ወያኔዎች ከሆዳቸው ባለፈ ሀገር እና ህዝብ ብሎ ነገር አይገባቸውም፡፡አሰራ ሰባት ዓመት ተዋጋንለት የሚሉትም የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት እንጂ ለህዝብ የሚጠቅም አንዳች ሀገራዊ አጀንዳ ኑፘቸው አደለም፡፡የወያኔዎች
ዋነኛ መገለጫቸው እና ግባቸው ሀገራዊ ውርደት ማሰፈን ነው፡፡ ይሕን ደግሞ ባለፉት አመታት ሁላችንም በደንብ የምናውቀው ነው፡፡ለግራዚያኔ ሀውልት ማቆምን የተቃወሙ ህዝቦችን አስረዋል፡፡ሰላማዊ ሰልፉን በትነዋል፡፡የሀገሪቱን ቅርስ እና ታሪክ በማወደም ታረክ- አልቫ አድርገዋል፡፡የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም በተደጋጋሚ ለባእዳን አሳልፎው ሰጥተዋል፡፡አርሶ አደሮችን እያፈናቀሉ ለም መሬታችንን በርካሽ ዋጋ ሲቸበችቡት ቆይተዋል፡፡ዳር ድንበራችንን ለሱዳን አሳልፎው ሰጥተዋል፡፡በሰላም ማሰከበር ስም ወታደሮች በሶማሊያ መንገድ አስክሬናቸው እንዲበተን አድረገዋል፡፡ዜጎች እምነታቸውን በነፃነት እንዳያመልኩ አድርገዋል፡፡ሌላው እና መሰረታዊው ነገር ራሱ ወያኔ ዜጎችን አደህይቶ፤አደንቁሮ፤አዋርዶ መግዛት የአስተዳደር ስትራቴጅው ዋነኛ ማጠንጠኛው ነው፡፡
በሰሞኑ ያየነውም በአረብ ሀገራት የያኔን አንባገነን ስርዓት ሸሽተው የተሰደዱ ዜጎች በሳዉዲ ወሮበላ ፖሊሶች እንደ በግ ሲታረዱ ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝቡን በማስተባበር ሐገራዊ ውርደት እንዲያቆም፤በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ ፤አሰገድዶ መድፈር እና እንግልት እንዲቆም በሰላማዊ መንገድ ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡ የወገን ተቆርቋሪ ዜጎችን በፌዴራል ፖሊስ ማስቀጥቀጥ፤የፓርቲውን አመራሮች ማሰር የወያኔ ብሄራዊ ውርደት ለፍተኛው ማሳያ ነው፡፡ሰማያዊ ፓርቲ የሰራው መንግስት ሊሰራው የሚገባውን የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ስራ ነው፡፡
ምን እናድርግ?
የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ምንጭ ወያኔ ነው!ስለዚህ መፍትሄውም የችግሩን ምንጪ ከመሰረቱ ማድረቅ ነው፡፡ወያኔን ለማሰወገድ ደግሞ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሀዘናችንን አቁመን በልበ ሙሉነት ለዚህ ሀገራዊ ውርደት የዳረገንን አንባገነናዊ ስርዓት ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ዛሬ በሳውዲ ማጎሪያ ክምፕ ያለኸውም ሀገርህ ብትገባም ሊያስኖርህ የሚችል መንግስት አደለም ሀገሪቱን የሚመራት፡፡ያው ከመውጣትክ በፊት የምታውቀው በአንድ ዘር የበላይነት የተገነባው አብዛኛው ጾም የሚያድርበት ተቂቶች በብዙሀኑ ደም የሚንደላቀቁበት ነው፡፡ገብተህ ድምጽህን የምታሰማበት ምንም መንገድ የለህም፡፡ምናልባትም የሚጠብቅህ ሰበብ ተፈልጎ ቃሊቲ መወርወር ሊሆንም ይችላል፡፡ስለዚህ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የነፃነት ታጋዮችን በመቀላቀል ነፃነታችንን፤የተዋረደው ክብራችንን ፤በአለም አደባባይ የጎደፈው ስማችንን በጋራ ማደስ ይኖርብናል፡፡ እግዚያብሄር አምላክ የሞቱት እህት እና ወንዶሞቻችን ነፍስ በገነት ያሳርፍልን፡፡የጠላቶቻችንን ልብ ያራራልን፡፡
ሞት ረግጠው ለሚገዙን አንባገንን መሪዎች !ድል የነፃነትን ብርሀን ለመፈንጠቅ በየበረሀው ለምትንከራተቱ የቁርጥ ቀን ልጆች!
ፀሀፊውን ለማጋኘት fredom.ethiopia@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

በሽብርተንነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!


November 26, 2013
ከቅዱስ ዬሃንስ
ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ሁለት ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡ አንደኛ በፀረ- ሽብርተኝነት ስም ከምዕራባውያን ኃያላን ጎን በአጋርነት በመቆማቸው በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት (ለምሳሌ በመሣሪያ፣ በፖለቲካ ድጋፍ) ዳጎስ ያለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም የሚያወጡት ሕግ የውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ሽፋን ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ነው ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ከሰማይ የወረደ የተቀናቃኝ ማጥቂያ መሣሪያ ነው የሚባለው፡፡ ይህንን ያልኩበት አብይ ጉዳይ ዛሬ ሃገራችንንና ህዝቧን እያስጨነቀ ያለው የወያኔ አገዛዝ የፀረ ሽብርተኝነት ህግን ከለላ በማድረግ በሰላማዊ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣ፤ እጅግ የከፋ ደረጃ በመድረሱ ነው።
በሰላማዊ ትግል ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ለዉጥ ለማምጣት የሚታገሉ ሰላማዊ ዜጎችን አግባብ ባልሆነና ባልተጨበጠ ክስና ዉንጀላ ማሰር፣ አፍኖ መሰወር፣ ንብረትን ማዉደምና መዉረስ እንዲሁም የአደባባይ ግድያ ባለፉት 22 የወያኔ  የአገዛዝ ዘመናት የተለመዱ ተግባሮች ሆነዉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ይህ አምባገነናዊና ኢፍትሀዊ ተግባር በህግ ሽፋን ተጠናክሮ ቀጥሏል። ለገዥዉ ስርአት የአፈናና የጥርነፋ መዋቅር ተባባሪ ያልሆኑና ለመብታቸዉ መከበር የሚታገሉ ዜጎች በአሸባሪነት ስም በጅምላ እየታፈሱና እየታሰሩ ይገኛሉ። ታፍነዉ የተወሰዱና ያሉበት ቦታ የማይታወቀዉም ጥቂቶች አይደሉም። ባለፉት ጥቂት አመታት ብቻ በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሽብርተኝነት ተወንጅለዉ ታስረዋል። ሰብአዊ መብታቸዉም በማንአለብኝነት እየተረገጠ ይገኛል። ከነዚህ ንፁሀን ዜጎች ዉስጥ ብዙዎቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላቶች፤ የእምነት መሪዎችና ለሞያቸዉ ታማኝ የሆኑ ጋዜጠኞች መሆናቸዉን ስናይ ደግሞ ዘመቻዉ በሀገራችን ተጠናክሮ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል ለመጨፍለቅና ህዝብን ከትክክለኛ መረጃ አርቆና አፍኖ ለመግዛት ታስቦበትና ሆነ ተብሎ የተያዘ ስልት መሆኑን ግልፅ ነው።
በሽብርትኝነት ያለመከሰስ መብቱን በጠመንጃ ያስከበረው ወያኔ ግን ሰላማዊውን ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች  እያሸበረ የስልጣን ቆይታውን ለማርዘም ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። ዜጐችን በማፈናቀል፤ በእምነት ውስጥ ጣልቃ በመግባትና የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በመከፋፈል እያፋጀ የሽብር ሴራውን እየፈፀመ ይገኛል። ሰላማዊ ዜጋውን ፣አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን በልማት ስም ተወልዶ ባደገበት እትብቱ ከተቀበረበት ሃገር እያፈናቀለ ለስደት እየዳረገው ይገኛል፡፡ ለዚህም የሽብር ሴራው ሰለባ የሆኑት፤ የሚበሉት፤ የሚጠጡት እና በመጠለያ እጦት በየአደባባዩ ሰፍረው የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ የሚገኙት የአማራ ብሔረሰብ ወገኖቻችን ናቸው፤ እነዚህ ወገኖቻችን በሃገሪቱ አራቱም ማዕዘናት እየተፈናቀሉና እየተዋከቡ ይገኛሉ። ማፈናቀለ አልበቃ ያለው የወያኔ የሽብር መረብ ወደ እምነት ቦታዎችም በመዛመት ዋልድባን እና የተለያዩ የሃይማኖት ቦታዎችን በማፈራረስ በአለም ደረጃ እውቅና እና አድናቆት የተሰጣቸውን የሃገሪቱን የሃይማኖት፤ የታሪክ ቅርሶች በማውደም፤ ኢትዮጵያውያን በቀደምትነት በምንታወቅበት እምነታችን ላይ አደጋ በመፍጠር፤ አዋራጅ ድርጊቶችን በንቀት እና በጥላቻ እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ ከእምነት ቦታዎች ባሻገር በአለም ደረጃ እውቅናን ካገኙት ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ ተጠቃሹ የታችኛው አዋሽ እና ኦሞ ሸለቆዎች አንዱ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ቦታ ያራዊቶች እና የተለያዩ የደኖች ስብስብ ያለበት ሰፊ የሃገራችን ቅርስ የነበረው ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ወያኔዎች በልማት ስም ለውጭ ባለሃብቶች አስረክበውት ድብዛው እየጠፋ ነው፡፡ አምባገነኑ ወያኔ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ያነሱትን የመብት ጥያቄ ወደ ጎን በመተው በእኔ አውቅላችኋለሁ እብሪት የተሞላ አስተሳሰብ በማፈን ንፁሃኑን ሙስሊም እየገደሉ ብሎም በሽብርተኝነት በመወንጀል እያሰቃዩት ይገኛሉ። ሙስሊሙ ህብረተሰብ የተቃውሞ ድምፁን ያሰማበትን አላማ ምንድነው? ችግሩስ ከምን የመነጨ ነው? ብሎ እልባት ከመስጠት ይልቅ ጥያቄአቸውን በማንቋሸሽ እና በማጥላላት በጠመንጃ አፈ ሙዝ የሚመልሱት ይመስል ህዝበሙስሊሙን ለከፋ መከራና ስቃይ ዳርገውታል። ለዚህ ድርጊታቸው ደግሞ ሚስጥሩ ንፁሃኑ ህዝበ ሙስሊም ላይ የሃሰት ታርጋ በመለጠፍ አሸባሪነትንና አክራሪነትን እየተዋጋው ነው በሚል የማስመሰልና የማታለል ስራው የምዕራባውያን ሃገራትንና የአሜሪካ ቀልብ ለመሳብና እርዳታ ለማጋበስ ነው። ቢያውቁት ግን ይህ ድርጊታቸው አውሬ እንጅ ሰው አለመሆናቸውን ቁልጭ አድርጐ ያሳያል። ለገንዘብ ሲባል ሰውን ያክል ፍጡር መግደል፤ ማሰርና ማሰቃየት ከአንድ ሰው የሆነ ሰብአዊ ፍጡር አይጠበቅምና።
ሌላው ወያኔዎች 22 ዓመታት በጠመንጃ ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ ሲጠነስሱት የነበረው ሽብር የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በመከፋፈልና በማፋጀት የኢትዮጵያን ህልውና አንድነትን፣ ማንነትን በማናወጥ፤ የስልጣን እድሜያቸውን ማርዘም ነው። ይህ ስራቸው ከምን ጊዜውም በላይ በአሁኑ ሰአት እያፋፋሙትና፤ ሰላማዊውን ህዝብ በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት በማጋጨት የሽብር ሴራቸውን እያስፋፉ ይገኛሉ። ዳሩ ግን ለወያኔዎች ህዝብን መከፋፈል የሚበጅ ቢመስላቸውም የዚህ የሽብር ድራማቸው ተጠቂዎች ግን በፍፁም ልንሆን አልቻልንም፤ ወደፊትም ልንሆን አንችልምም። ምክንያቱም መቻቻል እና በፍቅር አብሮ መኖር መለዬ ባህላችንን በፍፁም ይህ ሰይጣናዊ ድርጊታቸው ሊያመክነው ስለማይችል ነው። ይህንን አንድነታችንን፤ ፍቅራችንን የመቻቻል ባህላችንን የበለጠ በማጎልበት፤ ባህላችንን፣ አንድነታችንን፣ ሃይማኖታችንን እየተፈታተነ ያለው የወያኔን የሽብር ስልት በማክሸፍ፤ ለበለጠ ድል እስክንበቃ ትግላችንን ማጠናከር ይኖርብናል።
በመጨረሻም የወያኔ ባለስልጣናት በፈረጠመ አምባገነናዊ ክንድ ህዝብን በማሸበርና በማፈን የስልጣን ዘመንን ለማራዘም መሞከር አወዳደቅን ማክፋት መሆኑን ካለፉት አምባገነናዊ ስርአቶች ሊማሩ ይገባል! አሁንም በድጋሚ ወያኔዎች ጠንቅቀው ሊያውቁት የሚገባ እውነት የኢትዮጵያ ህዝብ ሽብኝነትን በጽናትና በቁርጠኝነት ይቃወማል፤ ያወግዛልም፡፡ በፀረ -ሽብርተኝነት ሽፋን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እየጣሰ ያለውን የወያኔ አገዛዝንም በተመሳሳይ ጽናትና ቁርጠኝነት ይቃወማል፤ ይታገላልም!!!
ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ! 
ያለዎትን አስተያየት በፀሃፊው አድራሻ: kiduszethiopia@gmail.com ይላኩ።

Tuesday, November 26, 2013

ተዋርደን አንቀርም!! ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር) November 26, 2013


