Tuesday, March 19, 2013

ይድረስ ለክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
Click here for PDF
ይድረስ ለክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ለጤናዎት አንደ ምን አሉ ፣ እኔ በጣም ደኅና ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን ፤ በሎስ አንጀለስ ከየሁዎት ወዲህ በኢትዮ ሚዲያ እንዲሁ በጽሑፍዎ አየሁዎት ፤ ጽሑፉን ሳየው ማመን አቅቶኝ ሌላ ሰው በእርሰዎ ስም የጻፈው መስሎኝ ነበር ፤ ሁኖም ደጋግሜ ካነበብኩት በኋላ የእርሰዎ መሆኑን አወቅሁ ፤ ምንም እንኳን በስም በእድሜና በዕውቀት ባልመስለዎትም ዝም ማለት ግን ተገቢ መስሎ አልታየኝም ። በመሆኑም መልስ ለመስጠት ተገድጃለሁ ። ክቡርነተዎ በጻፉት ላይ ተመሥርቼ ምን መልእክት ሊያስተላለፉ እንደ ፈለጉ ባላውቅም ይህ አካሄድ አንድ ነገር ካልተባለ በትልቅ ስምዎ ሊያስተላለፉት የፈለጉትን ሐሳብ በጎ ነገር ሁኖ አላገኘሁትም ፤ ሆን ብለው ሊክዱትና ሊያስክዱት የፈሉጉት እውነት ስለ አለ እውነቱን ማሳወቅ ግድ ይላል እና ብዙኃኑን ከስህተት ለመጠበቅና እርስዎንም ለማስታወስ ስል ይህንን መልስ ጽፌልዎታለሁ ።
መግ
ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነው በክቡርነተዎ ተጽፎ በኢትዮ ሚድያ የተለቀቀው ሁለት ባሕርይ ያለው ጽሑፍ ነው ።
አንደኛው ባሕርዩ ጽሑፉ ውዳሴን ከዘለፋ ጋር ፥ ከፋፋይነትትን ከአንድነት ጋር ቀላቅሎ ፥ ምርቅና ፍትፍት ዓይነት ይዘት እንዲኖረው አድርገው ቀምመውታል ። በእውነት ክቡርነተዎ ይህን ጽሑፍ ሲጽፉ በሰከነ አእምሮ የጻፉት አይመስልም ፤ ከሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር የግል ቅራኔ ኑሮዎ ያን ለማስፋፋት ፥ ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ ለንድነትና ለሰላም ያቀረበውን ጥሪ ለመበከል ያለመ መሆኑን የጽሑፉ አንደኛ ባሕርይ ያመለክታል ።
ሁለተኛው ባሕርዩ የኢትዮጵያውንን የፖለቲካ አስተሳሰብ አልደግፍም በሚል ወዳጆቸዎን ያሳሰቡበትን ባሕርይ ይወክላል ። በስደተኛው ፓትርያርክና በሚመሩት ቅዱስ ሲኖዶስ ላይም ከአሳዳጆቻቸው የተረፈውን ከልክ ያለፈ ዘለፋ ሰንዝረዋል ። የዚህ መልስ ሰጭም በወቅቱ በስብሰባው የነበር ሰው ስለነበር ሳያውቁና ሳይፈቅዱ ሲኖዶሱን እንዲቀበሉ ያደረገዎ መሆኑን አንድን ኣባት በስም ጠርተው ስለ ጻፉ ከዚህ የሚከተለውን መልስ ለመስጠት አስፈለገ ።
ጽሑፉ ክቡርነተዎንም ሆነ ደጋፊዎቸዎን (ገለልተኞችን ወያኔዎችን) እንዲያስተምር እንጂ እንደማያሳዝን ተስፋ በማድረግ ፥ ግን ብዙኃኑን ከስሕተት ለመጠበቅና እውነቱን ለማሳወቅ ብቻ የተጻፈ ነው ።
የጽፉ መግቢያ በድርሰተዎ መግቢያ ላይ ቤተ ክርስቲያን አልተከፈለችም ይህንንም ራሳቸው ካህናቱ ደጋግመው ተናግረውታል ብለዋል ። ከሃያ ዓመት በኋላ ይህንን በመረዳተዎEthiopian-Orthodox-Church-Holy-Synod በጣም ደስ ብሎኛል ፤ እስከ አሁን ይህን ሲሉን ሰምተን አናውቅም ነበር ። እኛም ያልነው ቤተ ስቲያን ተከፈለች ሳይሆን ተሰደደች ነው ሰዎ የአቶ ስብሐት ነጋ አጫፋሪ ሊሆኑ ካልፈለጉ በቀር የሆነውና የተባለውም መንበሯ በጉልበታ የተያዘባት ስደተኛ ቤተ ክርስቲያን አለች ነው ። ሁለት ራስ ያላችሁት እርሰዎና ወያኔ ናቸሁ እንጂ ፥ እኛ አንድ ሕጋዊ ፓትርያርክ በስድት የሚንገላታ ፥ ከሕዝቡ ጋር እንደ ሕዝቡ በወያኔ አምባ ገነን መንግሥት የተሰደደ ፓትርያርክ ያላት መንበሯ በጫከኞች የተወሰደባትና ጥያቄዋን የማይመልሱ ፥ በውድ ሳይሆን በግድ የሚገዙ አምባ ገነኖች የወረሯት አንዲት ቤተ ክርስቲያን አለች ብለን እናምናለን ። በአገር ውስጥም በእንግልት የሚሰቃዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንም በስቃይ ግን ደግሞ ያለውን ሥርዓት እየተቃወሙ የሐገወጥ ሹመትና ተሻሚም መቀበል እንደማይፈልጉ እናምናለን ።
ከእርሰዎ ችግሮች አንዱ እርስዎ እንዳሉት የበፊቱን “የዶክተር ገብረ መድኅንን” ፕትርክና ሳይቀበሉ በሳቸው የሚመራውን ሲኖዶስ ተቀብያለሁ ማለተዎ ነው ። ያ ደግሞ አሁን ካሉበት የሕሊና ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ አድርጎዎታል ። ሕገ ወጥ ፓትርያርክ የበላይ የሆነበትን ሲኖዶስ ተቀብሎ ሰብሳቢውን አለመቀበል ማለትኮ ገለልተኛ በሚለው አዲስ ፍልስፍና ቤተ ክርስቲያኒቱን የንግድ ቤት ለማድረግና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ማለት ነው ። ከሃያ ዓመት በኋላ እንዲህ ማለት በተንኮል የተመረዘ ሐሳብ ነው ። ወይም አንድ ጤናማ አእምሮ የሚያስበው ሐሳብ ነው ብሎ ለመቀበል የሚያዳግት ነው ። ቤተ ርስቲያን አልተከፈለችም ሳትከፈ ተከፈለች ማለት ያሳዝናል ለውን ሲያበቁ ፣ ያኑ ፓራግራፍ ሳይጨርሱ ስለዚህ እስኪያልፍ ድረስ ቅዱስ ገብርኤል እንዳለው ንቁም በበነ» ብለው ጥሪ አቀረቡልን ። ከዚያው ሳያልፉ መዓት እንዳለ መርዶ ይነግሩናል ፤ ታዲያ መዓት ካለ እንዴት ብለን ይህንን መዓት እናሳልፈው ? መልስ ሳይሰጡ ነው መዓቱ እስኪያልፍ እንቁም ብለው መርዶውን ብቻ ነግረውን ያለፉት ። እንዳሉት ቤተ ክርስቲያን አልተከፈችም ግን ተወራለች ። እናም ቤተ ክርስቲያን በስደት ላይ ናት እንላለን ። መዓቱ ይህ ከሆነ እንስማማለን ። ወደ ገለልተኛ ሊወስዱን ከሆነ ጥሪው ወደ ሞት የሚውውስድ በመሆኑ የሚሰማዎት የለም ፣ ራሰዎትንም አያታሉ ።
ዶክተር አንድ ጥያቄ ልጠይቅ ፣ የት ላይ ነው የቆሙት ? እኛም አብረን እንድንቆም የሚጋብዙን ከወያኔ ሲኖዶስ ጋር እንድንሠራ ነው ? ምን እንድናደርግ ነው ? የወያኔን ሲኖዶስ ደግሞ እርሰዎ ራሰዎ አባ ገብረ መድኅንን አባ ማለት እንኳ አልመች ብሎዎት «ዶክተር ገብረ መድኅን» እያሉ የሚጠሯቸውን ሰው ሲኖዶስ እንዴት እንቀበል ? አሁንስ እርሳቸውም የሉም ከአቶስብሐት ነጋ ጋር እንዳይሉ እርሳቸውም ኦረቶዶክስና አማራ ተሰባብሮ ወድቋል የለም ብለዋል የትኛውን ነው እርሰዎ እንድንቆምበት የጋበዙን በአንድነት እንታገልም ብለውናል ፣ ምን ይዘን እንታገል ? አደራዎን ገለልተኛ ሁነን እንዳይሉ ? ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያኒቱን በብዙ መልኩ የሚጎዳ አዲስ ፍልስፍና ነውና ።
መቸም እርሰዎ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተምረው ቤተ ክርቲያን ያለ ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ኦርቶዶክሳዊት ናት ሊሉን አንደማይችሉ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ ። ይህን ካሉ ደግድሞ ሊያልፉት ከማይችሉት “የሕሊና ቀውስ ውስጥ ገብተዋል” ያልኩት ያለምንም ጥርጥር እውነት ነው ። አሁንም እየነሩን ያለው ሲኖዶስ አንድ ነው ያውም አዲስ አበባ ነውና ያን ተቀበሉ ነው ? ወይስ ሲኖዶስ የሚባል ሥርዓት አያስፈልግም ነው ? የአዲስ አበባውን ሲኖዶስ እንደ ሲኖዶስ ከተቀበሉት ወያኔ በጉልበት ያቋቋመው ነው ለምን ይሉናል ። ዝም ብለው ያን ተቀብለን ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ አምባ ገነናዊነት በጉልበት ያለ ሥርዓት ትመራ ነው ? ወይስ እንደ ሌሎች ያለ ክህነት ያለ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንኑር ማለትዎት ነው ? ምን ሁነን እንድንኖር ብለው ነው ጥሪ ያደረጉልን ? እንደሚመስለኝ የቆሙበትን ወይ አላወቁትም ወይም ክደዉታል ማለት ነው ።
በሁለተኛው አንቀጽ የጠቀሱት ስለ ሲኖዶስ ነው ። በዚህ ሐሳብዎ ላይ ቤተ ክርስቲያን የምትከፈልበትን ምክንያት ነግረውናል ። የእርሰዎን ሐሳብ እንደ ወረደ እንመልከተው ቤተ ክርስቲያን መከፈል የሚደርባት በነገረ መለኮት ላይ የተለያዩ ትርጉሞች ሲነ ስምምነ ሲጠፋ ነው በእንደዚህ ያለ ጊዜ ጉዳዩን በጉባኤ ለማየት የቤተ ስቲያን ባለ ልጣትና ሊቃውንት ስብሰባ ያደርጋሉ ስብሰባ ወይም ጉባኤ ሲኖዶስ ይባል ነበር ሲኖዶስ ማለት የቤተ ክርስያንን ጉዳይ ለማየትና ለመሰን የተሰበሰበ ጉባኤ ወይም ሲኖዶስ ማለት ነው
በዚህበእርሰዎ ሐሳብመሠረት
*. ቅዱስ ሲኖዶስ ያን ጊዜ ጉባኤ አድርጎ በዚያኑ ጉባኤው በተደረገበት ስዓት አልቋል አሁን ባለችው ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የለም ማለት ነው
*. ሲኖዶስ የሚሰበሰበው ችግር ሲያጋጥም ብቻ ነው እንጂ በዓመት ሁለት ጊዜ ምልዐተ ጉባኤ አድርጎ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉደዮች የሚመለከቱ ሕጎችንና ደንቦችን የሚያወጣ የቤተ ክርስቲያን የሥልጣን ምንጭ አይደለም? የጉባኤው አባላት የሆኑትም በትውፊታዊ ቀኖና መሠርት በሲኖዶሳዊ ምልዐተ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የተሾሙ ጳጳሳት ሳይሆኑ ለችግር ጊዜ የሚጠሩ በእርሰዎ አጠራር እንደ እርሰዎ ዓይነት ምሁራን ሰብሰብ ማለት ነው?
