በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለተከናወነ አሳዛኝ ተግባር የሚገልጸው ተንቀሳቃሽምስል መግለጫ።
ቀን፡ 27-02-2013
“የክህነት ተግባር እግዚአብሔርንም፤ ሰውንም ማገልገል ነው። እግዚአብሔርን ማገልገል ማለትም ካህናት መላእክትን መስለው በመዓልትና በሌሊት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ምስጋና ነው።
ሰውን ማገልገል ማለትም፡ ማስተማር፤ ማጥመቅ፤ ማቁረብ፤ መባረክ፤ መጠበቅ፤ መናዘዝ፤ መቀደስ፤ ማንጻት፤ ከኃጢአት መፍታት፤ ከእግዚአብሔር ማስታረቅ፤ በሞት ለሚለዩ ጸሎተ ፍትሐት ማድረግ፤ በጠቅላላው በትምሕርትና በትሩፋት ከርስቶስን መስሎ አብነት ሆኖ መገኘት ነው።”
(ማቴ.፩፫፡ ፩-፩፬ ፡ የሐ.ሥራ ፮:፬፡ ፳:፪፰-፫፩ ፡ ዮሐ. ፳:፪፩:፪፬፡ ፩ጢሞ. ፬:፩፫ ማቴ.፩፮:፩፱ ኤፌ.፬: ፩፩፡ ፩ጴጥ. ፭፡ ፩-፬)
ቀን፡ 10- 02-2013 ዕለቱ ዕለተ ሰንበት እሑድ ነበር።
ቦታ፡ ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን (United Kingdom)
- 1. በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ በመጀመሪያው ክፍል 10/02/2013 የሚል ጽሑፍ እስከሚወጣበት ድረስ ያለው ሁኔታ መግለጫ።
በ03-02-02013 የቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ (Management Committee) በገዛ ፍቃዳቸው ከሥራቸው በመልቀቃቸው ምክንያትና በተለይ 4 የምእመኑ ተወካዮች ሙሉ በሙሉ ስራቸውን አቁመው እቤታቸው በመቅረታቸው በምትካቸው አዲስ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ የሚያስመርጥ አስመራጭ ጉባኤ መምረጥ አስፈለገ።
በዚህ የምርጫ አፈጻጸም ላይ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪና ተከታዮቻቸው የሆኑ ካህናት የቤተ ክርስቲያኑን መተዳደሪያ ደንብና የቻሪቲ ሕግን በጣሰ ሁኔታ ለነሱ ሥጋዊ ጥቅም በሚያመች ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ እንዳቀዱ ስለታወቀ በምርጫው መካሄድ የሁሉም ስምምነት ቢኖርም ነገር ግን ምርጫው እንዴት እንደሚካሄድና የሚመረጠው አዲስ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ዓይነት አስመልክቶ የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር።
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር (ካህናቱ) ወገንተኝነትን የያዙ በመሆናቸው የሃሳብ ልዩነቱን ማቀራረብም ሆነ ማስታረቅና መዳኘት ባለመቻሉ ጉዳዩ ተካሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ሁከትና ረብሻ አስከተለ። ከዚህ በመቀጠል በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ያሉት ኮሚቴዎች ሁሉ በሚሳተፉበት ጥምር ጉባኤው ተሰብስቦ የመፍትሔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ተደርጎ ሁለት አማራጮችን አቅርቦ ስለነበር ምርጫው ከመካሄዱ (ከ03-02-02013) በፊት ጠቅላላ ጉባኤው በቅድሚያ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶበት አንዱን አማራጭ መርጦ እንዲወስን ከጉባኤው ቀን አስቀድሞ ብዙ ቁጥር ያላቸው አባላት ሕጋዊ ማመልከቻ (Petition) በመፈረም ለቤተ ክርስቲያኑ ጽ/ቤት አስገቡ፤ በቃልም ቀርበው አስረዱ።