November 26, 2013
ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰች ያለውን ግፍና በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ፓርቲያችን በወሰነው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀን ነበር፡፡መቸም ህዝባችን በጭቆና ውስጥ ስለኖረ በመብቱና በግዴታው መሀል ያለውን ድንበር በውል ካለመረዳቱ የተነሳ ሰልፉ እንዲደረግ ስለመፈቀዱ በተደጋጋሚ ስንጠየቅ ነበር፡፡ህጉ የሚለው ግን ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡በተቃራኒው መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ በእለቱ ለሰላማዊ ሰልፉ የደህንነት ከለላ መስጠት የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው ሰልፉን ለጠራው አካል ችግሩን ገልጾ ቀኑ እንዲተላለፍለት ይጠይቃል፡፡በመሆኑም ይህን መሰል ጥያቄ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ለፓርቲያችን ባለመቅረቡ በሙሉ ልብ ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ተያያዝን፡፡Interview Eng. Yilkal Getnet
ሁሌም ቢሆን መንግስት ሰበብ ፈልጎ ሊወነጅለንና ከመስመር ሊያስወጣን እንደሚፈልግ በሚገባ እናውቃለንና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ባሳወቅን በአስራ ሁለት ሰአታት ውስጥ ምላሽ ስላልመጣ ሙሉ በሙሉ ህጋዊነታችንን አረጋግጠናል ማለት ነው፣እነሱ ደግሞ ጠብ-መንጃ በእጃቸው አለና የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል ለሚዲያወች የሰጡትን ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላና ሰበብ አዳምጨዋለው፡፡ “ሰላማዊ ሰልፉን ያገድንበት ምክንያት ጸረ-አረብ መፈክሮች ስለነበሩ ነው“ብለዋል፡፡መጀመሪያ ደረጃ ሰልፉ ገና ከግቢው ፈቅ ሳይል ነው ያፈኑት፣ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ በአንድ እየሆንን ወደ ሰላማዊ ሰልፉ መዳረሻ ለመሄድ ስንሞክር የተወሰኑ አመራሮችን አራት ኪሎ አካባቢ ያዙን፣እነሱ ቀድሞውኑ ሰልፉ እንዳይካሄድ ስለወሰኑ ነው እንጅ ትንሽ እንኳ ተንቀሳቅሶ የሰልፉን ባህሪ ለመገምገም ምንም እድል አልሰጡንም፡፡
ለምሳሌ ሰልፉን እንደምናደርግ ይፋ ባደረግን ማግስት ከራዲዮ ፋና ተደውሎ አንዳንድ ጥያቄዎች ተጠይቄ ነበር፡፡በቃለ-መጠይቁ ሰላማው ሰልፉ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም እንደምናደርግ ተናግረናል፡፡ጋዜጠኛው ለሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መልዕክት ካለ ብሎ በጠየቀኝ ወቅት የሳውዲ አረቢያ ሰንደቅ አላማ ላይ ያለው ምልክትና ጽሁፍ ሀይማኖትን የሚመለከት በመሆኑ ዜጎች በስሜታዊነት ባንዲራ እንዳያቃጥሉ፣እነሱ ቢያዋርዱንም እኛ ግን ክብር ያለን ዜጎች ስለሆንን ተቃውሟችንን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እንዳለብን ተናግሬ ነበር፡፡ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በዚህና በተለያየ መንገድ በማያሻማ ሁኔታ መልዕክት ባስተላልፍም እነሱ ግን ይህን በመቁረጥ አላስተላለፉትም፡፡እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ የአቶ ሽመልስ ከማል ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
ሁለተኛ የአንድ ሀገር መንግስት ዜጎቹ እየተደፈሩ፣በማጎሪያ ካምፕ በረሀብና በውሃ ጥም፣ሌላው ቢቀር መጸዳጃ ቤት እንኳ ተከልክለው ፍጹም ከሰውነት ክብራቸው ወርደው እየተበደሉ፣እየተገደሉ ባለበት ወቅት ገና ለገና ተቃዋሚ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በሚንጸባረቅ ጥላቻና ተቃውሞ የዲፕሎማሲ ግንኙነቴ ይበላሽብኛል ብለን መናገር እንችላለን?ሌላው ይቅር አንድ ክፉና ደጉን የለየ ሰው የሚያስበው ጤነኛ ሃሳብ ነው ማለትስ ይቻላል?
ከእገዳው ባሻገር የሚደንቀው ነገር ደግሞ በፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ላይ የተደረገው ድብደባ ነው፣የሆነ ማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ያለ ይመስላል፡፡የጭካኔያቸውን መጠን እንድናውቅ የሚደበድቡት አቅመ-ደካሞችን፣ሽማግሌወችንና ሴቶችን እየመረጡ በፍጹም አረመኔነት ነበር፡፡ይህን ተግባራቸውን ስመለከት የደረሱበትን የዝቅጠት ደረጃ መታዘብ ችያለው፡፡ከፖለቲካ ልዩነትም፣ከአምባገነንነትም በላይ ሰወቹ እንደታመሙ ነው ለመረዳት የቻልኩት፣ስር የሰደደ የቁስ ሰቀቀንና የስልጣን ጥም የተጣባቸው፣ለዚያ ሲሉም የትኛውንም አይነት ውርደት ለመቀበል የቆረጡና የሞራል ልዕልናቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ሰዎች ናቸው፡፡ስነ-ልቦናቸው ክፉኛ ተቃውሷል እንጂ ሀገር እመራለው የሚል ቡድን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈጽማል ለማለት እቸገራለው፡፡በአባላቶቻችን ላይ ክፍኛ ድብደባ ተፈጽሟል፣እስከዛሬም እግሮቻቸው መራመድ የማያስችላቸው፣የሚያነክሱ ሰዎች አሉ፡፡እውነት ለመናገር ይሄ እብደት ነው፡፡አንዲት እራሷን መከላከል የማትችል ሴትን ለሶስት መደብደብን ከዚህ በተሸለ ልገልጸው አልችልም፡፡
አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር ለኛ ዋነው ጉዳይ የዜጎቹ ህጋዊነት ወይም ህጋዊ ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡በምንም አይነት መንገድ ሴቶች እየተደፈሩ፣ወንዶች በየስርቻው እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው እየተገደሉ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ታጉረው ይህን ሁሉ መከራ መቀበላቸውን ልንታገሰው፣ወይም ከህጋዊነት አንጻር እየተራቀቅን ልንመለከተው አንችልም፣ስለ ህግም ከተወራ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ጭፍጨፋው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ላይ ጭምር ሲፈጸም እንደነበር አምኗል፡፡
ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የአንዱ ሀገር ዜጋ ካለ ሀገሩ መገኘት አገር ይያዝ የሚያስብል አይደለም፡፡መውጣት ካለባቸው ጊዜ በመስጠት፣ከመንግስታቸው ጋር በመነጋገር በዘዴ ነገሩን መከዎን እየተቻለ አንድ ሀገርና መንግስት በሰዎች ላይ እንዲህ የጭካኔ ጥግ የሆነን አቋም ይዘው መንቀሳቀሳቸው ፍጹም ኢ-ሰብአዊነት ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ አስከፊ ጊዜ የለም፣እውነቱን ለመናገር ለአገዛዙ ሰዎች የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋም አፈር ተደፍቶባታል፣እንዲህ ግልጽ የሆነ ጭፍጨፋ እየደረሰብን እንኳ በድፍረት ለመናገር አልፈለጉም፡፡ስለ ኢትዮጵያውያን መገደል ለማውራት ሲፈልጉ ሌላ ሀገር ይጠቅሱና እነሱም እኮ እየተገደሉ ነው ይላሉ፣ወገን ከምንለው የማህበረሰባችን አካል ይሄን መስማቱ ከጥቃቱ ይበልጥ ያማል፡፡
ለምሳሌ ኢቲቪ ስጉዳዩ ሲያወራ ህገ ውጥ ሊባል የሚችል ድርጊት ተፈጽሟል በማለት ነው፡፡ተመልከቱ! እንዴት ያለ ባዕድነት ነው?ኢትዮጵያውያን በድህነትም ውስጥ እንኳ ለክብራችን የመሞት ባህሪ አለን፣ይሄ ከቀደሙት አንጡራ ኢትዮጵያውያን የወረስነውና ዛሬም ያለን ሀብታችን ነው፡፡
ትናንት ፍየል ጠባቂ የነበረ በረኸኛ ይህን ክብራችንን ገፍፎ እንደውሻ ቀጥቅጦ ስርቻ ሲጥለን ያልተቆጣ መንግስት ኢትዮጵያዊ ነው?ከዜጎቹ የወጣና ለህዝቡ የቆመ እውነተኛ መንግስት ከዚህ የበለጠ የሚቆጣበት ጉዳይ ከወዴት ይመጣል? እውነተኛ መንግስት ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሳውዲ ካምፓኒዎችን በሰአታት ውስጥ ማባረር፣ኢምባሲውን ዘግቶ አምባሳደሩን ማሰናበትን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር፡፡የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፣የድፕሎማሲ ግንኙነቴ ሊበላሽ ይችላል ብሎ እኛ ድምጻችን እንዳናሰማ ደበደበን፣አፈነን፡፡በግልጽ እንደሚታየው የጥቅም ትስስሩ ነው አፋቸውን ያዘጋቸው፣ይህች ጥቅማቸው እንዳትቋረጥ በዜጎች ህይዎት መደራደርን መርጠዋል፡፡
ስነ ልቦናቸው የተቃወሰ በመሆኑና ተራ ስስታሞች በመሆናቸው እንጂ ኢንቨስትመንትም ሆነ ዲፕሎማሲ ግብአትነታቸው ለሰው ልጅ ነው፣እንደ አህያ ሲያፈጋ ከርሞ ሬሳቸውን ለላከ መንግስት እንዴት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመመለስ ይገዳል?እንዴት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታሪካዊትና ለአፍሪካ የነጻነትና የኩራት ተምሳሌት የሆነች ሀገርን እየመሩ እንዴት ትናንት የነዳጅ ዘይት ባቆማቸው እረኞች ስትዋረድ ዝም ይላሉ?!::
እንዴት!በዜጎች ህይወት የተደራደረው አገዛዝ ማለፉ አይቀርም፣ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ታሪክ ለመጥቀስ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግኝም፡፡የቅርብ የሰሜን አፍሪካ አምባገነኖች የከፋ ፍጻሜ አለና፡፡ኢትዮጵያውያን ፍቅርም ጸብም እናውቃለን፣ሳውዲወችም የፈጸሙትን ግፍ ማወራረዳቸው አይቀርም፡፡በዚህ ክፉ ጊዜ ስለስብአዊ መብት ቆመናል የሚሉ አለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው እውነተኝነታቸውን ለመመርመር ጥሩ እድል ይሰጠናል፡፡
መንግስት ቢኖረን ኖሮ ይሄ ሁሉ ውርደት ይፈጸምብን ነበር ብየ አላስብም፡፡በዚህ ሰአት ርዕሰ-መንግስት ብሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ድርጅት እንደመሆኑ፣ወደየትኛውም ሀገር የሚደረገውን ጉዞ አቋርጨ ዜጎቸን ማስወጣትን አስቀድም ነበር፡፡ያሄ ጥቂት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊያመጣብን ቢችልም ከከፋው የዜጎች ስቃይ ጋር ግን በአንድ ሚዛን ላይ አይቀመጥም፡፡የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል ድርጅት አለ፡፡በዜጎቻችን ላይ ጎርፍና ድርቅ ሲመጣ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው? ይሄም ሰው ሰራሽ አደጋ ነው ሙሉ ሀይሉን ወደዚህ አዙሮ ሊንቀሳቀስ ይገባው ነበር፡፡
እርግጥ ነው ባቀድነው መሰረት ሰላማዊ ሰልፉ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ጩኸቱ ግን ይቀጥላል……ባለን አቅም ሁሉ አፈናውንም፣ወከባውንም ተቋቁመን ለዜጎቻችንና ለኢትዮጵያዊነት እንታገላለን፡፡
አገዛዙ ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያፍን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድ መልእክት አስተላልፏል፣ይህን መልእክት እንዲያስትላልፍ ማስገደዳችንም ለኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡የሳውዲ መንግስት ያሻውን ያደርግ ዘንድ የፈቀድኩት እኔ ነኝ፣በመሆኑም እሱን በመቃወም ግንኙነቴን አታበላሹ ብሎ እርምጃ በመውሰዱ ህዝቡ የነገሩ ቁልፍ የት እንዳለ፣የአጥቂወቹ በራስ መተማመን ምን ላይ እንደቆመ በጠራ ሁኔታ ለመመልከት እንዲችል ሆኗል፡፡
ይሄ ሁሉ ነገር እየተፈጸመ የተስተዋለ አንድ ነገር አለ፡፡የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታ እውነተኛ ማንነታቸው፣እውነተኛ በአገዛዙ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ያሳየን ክስተት ነው፡፡እንደሚታወቀው እሳቸው በኢህአዲግ እንጂ በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጡ አይደሉም፡፡ኢህአዲግ የሚናገረው ከሌለ እርሳቸው የሚሉት አይኖርም፡፡እንደ አንድ ሀገርና ህዝብ መሪ ግን የመኮነንም ሆነ የማጽናናት ቃል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
ባሉበት ቦታ ያስቀመጣቸው ህወሀት ነው፤ድርጅቱ ደግሞ ይሄን አቋም አልወሰደም፡፡ስለዚህ እንደሚቆጣቸው ስለሚያውቁ ዝምታን መረጡ፣ቸልታንም አስበለጡ፡፡በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ በላይ ሽንፈት ያለ አይመስለኝም፡፡
(ይህ ጽሁፍ በፋክት መጽሄት ተስተናግዷል፣ነገር ግን መጽሄቱ ላልደረሳቸው ሰዎች ይደርስ ዘንድ እዚህ ለማስተናገድ ወደድኩ፡፡)

Friday, November 15, 2013

በሳዑዲ አረብያ የመከራ ማጥ ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን ሲባል ፈጥነን እንነሳ!


November 11, 2013
ዳኛቸው ቢያድግልኝ
እንደ ሰው አንድ የሚያደርገን ባሕርይ፣ እንደ ኢትዮጵያዊነትም ሁላችንንም የሚመለከተንና የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት የማይነጣጥለው በደል በሳዑዲ አረብያ ግዛት እየተፈጸመ ነው። የጥቃት ዒላማዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የጥቃቱ ልክ የለሽነትና አሰቃቂነት ደግሞ ይበልጥ የጎላው በሴት እህቶቻችን ላይ ነው። ይህ ዛሬ በሳዑዲ አረብያ የሚደረገው ጥቃትን ማስቆምና ቁጣችን መቆምያ እንደማይኖረው ማሳየት ለነርሱ ብቻ ሳይሆን ለራሳችን ደህንነትም ጭምር የምናደርገው ነው። ምክንያቱም ነገ ተመሳሳይ ጥቃትና በደል በመላው አለም ይስፋፋል። በአፍሪካ ሀገሮች የተበተኑ ኢትዮጵያን ከሶማሌና ኤርትራ ከሚሰደዱት በተለየ ይዘረፋሉ፣ ይደፈራሉ ይዋረዳሉ። እንደ አገር ልጅ አብረው እንዳይቆሙ በዘር በሀይማኖትና በፖለቲካ አቋም ምክንየት የተበተኑ ናቸው። ለሰላሳና አርባ አመት አምባገነኖች ያደረጉት ጭፈጨፋና በደል ፍርሃትን ሰማይ ጥግ አውጥቶታል። እናም ኢትዮጵያዊ በየተበተነበት ሁሉ ተኛ ሲሉት የሚተኛ አውልቅ ሲሉት እርቃኑን የሚቆም ፈሪ እንዲሆን ተደርጓል። ሲቸግረው የሚጮኸውን ያህል ሲመቸው ለወገን የሚደርሰው ጥቂቱ ነው። ይህ ሊቀጥል አይገባም!Protest at Saudi Arabia Mission to United Nations!
ቀደም ባለው ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ ጥቃት ቢደርስበት ባገኘው መሳርያ ዘነጣጥሎም ቢሆን ይገድል ስለነበር ማንም አይደፍረውም ነበር። በዘመነ ኮሎኒያሊዝም ኢትዮጵያውያን በሄዱበት ሁሉ አንገት የማይደፉና ክብራቸውን የማያስነኩ ነበሩ። ዛሬ ጠቁመው የሚያስይዙ፣ ወገናቸውን የሚያሻሽጡና የሚሰልሉት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የዚህ ጽሁፍ መነሻም ሆነ መድረሻው የድሮውን አሁን እየሆነ ካለው ጋር ማወዳደር አይደለም። ለዚህ የሚሆን የቅንጦት ጊዜም የለንም። ዓላማው አሁን እየደረሰብን ያለውን በደል በቁርጠኛነት አንታገለው ነው። ይህ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ከዳር እስከዳር ማስነሳት ካልቻለና ቁጣቸውንም ለመላው አለም ማሳየት ካልቻለ እውነትም አገራችን እያበቃላት ነው ማለት ይቻላል።
የዱር አውሬ እንኳን ከዚህ የተሻለ ክብር አለው። እነዚህ አጅግ ሁዋላ ቀር የሆኑ አረመኔዎች ከእንስሳ እንኳን አንሰው አንዲት በፍርሃት ነብሷን የሳተችን ሴት አስር ሆነው የሚደፍሩትን እያየን የተደፈሩት ህጋዊ ናቸው ህገወጥ የሚል የሕግ አንቀጽ መረጣ ውስጥ ልንገባስ እንዴት ይቻለናል? በመላው አለም ያለ የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ሊደረግና የሳዑዲ ወሮበሎች በወጣት ሴቶች ላይ እያደረሱ ያለው ግፍ በመረጃም ተደገፎ በበራሪ ወረቀትም ተዘጋጅቶ ለአለም ሕዝብ ሊበተን ይገባዋል። ተፈጥሮ ዘይትን ስትቸራቸው አእምሮ ግን እንደነፈገቻቸው ከዚህ በላይ መረጃስ ከየት ይመጣል?
እንደ ትውስታ ከወሰድነው በኬንያ ያሉ ስደተኞች ላይ በደል ይደርስ በነበረበት ወቅት ያ በጨካኝነቱ የሚታወቀው መንግሥሰቱ ሀይለማርያም አንኳን “ኢትዮጵያውያኑ የተሰደዱት የምናራምደውን ፖለቲካ እንጂ ሀገራቸውን ጠልተው አይደለም…” በሚል ኬንያን ማስጠንቀቁን መስማቴ ትዝ ይለኛል። በየወሩ 40 ሺህ ሴቶችን እንልካለን እያለ እንደ እንቁላል በየአረብ ቤቱ ሲያከፋፍል የነበረው መንግስት ዛሬ ዜጎቹ እንዳይሆን መጫወቻ ሲሆኑ ዝም ብሎ መመልከቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። ኢትዮጵያውያኑ ምናልባትም ኤምባሲውን ራሱን መቆጣጠር የሚገባቸው እስኪመስል ያስቆጣል።
በኢትዮጵያዊነት ላይ የተነጣጠረን ክፋት እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ካላስቆምነው በሳዑዲ የተጀመረው መረን የጥላቻ ሰደድ ሊቀጣጥል የሚችልና የየሀገሩ የፖለቲካ ኪሳራ ማስተንፈሻ የሚሆነው አገር አጥቶ የተሰደደው ኢትዮጵያዊው ላይ ሁሉ ይሆናል። ይህንን በአስቸኳይ ለመቃወም ያሉ የትግል መንገዶች ሁሉ ክፍት ሊሆኑ ይገባል። እኔ አዘጋጀሁ እኔ ጠራሁ የሚል ደካማ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ መንቀሳቀስ ሳይሆን ለሰብዓዊ ክብርና የመከራ ማጥ ውስጥ ሆነው የወገን ያለህ ለሚሉት እህት ወንድሞቻችን የድረሱልን ጥሪ ምላሽ እንስጥ። በጣም የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ለስራ የሚሄዱት ወጣቶች የትምህርት ደረጃቸው አነስተኛ የሆነና በድህነት ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሆነው ይሁን ብለው ከቤታቸው የወጡ ናቸው። አንዳንዶቹም ግሩም እድል አንደሚገጥማቸው በደላላዎች እየተነገራቸው ከቤት ወጥተው የቀሩ ናቸው። ለኒህ አጋር መሆን ለሀገር እንኳን ደንታ ባይኖረን ለነብስ የሚበጅ ስራ ነው። የኢትዮጵያ ኮሙኒቲዎች፣ በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙ የሀይማኖት ማዕከላት፣ ሲቪክ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ለዚህ ዓላማ ቢቻል አደራጆች ካልተቻለም ዋንኛ ተሳታፊዎች ሊሆኑ ይገባል። ይህ በደል እጅ ለእጅ ሊያስተሳስረንና አንድ ላይ እንድንቆም ሊያደርገን የሚችል የጋራ ጉዳይ ነው። ዛሬ ነገ ሳንል በተደራጀና አለም አቀፍ ትኩረት ሊኖረው በሚያስችል አቅሙ እንነሳ ለወገንም አንድረስ።የመከራ ቀናችንን ለማሳጠር እንደ ሕዝብም ከአንገታችን ቀና እንድንል በያለንበት እንትጋ!
biyadegelgne@hotmail.com