*. በጠቅላላ የሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የሚያስፈልገው በቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮትና የእምነት መዛባት ሲገጥም ብቻ ነው ። በክቡርነተዎ አባባል መሠርት ይህን ሲኖዶስ ካልነው ለቤተ ክርስቲያን የዕለት ከዕለት ሐዋርያዊ ጥበቃና ሥራ አስፈለጊ አይደለም? ፕሮፌሰር እንዳሉት የክህነት ክቡርነትና የቤተ ከርስቲያን ቁልፍነት ቦታ የለውም ። በዚህ ሐሳብ መሠረት ክህነት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ሁኖ የቤተ ክርስቲያን የበላይ ኃላፊ በመሆን ማንኛውንም ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚጠይቀውን የሚሠራ አይደለም ።
በእርሰዎ ምሁራዊ ሐሳብ መሠረት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ የሥልጣን ምንጭነት አለመኖር ክህነትን ክዶ ከኦርቶዶካሳዊ ሥርዓት ውጭ መሆኑ አያስጨንቀዎትም ፤ ምክንያቱም ሲኖዶስ የሚያስፈለገው በቤተ ክርስቲያን ችግር በተከሠተ ጊዜ ብቻ ነው ። ችግር ካልተከሠተ የቤተ ክርስቲያን የዕለት ከዕለት እምነትን ሥርዓትን ማስጠበቅ ፥ ወንጌልን ማሠራጨት እንደ ተፈለገ ቢሆን ግድ የለም ። ቤተ ክርስቲያን ወደዚህ ሥርዓት አልበኝነት እንድትግባ ወደሚያደርግና የግለሰቦች የንግድ ተቅዋም እንድትሆን ነው የሚጠሩን ።
ፕሮፌሰር ! ሲኖዶስ ዓላማውም መሠረቱም እርሰዎ አንዳሉት አይደለም ። ሲኖዶስ የሊቃውንት ጉባኤ አይደለም ። ቅዱስ ሲኖዶስ ፣ የቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ሕግ አውጭና የምሥጢረ ክህነት የሥልጣን ምንጭ ነው ። ሲኖዶስ ችግር እስኪከሠት ድረስ ተጠብቆ ሳይሆን በቤተክርስቲያን ችግርም እንዳይኖር ስህተትም እንዳይፈጸም አስጠባቂ ተቋም ነው። ሥልጣኑም መንፈሳዊ ከአጭበርባሪነት የጸዳ የእግዚአብሔርን ቤተ እንደ ቤተ ክርስቲያን ጠብቆ የሚያስጠብቅ አካል ነው ። ቀኖና ሐዋርያት አንድ የኒቅያ ቀኖና ሃያዎቹ በሙሉ በዚህ ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው ። ይህን የሚያስተባብሉት ከሆነ ፍትሕ መንፈሳዊን አንቀጸ ጳጳሳትን ቢመለከቱ መልካም ነው ብየ አሳስበዎታለሁ ።
ጽሑፈዎን እያነበብኩ ስሄድ ተዝቆ ከማያልቀው እውቀተዎ ሊያካፍሉን ፈልገው ነው ብየ ስጓጓ ነፍገው ይሁን አውቀው በማይታወቅ መንገድ ለወጥ ብለው ወደተዘባረቀ መንገድ ገቡብኝ ። በዚያው ሊቅነተዎ ሰውን ለማሳሳት ያኑ የተሳሳተ የሲኖዶስ አወቃቀርና የሥራውንም ኃላፊነት ገልጠዋል ። እንዳልሳሳት እርሰዎም እንዳይከሱኝ የራሰዎን ድርሰት እንዳለ ላስቀመጥለዎ
ሲኖዶሱ የቀረቡለትን አስተያቶች በሰፊው መርምሮ አንዱን ሲመርጥ ሁሉም የተስማሙበትን አለዚያም በዲሞክራ ሥርዓት በእጅ ብልጫ ያለፈውን ሁሉም ከተቀበሉት በቤተ ክርስቲያን መከፋፈል አይፈጠርም ብለው የቤተ ክርስቲያንን ነገረ ሃይማኖት ከእውነት ይልቅ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በመውሰድ ሊቅነተዎንና የመብት ተቆርቋሪነተዎን ሊያሳዩን ፈለጉ.።
ፕሮፌሠር ምን ነካዎ ! በመሠረቱ እምነት የሚመረጠው በቀረበው አስተያየት ሳይሆን በታመነው እውነት ላይ ነው ። የሚቀርበውም የሰው አሰተያየት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ በተቀበለቻቸው በእግዚአብሔር መንፈስ በተጻፉት በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝኖ እውነትነቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው ። ስምምነቱም ያን እውነት በመካድና በማመን ላይ ይሆናል ። በዚህ ላይ የሚሠራው እጅ ብልጫ ሳይሆን የታመነው እውነት ነው ። ያን እውነት ያልተቀበለ ከአንድነቱ ይለያል ማለት ነው ። ይህም ማለት ፣ ያን እውነት ያልተቀበለ ሰው እውነቱን ከካደበት ሰዓት ጀምሮ የክርስቶስ አካል ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን ይለያል ።
በዚሁ ክፍል ላይ የገለጿቸው ሰዎችም የተለዩት ፥ በእጅ ብለጫ ተበልጠው ሳይሆን ፥ እውነት የሆነውን ስለ ካዱ ነው ። ሲለዩም እንደ ቤተ ክርስቲያን ተቈጥረው ሳየሆን እንደሌሉ ተቈጥረው ነው ። በዚያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ተከፈለች አልተባለም ። የተባለው እውነትን የካዱት ከቤተ ክርስቲያን ተለዩ ፥ ወይም ቤተ ክርስቲያን እውነትን የካዱትን ለይታ ፥ ትምህርቷን በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተውን እውነት በማስጠበቅ ቀጥላለች ። ከዚህ የተነሣ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ጉባኤያት ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ተብለው ክርቲያን የሆነው ሁሉ ተቀብሏቸ ይኖራሉ ። የነዚህን ጉባኤያት ከሌሎቹ ሲኖዶሳዊ ጉባኤያት የሚለው የአራቱ መናብርት የሲኖዶስ አባላትና መሪዎቻቸው በአንድ ላይ መገኘታቸውና በታመነው እውነት አንድ መሆናቸውን ማረጋገጣቸው ነው የጉባኤው አባላት በሙሉ ሊቃነውንት ቢሆኑም ግን የየአሉበት ክልል ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ናቸው ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ያለ ሲኖዶስ ቤተክርስቲያን አትሆንምና ነው።
ፕሮፌሰር፤ እንደሚታወቀው በአለንበት ዘመን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አባል የሚሆኑት እነዚያን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት የተቀቡሉት ናቸው ። ይህ ውሳኔ የተወሰነው እርሰዎ አንዳሉት ችግሩ በተከሠተ ጊዜ በተሰየመ ጉባኤ አይደለም ። ቤተ ክርስቲያን ስትመሠረት ጀምሮ እነቅዱስ ጴጥሮስ ያስተማሩትን ትምህርት የተቀበሉ ሐዋርያት ያስተማሩትን ተከትለው እነሄሬኔዎስ እነአግናጥዮስ ይዘውት የመጡትን ትምህርት ሲያስጠብቅ የቆየና በነበሩት አራት አበይት መናብርት ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ የነበሩ አባቶች ጉባኤ ነው ። ይህ ነው ሲኖዶስ የተባለው እንጂ እርሰዎ እንዳሉት በዲሞክራሲ የተሰበሰበ ሸንጎ አይደለም ። ከዚህ ላይ መብት የሚባል ጉዳይ የለም ይህ እምነት ነው በእምነት ውስጥ ደግሞ መብትን አስጠብቃለሁ ብሎ እምነትን የሚጻረር ተግባር መፈጽም ስሕተት እንጅ መብት አይባልም።
የችግራችን ንጭ የተባለው ሁለተኛው የተሻለ ይሆናል ብየ ስጓጓ የባሰ እያተራመሱት ሄዱ ። በዚያው በተራቀቀው የሊቅነት አባባልዎ እውነት ያልሆነ ነገር አመሥጥረው አስነበቡን። የችግር ምንጭ ያሉትን ዘርዝረዋል ቃሉን እንዳለ በትምህረተ ጥቅስ ስናስቀምጠው ።