በዕለቱ ስብሰባ ላይ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ግርማ ከበደና የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ((Management Committee) አባላት የሆኑ ቄስ ዳዊት አበበና ቄስ አባተ ጎበና ስብሰባውን እንደከፈቱ ከአሁን በፊት በጥምር ጉባኤው የተወሰነውን ሁለት አማራጭ ሳያነሱና የአባላቱንም ማመልከቻ (Petition) ንቀው ወደጎን በመተው ምርጫውን በጉልበት እናካሂዳለን በማለት ሕዝቡን ማስገደድ ጀመሩ።
በስብሰባው ላይ አባላት ድምጻችን ይሰማ በማለት ከፍተኛ ትግል ካካሄዱ በኋላ ለመጠየቅና አስተያየት ለመስጠት ዕድል አገኙና በርካታ ሕጋዊ ጥያቄዎችን አቀረቡ። ከዚህም ጋር በማያያዝ ገንቢና ወደ ሰላምና አንድነትም የሚያመራ የበሰለ አስተያየት ሰጡ።
የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪና ሁለቱ ካህናት ግን የተጠየቀውን ጥያቄ ለመመለስም ሆነ የተሰጠውን አስተያየት ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምርጫውን እናካሂዳለን በማለት ቀጠሉበት። በዚህ ወቅት ሕዝቡ ተቃውሞውን በጩኸትና በመዝሙር ገለጸ። ካህናቱ የሕዝቡን ጥሪና አቤቱታ ከመስማት ይልቅ ልባቸውን እንደ ድንጋይ በማጠጠር ሕዝቡን ቀርቶ እግዚአብሔርንም ባለመፍራት ምርጫውን በኃይል እናካሂዳለን በሚል ቀጥለውበት ሕዝቡን በተቃዋሚና በደጋፊ ጎራ ተከፍሎ እንዲበጣበጥ መቀስቀስ ጀመሩ።
ይባስ ብለው የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የተቃዋሚውን ሕዝብ ድምጽ በድምጽ ማጉያ ኃይል በመብለጥ አስቀድመው ያዘጋጇቸውን ተመራጭ እጮዎች ሥም ዝርዝር በመጥራት ጸሐፊውን መዝግብ እያሉ ምርጫውን ለማካሄድ ጣሩ።
የጌታችን የመድሃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ ቃል ግን እንዲህ ይላል።
በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን በበጎ ፈቃድ እንጂ፤ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጎብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማህበሮቻችሁን በግድ አትግዙ፤ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። (1ኛ ጴጥ. 5፡ 2-4)
አስተዳዳሪው ሰውንም እግዚአብሔርንም አልፈራም ብለው በድርጊታቸው ሲቀጥሉበት ስብሰባው በሁከት ተሞላና ምንም መቋጫ ሳይደረግና ቀጣዩ ሁኔታ ሳይገለጽ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ስብሰባውን ዘግቻለሁ በማለት ለጸሎት ተነሱ አሉ።
ከጸሎቱ በኋላ ግን አባላት ከቤተ ክርስቲያናችን አንወጣም በማለት ስብሰባውን በመቀጠል በሕዝብ ተመርጠው የተሾሙት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ቀደም ሲልም ሆነ በዕለቱ ያሳዩት ከአንድ መንፈሳዊ መሪና የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የማይጠበቅ አንባገነንነትና ሕዝብን ከሕዝብ የመከፋፈል ተግባርን በመገምገም በአስተዳዳሪው ላይ የVote of No confidence ለማካሄድ ሲል በስብሰባው ላይ ህጻናት፤ አቅመ ደካሞችና አዛውንቶች ሳይቀሩ እንደሚገኙበት እያወቁ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የቤተ ከርስቲያኑን መብራት በማስጠፋት ሕዝቡን ለከፍተኛ አደጋ አጋለጡ።