Wednesday, November 13, 2013

ትግሉ መሯል፤ እኛም ዝግጁዎች ነን


በንቅናቄዓችን ፀሐፊ እና በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አመራር አባላት ላይ የተቃጣው ረዥም ጊዜ የወሰደ የግድያ ሴራ መክሸፉ አስደስቶናል። ይህ ሴራ የወያኔ የስለላና የግድያ ኃላፊዎች በሆኑት ጌታቸው አሰፋ እና ጸጋየ በርሄ የቅርብ ክትትል የተመራ፤ የአሻንጉሊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ እውቅናና ይሁንታ የተሰጠው፤ ወያኔ ከፍ ያለ ተስፋ የጣለበት ሴራ ነበር።
“ወያኔ-ኦ-ሚሊኒየም” የተሰኘው ይህ በወያኔ የመጨረሻ ከፍተኛው አመራር የተመራው ሴራ ስለወያኔ ውስጣዊ አደረጃጀት ጠቃሚ መረጃዎችን ሰጥቶናል። ከዚህም በተጨማሪ የወያኔ ሹማምንት ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ንቀት፤ ከአመት በኋላ ስለሚደረገው ምርጫ ውጤት፤ ለሰላዮቻቸው ስለሚሰጡት ጉርሻ መጠን፤ እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ተስፋ ከጣሉበት ቅጥረኛ ነብሰ ገዳያቸው ጋር ካደረጉት የስልክ ንግግሮች ማድመጥ ይቻላል። ይህ ለበርካታ ጥናቶች በግብዓትነት ሊውል የሚችለውን በድምሩ ከስምንት ሰዓታት በላይ የሚፈጀው የስልክ ንግግር ቅጂ በሕዝባዊ ኃይሉ የመረጃ ክፍል አማካይነት ለሕዝብ በኢንተርኔት በነፃ ተለቋል። በአጋጣሚውም የወያኔ ገበና ተጋልጧል።
በአንፃሩ ደግሞ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የተደራጀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም ምን ያህል ወያኔን እንቅልፍ እንደነሳ ተጨባጭ ማስረጃ ሆኗል። ይህ ለነፃነት ታጋዮች ከፍተኛ የስነልቦና ብርታት የሚሰጥ ነገር ሆኖ ተገኝቷል።
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል የተቃጣበትን ጥቃት ከማክሸፍ በተጨማሪ የወያኔን ገበና ማጋለጥ በመቻሉ የመጀመሪያው ሁነኛ ድል ተቀዳጅቷል።
ግንቦት 7 : የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ወያኔ ኦ ሚሊኒየም” አፕሬሽንን ላከሸፉ የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አመራርና አባላት ያለውን አድናቆት ይገልፃል። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ጥቃቶች ሊደርሱ የሚችሉ መሆኑን በመገንዘብ የመከላከል ብሎም የማጥቃት ኃይሉን እንዲያጠናክር ይመክራል።
የንቅናቀዓችን እና የሕዝባዊ ኃይሉ አመራርና አባላት ለመስዋዕትነት የተዘጋጁ ናቸው። “ወያኔ ኦ ሚሊኒየም” ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ትግላችን ይገታ ነበር ማለት አይደለም። ትግላችን መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን እናውቃለን። ጓዶች ሲወድቁ ሌሎች ሺዎች አርማቸውን አንስተው ትግሉን ይቀጥላሉ።
ትግሉ የሚጠይቀንን መስዋትነት ከፍለን ወያኔን ከሥልጣን አስወግደን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሆነባት ኢትዮጵያ እንደምትኖረን እርግጠኞች ነኝ።
ትግሉ መሯል፤ እኛም ዝግጁዎች ነን።


    ድል ለግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል!!!
    ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

    Thursday, November 7, 2013

    “በሳዑዲ ኢትዮጵያዊ ህገ ወጥ ስደተኞች ሳንጃና ቆንጨራ መታጠቃቸውን አረጋግጠናል” አምባሳደሩ


    (አምባሳደሩ በአቶ ሙስጠፋ ሁሴን አሊዬ ስም በሚያንቀሳቅሱት የአሰሪ እና ስራተኛ ኤጄንሲ ለሞቱት 3 ሴቶች ተጠያቂ ናቸው)
    eth saudi
    ኖቬበር 4 2013 የሳውዲ አረቢያ መንግስት የምህረት አዋጅ የግዜ ገደብ መጠናቀቅ አስመልክቶ ለተለያዩ የልማት ማህበር አባላት ኤምባሲው አርብ ኖቬምበር 1 2013 በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒት አዳራሽ ስብሰባ ጠርቶ እንደነበር የሚገልጹ ምንጮች ስብሰባው በኢትዮጵያውያን ቆጨራ እና ሳንጃ መታጠቅ ዙሪያ ኤምባሲው ማህብረሰቡን ለመነጋጋር አጀንዳ ይዞ መቅረቡ ስብሰባው በጣም አሳፋሪ እና ኢትዮጵያውያንን በጅምላ ለመወንጀል ሆን ተብሎ የታቀደ ከስም ማጥፋት ዘመቻ ተለይቶ የማይታይ መሆኑንን ገልጸዋል።
    በተለይ አምባሳደር ዶ/ር መሃመድ ሃሰን በወቅቱ ለተሰባስቢው ስለአጀንዳው ሲገልጹ ሪያድ ከተማ በተለምዶ መንፉሃ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ አያሌ በባህር የመጡ ኢትዮጵያውያን በተለምዶ «ባህር ሃይል እየተባሉ የሚታወቁ» መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ጠቀሰው እነዚህ ህገወጦች የሳውዲ አረቢያ መንግስት ያወጣውን ህግ ተከትሎ የሚወሰድባቸውን እርምጃ ለመከላከል ሳንጃ መታጠቃቸውን ኤምባሲው በመረጃ አረጋገጦል ብለው መናገራቸው በአብዛኛው ተሰብሳቢ ዘንድ ተቃውሞን ቀስቅሷባቸዋል። አምባሳደሩ በዚህ ዙሪያ ሰላማዊ ወገኖቻችንን በመወንጀል የሃገራችንን በጎ ገጽታ ለማጠልሸት በኤምባሲ ደረጃ አጀንዳ ተይዞ ስብሰባ መጠራቱ ያበሳጫቸው ተሰብሳቢዎች የአምባሳደሩን ጤናማነት እስከ መጠራጠር መድረሳቸውን ምንጮቻን አክለው ገልጸዋል። ድጋፍ እናገኛለን ብለው የጠሯቸው ታማኝ የልማት ማህበራቱ ስራ አመራር የአምባሳደር መሃመድ ሃሰን ያቀረቡት ክስ ከምን ጭብጥ ተነስተው እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጦቸው ስብሰባው ላይ ወጥረው ይዘዋቸው እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች ስብሰባው ገና ከመነሻው በተሳታፊው ከፍተኛ ተቃውሞ አለመግባባቶች ተፈጥረው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
    mohammed hassenአንዳንድ የአምባሳደር መሃመድ ሃሰን አባባል ያንገበገባቸው አስተያየት ሰጪ የቀረበው አንጀዳ ስህተት መሆኑንን ገልጸው ሴት እህቶቻችን ጉልበታቸውን ያፈሰሱበትን የወር ደሞዛቸውን ተነጥቀው ተደብድበው እና ተደፍረው በየጎዳናው ወድቀው የፍትህ ያለህ እያልን ጣረሞት እያሰማን ባለንበት የስደት አለም እኛው አጥፊ እኛው ገዳይ አረመኔ እና ጨካኝ ተብለን በተለያዩ ሚዲያዎች ስማችን ሲጠፋ እና የሃገራችን በጎ ገጽታ በማጉደፍ በባእዳን ጥላቻ የተቃጣብንን የስም ማጥፋት ዘመቻ አምባሳደሩ እንደ አንድ ሃገር መሪ ተወካይ መጋፈጥ ሲገባቸው የዝሆን ጆሮ ይስጥኝ ብለው ከርመው ዛሬ በድፍረት እኛ ፊት ቆመው እኛኑ ለመወንጀል መቃጣታቸው በጣም ያሳዝናል ብለዋል።
    በሌላ በኩል አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ሲናገሩ አምባሳደር መሃመድ ሃሰንን ከእንግዲህ እንደማያውቋቸው ገልጸው ስለኢትዮጵያውያን ለመናገር የሞራል ብቃት የሌላቸው ከሳቸው ይልቅ በዲፕሎማት ደረጃ አንቱ የሚባሉ እንደነ አቶ መስፍን እና መሰል ዲሲፒሊን ያላቸው ኢትዮጵያዊያን የመንግስት ተወካዮች ስለኮሚኒቲው ችግር ህዝቡን ማወያየት እንደሚገባቸው በአጽኖት ጥቀስ በኤምባሲው ዝርክርክ አሰራር የእድሉ ተጠቃሚ መሆን የተሳናቸው ወገኖቻችን ላይ ለሚደረሰው ማንኛውም አደጋ አምባሳደሩ ሃላፊነትን መውሰድ እንደሚገባቸው በሰጡት አስተያየት ከተሰብሳቢው በተደረገላቸው የድጋፍ ጭብጨባ በወቅቱ የስብሰባ አዳራሹን ድባባ ለውጦታል።
    አምባሳደር መሃመድ ሃሰን በአምባሳደርነት ማዕረግ ተሹመው ወደ ሳውዲ አረቢያ ከተላኩ ጀምረው በተለያዩ የግል ንግድ ላይ በእጅ አዙር ተሰማርተው ያለአግባብ የበለጽጉ ከበርቴ አምባሳደር መሆናቸውን የሪያድ ነዋሪዎች ያናገራሉ። አምባሳደር መሃመድ ሃሰን ኢትዮጵያ ውስጥ በአቶ ሙስጠፋ ሁሴን አሊዬ ስም በከፈቱት 2 የአሰሪ እና ስራተኛ ኤጄንሲ አማኝነት ወደ ሳውዲ አረቢያ መጥተው እስካሁን ድረስ ህልፈተ ህይወታቸውን ቤተሰቦቻቸው ላልተረዱ 3 ሴት እህቶቻችን ሞት ተጠያቂ ከመሆናቸውም በላይ በቅርቡ 2 ሚሊዮን ሪያል «5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር» ወደ ሌላ ሃገር ለማሸሽ ሲሞክሩ በሳውዲ ደህንነት ሃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋሉት ከቀድሞው በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሊቀመንበር አቶ ሙስጠፋ ሁሴን አልዬ ጋር አምባሳደሩ እጃቸው እንዳለበት ይጠረጠራል።
    በአጠቃላይ አምባሳደር መሃመድ ሃሰን መንፍሃ ውስጥ ቆጨራ እና ሳንጃ ታጥቆ መሽጓል ብለው ለመወንጀል የፈለጉት የየተኛውን ብሄር አባል እንደሆነ ስብሰባው ላይ በይፋ ባይናገሩም በዚህ አካባቢ ቀደም ብሎ ጥቂት ስርዓት አልበኛ ኢትዮጵያውያን መሃከል አልፎ አልፎ በሚቀሰቀስ የጉሩፕ ግጭት በሳንጃ እርስ በእርሳቸው ይተራረዱ እንደነበርና በአካባቢው ማህበረሰብ የዕለት ተዕለት እንቅስቅሴ ላይ ቀላል የማይባል ተጸኖ ያሳድሩ የነበሩ ወጣቶችን ለማስታረቅ ኤምባሲው ቢጠይቀም ፈቅደኛ ሳይሆን መቅረቱ ይታወሳል። ይህ በተለምዶ መንፉሃ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ብዛት ያላቸው በባህር የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የከተሙባት እና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በንግድ ዘርፍ የተሰማራባት በመሆኑ በመርካቶነት የሚሰይሙት ወገኖች ለአያሌ ኢትዮጵያውያን የእድገት ማዕከል በመሆኗ በማውሳት የአምባሳደሩን ንግግር ቀደም ሲል በተለያዩ ሚዲያዎች በኢትዮጵያውያን ላይ ከተቃጣ ውንጀላ ለይተው እንደማያዩት ይገልጻሉ።
    የጎልጉል ደንበኛ በፌስቡክ የላኩት
    Ethiopian Hagere ጅዳ በዋዲ