የዛሬው ችግራችን ይህ አይደለም የዛሬው ችግራችን ሁለት ፓትርርኮች በአንድ ዘመን መኖር ነው በአንድ አካል ላይ ሁለት ራስ ፓትርያርኮቹ እንዱ ኢትየጵያ አንዱ ሪካ ሁነው ያንኛውን ትታችሁ እኔን ተከተሉ ስለ አሉን ግራ ተጋባን ግማሾቻችን አንዱን ግማቻችን ሌላውን ተከተልን ሌሎቻችን ሁሉንም አልተከተልንም ኖም የአንዱ ፓትርያርክ ተከታይና የሌለው ፓትርያርክ ተከታይ ወይም ገለልተኛ የሃይማኖት አማቾችና ወንድም አማቾች ናቸው እንዲውም ቤተ ክርስቲያን የምባለውም ሕዝበ ክርስቲያኑን ኤክሊስያን ለማመከት ነው ባኤ ዘሐዋርያት የሐዋርያት ስብሰብ የተባለውም ለዚህ ነው
ከዚህ ሐሳብ ውስጥ ሊያወጡ የፈሉጉት ሁለት ነጥቦችን ነው ። እነዚህም
* በላይ ለላይ የሚቃወሙትን ግን ደግሞ በልበዎ እንዲጸድቅለዎ የሚፈልጉትን የነአቶ ስብሐት ነጋን ሲኖዶስ ሕጋዊ ማደርግ ። ያን ሕጋዊ ካደረጉት አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ ምን ማለትዎ ነው ፕሮፌሰር ? ሲለዎ አይደለም ገለልተኛ ነኝ ለማለት ነው ። በሁሉም መንገድ ሁለቱን ቀኖና ጣሾች ማለትም በጉልበት ሥልጣን የያዙትንና ያለ ሕጋዊ የክህነት ውክልና በገለልተኝነት ካህን ነን የሚሉትን ለማስከበር አስበው ነው ።
* እንደ አለመታደል ሆነና ጠበቃ የቆሙላቸው ሁለቱንም ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አይቀበላቸውም ። ማለትም ሦስቱ ጉባኤያት የወሰኑትን የእምነት መግለጫ አሐቲ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ጥምቀት የሚለውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት የካዱና ያለተቀበሉ ማለት ነው ። በሦስቱ ጉባኤያት የተወሰነው የሃይማኖት መግለጫ ብቻ አይደለም ፤ ቤተ ክርስቲያን ትመራበትና ትጠብቀው ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጭምር ነበር እንጂ ። ቀኖናውም “እንደ ዶክተር አባ ገብረ መድኅን” ያሉት ዘመንተኞች በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሥልጣን ቀምተው ለተጠቃሚ ከሰጡና ከተቀበሉ ፣ ሥልጣናቸውና ክህነታቸው እንደማይሠራና እንደ ተወገዘ ሁሉ ፥ ያለ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ሲኖዶስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያን ያቋቋመና የቊርባን ሥርዓት የሠራ ለዘላለም የተወገዘ የተለየ ነው ስለሚል ነው ።
* እንደ ገና አስረግጦ ለመናገር ፣ ቤተክርቲያን አንድ ናት ፥ ፓትርያርኩም አንድ ናቸው፥ የአዲስ አበባው ሲኖዶስና አባላቱ እርሰዎም አንዳሉት የወያኔ ተላላኪዎች ናቸው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን አይወክሉም ብለን እየተናገርን ይኸው ሃያ ዓመት ሞላን ። እነሱን የወከላቸውን የዲስባባውን ሰብስብ እንደ ሲኖዶስ ስለሚቀበሉ ሁለት ሲኖዶስ ከማለታቸውም በላይ ሕጋዊውን ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን ከፋፋይ አድርገው ሲናገሩ ተደምጠዋል ።
ወያኔ የራሱን ወንጄል ለሌሎች ሰጥቶ መክሰስ አዲስ አይደለም ። አዲስ የሆነው የእነሱ ተቃዋሚ የተባሉት ፕሮፌሰር ያን ማራገበዎ ነው ። በተለይም አሁን ሕዝቡ አንድ ለመሆን ዓይኑን ባነሣበት ጊዜ ይህን ሐሳብ ያነሱሡበት ምክንያት ምን ለማግኘት እንደ ሆነ እርሰዎና ወያኔ ካልሆናችሁ ሌላ ሰው ሊያውቀው አይችልም ። እውነት ፊት ለፊት ተጋልጦ እያለ የወያኔ ባለሥልጣናት ሳይቀር ሊክዱት ያልቻሉበት ደረጃ ደርሶ እያለ ፣ እርሰዎ ሁለት ሲኖዶስ እያሉ የሚማፀኑት ምን አግኝተው ነው ?
*. እንዲያውም ቤተ ክርስቲያን የሚባለው የምእመናን ጉባኤ ነው ። በማለት “ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ኤክሌስያ” የተባለውን በመተርጎም የክህነትን አስፈላጊነት ያለ እፍረት ለመካድ ሲሉ በቻ ቃሉን ያለ ቦታው ተጠቅመዋል ። ‘ኤክሌሲያ’ የሚለው ቃል የሚያገለግለው ለማንኛውም ለተለየ ጉባኤ ነው ። የሮማ ዜጎች የሕዝብንና የአገርን ጉዳይ በሚመለከት የሚጠሩት ጉባኤም ኤክሌስያ ይባል ነበር ። ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሲውል ግን ፥ በክርስቶስ ጥሪ የተደረገላቸው ምእመናን ። በጳጳስ መሪነት በሚካሄድ የአኰቴተ ቊባን ፥ ወይም የሥርዓተ ቅዳሴ የሚካሐድ ጉባኤ ሲሆን ነው እንደሱ ካልሆነ ፣ እርሰዎ ያሉትን ትርጉም ሊሰጥ አይችልም ። ስለ ሆነም እርሰዎ ቤተ ክርስቲያን የሚሉት በሊቀ ጳጳስ ፈቃድና መሪነት በሚካሄድ የቅዱስ ቊርባን አንድነት ያልተመሠረተ ከሆነ ቤተ ክርስቲያንን አይወክልም ፣ ጉባኤ ዘሐዋርያት የሆነቺውን ቤተ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም ፥ አይደለምም ።
የካህናት ተልእኮ ድርሰተዎን እያነበብኩ ስሄድ ለቤተ ክርስቲያን ምን እንደሚመኙላት እና የካህናትን ሥራም እንዴት እንደደለደሉት ተረዳሁ ። ለምን ሲኖዶስን መቀበል እንዳቃተዎም አስተዋልኩ ። ችግረዎም የተመሠረተው ከዚህ ላይ ነው ።ያስቀመጡትን አብረን እንመልከተውና ለካህናቱና ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የመደቡላቸውን ሥራ አብረን እናብራራው ።
ካህናቱ ከላይ እስከ ታች ያሉት ልዑካን ጸሎት በመምራት ሃይማኖት በማስተማር ሕዝበ ክርስቲያኑን እንዲያገለግሉ የተላኩ ናቸውብለዋል ። እንዴት የተራቀቀ ፍልስፍና ነው ! የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሲበላሽ የሚያስተካክሉት ምእመናን ናቸው ማለት ነው ። የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አልባ ብትሆን ሥርዓት የሚያስይዝ አካል ሲኖዶዶስ አስፈላጊ አይደለም ማለት ነው ። ለዚህ ነው ለካ ከሁሉም አይደለንም የሚሉን ።
ካህናት ከላይ እስከ ታች ማለት ፣ ሊቃነ ጳጳሳት ፥ ጳጳሳት ፥ ቀሳውስት ፥ ዲያቆናት ማለት ነው ። የተሾሙ ሕዝብን እንዲላላኩ እንጂ እግዚአብሔርን እንዲያገልግሉ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዲመሩ ፥ እምነትን እንዲያስጠብቁ አይደለም ? እንዲህ ዓይነት ኦርቶዶክስ ምንአልባትም ከእርሰዎ አእምሮ የመነጨ አዲስ ኦርቶዶክስ ካልሆነ በቀር ፥ እስከአሁን በታሪክ አልተከሠተም ። የኦርቶዶክሳዊነትን መገለጫ በዚህ ጽሑፍ ማጠቃለያ እንመልከታለን አሁን ራሰዎ ወደ ጠቀሱትና የምእመናን ኃላፊነት ወዳሉት እንመለስ ። በዚህ ክፍል እንደ ተለመደው መልካም ምክር የሚሰጡ ይመስላል ፣ ግን ምክርዎ ወደ ጨለማ የሚወስድ ክህደት ነው ። ድርሰተዎን አብረን እንመልከተው ።