ከዛም በሕዝቡ ጩከትና ተቃውሞ መብራቱ እንደገና እንዲበራለት ካደረገ በኋላ አባላቱ ስብሰባውን በመቀጠል በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ላይ የጀመርውን Vote of No confidence በማካሄድ በውሳኔው ላይ ከተፈራረመ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት (በ10/03/2013) ከቅዳሴ አገልግሎት በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጠቅላላ ጉባኤውን ስብሰባ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዞ ተለያየ። ይህንንም የጉባኤ ውሳኔ ለሰበካ አስተዳደር ጉባኤው ጽ/ቤትና ለሚመለከተው ሁሉ አሳወቀ።
- 2. በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ 10/02/2013 የሚል ጽሑፍ ከሚታይበት ጀምሮ ወደ ፊት የሚታየው ሁኔታ መግለጫ።
ጠቅላላ ጉባኤው የቀጠረው ስብሰባ ቀን እስከሚደረስ ባለው የአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስልጣኔ ሊወሰድብኝ ነው ብለው የደነገጡት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ከሌሎች በሥጋዊ ዓላማ ከሚተባበሯቸው ካህናት ጋር በመሆን የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ሌሎችን በመቅረብ የተነሳውን የአስተዳደርና የሕዝብ መብት ጥያቄ የሃይማኖትና የቀኖና ጉዳይ አስመስሎ ሰፊ የሃሰት ቅስቀሳ በማድረግ የካህናቱን የሃሰት ቅስቀሳ አምነው የተቀበሉትንና ቤተ ክርስቲያኗ የምትከተለውን ገለልተኛ አቋም የሚቃወሙ የፓለቲካ ወገንተኞችን በማቀናጀት ለአመጽና ለረብሻ እንዲሰለፉ አደራጇቸው።
በዚህ መሠረት ነው በ10/02/2013 እሑድ ዕለት ከቅዳሴ አገልግሎት በኋላ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት የጠቅላላ ጉባኤውን ስብሰባ ለማካሄድ ባስቀደሱበት ወንበር ላይ እንደተቀመጡ በቪድዮው ላይ የሚታየው የስድብ ናዳ የወረደባቸው።
በጸጥታ የተቀመጡት የቤተ ክርስቲያን አባላት የሆኑ አዛውንቶች፤ ጎልማሶችና ወንድና ሴቶች ሁሉ ዓላማቸው ሰላማዊና የመብት ጥያቄ ሲሆን የሚጠይቁትም ሆነ የሚቃወሙት የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር እንጂ ከርስቲያን ወንድሞቻቸውን እህቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ባለመሆኑ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ እንደሚታየው የሚሰነዘርባቸውን ስድብ፤ ዛቻና ማስፈራሪያ ሁሉ በጸጋ ተቀብለውታል።
ሰው ናቸውና መናደድና መበሳጨት ቢኖርም መልስ ቢሰጡና ግብግብ ቢገጥሙ የሃይማኖታችውንና የቤተ ክርስቲያናቸውን ክብር ማስነካት ስለሚሆን ሁሉንም በእግዚአብሔር ፍቃድ ችለው አልፈውታል።
ተሳዳቢዎቹ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ተባባሪዎቻቸው አስተዳደሩን ወግነው፤ ሕዝቡን መቃወማቸው ያልተለመደና ትርጉም የለሽ ቢሆንም በመቃወሙ ካመኑበት ግን መብታቸው ስለሆነ ሥርዓትን ጠብቀውና የሌላውን መብት ሳይጋፉ ተቃውሞአቸውን ማሰማት በቻሉ ነበር።
እንኳንስ ከርስቶስ በደሙ በዋጃት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀርቶ በየትኛውም ቦታ የሌላውን መብት የሚጥስና፤ ሰብዓዊ ክብሩን የሚነካ ተቃውሞ ማካሄድ ምድራዊውም ሆነ ሰማያዊ ሕግ የሚፈቅደው አይደለም።