    Tuesday, November 5, 2013

    የሌለውን ፍለጋ - ክፍል አንድ


    ዳንኤል ክብረት

    ተስፋየ ገብረ አብ ‹የስደተኛው ማስተዋሻ› የተሰኘ መጽሐፍ ማውጣቱንና ባነበው መልካም እንደሆነ ገልጦ አንድ
    ወዳጄ ‹ስስ ቅጅውን› ከሀገረ አሜሪካ ላከልኝ፡፡ ከዚህ በፊት ሌሎች መጻሕፍቱን አንብቤያቸዋለሁ፤ በአጻጻፍ
    ችሎታው የምደሰተውን ያህል እንደ አበሻ መድኃኒት ነገሩን ሁሉ እርሱ ብቻ የሚያውቀው ምስጢር
    ስለሚያደርገው፤ በአንዳንድ ጉዳዮችም ሆን ብሎም ሊያናጋቸው የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ያሉ
    ስለሚመስለኝ፤ ተስፋዬ ለምን እንደዚህ ይጽፋል? እያልኩ የምጠይቃቸው ነገሮች ነበሩ፡፡
    በዚህ መጽሐፉ ውስጥም ያንን ጥርጣሬየን አጉልቶ ሥጋ ነሥቶ እንዳየው የሚያደርገኝ ነገር ገጠመኝ፡፡ ተስፋየ በገጽ
    306 ላይ ‹‹የፍስሐ ጽዮን ፖለቲካ› በሚል ርእስ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የማያውቀውን ነገር ጽፏል፡፡
    ስለማያውቀው ነገር የጻፈው ባለማወቁ ብቻ አይመስለኝም፡፡ አንድም ለማወቅ ባለመፈለጉ፣ አለያም ሆን ብሎ የማፍረስ ዓላማ ይዞ
    ይመስለኛል፡፡
    ይህን የምለው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለመጻፍ ሲፈልግ ሊያነባቸው የሚችላቸው መጻሕፍት
    በምድረ አውሮፓ እንደ ማክዶናልድ በዝተው ሞልተው ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ ሰዎች የተጻፉ ናቸው፡፡
    ሌላው ቢቀር ኤንሪኮ ቼሩሊ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔቶች ታሪክ(Gli Abbati di Dabra Libanos, 1945)፣ ኮንቲ ሮሲኒ ከሐተታ
    ጋር ያሳተመውን ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣በዋልድባ ቅጅ (Il Gadla Takla Haimanot secondo la redazione
    Waldebbana, 1896)፣ የዊልያም በጅን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወትና ተአምር (The Life and Miracles of Takla
    Haymanot, 1906)፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጸሐፍትም ውስጥ የታደሰ ታምራትን Church and State in Ethiopia, ማንበብ
    በተገባው ነበር፡፡
    ከዚህም ዘልሎ ጥልቅ ጥናት አድርጌ ደረቴን ነፍቼ እናገራለሁ ለሚል ደግሞ እንግሊዝ ምቹ ናትና ሎንዶን ወደሚገኘው ብሪቲሽ
    ሙዝየም ሄዶ በማይክሮ ፊልም የተነሡትንም ሆነ በአካል ያሉትን ብራናዎች ማየት ነው፡፡ እዚያም የማያደርሰው ከሆነ በዋና ከተማው
    በሆላንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙትን የጌታቸው ኃይሌን THE MONASTIC GENEALOGY OF THE LINE OF
    TÄKLÄ HAYMANOT OF SHOA, (Rassegna di Studi Etiopici, Vol. 29 (1982-1983), pp. 7-38)፤
    የተስፋዬ ገብረ ማርያምን A Structural Analysis of Gädlä Täklä Haymanot(African Languages and
    Cultures, Vol. 10, No. 2 (1997), pp. 181-198)፤ የሐንቲንግ ፎርድን (G.W.B. Huntingford, "The Lives of
    Saint Takla Haymanot," Journal of Ethiopian Studies, 4(1966), 34-35.) የአሉላ ፓንክረስትን Dabra
    Libanos Pilgrimage Past and Present, The Mytery of the Bones and the Legend of Saint Takla
    Haymanot,(the sociology ethnology Bulletin) 1,3 (1994), P. 14-26 ጥናቶችን ማየት ይቻል ነበር፡፡ ያም ካልሆነ
    ወደ ቤልጅየም ሄዶ ፒተርስ አሳታሚ ከጥልቅ ጥናት ጋር የሚያሳትማቸውን የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዛግብት ኅትመቶች ማገለባጥ ይቻል
    ነበር፡፡
    የገረመኝ ገድለ ተክለ ሃይማኖትን ያህል በኢትዮጵያ ታሪክ (History)ና የታሪክ አጻጻፍ(Historiography) ታላቅ ቦታ ያለው፣
    በኢትዮጵያ ገድላት ጥናት(Hagiography) ቀዳሚ የሆነና በብዙ አጥኝዎች የተጠና ጉዳይ ያለ ምንም በቂ ማስረጃ አፈርሳለሁ ብሎ
    መነሣቱ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ከማይወጣበት የክርክር አዘቅት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡
    ተስፋዬ ጽሑፉን የጀመረው በስድብ ነው፡፡ ኤርትራዊት እናቱ ‹ይዘምሩት ነበር‹ ብሎ ያቀረበው ጽሑፍ የራሱን ስድብ በእና ያሳበበበት
    ነው፡፡ የኤርትራን ቤተ ክርስቲያንና ኤርትራውያን ክርስቲያን እናቶችን ከእርሱ በላይ አውቃቸዋለሁ፡፡ ተሰድደው በየሀገሩ ከተበተኑት
    ጋር አብረን ቋንቋና ድንበር ሳያግደን አገልግለናል፡፡ አሥመራ ከተማ ከሚገኙት ታላላቅ አድባራት አንዱም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ
    ክርስቲያን ነው፡፡ በምንም መልኩ አንዲት ኤርትራዊት እናት ተስፋዬ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የተሳለቀውን ‹መዝሙር›
    አትዘምርም፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደማቸው የፈሰሰው ሰባት ዓመት ሙሉ ለጸሎት የቆሙበት እግራቸው በጸሎት ብዛት በመቆረጡ
    እንጂ ሰይጣን ‹ፈንግሏቸው› አለመሆኑን ኤርትራውያን እናቶች በሚገባ ያውቁታል፡፡ የሚገርመው ነገር ተስፋዬ በጆሮ ጠገብ የሆነ ቦታ
    የሰማውን መዝሙር አጣምሞት እንጂ መዝሙሩ እንዲህ አይደለም፡፡
    አቡነ ተ/ኃይማኖት ተክለ ሃይማኖት የዓለም ብርሃን ናቸው
    ይኼው ለዘላለም ያበራል ገድላቸው

    ነው የሚለው፡፡
    ተስፋዬ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ አነበብኳቸው የሚለን አምስት መጻሕፍትን ነው፡፡ የአባ ዮሐንስ ከማ፣ የኪዳነ ወልድ
    ክፍሌ፣ የጽጌ ስጦታው፣ የዳኛቸው ወርቁና የኢረይን ሙራይ፡፡ አባ ዮሐንስ ከማን እንደማያውቃቸው፣ የጻፉትንም ገድል እንዳላነበበ
    የሚያሳብቅበት ‹ደብተራ› ሲላቸው ነው፡፡ አባ ዮሐንስ ከማ ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ እንጂ ደብተራ አልነበሩም፡፡ በዚያ ዘመን
    ‹ደብተራ› ማለት የንጉሡን ደብር(ድንኳን) የሚያገለግሉት ካህናት ናቸው፡፡ አባ ዮሐንስ ከማ በዐፄ ይስሐቅ(1407-1423)ዘመንና
    በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ(1437-1461)የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበሩ ደብረ ሊባኖስን እንደገና ያሳነጹ ገድለ ተክለ ሃይማኖትንም ያስጻፉ
    አባት ናቸው፡፡ ተስፋዬ አባ ዮሐንስ ከማ ከ200 ዓመታት ቆይታ በኋላ ስለ ጻፉ ተሳስተዋል ይላል፡፡ ባታውቀው ነው እንጂ ሙሴ
    ኦሪትን የጻፈው ዓለም ከተፈጠረ ከሺዎች ዓመታት በኋላ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ገድሎች ዘግይተው የሚጻፉት የአንድን ቅዱስ ቅድስና
    ለመመስከር ካረፈ ቢያንስ ግማሽ ምእተ ዓመት ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ በመቃብሩ ላይ የሚሠሩት ተአምራት፣ በአማላጅነቱ
    የሚሠራቸው ተአምራትና ሌሎችም መታየት አለባቸው፡፡
    ተስፋዬ አላዋቂነቱን እንደ ዕውቀት ስለወሰደው እንጂ የአቡነ ዮሐንስ ከማ ገድል የመጀመሪያው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል
    አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አራት ቀደምት ሰዎች ጽፈዋል፡፡ 1)በስንክሳር ተጽፎ የሚገኘው(በተለይም
    በፓሪሱ ስንክሳር) አጭር የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ፣ 2) የትግራይ ተወላጅ በሆነው በተክለ ጽዮን የተጻፈው የዋልድባው ገድለ
    ተክለ ሃይማኖት [አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት (በቆብ) የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አቡነ መድኃኒነ
    እግዚእን ሲያመነኩሱ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ደግሞ ሰባቱ ከዋክብት የተባሉትንና በጣና ዙሪያ የሰበኩትን (አቡነ ዮሐንስ ዘቁየጻ፣ አቡነ
    ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቋ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልተዋርና አቡነ
    ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤን) ሲያመነኩሱ ነው ምንኩስናን ተቀብለው ለተልዕኮ የተሰማሩት፡፡ ለዚህም ነው የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን
    ገድል ዋልድባዎች የጻፉት፡፡] 3)ያልታወቀ ጸሐፊ አጭሩንና የሐይቅ እስጢፋኖስ ቅጅ የሚባለውን ጽፏል፡፡ ይኼኛው ገድል ቀዳሚ
    ሳይሆን አይቀርም፤ አንደኛ የተጻፈው ከሌሎች ቅዱሳን ገድሎች ጋር እስትግቡእ ሆኖ በስንክሳር መልክ ነው፡፡ ሁለተኛ የተጠቀማቸው
    አማርኛዎች በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ የሌሉ ዓይነት ናቸው፣ 4)አቡነ ዮሐንስ ከማ የጻፈው የደብረ ሊባኖስ ቅጅ ናቸው፡፡
    ይህ የአቡነ ዮሐንስ ከማ ገድል ምናልባት ከ1418-19 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ በዐፄ ይስሐቅ ዘመን የተጻፈ መሆኑ
    ይገመታል(Encyclopedia Aethiopica, Vol. IV, P. 832) በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው ዐረብኛው ገድል በዐፄ
    ገላውዴዎስ ዘመን(1533-1551) የተጻፈ ይመስላል(Encyclopedia Aethiopica,Vol.IV, P.832)፡፡ ያልተመዘገቡ አያሌ
    ገድላት በየገዳማቱ መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ 22 የብራና ገድሎች በአውሮፓ፣ 20 በኢትዮጵያ የማኑስክሪፕት ቤተ
    መጻፍት(EMML)፣ 3 በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት፣ 5 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት
    ገድሎች ይገኛሉ፡፡ በአንድ ቅዱስ ላይ የተለያዩ ቅጅዎች መገኘታቸው መረጃዎችን ያሰፋቸዋል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ስለ አንድ ክርስቶስ
    አራት ዓይነት ወንጌሎች መጻፋቸውን ማስታወስ ይበቃል፡፡
    አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በብዙ ሥራዎቻቸው የተከበሩና የተመሰገኑ ሊቅ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ላነሡት ሃሳብ
    ግን ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ ገድሎች ሁሉ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገድል ያህል የሚታወቅና የተጠና የለም፡፡
    ከሌሎች ጋር እየተነጻጸረም ሆነ በራሱ(Textual analysis) ገድለ ተክለ ሃይማኖት በአውሮፓውያንም ሆነ በኢትዮጵያውያን
    ሊቃውንት ተጠንቷል፡፡ እስካሁን ግን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ሆኑ ሌሎች የሚሉት ‹ሌላ ገድል› አልተገኘም፡፡ አለቃም ያነበቡት
    ከሆነ ያነበቡትን፣ ያገኙት ከሆነም ያገኙበትን አልነገሩንም፡፡ ምንጭ የላቸውምና ለታሪክ ክርክር ሊጠቀሱ አይችሉም፡፡
    ጽጌ ስጦታውም ቢሆን ምናቡንና አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን ጠቀሰ እንጂ አለ የሚለውን ‹የዚያኛውን ተክለ ሃይማኖት› ገድል
    ሊያመጣልን አልቻለም፡፡ ዳኛቸው ወርቁ የጻፈው ልቦለድ እንጂ ታሪካዊ ዋጋ ያለው ነገር ስላልሆነ ለክርክር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ይባስ
    ብሎ ተስፋዬ ኢለይን ሙራይ ለልጆች ብላ የጻፈችውን ተረት ጠቅሶልናል፡፡ ይህ ነገር የቦሩ ሜዳን ክርክር ነው ያስታወሰኝ፡፡
     በቦሩ ሜዳ ክርክር ‹ለኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደት አለው› የሚሉና ‹ሦስት ልደት አለው› የሚሉ ሊቃውንት ተከራክረው ነበር፡፡
    በዚህ ክርክር የሁለት ልደትን ወክለው ከተከራከሩት መካከል የነበሩት መልከአ ብርሃን ወልደ ዮሐንስ ‹ነአምን ክልኤተ ልደታተ› የሚል
    ንባብ ከሊቃውንት መጽሐፍ ጠቅሰው ተከራከሩ፡፡ ዐፄ ዮሐንስም የሦስት ልደቶችን ተከራካሪ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስን ‹በል አንተም እንደ
    እርሱ ከሊቃውንት መጽሐፍ ሦስት ልደት የሚል ንባብ አምጣ› አሉት በዚህ ጊዜ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ ‹በደብረ ብርሃን ተአምረ ማርያም ይገኛል› አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ‹ከምታስተምረው ከአራቱ ጉባኤ አጣህና ነው ከተአምረ ማርያም ትጠቅሳለህ›› ቢሏቸው ‹ ከጉባኤው
    መጽሐፍስ የለም›› አሉ ይባላል፡፡
    የተስፋዬ አጠቃቀስ ከዚህም የወረደ ነው፡፡ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ የተወቀሱት ለእምነት ክርክር የማይጠቀስ የተአምር መጽሐፍ
    በመጥቀሳቸው ነው፡፡ ተስፋዬም ከዚያ ወርዶ ወርዶ ለታሪክ ክርክር የማይጠቀስ የተረትና የልቦለድ መጽሐፍ ሲጠቅስ ይገኛል፡፡
    ተስፋዬ ወግዳ የተሸሸገ ለሕዝብ የማይቀርብ ገድለ ተክለ ሃይማኖት አለ ይላል፡፡ በሀገራችን ጠንቋይ እንዳይጋለጥ ሲፈልግ የሌለ ነገር
    ያዝዛል ይባላል፡፡ ተስፋዬም ወግዳ የተደበቀ ገድል አለ አለ፡፡ ወግዳ በሰሜን ሸዋ በደብረ ብርሃን ዙሪያ ወረዳ ሥር የሚገኝ ቦታ ነው፡፡
    የኢትዮጵያ የብራና መጻሕፍት በ1964 ዓም ማይክሮ ፊልም መነሣት ሲጀምሩ ከሰሜን ሸዋ ነበር የተጀመረው፡፡ እነ ሥርግው ሐብለ
    ሥላሴ(አጥንታቸውን ያለምልመው እንጂ) እያንዳንዷን ወረዳ ለቅመው አንሥተውታል፡፡ እንኳን በገዳማት አድባራት የሚገኙት
    በግለሰቦች እጅ የሚገኙትም አልቀሯቸውም፡፡ እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍ የሕንድ፣ የግሪክ መጻሕፍት አልቀራቸውም፤ እንኳን
    ገድልና ተአምር የቤተ ክርስቲያንን እምነት የሚቃረኑ መጻሕፍት በክብር ተጠብቀው ነው የተገኙት፡፡ ተስፋዬ ወግዳ የማይደረስበት
    መስሎት መደበቂያ ዋሻ አለ ይላል፡፡ ወግዳኮ ከአዲስ አበባ የ120 ኪሎ ሜትር ጉዳይ ነው፡፡
    በማይክሮ ፊልም ቀረጻው ወቅት በሥራ ላይ የተሠማሩት የሀገሬው ተወላጆች ነበሩና ያስቸገራቸው ነገር አልነበረም፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ
    ይህ ‹የወግዳ ገድል› ይገኝ ነበር፡፡ ግን የለምና አልተገኘም፡፡ ይህ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ዛሬ አልተጀመረም፡፡ በትግራይ፣ በወሎ፣ በጎጃም
    በተክለ ሃይማኖት ስም ስለሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን የተጻፉ ገድሎች አሉ እየተባለ እንዲሁ በአፍ ታሪክ ይነገራል፡፡ እስካሁን ግን ማስረጃ
    አምጥቶ ያረጋገጠ አልተገኘም፡፡ የትግራይ ገዳማት የብራና መጻሕፍት በቅርቡ ዲጂታላይዝ ተደርገዋል፡፡ ግን የተባለው አልተገኘም፡፡
    በመካከለኛው ዘመን ሌላው ቀርቶ ከማዕከላዊው መንግሥት ተጋጭተው ርቀው በነበሩት የደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ገዳም በጉንዳ ጉንዲ
    እንኳን የደብረ ሊባኖሱን ገድል የመሰለ ቅጅ ነው የተገኘው፡፡
    ማንኛውም ክርክር ሲቀርብ ለክርክሩ ብቁ የሆነ ማስረጃ መቅረብ አለበት፡፡ ልቦለዱንም፣ ቀልዱንም ለታሪክ ማስረጃ መጥቀስ ቧልት
    እንጂ ቁም ነገር አይሆንም፡፡ ተስፋዬ ስለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚባለውን የታወቀ ታሪክ (official history) ለመቀበል
    አልፈለገም።ያ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ አዲስ ማስረጃ አምጥቶ ወይም ነባሩን ማስረጃ በክርክር አፍርሶ ያላየነውን ካሳየን እናመሰግነው
    ነበር፡፡ እርሱ ግን ወይ የታወቀውን አልተቀበለ፣ አለያም አዲስ ማስረጃ አላመጣ፣ ከሁለት የወጣ ጎመን ሆነብን፡፡
    ሮማውያን የሕግ ሊቃውንት Argumentum ad Contrario የሚል መርሕ ነበራቸው፡፡ ‹አንድን ነገር የታመነውንና የታወቀውን
    ትተህ በተቃራኒው ያለውን አረጋግጥ› ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ የሚባለውንና የሚታመነውን ተወውና
    ተቃራኒውን በማስረጃ፣ በተጠየቅና በትንታኔ አረጋግጥ ማለት ነው፡፡ ተስፋዬ ይህንን ለማረጋገጥ ዐቅም አላገኘም፡፡ እንዲሁ ቧልቱን ብቻ
    ነገረን፡፡
    ተስፋዬ የታሪክ ስሕተቱን የሚጀምረው በሰባተኛው መክዘ ዐፄ ዳዊት የሚባሉ ንጉሥ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩ ሲለን ነው፡፡ ተስፋዬ
    በቀላሉ የሚገኘውን የሬኔ ባሴን ታሪከ ነገሥት፣ የሥርግው ሐብለ ሥላሴን የነገሥታት ዝርዝር፣ የተክለ ጻድቅ መኩሪያን መጻሕፍት
    አለያም የብላቴን ጌታ ኅሩይን ‹ዋዜማ›፣ የጌታቸው ኃይሌን ባሕረ ሐሳብ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1975 አሳትሞት የነበረውን The
    Dictionary of Ethiopian Biography, ብታይኮ እንዲህ ካለ ስሕተት ውስጥ አትወድቅም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ዳዊት
    በሚል ንጉሥ መጀመሪያ የነገሠው ዐፄ ዳዊት አንደኛ ከ1374-1406 ዓም ነው፡፡ ከየት አምጥተህ ነው በሰባተኛው መክዘ ያደረግከው።
    እጂግ የሚገርመው ነገር የሀገራችን ሊቃውንት ‹ጨዋ ደፋር ነው› እንደሚሉት ተስፋዬም ያለ ምን ጥናት፣ ያለ ምንም ማስረጃ እርሱ
    ራሱም እንደሚለን ‹ኢትዮጵያ ሳለ የሰማቸውን አፈ ታሪኮች ሰብስቦ›(እኔ ግን አይመስለኝም፣ አሜሪካ ሆኖ ፈጥሮ እንጂ) በድፍረት
    ‹ሦስት ተክለ ሃይማኖቶች አሉ ይላል፡፡ ቢያንስ ለዕውቀት ክብር ሰጥቶ ‹ያሉ ይመስለኛል› ቢል እንኳን ምን አለበት፡፡ ለካስ እስከዛሬም
    በሌሎች መጻሕፍቱ ሲነግረን የነበሩት ‹የመንግሥት ምሥጢሮች› እንዲህ የተሰበሰቡ አፈ ታሪኮች ነበሩ ማለት ነው?
    ለመሆኑ ተስፋዬ እናዳለው ሦስት ተክለ ሃይማኖቶች አሉን? ሦስቱስ በገድለ ተክለ ሃይማኖት ተቀላቅለዋልን? ሳምንት እንመለሳለን፡

    © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ ላይ የወጣ ነው -
    (ኢትዮሚድያ November 3, 2013)

    Monday, November 4, 2013

    የፖለቲካው ስር ቁማርተኞች! (ተመስገን ደሳለኝ)



     በሀገራችን መንግስታዊ አስተዳደር የ‹‹ቁማር ህግ››ን ችግር መፍቻ አድርጎ መጠቀም የጀመረበትን ጊዜ
    ለማስላት ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምንሊክ እንደ"ተበሉበት" ከሚነግረን የሽኩሹክታ ታሪካችን አንስቶ አንድ፣
    ሁለት፣ ሶስት… እያልን ለመቁጠር እንገደዳለን፡፡ ይሁንና ባለሙያ (በንባብ የደረጀ) ቁማርተኛ ፖለቲከኛ እንደ
    ሰማይ ከዋክብት የበዛበት ድንገቴ ክስተት የ1966ቱ አብዮት ዋዜማ ነው ቢባል ወደ እውነታው ይጠጋል፡፡
    ከመንግስቱ ኃ/ማሪያም ‹‹ለምሳ ያሰቡንን፣ ቁርስ አደረግናቸው›› እና የአጥናፉ አባተ ፍፃሜን ጨምሮ
    የእነተስፋዬ ደበሳይና ብርሃነ መስቀል ረዳ፤ የእነኃይሌ ፊዳና አለሙ አበበ፤ የእነሌንጮ ለታና ባሮ ቱምሳ፤ የእነ
    አባይ ፀሀዬና አረጋዊ በርሄ፤ የእነታምራት ላይኔና ያሬድ ጥበቡ… ከትግል መድረክ መገለል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

     ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ደግሞ በእነመለስ ዜናዊና ስዬ አብርሃ፤ በእነኃይሉ ሻውልና ቀኝ አዝማች ነቅዐ ጥበብ፤ በእነብርሃኑ ነጋና
    ልደቱ አያሌው፤ በእነመረራ ጉዲናና አልማዝ ሰይፉ፤ በእነግዛቸውና ያዕቆብ ኃ/ማርያም… መካከል የተፈጠሩ የሃሳብ ልዩነቶች የተፈቱበት
    መንገድ በዚሁ የጨዋታ ህግ የተስተናገደ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ተጨባጭ ሁነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች የተቋጩት ከመተዳደሪያ
    ደንብ ውጪ፣ የተሻለ ዕድል ያለውን ካርታ ቀድሞ በመዘዘ ብልጣ ብልጥ አሸናፊነት ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ የምናየው ‹መልክአ ቁማር›ም
    ከእንዲህ አይነቱ የጥሎ ማለፉ ጨዋታ በተጨማሪ የመንፈስ ልዕልናቸውን ያረከሱትንም የሚያካትት ይሆናል፡፡

     ቁማርተኞቹ…

     የተለመደውን ‹‹ፖለቲካ፣ ቆሻሻ ጨዋታ ነው›› ፈረንጅኛ አባባል እንደፈጣሪ ትዕዛዝ በልባቸው ያሳደሩ ፖለቲከኞች እንደአሸን የፈሉት
    በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ነው፤ የሀገሬንም ‹ዕድል ፈንታ› በመዳፋቸው የጨበጡ መሪዎች ከዚሁ መልክአ ምድር መብቀላቸው ይመስለኛል
    አስከፊ ድህነት፣ ተደጋጋሚ ድርቅ (ችጋር)፣ ሀገር ለቆ መሰደድ፣ የነፃነት እጦት፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ… በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ
    እንደ ምርጊት የተጣባን፡፡ ይሁንና ‹ይህ ለምን ሆነ?› የሚለው ጥያቄ የባለሙያ ጥናት የሚሻ ጉዳይ ቢሆንም በአይን የሚታየውን፣ በጆሮ
    የሚሰማውን አንድ ምክንያትን ግን መጥቀስ ይቻላል፡- ‹‹ባለስልጣናቱ ከሚያስተዳድሩት ህዝብ በላይ፣ ለሹመት ያበቃቸውን ድርጅት
    አጥብቀው መፍራታቸው››ን፡፡

     በእኔ አተያይም ይህ ስር የሰደደ ፍርሀት ከህግና መርህ ይልቅ፣ የጥቂት ወሳኝ ሰዎችን ፍላጎት እንዲያስፈፅሙ፤ ከሀገር ይልቅ ድርጅትን፣
    ከድርጅት ይልቅ ሥልጣንንና የግል ጥቅምን እንዲያስቀድሙ አስገድዷቸዋል፤ ወደዚህ አይነቱ ቅጥ ያጣ ፍርሃት ለመገፋታቸውም ሁለት
    ምክንያት መጥቀስ ይቻላል፤ የመጀመሪያው ከብቃትና አቅም ጋር በተያያዘ (ከትምህርት ዝግጅትም ሆነ ከፖለቲካ ብስለታቸው ጋር
    በማይመጣጠን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ እንዲቀመጡ መደረጉ) ሲሆን፤ ሌላኛው በሥልጣን ዘመናቸው የስግብግብ ነጋዴ ባህሪ
    የተጠናወታቸው ዘራፊ መሆናቸውን ነው፡፡ እነዚህ ኩነቶች ደግሞ ለከፍተኛ ስልጣን ላበቋቸው አንጋፋ ታጋዮች ለጥ-ሰጥ ብለው የሚገዙ
    ‹ትጉህ ባሪያ› እንዲሆኑ ተፅዕኖ አድርገውባቸዋል፤ ታማኝነታቸውን ያጎደሉ ዕለት ደግሞ ወደ ወህኒ ሊያስወረውር የሚችል ‹ጥቁር
    መዝገብ› (ሙስኛነታቸውን የሚያጋልጥ) መጠባበቂያ ተደርጎ መቀመጡን ማወቃቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንደ ‹የግል አዳኝ› አድርጎ
    ከመቀበል በቀር አማራጭ አሳጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ብሔራዊ ጥቅምንና ህዝብን የሚጎዳ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ‹ለምን?› ብለው
    መከራከር አይችሉም፡፡ በርግጥ ስልቱ ቃል-በቃል የተቀዳው ጨቋኝ ገዥዎችን ምክር ይለግስ ከነበረው ኒኮሎ ማኪያቬሊ ‹‹ዘ ፕሪንስ››
    ከተሰኘ መፅሀፍ ነው፡-
    ‹‹የሚሾማቸውን ባለሥልጣናት በሚጠቅመው መልኩ መቅረፅ የሚሻ ገዥ፣ ባለስልጣናቱን መንከባከብ፣ ለክብር ማብቃትና በሀብት
    ማበልፀግን መዘንጋት የለበትም፤ ከዚህም በላይ ክብሩንና ስልጣኑን ከእነርሱ ጋር በመጋራት ባለውለታው ሊያደርጋቸው ይገባል፤ ይህ
    ሲሆንም የገዥው ፍፁማዊ አገልጋይ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡››

     በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሰብዕናው ‹ፈርሶ የተሰራ› ተሿሚም በሥልጣን ዘመኑ ሀገር፣ ህዝብ፣ ህገ-መንግስት፣ ህሊና… እያለ የሚጨነቅበት
    ሁናቴ አይኖርም፡፡ ፍትህ ቢዛባ፣ ንፁሀን በጥይት ቢደበደቡ፣ ሚሊየኖች በረሀብ ቢረግፉ… አይቆረቁረውም፤ የእርሱ ጭንቀት ለሿሚዎቹ
    ያለውን ታማኝነት ሳያጓድል በስልጣን መቀጠሉ እና ከለታት አንድ ቀን ‹ይመጣል› ብሎ ለሚሰጋበት ክፉ ቀን ራስን አዘጋጅቶ መጠበቁን
    አለመዘንጋት ነው፤ የትዳር አጋር እና ልጆችም አሜሪካና አውሮፓን የሙጢኝ የማለታቸው መግፍኤ ይህ ይመስለኛል፡፡ መቼም ስንት
    ሚኒስትር፣ ስንት ጄነራል ያችን የቀን ጎደሎ ‹ታጥቦና ታጥኖ› እየጠበቀ መሆኑን ‹‹ጊዜ ይቁጠረው›› ከማለት ውጪ ስም ዝርዝሩ ውስጥ
    መግባቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም፡፡ የገዥዎችን ስነ-ልቦና ጠልቆ የተረዳው ማኪያቬሊም ቢሆን ሰዎቹ በእንዲህ አይነት ወቅት
    የሚወስዱትን እርምጃ ገና ድሮ እንደሚከተለው ገልፆት ነበር፡-
    ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ‹‹ህዝባዊ አመፅ በአጉረመረመበት ቅፅበት፣ መሪዎች መጀመሪያ ትዝ የሚላቸው ሀሳብ ሁሉንም ጥሎ መፈርጠጥ እንጂ፣ አደጋውን መጋፈጥ
    አይደለም፡፡››
    አቶ መለስ ዜናዊም በአንድ ወቅት ‹‹የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው›› በማለት ያስተላለፈውን ማስጠንቀቂያ ሹማምንቱ እንደ
    ‹አብሪ ጥይት› የቆጠሩት ይመስለኛል፡፡ በጥቅሉ አገዛዙ በሃያ ሁለት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ፣ ያሰባሰባቸው ባለስልጣናትም ሆኑ የጦር
    አዛዦቹ ‹ሎሌ› ለመሆን ራሳቸውን አሳልፈው መስጠታቸው ሀገሪቱን ለተራዘመ መከራ ማጋፈጡ አያከራክርም፡፡ በተለይም የታጠቀውን
    ኃይል የማንቀሳቀስ ሥልጣን በህግ የተሰጣቸው ጄነራል መኮንኖች፣ ከሲቪል ባለሥልጣናት በባሰ ፍርሃት ውስጥ መውደቃቸው አስተዛዛቢ
    ነው፡፡

     ቁማርተኞቹ…

     የአብዛኛው የኢህአዴግ ባለስልጣናት ልጆች በውጪ ሀገር ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ዓመታትን
    አስቆጥሯል፡፡ በግልባጩ ልጅን በመንግስት ካዝና በውጪ ሀገር ማስተማር ከሙስና ጋር የሚያያዝ መሆኑን ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገና
    አልተረዳውም፤ ወይም መረዳት አይፈልግም፤ እነርሱም ቢሆኑ እንደ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ‹በደሞዛችን ከወር እስከ ወር መድረስ
    እንቸገር ነበር› ብለው ካልቀለዱ በቀር፣ እንዲህ አይነቱን ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቀውን ትምህርት ‹በሚከፈለን ደሞዝ ነው የምንሸፍነው›
    ብለው ሊከራከሩ አይችሉም፡፡

     ሌላው የልጆቻቸው ባህር ማዶ መማር የሚያመላክተው ጉዳይ፣ የቀረፁት የትምህርት ፖሊሲ፣ የትምህርት ጥራትን ማዳከሙንና
    ለእነርሱ ልጆች አለመመጠኑን ነው፡፡ በርግጥ ይህ ቅስም ይሰብራል፤ ‹አስራ ሰባት ዓመት በዱር-በገደል ታግለን አሸንፈናልና፣ ለሀምሳ
    ዓመት ምርጥ ምርጡን ለእኛና ለልጆቻችን› የሚለው ራስ ወዳድነት ከፖለቲካ ብልሽውና በቀር ሌላ ስያሜ ሊሰጠው አይችልም፤ ለብዙሀኑ
    ኢትዮጵያዊ ድንጋይ ከመፍለጥ የማያስጥል ዲግሪን እንደ ፀበል መርጨቱም ቢሆን ትውልድን መግደል እንጂ ሀገርን በዕድገት ጎዳና
    የሚያራምድ ከቶም ሊሆን አይችልም (በነገራችን ላይ የዛሬ ሶስት ዓመት ‹‹ልጆቻችሁ ቻይና ምን ይሰራሉ?›› በሚል ርዕስ ከመለስ ዜናዊ
    ጋር አብረው መቃብር ባወረዷት ‹ፍትህ› ጋዜጣ ላይ በወጣ ፅሁፍ፣ ጥቂት የማይባሉ ባለስልጣናት ልጆቻቸውን ቻይና ልከው በአብዮታዊ
    ዲሞክራሲ፣ በአስተዳደርና መሰል ዘርፍ አሰልጥነው በወራሽነት የማስቀመጥ ዕቅድ እንዳላቸው ተገልፆ እንደነበረ ይታወሳል፤ አሁን ደግሞ
    አብዛኛዎቹ ልጆች ትምህርታቸውን በማጠናቀቃቸው በአፍሪካ ወጣቶች ማህበር ውስጥ ገብተው የአመራር ተሞክሮ እንዲቀስሙ
    እየተመቻቸላቸው መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡ በተጨማሪም ከዚሁ ጋር ይያያዝ አይያዝ ባላረጋግጥም በዚሁ
    ዓመት ‹‹የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር››ን በፓርላማ ለማፀደቅ ዝግጅቱ ተጠናቋል)

     በሀገራችን ነባራዊ እውነታ አንገታችንን የምንደፋው ሚኒስትሮቻችን ባህር ማዶን፣ ቀን የከዳ ዕለት የሚወርሱት "ከናዓን" ማድረጋቸው
    ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የትኛውንም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያነበሩትን ስርዓት አግልለው፣ በውጪ ሀገራት ገበያ መሸፈንን
    መምረጣቸውን ማወቃችንም ጭምር ነው፡፡ አቶ በረከት ስምዖን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› የሚለው መፅሀፉን ለማሳተም ኬንያ ድረስ
    መሄዱ የዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው፤ ያውም በምረቃው ዕለት እንደተሰማው የህትመት ወጪውን ቱጃሩ ሼህ መሀመድ አላሙዲን
    ሸፍኖለትም ነው በዋጋ ውድነት ጭምር ጎረቤት ሀገርን መምረጡን አቃሎ የነገረን (አላሙዲ ግን ይህ ውለታው በምን ተካክሶለት ይሆን?)
    መቼም ‹የዋጋ ንረቱን ያባባሰውን ስርዓት ማን ነው ያነበረው?› ለሚለው ጥያቄ የበረከትን ምላሽ መስማቱ ለብዙሀኑ ኢትዮጵያዊ አጓጊ
    ይመስለኛል፡፡