ይህ ብቻ ሳይሆን በመብታችን ተጠቅመን መፍት መፈለግና ውዝግቡን ማብረድ ግዴታችን ነው መፍት ከተወዳዳሪዎች አይጠበቅም ሁኖም ተከለች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሊኖራት ስለማይገባ አንዱን ብቻ እንከተላለን ያንን ማድረግ ንችለው ሜትና በምኞት ሳይሆን የችግሩ መን ግልጽ ሲሆንል ነው” ብለዋል ።ገለልተኛ ነኝ ብለውን እያለ የት ላይ ሁነው ፥ በየትኛው ዓላማ ቁመው ነው ይህን መፍትሔ የሚሰጡን ? ሌላ ፓትርያርክ ያስቀመጡልን አለ ? ወይስ ከሁሉም የሌለ እንምረጥ ሊሉን ይሆን ? ሁለተኛው እንከተለው የሚሉን የትኛውን ነው ? ከላይ እንዳልኩት በእኛ እምነት አሁንም ሁለት ፓትርያርክ አለ ብለን አናምንም ሲኖዶስም እንዲሁ ። የእርሰዎን ብንሰማ መልካም ነው ይህንን በር ስላልዘጉት ባቀረቡልን ግብዣ መሠረት የችግራችን መንሥኤ ያሉትን መመልከት አስፈላጊ ስለ ሆነ እኔም በመስማማት ችግሩን አብረን እንመልከተው ።
እንዳሉት የወያኔን ጥፋት ሁሉም ስለሚያውቀው እኔም አልሄድበትም ፣ የፓትርያረኩን በግፍ ከመንበር መውረድ ፥ የዶክተር አባ ገብረ መድኅንን በሕገ ወጥ መንገድ መሾም ፣ሁሉም ያውቀዋል ፤ መዘርዘሩም ጊዜ ማጥፋት ነው ። በዚህም ክፍል እርሰዎን ያሳሰበዎ ፥ ግን መልካም ያልሆነ ሐሳብ ተጠቁሟል ። እርሱም የሚከተለው ነው ።
አባቶች መነኮሳት ከጸሎታቸው አንዱ ለስምህ ሰማ የምንሆንበትን አጋጣሚ ፍጠርልን የሚል እንደ ነበረ መንኩሴው ፓትርያርክ ወያኔ ገፋቸው ሰማዕትነቱን ባይገፉት ክብሩ ለቤተ ክርስቲያኗ ለመነጋቸውም ከሁሉም ይልቅ ለራሳቸውም ይሆን ነበር ብለዋል ።
ይህ በረቀቀ የሥነ መለኮት ቋንቋ የተቀመመ ክፉ ሐሳብና ፣ በሌላ መልኩ ብናነበው እኒህ ስደተኛ ፓትርያርክ በሕይወት ኑረው የስደት ሰማዕትነት ከሚቀበሉ ይልቅ ቢሞቱ ኑሮ ፥ ወያኔም አይጋለጥም ነበር ፣ ይህ ገለልተኛ መባልም ትዝብት ውስጥ አይገባም ማለት ይሆናል ። ሳነበው ልቤ በጣም አዘነ ፣ እውነት ለመናገር እንባም አነባሁ ፣ እንዴት ከአንድ በዓለም እውቅና ካገኙ ታላቅ ምሁር ይህ ስሜት ሊመጣ ቻለ ? ምክንያቱ ምንድን ነው ? እውነት ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስደት የሰማዕትነት አንደኛው ክፍል መሆኑን ለመረዳት ተስኗቸው ነውን ? ምን ይሆን ? አልኩና እርሰዎ የጻፉትን እያነበብኩ በአርባዎቹ ዓመታት በጨካኞች የተገደሉትን ንጹሑን አባት ፓትርያርክ ቴዎፍሎስንና ፥ ንጹሐን ወገኖቼን ሁሉ አሰበኳቸው ። ያ ሁሉ ወገኔ አልቆ እግዚአብሔር በተአምር አውጥቶ ለራሳቸው ሳይሆን ለሕዝቡ ተስፋ ይሆኑ ዘንድ በስደት የሚንከራተቱትን አባት ቢሞቱ ኑሮ ብሎ ሞታቸውን መመኘት ምን ለማለት ይሆን ?
አገሪቱ እኮ እርሰዎ በመጽሐፍዎ ጨካኝ ብለው ከገለጡት ከዘርዓ ያዕቆብ አንሥቶ አሁን እስካለነው ትውልድ ድረስ በታረዱ ቅዱስንና ንጹሓን ወገኖች ደም የጨቀየ ታሪክ ያላት አገር ናት ? ለዘመናት የፈሰሰው ደም እየጮኸ መልስ ሳያገኝ ዛሬ ያሉትን ቢሞቱ እንዴት ክብር ነበር ብሎ መመጻደቅ ምን ይባላል ።
ፕሮፌሰር እውነት እኒህ ቅዱስ ፓትርያርክ ቢሞቱ ሰማዕት ናቸው ይሉ ነበር ? እስቲ እውነቱን ይናገሩ ። በክፉዎች መሰቃየትን እርሰዎም አኮ ቀምሰውታል?። እንዴት እንደ ተሰቃዩ በመጽሐፍዎ ላይ የተጠቀሙት ቋንቋ ፥ ይህን እየጻፍኩ ትዝ አለኝ። እንዴት ዘመድ ወዳጆቸዎ እንደ ተሰቃዩ ገልጸውታል ፣ ምነው እነዚያ ብዙዎቹ የእርሰዎ ጓደኞች የነበሩት ስድሳዎቹ አምልጠው አሁን ባስተማሩን ፣ ፕሮፌሰር ፣ እርሰዎ ደርግና ወያኔ የፈጀውን ወገን አንድ ቀን ሰማዕት ነው ሲሉ ሰምቸዎት አላውቅም ? ፕሮፌሰር አስራትን ጭምር እኒህን ቅዱስ አባትም ከእነዚያ ለይተው እንደማይመለከቷቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ። የእርሰዎ መኖር ለቤተ ሰበዎ ፤ ለትውልዱና ለቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደሚጠቅም እስቲ ይመልከቱት ፕሮፌሰር ሆይ ! በዚህ ሐሳብዎ ወያኔ ካልሆነ በቀር ሌላ ማንም አይስማማም ።
ሰማዕትነት መች በግፍ በመሞት ብቻ ሆነ ፣ ስደትም እኮ የሰማዕትነት አንዱ ክፍል ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ የእምነት አርበኞችን ዝርዝር በጻፈበት አንቀጹ የተገለጸው የሰማዕትነት ዓይነት ፣ በበርሀ በመንከራተት ፥ ዋሻ ለዋሻ በመዞር ፥ ሀገር ለሀገር በመሰደድ ፥ በእሳት በመቃጠል ፥ በመራብ የሚል አይደለምን ? እና የቀድሞዎቹ ይህን እድል በስደት ካገኙት የአሁኖቹ የሰማዕትነት እድል በሞት ካልሆነ በስደት አያገኙም ያለው ማን ነው ? የትኛውም የሥነ መለኮት ተማሪና አስተማሪ ሊቅ የሆነ ሁሉ ከእርሰዎ በቀር ይህን እውነት ይቀበላል ። ችግሩ የእርሰዎም ሆነ የእርሰዎ መሰሎች ሰማዕታት ለሆኑ ሰዎች ሰማዕትነት የሚያስገኘውን የመከራ ዓይነት ሳይሆን ፣ እናንተ ልታደርጉት ያልፈለጋችሁትንና የማትፈልጉትን ሰማዕትነት ሌላ ሰው ካልሞተ ክብር አያገኝም ብላችሁ ማመናችሁ ፥ እንደ ኔሮን በሚሞቱ ቅዱሳን መደሰት መፈለጋችሁን ያሳያል ።
ይህንንም ትመኛላችሁ ትሰብካላችሁም ፣ እንዲህ ከሆነ በደም ተነክረው ሲቃስቱ በነበረ ጊዜ ላነሣዎ ሰው ምነው ተወኝ ሰማዕት ልሁን አላሉና አላሳዩንም ። ለእኔ ሐሣባችሁ እንደ ገባኝ ከሆነ የእናንተ ችግር የሰማዕትነት ክብር የሚያሰጠው የመከራ ዓይነት ሳይሆን ፣እናንተ ሰው ካልሞተ አንደሰትም ብላችሁ የደመደማቸሁ በመሆናችሁ በውስጣችሁ ያለው ክፉ ኔሮናዊ ሐሳበ ነው እንጅ ሌላ ሊገለጥበት የሚችል ቋንቋ የለም ።
ድርሩና ስጋተዎ እንዲህ እንዲያስቡ ያደረገው በሚቀጥለው ክፍል የገለጹት ሐሳብ ነው ። በሚቀጥሉት ተከታታይ ክሎች እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሐሳቦችን በአንድ ላይ እየገለጹ ስለ ሄዱ እኔም እንደ ቅደም ተከተላቸው በጥንቃቄ ለማየት እሞክራለሁ። በድርድሩ ላይ ያዩትን ሐሳብ ስለ ወያኔ ምንነት የገለጹትን እስማማለሁ ቢሳካ አካሄዱ ምን ይሆናል የሚለው ግን አካሄዱ እርሰዎ ባዩት መልክ አይደለም ።ይታይ የነበረውም እንዳሉት ሀገራዊ ጉዳዮችም ተጠቃለው ነበር ። የወያኔ መንግሥት አስቀድሞ በሩን ጥርቅም አድርጎ የዘጋው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ መጨረሻ ምን እንደሚጠይቅ ስለ ገባው ሳይሆን አይቀርም ብየ አስባለሁ ። በዚህ ክፍል አንዳስብበት ያደረገኝ ነጥብ ፓትርያርኩ ከገቡ ወያኔ ካድሪ ያደርጋቸዋል ትግላችንንም ያዳክማል የሚዳከመው ፓትርያርክ ስለምናጣ ሳይሆን ወያኔ ከመንበራቸው ላይ አስቀምጦ መግለጫ እንዲያወጡ እያደረገ በዓለም ፊት አፋችንን ስለሚያዘጋን ነው።
ግሩም አባባል ነው እንግዲህ እርሰዎን ሁለት ጥያቄ ልጠይቅ ይፈቅደልኝ ። አንደኛው እርሳቸው ከገቡና እንዳሉት ወያኔ ከተጠቀመባቸው ፓትርያርክ የማናጣው ስለምንሾም ነው ? ወይስ ሌላ የተሾመ አለ? ሁለተኛው ቅዱስ ፓትርያርኩ ከዚህ ካሉና የእርሳቸው መኖር ስደተኛውን የሚያጠናክር ከሆነ ለምን እስከ አሁን ዝም ብለው አሁን ይግቡ በተባሉ ጊዜ ይህን ሐሳብ ሊያቀርቡ ቻሉ ? በሌላ በኩል እርሰዎ ያሉባቸው ዓለም አቀፍ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አንድነቱ እንዲከናወን ጥሪ ሲያደርጉ የነበረው ገለልተኛው ጭምር ምን ለማትረፍ ነበር ። በሌላ መልኩ ወያኔ ለራሱ ጥቅም እንደሚጠቀምባቸው ካወቁ እርሰዎ ለምን ሞታቸውን ተመኙ ወያኔ በሕይታቸው ሲጠቀም እርሰዎ ግን ገለው መጠቀም ፈለጉ ምን ደም የማፍሰስ እርግማን ያዘዎት ዶክተር?