የጌታ ቃል ግን እንዲህ ይላል።
አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ፤ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ሰው ቢኖር የርሱ አምልኮ ከንቱ ነው (ያዕ. ፩፡ ፪፮)
- 3. የተንቀሳቃሽ ምስሉ ዝርዝር መግለጫ።
3.1 በተንቀሳቃሽ ምስሉ መጀመሪያ ላይ የሚታየው በተራ ቁጥር 1 ላይ የተጠቀሰውን የመጨረሻ ክንውን አነስተኛ ክፍል ቀንጭቦ የሚያሳይ ነው።
3.2 በቀጣዩ ላይ ያለው በቪዲዮው ላይ እንደተመለከተው በተራ ቁጥር 2 ላይ ያለውን አብዛኛውን ክንውን የሚገልጽ ነው።
3.3 በዚህ ቪዲዮ ላይ በግልጽ የሚታየው የሁከቱ ጠንሳሽ፤ አቀነባባሪና፤ አዝማች ከኋላ በኩል ጥቁር ቆብና የደፉና ነጭና ጥቁር የመነኩሴ ልብስ የለበሱ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ግርማ ከበደ ናቸው።
3.4 አንድ ምስል ከአንድ ሺህ ቃል የበለጠ ገላጭ ነው እንደሚባለው፤ ገና ከጅምሩ ስብሰባው አይካሄድም ብለው በድምጽ ማጉያ በመናገር ሁኩቱ እንዲጀመር መመሪያ የሰጡትና ሁከቱን ከኋላ ሆነው እየተንጎራደዱ ከማየት በስተቀር እንደ መንፈሳዊ አባት ልጆቼ አንተም ተው፤ አንቺም ተይ ሳይሉ በል ግፋ የሚሉት እኚሁ መነኩሴ ናቸው።
3.5 ሌላ የእኚሁ አስገራሚ መነኩሴን ሥራ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ውስጥ እንመለከታለን፡ እሱም አንድ ጥቁር ካፓርት መሳይ የለበሰ ጠይም ሰው ስድቡና ጫጫታው ወደ በርከተበት ቦታ መጥቶ ነገሩን ለማረጋጋትና ለማበረድ ሲሞክር መነኩሴው ከኋላ ተንደርድረው በመምጣት ያ ሰው የሚያደርገውን የማረጋጋት ሙከራ ትቶ ወደ እሳቸው እንዲሄድ ልብሱን ነክተው ይጠሩታል። ይህ ምስል መነኩሴው ሁከትና ረብሻውን መቀጠሉን እንደሚፈልጉትና እሳቸው ቀርቶ ሌላም ሰው እንዲያበርደው እንደማይፈልጉ በግልጽ ያሳያል።
3.6 እዚህ ላይ ከሚታዩት ነገሮች ውስጥ ከምንም በላይ የሚያስገርመው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀርቶ በየትም ሕግና ሥርዓት አለ በተባለበት ቦታ መነገር የሌለበትን ስድብና ማስፈራሪያ በሰዎች ላይ ሲወርድ መስማት ቢሆንም ከዛ ቀጥሎ ሌላውና እጅግ አስገራሚው ነገር ግን መሳደብ ቀርቶ ምንም ቃል ያልተነፈሰንና አርፎ የተቀመጠ ሰው ላይ ያለማቋረጥ የስድብ ናዳ ሲወርድበት ማየት ነው።
3.7 ስድቡን በተመለከተ ደግሞ እጅግ አስገራሚው ነገር ከተሰነዘሩት ስድቦች፤ ዘለፋዎችና ማስፈራሪያዎች ውስጥ ታናሽ፤ ታላቁን፤ ልጅ አባቱና እናቱ የሚሆኑ አዛውንትና ባልቴቶችን ቀርቶ ክርስቲያን ክርስቲያኑንም ሆነ ማንም ሰብዓዊ ፍጡር ሌላውን ሰብዓዊ ፍጡር ሊሰድበው የማይገባውን ስድብ ሲሳደብ የነበረው ሰው ከሰንበት ት/ቤት ወጣትነትም በላይ ዲያቆን መሆኑ ነው።
3.8 ይህ iPod ይዞ ምስል የሚቀርጽ ሰው ዲያቆን ሲሆን ይህም ሰው አዕምሮው ያልበሰለ ህፃን ወይም (Tin age) ሳይሆን በሠላሳዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለ ጎልማሳና ነገሮችን ለማመዛዘን የሚያስችል ዕድሜ ላይ የደረሰ የተሟላ ሰው ሆኖ የሚያወርደው እጅግ ዘግናኝ ስድብ ግን ከሁሉም የከፋ ነው።
3.9 ይህ የከፋውንና የሚሰቀጥጠውን ስድብ ሲሳደብ የነበረው አንድ ዲያቆን ይሁን እንጂ በስድቡ ውስጥ ተሳታፊ የሆነ ሌላ ዲያቆንም አለ። ይህም ዲያቆን የሁለት እጆቹን ሁለት ጣቶች በማውጣት በማሾፍ መልክ ወደ ቪዲዮው ቀርቦ የተቀረጸው ወጣት ነው።