     እንዲህ አይነት ጉዳዮች ናቸው የሰዎቹን ደንታ ቢስነትና የፖለቲካ ቁመራቸውን ወለል አድርገው የሚያሳዩን፡፡ ህመሙ አጥንታችን ድረስ
    ዘልቆ የሚሰማን ደግሞ በየቀኑ ‹‹በከፈልነው መስዋዕትነት ሀገሪቷን በዲሞክራሲ አጥለቀለቅናት፣ በኢኮኖሚም የተሻለ ደረጃ አደረስናት፣
    አሁንም የታላቁ መሪያችንን ራዕይ አንግብን…›› ጂኒ ቁልቋል የሚለው ተራ ፕሮፓጋንዳቸውን ስንሰማ ነው፤ ምክንያቱም በአንደበታቸው
    ‹‹ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!›› እያሉ፣ በተግባር ግን ደግመው ደጋግመው ሸጠዋታልና (የመሬት ቅርምቱ /Land Grab/ አንዱ አስረጅ
    ነው)፤ የሆነው ሆኖ በጨነገፈ ህልም፣ በተሰበረ ቃል፣ በሸንጋይ አንደበት፣ በወረደ ሰብዕና፣ በሞተ ኢትዮጵያዊነት… ‹እንመራሀለን›
    ማለታቸውን በቸልታ መመልከቱ ሀገርን ወደ ‹ተረትነት› እንዲቀይሩ የመፍቀድ ያህል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

     እዚህ ጋ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ፣ የሰላምና ደህንነት ዋስትና ጥያቄ ላይ መውደቁ ነው፤ ምክንያቱም በብሔራዊ ስሜትና በሙስና
    የሚጠረጠር መንግስት ህዝብን ከጥቃት የመከላከል ገቱም ሆነ ንቃቱ በእጅጉ ዝቅተኛ መሆኑን ከመሰል ደካማ ሀገራት የታሪክ ድርሳናት
    መረዳት ይቻላል፤ ከጥቂት ሳምንት በፊት አልሸባብ በኬንያ፣ ‹‹ዌስት ጌት›› በተባለ የገበያ ማዕከል ካደረሰው ጥቃት ጋር ሙሰኞቹ የሀገሪቱ
    የደህንነት ኃላፊዎች እጅ እንዳለበት ከናይሮቢ ሾልከው ከሚወጡ መረጃዎች መሰማቱ ስጋታችንን ያጠናክረዋል፡፡ ‹ይህ አይነቱ ክህደት
    በሀገራችን ሰዎችስ ላለመደገሙ ዋስትና የሚሰጠው ማን ነው?› ለሚለው ጥያቄም በቂ መልስ ያስፈልጋል፡፡ እዚህም የአልሸባብ አባላት
    ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች የኢትዮጵያና ናይጄሪያ እግር ኳስ ጨዋታ ዕለት የሽብር ጥቃት ሊፈፅሙ አቅደው እንደነበርና፣ ሆኖም
    ለተልዕኮአቸው ያዘጋጁት ፈንጂ በስህተት እጃቸው ላይ ፈንድቶ ማለቃቸውን መንግስት በይፋ መናገሩን እንደ ተጨባጭ ምሳሌ ወስዶ
    ተጨማሪ ጥያቄ ማንሳቱም አግባብ ነው፡- አሸባሪዎቹ ጅምላ ጨራሽ ፈንጂዎችን እንደታጠቁ የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው፣ የፍተሻ ኬላዎችን በቀላሉ አልፈው፣ ከደህንነት ሰራተኞች እይታ ተሰውረው፣ ቤት ተከራይተው ከሃያ ቀን በላይ ሴራቸውን ሲፈትሉና ሲገምዱ ማን
    ተከታትሎ ደረሰባቸው? እንደተባለው በስህተት ራሳቸው ላይ አፈንድተው ሴራቸው ባይከሽፍስ ኖሮ? የጉዳቱ መጠን ምን ያህል ዘግናኝ
    ይሆን እንደነበር ማን በርግጠኝነት መናገር ይቻለዋል? ለወደፊቱስ ይህ አይነቱ እልቂት እንዳይከሰት ስለህዝቡ ደህንነት ግድ ኖሮት ‹ጋሻ
    መከታ› የሚሆነው ማን ነው?

     ቁማርተኞቹ…

     ከባለስልጣናቱ ዝቅ ስንል የምናገኛቸው ‹‹የፖለቲካው ስር ቁማርተኞች›› ደግሞ በመንፈስ ልዕልናቸው፣ በተሰጣቸው ክብር፣ በተናገሩት
    ቃል… የሚወራረዱ (የሚቆምሩ) ወንድም እህቶቻችንን ነው፡፡ በርግጥ ይህ በሽታ ይስተዋል የነበረው (ምንም እንኳ ‹ልንታሰር ስንል፣
    ለጥቂት አመለጥን› በሚል ምክንያት ከሀገር ባይሰደዱም) በኪነት ባለሙያዎች ላይ ነበር (ሠለሞን ተካልኝ፣ ንዋይ ደበበ፣ አሊ ሚራህ፣
    ቀመር የሱፍ… ከስርዓቱ ነቃፊነት ወደ አፍቃሪነት ተቀይረዋል) አሁን ደግሞ በአንድ ወቅት ‹‹ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን››
    ለማስከበር ባሳዩት ቁርጠኝነት ያጀገናቸው ጋዜጠኞችም በተመሳሳይ መልኩ የኢህአዴግን ‹የለመለመ መስክ› ጥላ ከለላነት የሻቱ
    ይመስላሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜው ክስተት እንኳን ብንነሳ የ‹‹አውራምባ ታይምሱ›› ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ አንዱ ማሳያ ሊሆነን ይችላል፡፡ ዳዊት
    ለመሰደድ የተገደደበትን ምክንያት አስመልክቶ ህዳር 23/2004 ዓ.ም ለንባብ በበቃችው ‹‹ፍትህ›› ጋዜጣ ከአሜሪካን ሀገር በስልክ
    በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ‹‹ከሀገሬ እንድወጣ ያደረገኝ ይቅርታውን አንስተውና ሌላም ነገር አምጥተው ዕድሜ ልክ የሚያሳስር እንቅስቃሴ
    ማድረግ መጀመራቸውን በተጨባጭ መረጃ ስላአገኘሁ ነው›› ብሎ ነበር፡፡ አሁን ታዲያ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ምን ተአምር ተፈጥሮ፣
    ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ይሆን? ስር-ነቀል የአቋም ለውጥ ያደረገው ማን ነው? እሱ ራሱ ወይስ ስርዓቱ? እርግጥ ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣን
    ሳነብ ዳዊት የአቋም ለውጥ ማድረጉን በአርምሞ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ከአገሩ ሲሰደድ ‹‹ኢህአዴግ ይቅርታዬን አንስቶ እስር ቤት ሊከተኝ
    እንደሆነ መረጃ ደረሰኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት የለም፣ ስርዓቱ አፋኝ ነው…›› ሲል የኮነነውን አስተዳደር አስመልክቶ
    ለተጠቀሰው ጋዜጣ በሰጠው መግለጫ ‹‹በሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ የተሻሻለ መሆኑን›› ከገለፀ በኋላ፣ በዚህ ምክንያት ወደ ሀገሩ
    ለመመለስ መወሰኑን መግለፁ በበኩሌ እጅግ አስገራሚ የአቋም ለውጥ ሆኖብኛል፡፡ ለመሆኑ ለዳዊት የፕሬስ ነፃነት መከበር ማሳያው ምን
    ይሆን? እርሱ ከተሰደደ በኋላ በጉልበት እንዲዘጉ የተደረጉት ጋዜጣና መፅሄትስ? ሌላው ቀርቶ እስር ቤት ትቶት የሄደው ባልደረባው
    ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ እነለገሰ አስፋው እንኳ ያገኙትን ይቅርታ መነፈጉ ምን ሊባል ነው?

    …እነዚህና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ካገኙ የዳዊት ሀገሩ መግባት ፀጉር የሚያስነጭ አይመስለኝም፡፡ በአናቱም ከሀገር
    ‹‹ከመሰደዱ›› በፊት ‹‹የኢህአዴግ ሰላይ ነበር›› የሚለው ውንጀላ ዘርን ያሰላ ፍረጃ ሊሆን ይችላል እንጂ እስከዛሬ ድረስ በማስረጃ
    የተደገፈ አይመስለኝም፡፡

     ሌላው ዳዊት ቀደም ሲል ስለስርዓቱ አይረቤነትና አምባገነንነት የሰበከበትን የፖለቲካ አመለካከት በምክንያታዊነት ቀይሮ ‹የኢህአዴግ
    አስተዳደር ሀገሬን ይበጃል› ካለ መብቱ ነው፤ ቁማርተኛ የሚያስብለው ማዕተቡን ለባለሟልነት ከበጠሰ ነው፣ ብኩርናውን በምስር ወጥ
    ከለወጠ ነው፤ ያወግዘው የነበረውን የቁማር ፖለቲካ እሱም በተራው ለመተዳደሪያነት ከመረጠው ነው፤ ያቀነቅነው የነበረውን የፕሬስ
    ነፃነት ለ‹እህል-ውሃ› አሳልፎ ከሰጠ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ምንም እንኳ ጊዜ የሚፈታቸው ‹ምስጢረ-ዳዊት› ቢሆንም፡፡

     እርግጥ ነው ‹ምስጢረ-ዳዊት› እስኪገለፅልን ድረስ በዚህ ዙርያ ብዙ ማለት አይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ክስተት ምን
    ጊዜም ጥያቄ ማስነሳቱ፣ ከፖለቲካም ጋር መያያዙና ግርታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ በዚህ መልኩ ከሀገር
    የተሰደዱ ሰዎች የደህንነት ሰራተኞች እንደጉንዳን የሚርመሰመሱበትን የቦሌ ተርሚናል አልፈው ሻንጣቸውን እየገፉ በሰላም
    ቤተሰቦቻቸውን ሲቀላቀሉ አይቼም ሰምቼም አላውቅም (በነገራችን ላይ በዛው ሰሞን አርከበ ዕቁባይም ወደሀገሩ መመለሱን ሰምቻለሁ፤
    በአንድ አውሮፕላን አብረው ይመለሱ ወይንም ለየብቻ መሆኑን አላረጋገጥኩም) እናም ወዳጄ ዳዊት አንድም አሪዞናን ከመልቀቁ በፊት
    የድርጅቱን ‹ቡራኬ› ተቀብሏል፤ አሊያም አዲስ አበባ የገባው የትኛውም ባለሥልጣን ሳያውቅ እንደ ‹ነብዩ ኤልያስ› በእሳት ሰረገላ ተሳፍሮ
    መሆን አለበት፡፡ መቼም አበራ የማነና ታዬ ወልደሰማያት ለስራ ጉዳይ ከሀገር ወጥተው ሲመለሱ፣ ከዚሁ አውሮፕላን ማረፊያ የደህንነት
    ሰዎች ጆሮአቸውን አንጠልጥለው ለ15 እና 20 ዓመታት ከርቸሌ እንዲበሰብሱ ማድረጋቸውን ዳዊት አልሰማም ብዬ አላስብም፡፡ ይህ
    የአገዛዙ እውነተኛ ማንነት እንደሆነም ለእርሱ ይጠፋዋል ብዬ አላምንም፡፡ እናም ‹ዛሬም የሞራል ልዕልናዬን እንደጠበኩ ነው› (‹መናፍቅ
    አይደለሁም) ካለ፣ በአስር ሺህ ማይል ዕርቀት ላይ ሆኖ ‹የሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ ተሻሽሏል› ያለበትን አውድ አፍታቶ ማስረዳት
    የሚጠበቅበት ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም፡-

    ‹‹መንገድ ዓይኑ ይፍሰስ አይባልም ደርሶ
     የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ›› እንዲል አዳም ረታ፣ ዳዊት ሆይ፡- እንኳንም በሰላም ለሀገርህ አበቃህ!

     እንደ መውጫ
     ስርዓቱ የሚያራምደው ርዕዮተ-ዓለም የተሻለች ሀገር ሊፈጥር አለመቻሉ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት የታየ ቢሆንም፣ ዛሬም
    ፖሊሲዎቹንና ዕቅዶቹን የመከለስና የመፈተሽ ፍላጎት የለውም፤ የሀገርን ሀብትም ሆነ የህዝብን ጥቅም ለማስከበር ዝግጁነቱም
    ቁርጠኝነቱም የለውም፡፡ በርግጥ ፍርሃት ‹ሎሌ› ካደረጋቸው፣ ለሽሽት ካኮበኮቡ፣ የግል ጥቅማቸውን እያሰሉ በፖለቲካ ዥዋዥዌ
    ከሚያምታቱ… ‹ክቡራን› ሚንስትሮችም ሆነ ኃላፊዎች መልካም አስተዳደርን መጠበቅ ቂልነት ነው፡፡ ይህ አይነቱ እውነታም ነው
    በመሪዎቻችን ላይ በድፍረት ‹የፖለቲካው ስር ቁማርተኞች› የሚል ውግዘት እንድናሰማ የሚገፋን፡፡ የሆነው ሆኖ ‹የሚበላው ያጣ ህዝብ
    መሪዎቹን ይበላል› እንዲል መረራ ጉዲና ‹ህዝብ›ን ደጋፊ ብቻ አድርጎ ማሰቡ ስህተት ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ቁልቁል ዘቅዝቆ ‹አራጋፊ›
    የሚሆንበት ታሪካዊ ጊዜ ይመጣልና፡፡







    ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
    November 3, 2013

    Saturday, November 2, 2013

    ለእንጀራየ ብዬ !!!