ቅዱስ ሲኖዶስ ቀጣዩ ክፍል የእርሰዎን ማንነት በግልጽ የሚያሳየው ስለ ሲኖዶስ የገለጡበት ነጥብ ነው ። ይህም ነጥብ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ እውነት የሆነውን ዐቢይ ጉዳይ ክደው በተከሸነ ቋንቋ ያስቀመጡትን በአንድ ቃል ብንገልጠው ፣ ሲኖዶስ ያለው አዲስ አበባ ነው ፥ ያም የወያኔ ነው የሚል ሲሆን ፣ ይህን ተቃውሞ ቢገጥመው ሁሉም ሕገ ወጦች ናቸው ። ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ የላትም ማለት ነው ። በእርሰዎ ሐሳብ መሠረት ሁሉም ሕገ ወጦች ናቸው ። ስለ ሆነም ቤተ ክርስቲያን ያለክህነት ነው ያለችው ማለት ነው? ክህነት ከሌላት ቊርባን የላትም ማለት ነው? እንደ አጋጣሚ እርሰዎን ብዙ ጊዜ ቅዱስ ቊርባን ሲቀበሉ አይቻለሁ ። እንዴት አድርገው ነው ክህነት በሌለው ቀዳሽ ቅዱስ ቊርባንን የተቀበሉት ? ለታይታ ነው ማለት ነው? ወይስ አያምኑበትም?
ምን አልባት ክህነት የሌለው ካህን አለ ብለው እንዳይወቅሱኝ ፣ አንድ ካህን ክህነት አለው የሚባለው በሕጋዊ ሲኖዶሳዊ ምልዐተ ጉባኤ በተሾመ ጳጳስ ክህነትና ያገልግሎት ፈቃድ የተቀበለ ካህን ሲሆን ብቻ ነው በኦርቶዶክሳዊ ቀኖና መሠረት ካህን ሊሆንና ሊባል የሚችለው ።ፕሮፌሰር የገለልተኛና የወያኔን ጉዳይ አስፈጽማለሁ ብለው በሚያደርጉት ጥረት ምክንያት ትዝብት ላይ እየወደቁ መሆኑን በአክብሮት ልገልጽለዎት እወዳለሁ ።
ይህ ሐሳብ በጣም አስፈላጊ ስለ ሆነ ቃል በቃል መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ። በመሆኑም እንደሚከተለው እንመለከተዋለን ። ለአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚኖራት አንድ ሲኖዶስ አንድ አመራራ ብቻ ነው ይህንን ሕግ ሁለት ኖዶስ የፈጠሩት አዲስ አበባ ሉት ናትና ስደተኞቹ ካህናት ያውቁታል።ብለዋል ።
አሁንም ደግሜ እናገራለሁ ሲኖዶስ አንድ ነው ። ሁለት ነው የምትሉ የእርሰዎ መሰል ገለልተኞችና ወያኔዎች ብቻ ናችሁ። በቤተ ክርስቲያን የቋንቋ አጠቃቀም ካህንና ዲያቆን የሚባል አንድ አይነት ስም ሲሰጥ የቤተ ክርስቲያን የክህነት ምንጭ የሆነው የሲኖዶስ አባላት ግን ኤጲስ ቆጶሳት ፥ጳጳሳት ፥ ሊቃነ ጳጳሳት በመባል ይጠራሉ ። እርሰዎ ግን አዲስ አበባ ያሉት ካህናት ስደተኞች ካህናት የሚል መጠሪያ የሰጧቸውና ይህን ቃል የተጠቀሙት ጳጳስ የሚለውን ስም ላለመጥራት ስለፈለጉ ንቀተዎን ለመግልጥ ሆን ብለው በቋንቋ ለመጫወት ፈልገው ነው ።
እንደገና ጥያቄየን ይመልሱልኝ አንዱ አመራርና አንዱ ሲኖዶስ የት ነው ? በየትኛው ሥር ነው ያሉት ? አዲስ አበባ ያሉት እርሰዎም እንደ ተናገሩት የወያኔ ካድሬዎች ናቸው ። እና ከምን ተነሥተው ነው አዲስ አባባ እያሉ የሚገልጡልን ? ከወያኔ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ የሚያውቋቸው ሰዎች ስለ አሉ ለእነሱ መጽናኛ ቢሆናቸው ብለው ይሆን ? ክቡር ፕሮፌሰር ! እየቀጠሉ ሲሔዱ እውነትን የካዱበት ዋናው ሐሳብዎ ተገለጠ ።
ከኢትዮጵያ ውጭ ያለነው ሕዝበ ክርስቲያን ካህናቱን ጨምሮ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደተኞች ነን የምናደርገው ትግል ሀገራችን ነጻ ሁና በነነት እንድንኖር እን በተሰደድንበት አገር ኢትዮጵያዊት ቤተ ክርስቲያንና ኢትዮጵያዊ መንግሥት ልናቋቁም አይደለም ስለዚህ የተሰደዱትን ካህናት የምንጠይቃቸው የእኛን ሲኖዶስ ተከተሉ እያሉ ሕዝብ ማስጨነቃቸውና የመከፋፈል ምክንያት መሆናቸው ትተው የዲዮስጶራው ሕዝብ ወያኔን ሲቃወም ተጨማሪ ኃይል አንዲሆኑብለዋል ።
በዚሁ አንቀጽ መጨረሻ ላይየእኛን ሲኖዶስ ተከተሉ ማለት የሃይማኖት ስደተኞች ሳይሆኑ የሃይማኖት ስደተኞች ሁኑ ማለት ነው ብለዋል ።
ምን ማለትዎ ነው ? ይህን ክፍል ካነበብኩ በኋላ እያነበብኩ ያለሁት የአቶ ስብሐትን ጽሑፍ ነው ? ወይስ እቃወማለሁ የሚሉትን የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ጽሑፍ ነው ? ብየ ለተወሰነ ጊዜ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ ። በሚያሳዝን ሁኔታ ከመጨረሻው ቦታ ላይ ወርደው አገኘሁዎት ። ጨርሶ ሐሳብዎ አንድን እውነት ለመቃወም ሲሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር ዋጋቢስ አደረጉት ። ወያኔ ፓትርያርኩን በኃይል ከመንበራቸው አውርዶ “ዶከተር አባ ገብረ መድኅንን አስቀመጠ” ብለው ፣ ፓትርያርኩ ሰማዕት መሆን ነበረባቸው እያሉ ሲያስነብቡን ቆይተው አሁን ያንኑ አንብበን ሳንጨርስ የሃይማኖት ስደት ብሎ ነገር የለም አሉን ። የሃይማኖት ስደትስ ከሌለ ሰማዕትነት ከየት ይመጣል?