3.10 ዲያቆናትን አስመልክቶ የሃይማኖታችንና የቤተ ክርስቲያናችን ሕግ ቀጥሎ የተመለከተውን የሚል ሲሆን ይህንን ከዲያቆናቱ ድርጊት ጋር በማመዛዘን ለመረዳት ፍርዱን ለተመልካች ትተነዋል።
3.11 ዲያቆናት ጸጥ ያሉ፤ የሚታዘዙ ይሁኑ፤ በሁለት አንደበት አይናገሩ፤ ቁጡዎች አይሁኑ፤ቁጣ አዋቂውንም ሰው ያጠፋል (ረስጣ ፩፯ ጤት ፬)
3.12 ዲያቆናት መልካም ሥራን በመዓልትም በሌሊትም፤ በቦታው ሁሉ የሚሠሩ ይሁኑ፤ ያለ ኃጢዓት በጎ ማገልገልን ያገለገለ ይህ ይጠቅማል፤ በጎ ድርሻንም ይቀበላል። (ፍትሐ ነገሥት)
3.13 በቪድዮው ላይ ከሚደመጠው ስድብ የከፋውንና ጆሮ ሰምቶ ለመቀበል የሚያዳግተውን ድቁናን በተቀበለ ሰው አንደበት የተነገረ በመሆኑ ተጠቀስ እንጂ አብዛኞቹ ስድቦች ያነጣጠሩት በአዛውንቶችና የዕድሜ ባለጸጋ በሆኑ ሰዎች ላይ ነበር።
3.14 አብዛኛዎቹ እነዚህ አዛውንቶችና ጎልማሶች ደግሞ በስደት ሃገር ከተመሠረተች 40 ዓመታትን ባስቆጠረችው ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስር፤ ሃያ፤ ሰላሳና ከዛም በላይ ዓመታት እንደውም አንዳንዶቹ ተሳዳቢዎች ሳይወለዱ ጀምሮ የኖሩና ያገለገሉ ናቸው።
3.15 ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ምሳሌ የሚሆንና የክርስቶስን መንገድ የሚከተል ማለት ነው። እንዴት ብሎ ታላቁን፤ የሚወልደውንና አንዳንዱም አያቱ የሚሆነውን አዛውንት ምንም ሳይለው እየሰደበና እያዋረደ መልሶ እኔ ክርስቲያን ነኝ ሊል ይችላል?
3.16 እንዴትስ ካህናትና የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መነኩሴ ሰውን ቀስቅሶና አደራጅቶ ይህን መሰል ድርጊት እንዲፈጸም ያደርጋል? ድርጊቱ ሲፈጸምስ እያየስ በጭካኔ ዝም ብሎ ካሳለፈ በኋላ ተመልሶ እኔ ከእግዚአብሔር ጋር የማገናኝ ድልድይ ነኝ በማለት ለመናገር የሚችል ሂልና ሊኖረው ይችላል?
ወስብሐት እግዚአብሔር!! አሜን።
Search ECADF
Recent Posts
- የህወሓት ስረወመንግስት በኢሕኣዴግ ጡዘት
- በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለተከናወነ አሳዛኝ ተግባር የሚገልጸው ተንቀሳቃሽምስል መግለጫ።
- አለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 በኦስሎ ኖርዌይ ንግስት ሶኒያ በተገኙበት በደማቅ ስነስርአት ተከብሮ ዋለ
- እንደምን ሰነበታችሁ? ይህ ለአፋና እጅ የማይሰጥ የህዝብ ድምፅ ነው፡፡
- ሲገርሙ አውስትራልያዎች …. ከግራጫ ፀጉር ጋር – ውድድር?
- እኛም እንድገመዋ… ርዕዮትን እያሰሩ … ቐሽ ገብሩን ቢዘክሩ… “ሼም” የለም በአገሩ…!?
- “ድህነታቸውን ህዝቡ ላይ አራግፈው ለራሳቸው ባለፎቆች ሆነዋል” ስማቸው ያልተገለጸ እናት
- ለታማኝ ሚዲያ ታማኝ አምባሳደር
- በባለፈው አመት የአሳሳ ግርግር የታሰሩ ከ45 በላይ ሙስሊሞች ተፈረደባቸው፡፡
- የህወሓት/ኢህአዴግ የውስጥ ፍጥጫ፣ ዴሞክራሲን አይወልድም
- ከኬኒያው ፕሬዜዳንታዊ ምርጫ ምን እንማራለን?
- ኢህአዴግ አሣ አስጋሪዎችን ጨፈጨፈ
- ተጋዳላይ ማትያስ ሹመት ያዳብር!
- ደጀ ሰላም ከወራት በፊት አቡነ ማትያስ እንደሚሾሙ ያሳወቀችው እውን ሆኗል፤
- የሕወሐት ፍጥጫ ቀጥሏል (ከኢየሩሳሌም አርአያ)
Widgetized Section
Go to Admin » Appearance » Widgets » and move a widget into FooterLeft Widget Zone
No comments:
Post a Comment