    በሬ ሆይ በሬ ሆይ፤
    ሞኙ በሬ ሆይ፤
    ሳሩና አየህና ገደሉን ሳታይ፤
    እልም ካለው ገደል ወደክብን ወይ።
    ዛሬ ዛሬ “ለእንጀራየ ብየ ወይንኩ ለመኖር” የሚሉ አካሎች ቁጥር እና የአስተሳሰባቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።በተለይም ህግን እናስከብራለን ብለው የቆሙ አካሎች “ለእንጀራየ ብዬ ምንም ይሁን ምን የታዘዝኩትን ሳላቅማማ እፈጽማለሁ” የማለታቸው ነገር ከአሳሳቢ በላይም ነው።እነዚህ አካላት ዛሬ መረቅ የበዛበትን ወጥ በእንጀራ ለመጉርስ ሲሉ ነገና ተነገ ወዲያ የሚሆነውን ማየት ተስኗቸዋል። ዛሬ በያዙት ጠመንጃ ንጹሃን ዜጎችን ገድለው የሚበሉት እንጀራ ነገ ከማይወጡበት ገደል ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል ቆም ብለው ማሳብ ይኖርባቸዋል።
    የህግ አስፈፃሚ አካላት ከእንጀራቸው በላይ የሚኖሩለት ትልቅ ቁምነገር ቢኖር የህግ የበላይነትን ማስከበር ነው። እነዚህ አካላት ከማንኛውም ተራ ዜጋ ተለይተው ህግን ለማስከበር ቃለ ማሃላ ፈፅመዋል። ይህን ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ ዳኛው እና ተመልካቹ ሂሊናቸው ከፍ ሲል አምላክ ካላቸው አምላካቸው እንዲሁም ህዝብ ነው። ከዚህ ቃለ መሃላ በኋላ ህግ አስከባሪዎች በዋናነት የሚኖሩለትም ሆነ የሚሞቱለት ቁም ነገር እንጀራ ሳይሆን የህግ የበላይነት ነው። የምንኖርለትም ሆነ የምንሞትለት ዋናው ቁም ነገር የህግ የበላይነት እንጂ እንጀራ አይደለም ብለው የሚቆሙ የህግ አስከባሪዎች ባሉበት አገር ህግ ተከብሮ ዜጎች በሠላም ተረጋግተው ለመኖር እድሉን ያገኛሉ። ይህ ግን በኢትዮጵያችን እየሆነ አይደለም።
    በኢትዮጵያችን የህግ አስከባሪዎች የሚኖሩለትም ሆነ የሚሞቱለት ዋናው ቁም ነገር “እንጀራዬ!” የሚባል ነገር ከሆነ ሃያ ሁለት ዓመት ሆነው።ህወሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያችንን ድርና ማግ ሆነው እንደ አገር ሊያቆሟት የሚችሉ ዋና ዋና ክሮችን ሲበጣጥስ መኖሩ ከማንም የተሰወረ አይደለም። እየተበጣጠሱ ካሉ ክሮች መካከልም እውነትና ፍትህ ይገኙበታል። የህግ አስከባሪ አካላት ከፍትህና ከእውነት ይልቅ ለሚበላና ለሚጠጣ ከንቱ ነገር የበለጠ ትኩረት የሚሰጡ ሆነው እንዲያስቡ የተደረጉ ይመስላል። በዚህ በህወሃት ዘመን ህግን አስከብራለሁ ብሎ የማለ አካል “ለእንጅራ” ብሎ መሃላውን ያፈርስና ፍትህን ያጎድላል። ”ለእንጀራ”ብሎ በሃሰት ይከሰል ዳኛውም ያለ በቂ ማስረጃ ለእንጀራ ብሎ በሃሰት የእድሜ ልክ እስራት ይፈርዳል። በዚህም ዜጎች ይጎዳሉ ቤተሰብም ይፈርሳል።
    ለእንጀራ ብሎ የገዛ ወገኑን የሚገድል ትውልድ መፈጠሩ አገሪቷን በእጅጉ የሚጎዳ ቢሆንም ህወሃቶች እንዲህ ያሉ ትውልዶችን መፍጠር በመቻላቸው ተሳክቶልናል ይላሉ ።በአንዲት አገር ውስጥ ፍትህ እና እውነት ከሚበላ ምናምን ነገር አንሳ ከተገኘች ያቺ አገር እንደ ባቢሎን ግንቦች ወድቃ ከመበታተን የሚጠብቃት ምንም ዓይነት ዋስትና የላትም።ኢትዮጵያ እንዲያ ነች። ኢትዮጵያ ውስጥ ነገን ተስፋ አድርጎ እና ተረጋግቶ ለመኖር የሚቻልበት ሁኔታ የለም። እንዲህም በመሆኑ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚሰደድባት አገር ሁና የዓለምን ትኩረት ለመሳብ በቅታለች። ኢትዮጵያችን ከቄስ እስከ ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር፤ ከተማሪ እስከ ገበሬ፤ ከበረንዳ አዳሪው አንቱ እስከ ተባለ ባለ ሙያ ሁሉም በአንድ ላይ የሚሰደዱባት አገር ሁናለች።
    ይሄ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ውርደት ነው።ዘረኞቹ ህወሃቶችና በዙሪያው የተሰባሰቡ ዴማጎጎች ግን ይሄን ውረደት ለመረዳት አልቻሉም።
    ለእንጀራው ብሎ ኢ-ፍትሃዊ ደርጊትን የሚፈጽም የህግ አስከባሪ አቅመ ቢስ ወገኖቹን ለስደት ይዳርጋል። ይሄ ሁኔታም አገርን ያፈርሳል እንጂ አይገነባም። በፈረሰ አገር ላይ ደግሞ ለእጀራ ተብሎ የሚሠራ ሥራ አይኖርም። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህግ አስከባሪዎች “እኔ ምን ላድርግ ለእንጀራዬ ብዬ ነው ህገ ወጥ ድርጊት የምፈጽመው” ሲሉ አለማፈራቸው በእጅጉ ያስገርማል። ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን ብለንም እንድንጠይቅ እንገደዳለን። እነዚህ ህግ አስከባሪዎች “ለእንጀራየ ስል ፍትህን አጓደልኩ” ማለታቸው በሌላ መልኩ ሲታይ “ለእንጅራየ ስል አገሪቷ እንድትፈርስ እኔም የበኩሌን ሚና ተጫወትኩ” ማለታቸው መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው ልናሳስባቸው እንወዳለን።
    አንድ ህግ በማስከበር ወይንም ደግሞ የአገርን ደህንነት እጠብቃለው ብሎ የቆመ ዜጋ የገዛ ወገኑን በትእዛዝ የሚገድል ከሆነ ከያዘው ብረት በምን እንደሚለይ ራሱን መጠየቅ አለበት። በምንም ዓይነት መለኪያ “አለቃየ ስላዘዘኝ ሰውን ገድያለሁ” ማለት ከፍርድ ነፃ የሚያደርግ አይሆንም።በኢትዮጵያ ውስጥ አገራችሁንና ዜጎቻችሁን ከጥቃት ለመከላከል ቃል ኪዳን ገብታችሁ ስታበቁ የገዛ ወገኖቻችሁን በማስጨነቅ ላይ ያላችሁ የህግ አስከባሪ አካላት ቆም ብላችሁ እንድታስቡ እንመክራችኋለን። የፈጠራችሁ አምላክ ከተሸከማችሁት ብረት ለይቶ ሰው የሚያደርጋችሁን ፈራጅ ሂሊና የሰጣችሁ መሆኑንም ማስታወስ ይኖርባችኋል።
    እናንተ ለእንጀራ ብላችሁ በገዛ ወገኖቻችሁ ላይ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ድርጊት ስትፈጽሙ ዜጎች በህግ ላይ እምነት እንዳይኖራችሁ እያደረጋችሁ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል። በህግ ላይ እምነት ያጣ ዜጋ እጅግ የከፉ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚስችል አቅም ያለው መሆኑንም መረዳት አለባችሁ።
    እስኪ “የህግ አስከባሪ” አባላትን እንዲህ ብለን እንጠይቃችሁ ፤
    አንድ ወንድ ልጃችሁን ይማርልኝ ብላችሁ ተማሪ ቤት ሰዳችሁታል። ይሄ ብላቴና በትምህርቱ ጎብዞ ወላጆቹን የሚያስመሰግን ሁኗል። እናትም እሰይ ልጄ በርታልኝ እያለች ሃሴት ታደርጋለች። አባትም እንዲህ ነው እንጂ ልጅ እያለ በልጁ ጉብዝና የሚኮራ ሁኗል። ልጁም ከተማሪ ቤት እንደ ወጣ ፈጥኖ ቤቱ የሚደረስ የቤተሰቡ የዓይን ማረፊያ ነው። ከእለታት አንድ ቀን ይሄ ብላቴና በተለመደው ሠዓት አልደረሰም። ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድምጹ የሚሰማ አልሆነም። የዓይኖ ማረፊያ የደስታዎ ምንጭ እና የኩራትዎ ምክንያት የሆነው ልጅዎ አሁንም አልመጣም። ነገሩ ያሳስብዎትና ፍለጋ ብለው ሲወጡ ከደጅ የቆመ አንድ ሰው የልጅዎን መገደል ያረድዎታል።የልጅዎ ገዳይ መንግስት የቀጠረው አነጣጥሮ ተኳሽ መሆኑንም ጨምሮ ይረዳሉ።
    ልጅዎን ተኩሶ ጭንቅላቱን በርቅሶ የገደለው ህግ አስከባሪ ተብየም “እኔ ምን ላድርግ ለእንጀራየ ስል የታዘዝኩትን ፈፀምኩ” ማለቱንም ሰሙ።በዚህ ሁኔታ የሚኮሩበትን አንድያ ልጅዎን አጥተው ሃዘን ተቀምጠዋል። በዚህ ግዜ የመንግስቱ ጋዜጦች የእርስዎ ልጅ የተገደለው ባንክ ሊዘረፍ ሲል ነው ብለው ዜና ይዘው ብቅ አሉ። የዚያ የንጹህ ልጅዎ ታሪክ ላይም እውነት ያልሆነ ታሪክ ተጨምሮበት የብላቴናው ፍፃሜ ሆነ። እርስዎም በዚህ ተቆጥተው የልጅዎን ገዳይ ወደ ፍትህ ለማቅረብ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ። እንዲህ በማድረግዎ መንግስት የአገሪቷን ሠላም ለማስጠበቅ የወሰደውን እርምጃ ተቃወሙ ተብለው እጆ ተይዞ ወህኒ ይወረወራሉ።
    ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ግፉ ተፈፅሞ አይተናል።በዚህ ሁኔታ የዓይኖቻቸው ማረፊያ የሆኑ ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች ደጃቸውን ዘግተው የሚያዜሙት የሃዘን እንጉርጉሮ ሰማየ ሰማያቱን ሰንጥቆ እፈጣሪ ደጅ ደርሷል። ሌሎችም አገር አልባነት ተሰምቷቸው “ለመሆኑ ይህች አገር የማን ነች” እያሉ እየጠየቁ ነው። ህወሃቶች ለዚህ ሮሮና ጥያቄ በቂ መልስ የላቸውም። ወደፊትም አይኖራቸውም። እነርሱ አገራቸው ሆዳቸውና እየዘረፉ የሚያከማቹት የገንዘብ ብዛት እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም።
    እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላችሁ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና የደህንነት ሠራተኞች ይሄ በደል የተፈፀመው በእናንተ ላይ ቢሆን “ለእንጀራየ ብዬ የታዘዝኩትን ፈፅሜያለሁ” ለሚል ህግ አስከባሪ እና እርሱን ለሚያዘው አካል መልሳችሁ ምን ይሆን ?
    በመጨረሻም እንዲህ እንላለን። አንድ መንግስት መፍረስ የሚጀምረው ዜጎች እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ ሲጀምሩ ነው።እነዚህ ጥያቄዎች ለአገር መፍረስ ምልክቶች ናቸው።ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከውዳቂ መንግስታት ተርታ ገብታ ልትቆጠር የበቃችሁ። ኢትዮጵያችንን ለመታደግ የህግ አስከባሪዎች ለህግ የበላይነት እንዲሰሩ እንመክራቸዋለን። ዋስትናችሁ የሚያዛችሁ የጨለማው ንጉስ ህውሃት ሳይሆን ዜጎች በህግ ፊት በእውነት በፍትህ እና በእኩልነት መዳኘት መቻላቸው ነው።ፍትህን ከህወሃት ለሚወረወርላችሁ ፍርፋሪ እንጀራ ብላችሁ ማጓደላችሁን የምትቀጥሉ ከሆነ ፍፃሜያችሁ ከመቸውም ግዜ የከፋ እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ፍትህ ማለት እውነት ነች። እውነትም ፍትህ ነች። እነዚህን ሁለት ገፀ በረከቶችን ልሞተ ለእንጀራ ብላችሁ መርገጣችሁን ካላቆማችሁ የሰደታችሁ ዘመን የጠነክርባችኋል።
    የጨለማው ንጉስ የህወሃት መሪዎች እንደሆኑ ሁሉን ትተው በዝሪፊያ ላይ ተጠምደዋል።የዘረፉትንም ይዘው የሚሰወሩበትን ሥፍራ እየፈለጉም ነው።እነዚህ ዘረኞች “ካለኛ ጀግና የለም” እያሉ የሚዘባበቱበትና ብዙሃኑን ተጭነው የሚኖሩበት ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ ልናስታውሳቸው እንወዳለን። ያለምንም ጥርጥር ህውሃት ከህግ በታች የሚሆንበት ግዜ እየመጣ ነው። በዙሪውያውም የተሰባሰቡ ጉግማንጉጎች የጠዋት ፀሃይ እንዳየው ጤዛ መርገፋቸው አይቀርም። እኛም ለዚህ ግብ እየሰራን ነው።
    የጨለማው ንጉስ ተወግዶ የነፃነት ጎህ በኢትዮጵያ ላይ ሲያበራ “ለእንጀራየ ስል ታዝዤ ንጹሃን ዜጎችን ገደልኩ” ማለት መልስ አይሆንም።የህግ አስከባሪዎች ሆይ ስሙ ! አልመሸም። አሁንም በቂ ግዜ አለ።ፍትህን፤ እኩልነትን እና ነፃነትን በኢትዮጵያ ለማንገስ በሚደረገው ትግል ውስጥ ተቀላቀሉ።ብትወድቁ የሚያነሳችሁ፤ መሸሸጊያ ብትሹ መደበቂያ የሚሆናችሁ ህዝብ እንጂ ዘረኞቹና ዘራፊዎቹ ህውሃቶች አይደሉም። እነሱማ እንደ ሸንኮራ መጥጠው ይተፏችኋል እንጂ መድህን አይሆኗችሁምና አሁኑኑ ከህዛባዊ ትግሉ ግን እንድትቆሙ ደግመን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
    ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

    አንድነት በመንግሥት ላይ ክሥ አሰማ፤ ሪፖርት ሊያወጣ ነው


    Posted: November 2, 2013 in Uncategorized
    0
    ባለፉ ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈፀሙ ቆይተዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና በደሎችን የያዘ ሰነድ በቅርቡ እንደሚያወጣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አስታውቋል፡፡
    የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ዛሬ ማምሻውን ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ካለፈው ሐምሌ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ከ150 በላይ የፓርቲያቸው አመራር አባላትና ደጋፊዎቻቸው መጠለፋቸውን፤ ያለአግባብ መታሠራቸውን መደብደባቸውንና እንግልትና ወከባ የደረሰባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
    የአርትኦት ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ሪፖርቱ በጥቂት ሣምንታት ውስጥ እንደሚወጣ፣ ፓርቲያቸው ለሃገር ውስጥ የፌደራልና መንግሥትና የክልሎች የሥልጣን አካላት፣ ለዓለምአቀፍም የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማትና ለመገናኛ ብዙኃን ቅጂዎችን እንደሚያደርሱ፣ በዌብ ሣይታቸው ላይም እንደሚያወጡት ዶ/ር ነጋሦ ገልፀዋል፡፡
    “ተፈፅመዋል” የሚሏቸውን በደሎች አስመልክቶ ክሥ ይመሠርቱ እንደሆነ ዶ/ር ነጋሦ ሲጠየቁ እያንዳንዱን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ አቅም እንደሌላቸው አመልክተው የፓርቲያቸው በሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን ወደ ሕግ እንደሚሄዱ ጠቁመዋል፡፡
    ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ
    ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ
    በሌላ በኩል ግን “… እስከአሁን ካለው ልምዳችን እንደምናውቀው ፍትሕ የለም፣ ፍትሕ አናገኝም፣ ዜጎች ፍትሕ አያገኙም፤ በተለይ በፖለቲካ ጉዳይ ችግር የደረሰባቸው፤ ወንጀል የተፈፀመባቸው ሰዎች፤ በተጨማም የማይሆን ፀረ-ሽብር ሕግ ወጥቶ ትክክል ባልሆነ ውንጀላ ከሽብርተኞች ጋር ግንኙነት አላችሁ፤ እናንተ ሽብርተኛ ድርጅቶችን የሚደግፍ ድርጅት አባል ናችሁ እየተባሉ የሚንገላቱ፣ የሚታሠሩ ሰዎች አሉ፤ ይህ እየተከሰተ ያለው መንግሥት እያወቀው ነው፤ ፍርድ ቤቶችም አልረዱንም” ብለዋል ዶ/ር ነጋሦ፡፡
    “በአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ግምገማና ዕምነት ኢትዮጵያ እያደገችና እየለማች ነው ወይስ አይደለም?” ተብለው የተጠየቁት የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሦ “ዜጎችን ሁሉ ያላሣተፈ ልማት ዕድገት አያመጣም፤ ሕንፃዎች እየተገነቡ ቢሆንም እኛ የምናውቀው ድሕነት እየበዛ መምጣቱን ነው” ብለዋል፡፡
    የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝን ማስጠንቀቂያዎች አስመልክቶም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ዓይነት ውንጀላዎችን ባሰሙ ቁጥር የበታች ካድሬዎችና የመንግሥቱ ባለሥልጣናት በአባሎቻቸው ላይ የሚያደርሱትን ወከባ እንደሚያበረቱ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡
    ለአንድነት ክሦች ምላሽ ከመንግሥት አካላት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሣካም፡፡