የስደቱን ሁኔታ ሲያብራሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስደት ነው የተሰደድነው ፤ ለአገራችን ነጻነት ነው የምንታገለው ፣ በአገራችን በነጻነት እንደልባችን እንድንኖር ብለን ነው አሉን ። ለመሆኑ እርሰዎ ነጻነት የሚሉት ምን ምን ሲሟላ ነው ? ወያኔን የማይደግፍ ሰው በኢትዮጵያ የእምነት የመናገርና የመጻፍ ነጻነት አለው የሚል ከወያኔ አባል ውጭ የሆነ ሰው ለመጀመሪ ጊዜ እርሰዎን ማየቴ ነው ።
እንደሚመስለኝ በዚህ የእርሰዎ ከፍተኛ ጸጸት፤ ቁጭትና ጥላቻ የተሞላ ጽሁፈዎ የተመለከትኩት ሲኖዶስ የሚባለውን ተቋም የጠሉበት ጥላቻ ነው ። አታስጨንቁን የሚለው ሐረግ እውነትም አስጨንቆዎታል ፣ የተጨነቁበት አንድን እውነት ከሁለት ውሸት ጋር በማወዳደር እውነቱን መምረጥ አቅቶዎት ነው ። የተከፋፈውለውም የእርሰዎ ሐሳብ ነው ፣ አንዱ ሐሳብዎ እውነት ያልሆነ ገለልተኛ ልቀበል ይላል ፣ ሌላው በልብዎ ኢትዮጵያ ያሉ የሚያውቋቸው ሰዎች ስለአሉ እነሱን ልደግፍ ይላል ፣ ያን እንዳይቀበሉ ከዚያው ሳይወጡ አንተ የወያኔ ሲኖዶስ ነው ብለህ እንዴት ነው ምን ነካህ ይላል ። የሚቀረዎ ሕጋዊ የሆነው ሲኖዶስ ነው ይህን እንዳይቀበሉ ከላይ የተመለከትናቸው ሁለቱ ሐሰቶች በአእምሮዎ እያቃጨሉ አስቸገሩ ፤ ከዚህ የሕሊና ውጥረት ለመውጣት ብለው ነው አታስጨንቁን ብለው በምሬት እንዲገልጹ ያደረገዎ ። ከዚህ ጭንቀተዎ ለመገላገል የተጠቀሙት ቃል ፣ ከሕጋዊው ሲኖዶስ አላማ ጋር የማይመሳሰል የአቶ ስብሐትን ቁልፍ ቃል ተጠቅመው ከፋፈሉን አሉ ። እንዴት ምን ያህል እውነትን ቢክዱ ነው አስከ አሁን ለሕዝብ ተስፋ የሆነውን ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፋፋይ ብለው የሚወነጅሉት ? የቀረዎት አቶ ስብሐት እንዳሉት አሸባሪ ማለት ብቻ ነው ።
ፕሮፌሰር! በዚሁ ክፍል የመጨረሻ አንቀጽ የተጠቀሙት የመመጻደቅ ሐሳብ ደግሞ የበለጠ ትዝብት ላይ እንዲወድቁ አድርጎዎታል ። ሁለቱን ሲኖዶሶች ሕገ ወጥ ናቸው ብለው የሰጡት ምክንያት ፣ የአዲስ አበባው መንግሥት አስገድዶት የሚል ሲሆን ፣ ውጭ አገር ያሉት ግን በሕዝብ ብዛት ነው ይሉናል ታላቁ ሰው !
ክቡር ፕሮፌሰር ! የአዲስ አበባዎቹ በመንግሥት ለመንግሥት የተመደቡ ሲሆን ስደተኞች ግን ሕዝብ ስለበዛ የተሾሙ ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ ተመርጠው የተሾሙ ፓትርያርክ የሚመሩት ቀኖናውያን ጳጳሳት የሚገኙበት ሲኖዶስ ነው ። እንዴት ሁኖ ነው ሰው ስለበዛ ነው የሚሉን ፣ ብዙ ሰው አግኝተው ተሾሙ ብለው ወደ ሌላ ስሕተት ውስጥ እንዳይገቡ ይጠንቀቁ ! ሆን ብለው የሚጠቀሙት ቋንቋ ያልሆነና ያልተባለ ነው ። በስደት ሲኖዶስ አልተቋቋመም ፥ የተባለው ሕጋዊው ፓትርያርክ ከተሰደዱ የሲኖዶስ አባላት ጋር በመሆን ሥራቸውን ቀጠሉ ነው የተባለው ። በሥጋዊ ሥልጣንና በመንፈሳዊ ሥልጣን መካከል ያለው ልዩነት ከዚህ ላይ ነው ፣ የእርሰዎ ችግር ይህን መንፈሳዊ ጉዳይ ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር ስለሚያያይዙት ነው ። የሚገርም ምጽድቅ ያደረጉት ግን ሲኖዶስ ከሕዝብ መሐል ነው የሚለው አባባል ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ከተጀመረ ሃምሳ ዐመት እንኳ ገና አልሞላውም ፤ ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለሲኖዶስና ያለጳጳስ አልኖረችም ። በየትኛውም በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሲኖዶስ ከእኛ መካከል ካልሆነ ሲኖዶስን አንቀበልም ብለው ገለልተኛ ሲሆኑ የተጻፈ ታሪክ የለም ። ከእርሰዎ ቡድን በስተቀር ። የማያቁ አንደሆነ የዓለሙ የኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ያለው እስታንቡል ነው ። አስታንቡል ያለው አንድ ቤተ ክርስቲያን ነው ።
የራሽያ ቤተ ክርስቲያን እንደ አሁኑ እንደኛ ጨካኝ ኮሚኒስቶች በነበሩበት ጊዜ በሦስት የተከፈለ ሲኖዶስ እንደ ነበራቸው ታሪካቸው ያስረዳል ።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በፈረንሳይ ጨካኝ መሪዎች አማካይነት መንበረ ፓትርያርካቸውን ሮምን ለቀው ለሰብአ ዓመት አቡጃ ከተባለ የፈረንሳይ ደንበር ከተማ በስደት ነበሩ ።
የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አሁን ድረስ ሦስት ፓትርያርኮች አሏት ። አነዚህ ሁሉ ችግር ያስከተለውን አጋጣሚ እንዲሁ አሁን እኛ እንደምናደርገው በስደት ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት በሲኖዶስ አደረጉ አንጂ አሁን እርሰዎ አንደሚሉት ያለጳጳስ በገለልተኝነት አለተበታተኑም ። ቤተ ክርስቲያንን የሚበትናት የንግድ ሥርዓት አራማጆች የመሠረቱት ‘ገለልተኝነት’ እንጂ በስደት ሲኖዶሳዊ የክህነት ሥራ መሥራት ቤተ ክርስቲያንን አይከፍልም ዶክተር ።
እንደማየው ሲኖዶስ ራሱ ምን ማለት እንደ ሆነ የመረዳት ችግር ያለ መሰለኝ ። የዚህ ችግር ነው ብዙዎች ሲኖዶስ ቦታ አይለቅም ፣ ሲኖዶስ በሳጥን አይያዝም በማለት ሲናገሩ እምንሰማው ። እርሰዎም ከዚያ ያልተሻለ ቁልፍ ቃል ነው የተጠቀሙት ። “ሲኖዶስ ከሕዝብ መሐል ነው የሚሆነው” ማለት ምን ማለት ነው ? ይህ ጉዳይ ለእርሰዎ ግልጽ አይደለም ብየ አላምንም ፤ ግን እርሰዎን የሚያምኑዎትና የሚሰሙዎት ሁሉ ስህተት ውስጥ እንዳይገቡ የቅዱስ ሲኖዶስን አወቃቀር መግለጽ አስፈላጊ ነው ።
ሲኖዶስ ማለት በሕጋዊ ሶኖዶሳዊ በቀኖና የተሾሙ ጳጳሳት ከሁለት በላይ ከተሰበሰቡ በኦርቶዶክስ ቀኖና መሠርት እርሱ ሲኖዶስ ይባላል ። ሲኖዶስ ማለት በህጋዊ መንገድ የተሾሙ ጳጳት በቊጥር ብዛት ከሁለት በላይ ሁነው ስብሰባ ካካሄዱ የወሰኑት ወሳኔ ፥ የደነገጉት ድንጋጌ ተቀባይነት አለው ማለት ነው ። የክርስቶስ ኣካል የሆነቸውን ቤተ ክርስቲያን ስለሚወክሉም ሲኖድስ የሚለውን ስያሜ ይወስዳሉ ። ይህን ስም ሊያገኙ የቻሉበት ምክንያት ከሐዋርያት ተያይዞ የመጣው ሥልጣነ ክህነት ስለ አላቸው ነው ። በሌላ ቋንቋ ታላቁን የቤተ ክርስቲያን የሥልጣን ምንጭ የሆነውን ክህነት ስለ ያዙ ነው። አንድ ተራ ካህን ከሀገሩ ወጥቶ ክህነቱ ከሠራ ቀኖናውን ያሟላ የጳጳሳት ጉባኤ ሥልጣን አይሠራም ያለው ማን ነው ? በአንድ ቃል ለማስቀመጥ ሲኖዶስ ማለት የጵጵስና ስልጣን ያቸው ሰዎች ስብሰባ ማለት ነው ።የፖለቲካ ነጻነት ያላገኙ ሰዎች በስደት ለነጻነት እንደሚሠሩ ሁሉ ፣ የእምነት ነጻነታቸውን ያጡ ጳጳሳትም የእምነት ነጻነታቸውን እስኪአገኙ ባሉበት አገር ሁነው የሃይማኖት ሥራቸውን ያካሂዳሉ ማለትነው ። ይህ አካሄድ ምኑ ነው በታኝ የሚያሰኘው ?
የሚገርመው እርሰዎን ጨምሮ ከሲኖዶስ ተለይተው ተወግዘው የነበሩትን እነ አባ ማትያስን ጳጳስ አድርጋችሁ ተቀብላቸሁ ስተገለገሉ ነበር ፣ እንግዲያውስ ሕገ ወጥ ማለት እርሱ ነበር ። አንድ ጳጳስ ብቻውን ቤተ ክርስቲያንን ሊወክልና በክህነቱም ብቻውን አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም ። ምክንያት የቤተ ክርስቲያንን ሕግ ስላልተቀበለ ነው ። ይህን መርሕ ግን እርሰዎን ጨምሮ ብዙዎቻችሁ ታካሂዱት ነበር። ያን ግን ቤተ ክርስቲያንን መክፈል አላላችሁትም ፣ ድርጊቱንም ሕገ ወጥ ብላችሁ አልጠራችሁትም ፣ በዚያ ፈንታ የጉዳዩ አጫፋሪ ሁናቸሁ ስታጧጡፉት ነበር።
ለጠየቃችሁ ሰው ሌሎቹ ስደተኞች እነዚህ ባለቤቶች በማለት ስትመልሱ አልነበረምን ? አሁን ብዙዎቹ ከሞቱ ግማሾቹም ከከዱ በኋላ ስደተኛ ያሉን እንዴት ነው ? ዶክተር እንዲህ የሚገለባበጡት ምን ሊያገኙ ነው ? ወይ ለሕዝብ አይጠቅም ፥ ወይ ለችግራችን መፍትሔ አይሆን ፥ ባለቀ ጊዜ ምን ለመሆን ነው ?
ከኑዛዜ በፊት ያሰፈሩት ሐሳብስ አንድያውን ግራ የገባው ሐሳብ ነው ። ይመኑኝ ደግመው ቢያነቡት ምን ለማለት እንደፈለጉ ግራ ይገባወታል ብየ አምናለሁ ። በግምት የምናገር አንዳይመስልብኝ የጻፉትን አብረን እንመልከተው
የዲዮስጶራው ካህናት ድርጅት አቋቁመው የሕዝቡን ችግር ለመረዳትና መፍትሔ ለመፈለግ በየጊዜው እየተሰባሰቡ መመካከር ርስበርሳቸው መማምድ ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ተናጋሪ እየጋበዙ ልምዱን እዲያካፍላቸው መጠየቅ ያስፈልጋቸዋል ያነን ጉባኤ መካናዊ (ሀገረ ብከታዊ) ሲኖዶስ ወይም የርክበ ካህናት ጉባኤ ሊሉት ይችላሉ ቀኖና ነው ፣ የሚከፋፍለንን ሲኖዶስ በዚህ በሚያተባብረን ሲኖዶስ ስም ቢጠሩት ያስከብራቸዋል ሁላችንም እንከተላቸውና ከፋፋይ የሚለው ታሪካቸው ይቅላቸዋል” ብለዋል ። ይገርማል !!
ፕሮፌሰር ! ምን እያሉ ነው ? በመጀመሪያ ካህናት ለመባል እኮ የጳጳሳት ጉባኤ ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስፈልጋል ። የአዲስ አበባውን ሲኖዶስ የወያኔ ነው ብለው ፈርጀው ሕገ ወጥ ነው ብለዋል ። ከሕገ ወጥ ሲኖዶስ ደግሞ ህጋዊ ክህነት አይገኝም ፣ ስለዚህ ይህን ክህነት አልባ ጉባኤ የፓርቲ ጉባኤ ይሉት እንደ ሆነ እንጂ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያለ ሕጋዊ ሲኖዶስ የካህናት ጉባኤ የሚባል ነገር የለም ።የካህናት ጉባኤ የሚባለው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ሥር ያልሆነ ካህን ካህን አይደለም ። ያለ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ የሚቀድስ ካህን የተወገዘ ነው ይላል ። እንደሚመስለኝ አጥብቀው የጠሉት ሲኖዶስ የሚለውን ስም የያዙትን ሰዎች መሆን አለበት በብዙ ቦታዎች እየገለጿቸው ያሉት ሐሳቦች የአንድን አካባቢ የጥላቻ መርዝ በመበትን ነው እንዲህ አላስቆም አላስቀምጥ ያለዎት አንጂ በየትኛውም መመዘኛ ክህነታዊ ጉባኤ የክፍፍል ምክንያት ይሆናል ብሎ ማሰብ አርቆ ማስብ ችግር እንጅ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል ሐሳብ አይደለም።
እናንተ ያለ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድና ይሁንታ በየቦታው ቤተ ክርስቲያን ያቋቋማችሁት በምን ዓይነት ቀኖና ነው ? እስቲ የጻፉትን መልሰው ያንቡት ፣ የካህናት ስብሰባ የአንድነት ምክንያት ፤ ሲኖዶስ ሲሆን ከፋፋይ የሚሆነው እርሰዎ ስለጠሉት ካልሆነ በቀር ልዩነቱ የክህነት አልባ ካህናት ጉባኤና ፥ በክህነት ሥር ያሉ ካህናት ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ነው ። ስለዚህ ልዩነቱ ኦርቶዶክሳዊ በመሆንና ባለመሆን መካከል ይሆናል ። የሚገርመው ቀኖና ነው የሚለው አባባለዎ ነው ፤ የትኛው ቀኖና ነው ያለ ክህነት ሰጭ ለካህናት ጉባኤ እወቅና የሚሰጠው ። በቀኖና ሠላሳ ካህናት ተሰብስበው አንድን ምእምን ዲያቆን ፥ አንድን ዲያቆን ካህን ሊአደርጉ አይችሉም ። አንድ ጳጳስ ግን አንድን ምእመን ዲያቆን አንድን ዲያቆን ካህን ማድረግ ይችላል ፤ ምክንያቱም ቀኖና ቤተክርስቲያን የሚያዝዘው እንደዚህ ነውና ።
እንዲሁም አንድን ቆሞስ አንድ ጳጳስ ብቻውን ጵጵስና ሊስጠው አይችልም ፣ ከሁለት በላይ ቊጥር ያላቸው ኤጲስ ቆጶሳት ግን በሊቀ ጳጳሳቸው ወይም በፓትርያርካቸው ፈቃድና ትእዛዝ ፥ አንድን ቆሞስ ኤጲስ ቆጶስ አድርገው መሾም ይችላሉ ። ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን ያለ ሲኖዶስ ህልውልና የላትም የተባለው ። በአንጻሩ ሲኖዶስም ያለ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ሊሆን አይችልም ። ይህን ካልኩኝ የተወሰኑ የኦርቶዶክሳዊነት መገለጫዎችን ልጠቁም ።
ኦርቶዶክስ በቦታ በጊዜ የተገለጠች ታሪካዊት ናት ፣ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊት ናት ፣ኦርቶዶክስ ጉባኤያዊት ናት ፣ ኦርቶዶክስ ከሁሉ በላይ ፥ በሁሉም ያለች ፥ (አለማቀፋዊ) ናት ፣ ኦርቶዶክስ ምስጢራዊት ናት ፣ ኦርቶዶክስ አምላኮዋዊት ናት ፣ኦርቶዶክስ መጽሐፍ ቅዱሳዊት ናት ፣ ሲጠቃለል ሦስቱ የኦርቶዶክስ ምሰሶዎች ቅዱስ መጽሐፍ ፥ ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ፥ ትውፊታዊ ቀኖና ይሆናል ። ይህን ሁሉ የሚያከናውን ክህነት ነው ፤ ክህነት ደግሞ ያለ ሲኖዶስ አይኖርምና ክቡርነተዎ እንዲያስቡበት በአክብሮት አሳስባለሁ ።
በማጠቃለያ ኑዛዜ “ስደተኞቹ ጳጳሳት አባ ይስሐቅ አባ መልከ ጼዴቅ አባ ኤልያስ ፥ አንድ ጊዜ ኒውዮርክ ከተማ ስብስባ አድርገው በማግስቱ ሲኖዶስ ማቋቋማቸውን ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለተሰበሰብነው ነገሩን ጥቂቶች ብዙዎችን አይወክሉም ይህ ንዴት ይሁናል ? በሚገባ አስባችሁበታልን ? የሚል ጥያቄ ሳነ ዶክተር በላቸው አሥራት ፖለቲካዊ ጥቅሙን ካስረዳ በኋላ አባ ገብረ ሥላሴ ተነሥተው በወያኔ ያሉ ጳጳሳትም ከእኛ ጋር አሉ አሉ በኢትዩጵያ ጳጳሳትም ከደገፉት ወያኔን የሚያጠቃ ኃይል ካለው በማለት ደግ ነበር አሁን ግን ሳየው አንዱም ተስፋ አልፈጸመልንም እንዲያውም ገደል ያሚያገባ መንድ ስለ ሆ እንመለስ” ብለው ተናዝዘዋል ። ክቡርነተዎ ወያኔያዊ መልእክተዎን በደንብ አስተላለፉ እኔም እንድጽፍ ያነሣሣኝ ይኸው አባባለዎት ስለ ሆነ በዚህ ዙሪያ እውነት የሆነውን ማብራሪያ ለመስጠት ግድ ይለኛል ።
ስደተኞቹ ጳጳሳት አባ ይስሐቅ … ፕሮፌሰር እንዴት ነው ? አቡነ ይስሐቅ ስለ ሞቱ ነው አሁን ስደተኛ ያሏቸው ? ስደተኞቹ የአቡነ ይስሐቅን ሀገረ ስብከት ቀምተው እያሉ ሲሰብኩ የነበረውን ምን ጊዜ እረሱት ? እኛ ሁሉም ስደተኞች ናቸው ፥ ቦታው በክፉዎች ስለ ተያዘ ቤተ ክርስቲያን ተሰዳለች ብለን ነበር ያን ጊዜ የጀመርነው ። እናንተ ግን በተለይ እርሰዎ አይደላችሁም እንዴ አቡነ ይስሐቅ ስደተኛ አይደሉም ብላችሁ ከአባቶቻቸው የለያችኋቸው ። የቀብር ወጉ እንኳ እንዳያምር አድርጋችሁ ፥የሲኖዶስ አባል እንዳይሆኑ አስወጥታችሁ ፥ የሌለ ሀገረ ስብከት ሰጥታችሁ ስትቀልዱ የነበረውን እንዴት እረሱትና ነው አቡነ ይስሐቅን ስደተኛ የሚሏቸው ? ምነው ክቡር ፕሮፌሰር እንዲህ ይረሳሉ ? በሌላው ጽሁፈዎ ላይ እንዲዚሁ እጅ እጅ የሚል ምጽድቅ አስፈረዋል በውጭ ያለው ሕዝብ በታላቋ ኢትዮጵያ ሥር ያለእንደ ሀገረ ስብከት መሆን ይችላል ይሉናል ምን አይነት ሊቀነት ነው እንዲህ ማስተዋል የተነሣው ነፍሳቸውን ይማርና አቡነ ይስሐቅ እኮ ክህነታቸው ተይዞ የነበረው ሀገረ ስብከት ብለው ጠርተው ስለነበር ነው ሀገረ ስብከት ማለት በእነ አቦይ ስበሐት ነጋ ሥር መሆን ማለት ነው አሁንስ በጣም እየተጠራጠርከዎት መጣሁ።
ሲኖዶስ ማቋቋማቸውን ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ለተሰበሰብነው ነገሩን ። ይህ አባባል ደግሞ የሚገርም ነው ፤ ለየትኛው ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነበር የተሰበሰባችሁት ? ፣ ማን ነው የጠራቸሁ ? የተሰበሰባቸሁት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጠርተዋችሁ ነው ? ላስታውሰዎ የተሰበሰባቸሁት ስደተኛ ብለው በጠሯቸው አቡነ ይስሐቅና አቡነ መልከ ጼዴቅ አማካይነት ነው ። ምክንያት ያን ጊዜ የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ገና አልተወሰደም ነበረና ነው ። የተጠራችሁትም ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አልነበረም ፣ እንደሚታወቀው ያን ጊዜ አቡነ ይስሐቅን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናቱ በክስ ላይ ስለ ነበሩ አቡነ ይስሐቅም በየተኛውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ከርስቲያን ክህነታዊ ሥራ አንዳይሠሩ በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው ስለነበር በዚያ ዙሪያ ሕጋዊ ምክር ትሰጣላችሁ ተብሎ ነበር የተጠራችሁት ።
ነገር ግን እንደ አለመታደል ሆነና ከስብሰባው በሰዓቱ በመምጣት ፈንታ በዚህ ጽሑፍ ልገልጠው በማልፈልገው ግለሰብ ቤት ተሰብስባችሁ ስታድሙ ቆይታችሁ ሰዓት አሳልፋቹሁ መጥታችሁ እንዴት የሥልጣን ተካፋይ እንደምትሆኑ ስትከራከሩ መዋላችሁ የሚታወስ ነው ። ሲኖዶስም የተባለው ተቋቋመ ሳይሆን ሥራውን ቀጠለ ነበር ። የጠየቁትን ጥያቄ እንደ ብዙው ጉዳይ ረስተውታል ፣ እኔ ግን አረሳሁትም “ሁሉ እየወጣ ሲኖዶስ ላቋቁም ቢል ምን መልስ አለን”? ነበር ጥያቄዎት ። መልሱ አንደኛ ሲኖዶስ አልተቋቋመም ፥ ሥራውን ቀጠለ እንጂ ። ሁለተኛ ሲኖዶስ ሥራውን የቀጠለው ሕጋዊው ፓትርያርክ ስለ አሉና እርሳቸው ስለ ፈቀዱ ነው ነበር መልሱ ። ያን አምነውበት ፥ በፊርማዎ አረጋግጠው ፥ እርሰዎም በእውቀተዎ እንደሚረዱ ቃል ገብተው ፣ ለዚህ ስምምነት የጉባኤው መጨረሻ ቀን ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ቤት የቀለጠ ግብዣ ተደርጎ ነበር የተለያየነው እንጂ ፣ እርሰዎ እንዳሉት አባ ገብረ ሥላሴ የወያኔ ጳጳሳት ከእኛ ጋር ናቸው ብለው ነው ማለተዎ በሁለት መንገድ ተሳስተዋል ።
ንደኛ እንዴት ያለ ቀላል ልብ ቢኖረዎ ነው እንዲህ በአንድ ቃል ተለውጠው እምነትን ያህል ነገር ጥለው በማይሆን መንገድ ለመሄድ ያመኑት ። ሁለተኛ አባ ገብረ ሥላሴ ያን ጊዜም ፥ ከዚያ በፊትም ፥ አሁንም የወያኔ ሰዎች ከእኛ ጋር ናቸው ሲሉ ሰምተን አናውቅም፤ እኛ የያዝነው እውነት ስለ ሆነ ፥ ብዙ ሰው ባይቀበለውም እንኳ እውነት እስከ ሆነ ድረስ ብቻችንም ቢሆን አንደምንቀጥልበት ስለ አመንበት ነው ። የወያኔ ሰዎችማ ከእኛ ጋር ቢሆኑ ድሮውንስ ምን ችግር ነበረው? አሁን ይህን ምክንያት ብለው ሰው ሊያመነውት ከአደባባይ አወጡት!
እምነት ብዙዎች ስላልደገፉት ሊለወጥ የሚችል ተራ ነገር አይደለም ። እምነት ማንም ባይቀበለው ብቻን እንኳ በታማኝነት ሁኖ የሚሞትበት ነው ። እኔ ይህንን ጉዳይ ይዤው የተነሣሁት እንደ እርሰዎ ውጭ አገር ሁኜ አይደለም ወይም ፖለቲካ ጠቀሚታ አለው ብየ አይደለም፤ እውነት እና እምነት ስለሆነ ከዚያው ከሀገር ውስጥ ከሥራ ቦታ ሁኜ ነበር ። በዚህ አቋሜም ተንገላትቼ ተሰድጀአለሁ ፤ በዚህም እደሰትበታለሁ ። ክቡርነተዎ ግን የማያምኑበትን ጉዳይ በአንድ ቃል የሚጥሉ ከሆነ በጣም ያሚያሰጋ ባሕርይ ነው ያለዎትና ሊያስቡበት ይገባል እላለሁ ።
በዚሁ ኑዛዜዎት ላይ ሁለተኛው ሐሳቡን የተቀበሉበት ምክንያት “ዶክተር በላቸው ለፖለቲካ ጥቅም አለው በማለታቸው ምክንያት ነው ብለዋል” ። ትልቁ ችርግም ይኸው ነው ። ቤተ ክርስቲያንን ለፖለቲካ ጥቅም መቀበል ይህን አካሄድ አደገኛ የሚያደርገው እምነትን ሳያምኑ ለማያምኑበት አላማ ለማዋል በሚደረግ ጥረት የሚመጣው ጥፋት አሁን እርሰዎ ከደረሰበዎ ጭንቀት ውስጥ ስለሚያስገባ መጨረሻው አሁን እርሰዎ እንደ ሆኑት ገደል የመግባት ያህል ተስፋ ያስቆርጣል ። ወደ ገደል ስለ ገባን እንመለስ አሉ ፣ መጀመሪያ ገደል ነበራችሁ ከገደል ወጥታቸሁ መንገድ ጀመራችሁ ግን የፖለቲካ ንግድ ትርፉ የሚጠቅም ስላልመሰላችሁ እንመለሳለን ስትሉ ደግሞ መጀመሪያውኑ እናገኘዋለን ያለችሁትን ጥቅም ስላላገኛችሁ ገደል ገባን አሉ ።
ሐሳብዎትን የደመደሙት እንመለስ ብለው ነው ። እንደሚመስለኝ ወደ ወያኔ ሳይሆን አይቀርም ። የጠሩን እንግዲያውስ ገደሉ እርሱ ነውና እራሰዎት ይመለሱ ያሉበት ሁኔታ አላማረኝምና ይህን ጉዳይ ያስቡበት እላለሁ። አለመታደል ሆነና ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሀገራችን ፖለቲካ በአካባቢ የምትወሰን ይመስል በውጭ ሀገር ኢትዮጵያዊት ቤተ ክርስቲያን ልናቋቁም አልመጣ ብለዋል ኦፊስ (ቢሮ) የተባለው እኮ ሕንጻው አይደለም ክህነቱ ነው የጵጵስና ቢሮ (ኦፊስ)የቅስና (ቢሮ) ኦፊስ የዲቁና ቦሮ( ኦፊስ) ማለት ክህነቱ የሚሰጠው አገልግሎት ነው ይህ አገልልግሎት ደግሞ የትኛውም ቦታ ሁኖ ይሠራል ስለዚህ ገደል ከታች፣ በታኝ፣ ከፋፋይ፣ የሚለው ስያሜ ለዚህ ሥልጣን የሚሰጥበት ምክንያት ምኑ ላይ ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ናት ፣ በዓለም እንድትስፋፋ ነው ወንጌል የተሰጣት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የትም ሀገር አገልግሎቷን መስጠት ትችላለች ። የተሰደደችበትንም ሆነ ለሐዋርያዊ ተልእኮ በፈቃደ እግዚአብሔር የወጣችበትን ሁሉ ይባረካልና እንደ ምድራዊ መንግሥት ስደትም መልክአ ምድርም አይወስናትም እና ሊስተዋል ይገባዋል እንላለን። ይህን ጽሁፍ ሲያነቡ እንደማይቀየሙ ተስፋ አለኝ በመልሱ ላይ ያላስተዋልኳቸው ሐሳቦች ካሉ እውነት የሆነውን ብቻ እንዲያስተምሩን እንጅ እንዲሁ እውነት ያልሆነ ጉዳይ ውስጥ ገብተው የሰውን ልብ መክፈል አስፈላጊ ነው ብየ አላምንም።
አክባሪዎ ቀስቶ ወጠረ ነኝ

No comments:

Post a Comment