    የተበተኑ የኢትዮጵያ ፍርስራሾች


    October 31, 2013
    ዳኛቸው ቢያድግልኝ
    አገር ማለት ሕዝብ ነው ሕዝብም የሰዎች ስብስብ፡፡ መልክዐምድሩና የተፈጥሮ ሀብት ደግሞ የሰዎችን አኗኗርና አስተሳሰብ የሚቀርጽና ማንነትንም የሚያላብስ ነው። በየመንደሩና አካባቢው ያለው የተለያየ የአኗኗር ሁኔታ የቋንቋና የባህል መስተጋብር ደግሞ ትብብርንና አንድነትን የሚያወርስ እኔነትንና የእኔነትን የሚሰጥ ይሆናል። ኢትዮጵያዊነትም እንደዚያ ነው።
    ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ግን በሁሉም አቅጣጫ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ያቺ የሰውን ዘር ትልቅ የመሆን ተስፋን የሰነቀች ምንጭ ትደርቅ ዘንድ የራስዋ ልጆች እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እያሉ በፉክክር ሊያጠፏት ይሽቀዳደማሉ። የቀጨጨ ትውልድና የጫጨ አእምሮ ያለው ዘር ይጠፋ ዘንድ እውነት ነውና ኩራታችንን ተቀምተን አናሳና ሁዋላ ቀርነታችንን ተቀብለን እንድንጠፋ ተፈርዶብን መጥፋትንም ተለማምደን በዚህም ዳር እንቁም በዚያኛው እግር በእግር እየተጠላለፍን እንዘጭ እንዘጭ የምንልም በርካቶች ሆነናል። ከትናነንት በመማር ፈንታ በትናንቱ እያማረርን ቂም አርግዘን ሞት የምናምጥ በየጎጡ የሰፈርንም ብዙ ነን። “ለመጥፋት መጋፋታችን መቆም አለበት! መኖር ይገባናል! እኛ እኮ ምንጮች፤ የሰው ዘር፣ የእህል ዘርና የስልጣኔ ፈር ቀዳጆች ነን!” ብለን በነበረን ላይ ያለችንን አክለን “የነገን ተስፋ ብሩህ አድርገን ማለፍ የሚገባንና ጮክ ብለን የማሰብ ሃላፊነት ያለብን የኢትዮጵያ ልጆች ነን” የሚል መነሳሳት ያስፈልገናል። ኮሎኒያሊስቶች ባሻቸው ቀጣጥፈው የሰሯቸው አገሮች እንኳን አገር ነን ብለው በሚኮሩበት በዚህ ዘመን የፈረንጅ የእውቀት ቃርሚያ የቀመሱቱ የኛው ልጆች  ኢትዮጵያ የምትባል አገር እኮ አልነበረቺም እያሉን መቃብራችንን ሊያስቆፍሩን ይውተረተራሉ። ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት ይሆን? ኢትዮጵያዊነት ለኔ እንዲህ ይገለፃል ወይም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል የሚሰማኝ ስሜት እንዲህ ነው።
    “ከኢትዮጵያ አፈር ውሀና አየር የተሰራሁ፣ ማለትም የበላሁት የጠጣሁት፣ የተነፈስኩት አየርና የሞቅሁት ፀሀይ ያለኝን ተክለ ሰውነት እውነት ያደረገ፤ አስተሳሰቤን፣ ወግና ልማዴን ስነልቦናዬን ጭምር ያወረሰኝ፣ ሀሳቤን እግለጽበት ዘንድም አፍ የፈታሁበትን ቋንቋ የሰጠኝ የምንነቴ መገለጫ ነው”
    ግን በዚህም አላበቃም ከዚህ በላይ የማንነቴ መገለጫ ትልቅ እውነትም አለና። ኢትዮጵያዊ ነኝ እንድል የሚያደርገኝ ሌላው እውነት ከውልደቴ በሁዋላ የተማርኩት ብቻ ሳይሆን በውርስ የተቀበልኩትምእኔነት ነው እላለሁ። ይህም ውርስ….
    ከእናቴና አባቴ እኩል በእኩል በተቀበልኩት ክሮሞዞም ይት ድርና ማግ የተሸመንኩ ‘ጂን’ በሚሉት ዝንጉርጉር የዘርማንዘሮቼ አሻራ  ጥበብ የደመቅሁ አንድም ብዙም ሰው መሆኔም ጭምር ነው። አያቶቼን፣ ቅም አያቶቼን ከዚያም በፊት የነበሩትና የመጀመርያው ለተከታዩ ሲያወርሱት የቆዩት አሻራቸውን ሁሉ መረከቤና የዚያም ነጸብራቅ መሆኔ ነው ኢትዮጵያዊነቴ።  ከኔ ጋር በአካል ምንም ግንኙነት ሳይኖራቸው ሳላያቸው ሳያዩኝ ግን እነሱን እንድመስል የሚያደርጉኝን መሰረታዊ የሆኑ ባህርያት የተረከብኩበት መገለጫዬ ነው ኢትዮጵያዊነቴ።”
    ስለዚህ እያንዳንዳችን የተሸከምነው ጓዝ ብዛቱ የትየለሌ በመሆኑ ግለሰብም ሕዝብን (ያሉትንና የነበሩትን) ይወክል ዘንድ እውነት ነው።  ዘር ከልጓም ሲሉ፣ የእናት ሆድ ዥጉርጉር ሲሉም ያንን ትልቅ እውነት በሀገራዊ ብሂል የሚገልጹበትና ሳይንሱም ይህንን እውነት የሚመሰክርበት ነው። ለዚህም ነው በሌላ ሀገር ተወልደው፣ የሌላ አገር ማንነትን ይዘው ነገር ግን ምንነታቸውን በሰጣቸው የጂን አሻራ ምክንያት ኢትዮጵያዊ የሚያስብሉ ባህርያትን የሚያንጸባርቁ ወገኖችን የምንመለከተው።
    እንዲያም ሆኖ ግን እኔ የተሰራሁበት አፈር፣ ወሀና አየር የኢትዮጵያው ስለሆነ ዛሬ በዐለም ዙርያ በመዞሬ ያካበትኩት እውቀትና ልምድም ተጨምሮበት እንኳን ኢትዮጵያ ከውስጤ ከወጣች ባዶዬን የምቀር ነኝ። መሰረቴ ሀገሬ በመሆንዋ ያለሀገሬ ባዶ ነኝ። ብዙዎች ላይ የሚነበበውና ምትሀታዊ ሀይል የሚመስለው እውነትም ይኸው ነው። ስለዚህ ሀገራችን ከሌለች ሀገርም ከሌለን የኛ መኖር ካለመኖራችን ጋር አንድ ነው። ጎዶሎ ስሜት ያልተሟላ ማንነት ይዞ መንገታገት! በስደት አካላዊ ምቾት እንኳን ቢኖር የተሰበረ ቅስም የመያዛችን ትልቁ ምክንያትም ይኸው ይመስለኛል። ለዚህ ነው አገር አልፈረሰችም ሲሉኝ ስብርባሪዎችዋን ተበታትነው እያየሁ እንደምን አልተነካችም ልበል? አገር ሕዝብ ከሆነ ሕዝብ ሲበተን አገር እየፈረሰ ነው ማለት ምን ውሸት አለው? የሚያሰኘኝ።
    የኢትዮጵያ ጠላት ኢትዮጵያን ካስተዳደረ፣ የኢትዮጵያ ምሁራን ለሕዝባቸውና ለወገናቸው ማገልገል ተስኗቸው በስደት ለአፍሪካ ሀገሮች፣ አውሮፓና አሜሪካ እውቀታቸውን የሚሰጡ ከሆነ፣ የነገ ሀገር ተረካቢዎች የሆኑ ወጣቶች በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ “በሀገር ተዋርዶ ከመኖር እየሄዱ መሞት” ብለው የሚሰደዱ ከሆነ፤ ወይዛዝርቶች  ወደ አረብ ሀገር ለባርነትና፣ ለግርድና ሲያቀኑ ባዕድ ሀገራት ለም መሬታችን እየተሰጣቸው ሕዝባቸውን ሲመግቡ እንደሞኝ እየተመለከትን እድሜ የምንገፋ ከሆነ አገር ምንም አልሆነች ማለት እንደምን ይቻለናል? እንደ መለስ ዜናዊ “መሬቱ እኮ እዚያው ነው ሱዳኖች መጥተው አረሱት እንጂ” አይነት አባባል እኛም “ኢትዮጵያ እኮ አለች ሕዝብዋ እየተሰደደና እየተፈናቀለ ነው እንጂ …” ብለን በራሳችን ካልቀለድን በቀር እየፈረሰች ያለች አገር ናት።
    ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስንደረደር የካፒቴን ተሾመ ተንኮሉን ቃለመጠይቅ ኢሳት ላይ እየተመለከትኩ ነበር። የደረሰበት በደል በጫካ ሕግ ላይ የተመሰረተ የጠላትነትና የማንአለብኝነት ተግባር ነበር። ለማመንም ለመቀበልም እጅግ የሚያዳግት ነው። እስከዛሬው ቀን ድረስ ለተቀበለው ስቃይ ምክንያት ምን እንደሆነ አልተነገረውም። ሀገሩን ማፍቀሩና ማገልገሉ በወያኔ ዘንድ እንደ ከባድ ጥፋት ከመቆጠሩ በስተቀር። ከዚያ በደል ሁሉ በሁዋላ ደግሞ አገርህ ትፈልግሀለች መባሉ ይበልጥ የሚያቆስል ነው። እንደ ካፒቴን ተሾመ ተንኮሉ አይነት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ ያስተማረቻቸውና የሀገር መከታ የሆኑት ሁሉ ተሰደው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የተገኘውን ስራ እየሰሩ ተበትነው ይኖራሉ። በሙያቸው እየሰሩ ያሉትም ቢሆኑ ለመኖር እንጂ ሀሴትን ለማግኘት እንዳልታደሉ ይታወቃል። በ42 ፕሮፌሰሮች መባረር የተጀመረው ዘመቻ ዛሬ ከየተቋማቱ አገር ጥለው የሚኮበልሉ ምሁራን ቁጥር ከግምትም በላይ ነው። የመውጫ ቀዳዳ አበጅተው አገሬን የሚለውን በርካታ ወገን ከሀገሩ አስጨንቀው አስወጥተውታል እያስወጡም ነው የምንል ከሆነ በዚያች አገር መኖር የሚችለው መከራን ለመቀበልና ለመጋፈጥም ዝግጁ የሆነና ባርነትን በግዱና ምርጫ በማጣት የተቀበለው ነው ማለት ነው። ባለሀገር ነን ባዮቹና የሀገሪቱን ጸጋ እየተቀራመቱ ያሉት ጥቂት የወያኔ አባላትና ተላላኪዎቻቸው ብቻ ናቸው። እነርሱም የቆቅ እንቅልፍ የሚተኙና ሀብት የሚያሸሹቱ ይበዙባቸዋል።
    ትውልድን የሚያንጽና የሚቀርጽ አካል ከሌለ የሚጠብቀን ለባርነትና ለውርደት የተመቸ ዜጋን መተካት ግድ ይሆናል።ሀገረገዢዎቹ ደግሞ ከነርሱ የተሻለ የሚያስብ እንዲኖር አይሹም እንዲሁ እየተንገታገቱ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘመኑ የሚመጥን እውቀትና ሀብት ይዘው የሚፈነጩበትን አገር እየሰሩ ነው። በቁም መፍረስና መሞት ማለትም ይኸው ነው። በተለያየ የሙያ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ወገኖች በውጭው አለም ከእውቀታቸውና ከልምዳቸው ጋር የማይመጣጠን ስራ ሲሰሩ ማየት ትልቅ የሀገር ሀብት ከንቱ መቅረቱን መመስከር ስለሆነ ያማል። በሙያቸው የሚሰሩትም ቢሆኑ ለሀገርና ለወገን የሚገባውን ማድረግ ካልቻሉ በደሉ ያው ነው። በጥቂት የወያኔ ባለስልጣኖች ባለንብረትነት የሚገነባው ሕንጻ ሽቅብ ሲወጣና ወደ ጎን ሲሰፋ ኢትዮጵያዊነት ግን ቁልቁል ሲሄድና የሃገሪቱም ጠረፍ ወደጎን ሲጠብ ማየትስ ምንኛ አሳዛኝ ነው?
    ያለው መንግስት ባመነው መሰረት ብቻ እንኳን በሁለት አመት ውስጥ አራት መቶ ሺህ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ተሰደዋል የሚል ዜና ሰምተናል። ምናልባትም ተመሳሳይ ቁጥር በህጋዊ መንገድ ከሀገር ለቀው ወጥተዋል ይህ ከቶ ምንን ያመለክታል? የኢትዮጵያ ወጣቶች ደም የሰሃራ በረሃን እያጠጣው ነው፣ የውቅያኖስ አሳዎችን እየቀለበ ነው። በየመን ሞት ነው፣ በሊቢያም ሞት ነው። በኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክ የኢትዮጵያ ወጣቶች እስርቤቶችን አጨናንቀውታል። የአለም ደቻሳ የጣር ድምጽ ዛሬን ድረስ ይሰማል። በፈላ ውሃ የተቃጠለችው ሸዋዬ ሞላ ምስል አሁንም አለ፤ የሚደርስላት ጠፍቶ አስፋልት ላይ ደሟ የተነዠቀዠቀው ወጣት ምስል በሃሳባችን ወስጥ ትኩስ ሀዘን አስፍሯል። ኤምባሲዎቻችን ሱቅ በደረቴዎችና ሰላዮችን እንጂ ኢትዮጵያን ጉዳዬ የሚሉ ሰዎችን አልያዘም። ወደ ሞታቸው እየተጋፉ መርከብ ወይም ጀልባ የተሳፈሩ ወጣቶች በላምባዱዛ መርገፋቸው አንገት ያስደፋል። በአንድ ዘመን አረቦች በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰደው እየኖሩ የእለት ጉርሳቸውን ያገኙ እንዳልነበር ዛሬ አረቦች በጋጠወጥ ድርጊት ልጆቻቸንን እህቶቻቸንን ሚስቶችንም ጨምሮ እንደ አሻንጉሊት እየተጫወቱባቸው ነው። ቀኑን በስራና በችጋር ለሊቱን በመደፈር እያሳለፉት መጨረሻቸው እብደትና ሞት ሆኗል። በዚህ አይነት መከራ የሚመጣ ገንዘብን የሚጠብቁ ተጧሪዎች ደግሞ ልጆቻቸውንህቶቻቸውን ወንደሞቻቸውን እና ሚስቶቻቸውን ለዚህ መከራ አሳልፈው ከሰጡ በርህራሄና በመተሳሰብ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊነት አብቅቶለታል።  መከታነት አጋርነትም በችጋር ምክንያት ተሟጥጦ ሄዷል፣ ክብርም እንዲሁ። ወጣቶቻችን እንደ ባርያ እየተሸጡ ነው፣ የኛው ጉዶችም ባርያ ፈንጋይና ደላሎች ሆነው ወገኖቻቸውን  ያሻሽጣሉ። እንዲህ ከዘቀጥን እውነት ኢተዮጵያ የምንላት ሀገር አልፈረሰችምን? በትክክል እየፈረሰች ነው የሚያሰኘኝ የተበታተኑ የኢትዮጵያ ፍርስራሾች በመላው አለም መበተናቸውን መመስከሬና አንዱም እኔው መሆኔ ነው።
    ወድቀናል መነሳት ግን ይቻለናል። ፈርሰናል መልሰን የመጠገን አቅም ግን አለን። ስለዚህ በዚህች በምንወዳት አገራችን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ከየተበተንበት ጉድባ ከየወዳደቅንበት ቀዬ ደልቶን ከምንኖርበት የሰው አገርም ቢሆን ቀና ብለን ተስፋችንን ልናለመልም ቃልኪዳናችን ልናድስ ይገባል። ሀገር የሌለው፣ መሸሻ፣ ማኩረፊያና ማረፊያ የሌለው ሰው ያበቃለት ነው። የተቀበልነው ፓስፖርትና የያዝነው ዜግነት አገሮች በመልካም ፈቃድ የሰጡንን ባልፈቀዱ ጊዜም የሚነጥቁን መሆኑን ልናስተውል ይገባል። ባይነጥቁንም ሁለተኛ ዜጎች ጥገኞችም ነን።
    በኢትዮጵያ ተስፋ እንዳንቆርጥ ማንነታችንን አሽቀንጥረን እንዳንጥል የሚያደርጉ ክስተቶች ስንመለከት ደግሞ ታላቅ  ብርሃን ይሆንልናል። ኢትዮጵያችንን በዚያም በዚህም ቢቀጠቅጧትና እያንዳንዱ ሰው ሀገሩን እንዲጠላ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በቀን በቀን ቢገጥሙት፣ ምርር ብሎት በሰሃራ በረሃም ቢያቋርጥ፣ በኬንያ ቢፈተለክ በሱዳን ቢያቀጥን በቦሌም ቢከንፍ ሃሳቡ አረፍ ሲልለት ኢትዮጵያዊነቱ ይነግስበታል፤ በረሃውን ሲያቋርጥ ድህነት ቢያሸማቅቀውም እንኳን ኢትዮጵያዊ ኩራቱን ይዞ ቀን እስኪያልፍ እያለ የጭለማውን ጊዜ ይገፋዋል። ሰው እንጂ ሀገር አይሞትም የሚል የተስፋ ደወል አድማስ እየሰነጠቀ ግም ድው ኳ ሲል ይሰማዋል። ሰለዚህም ነው ባንዲራውን ሲያሳንሱበት ለብሶት፣ ቆብ አድርጎት፣ የአንገት ልብስ አሰርቶት ጉንጭና ሌላም የሰውነት ክፍሉን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀብቶት አደባባዩን የሚያደምቀው። ሀውልቱን ሲያፈርሱበት ታሪኩን አስውቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ መጽሃፍ አድርጎ ያወጣዋል። በሃይማኖቱ ሊያናክሱት ሲፈልጉ ተቃቅፎ ይሳሳማል። ይህን ስሜት እንደ ምርኩዝ ይዞ ኢትዮጵያን ማዳን ይቻለናል። መንደርደርያና ማኮብኮብያውን ግብ አድርገው ነገር የሚወናጨፉቱ ይህንን ታላቅ ነገርም ሊገነዘቡ ይገባል። የምቾት ፖለቲካ ለማሻመድ ጊዜው የለንም፣ አገር የማዳን ጥድፊያ እንጂ የምርጫና የድምጽ ብልጫ ጊዜ ላይ አይደለንምና ቀዳሚውን ቀዳማይ ዓላማ አድርገን እንጀግን። ወደ ድል ለሚወስደው ጎዳና መንገድ ጠራጊ እንሁን ያም ቢያቅተን እንቅፋት መሆናችን ይብቃ በማለት ኢትዮጵያችን በነጻነት ለዘለዐለም ትኖርልን ዘንድ ጀግነው የተነሱትን እናበረታታ።
    ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁን!